Thursday, July 25, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የሕክምና ተቋማትን ጨምሮ ሰባት ድርጅቶች የአክሬዲቴሽን ዕውቅና ተሰጣቸው

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ብሔራዊ አክሬዲቴሽን ጽሕፈት ቤት ሐሙስ ጥር 7 ቀን 2012 ዓ.ም. በሕክምና፣ በፍተሻ፣ በኢንስፔክሽንና በሠርተፊኬሽን ዘርፍ ለሰባት ተቋማት አክሬዲቴሽን ሰጠ፡፡

በሕክምና ላቦራቶሪ አክሬዲቴሽንስ ዘርፍ በባህር ዳር የሚገኙት የፈለገ ሕይወት ኮምፕሬንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልና የጋምቢ ጠቅላላ ሆስፒታል ላቦራቶሪዎች፣ በጌዶ የሚገኘው የጌዶ ጠቅላላ ሆስፒታል እንዲሁም በአዲስ አበባ የሚገኘው የአዲስ አበባ የኅብረተሰብ ጤና ምርምርና ሪፈራል ላቦራቶሪ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡

በሠርተፊኬሽን ዘርፍ እንዲሁ የመጀመርያው የአክሬዲቴሽን ተጠቃሚ የሆነው የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት ሲሆን፣ ድርጅቱ የአክሬዲቴሽን አገልግሎት ተጠቃሚ የሆነው በሲስተም ሠርተፊኬሽን ነው፡፡ ሌላው የፍተሻ ላቦራቶሪ ዘርፍ ሲሆን በኬሚካል የፍተሻ ወሰን የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የአክሬዲቴሽን ተጠቃሚ ሆኗል፡፡ በኢንስፔክሽን ዘርፍ የአክሬዲቴሽን ተጠቃሚ የሆነው ደግሞ ኪውአይቲኤስ የተባለ ድርጅት ነው፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ አክሬዲቴሽን ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ አርዓያ ፍሰሐ እንደገለጹት፣ የፈለገ ሕይወት ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ የጋምቢና የጌዶ ጠቅላላ ሆስፒታል ላቦራቶሪዎች በሞሎኪዩላር ባዮሎጂ የአክሬዲቴሽን ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ የአዲስ አበባ የኅብረተሰብ ጤና ምርመራና ሪፈራል ላቦራቶሪ በኤችአይቪ፣ ዲኤንኤ እንዲሁም፣ ፒሲአር የፍተሻ ወሰን አክሬዲቴሽን ተጠቃሚ እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፣ ተቋማቱ የአክሬዲቴሽን አገልግሎት ተጠቃሚ በሆኑባቸው የፍተሻ ወሰኖች የተለያዩ የላቦራቶሪ ፍተሻዎችን ለማካሄድ የሚያስችላቸው ዕውቅና ያገኙ ሲሆን፣ የአክሬዲቴሽን ተጠቃሚ የሆኑት ተቋማት አክሬዲቴሽን ባገኙባቸው የፍተሻ ወሰኖች አማካይነት ለኅብረተሰቡ የሚሰጧቸው የላቦራቶሪ ፍተሻ ውጤቶች አስተማማኝና ተገልጋዩንም ከተደጋጋሚ ምርመራ ወጪ የሚታደጉት በመሆናቸው ፋይዳው ትልቅ ነው ብለዋል፡፡ ለሰባቱ ድርጅቶች የተሰጣቸው የአክሪዲቴሽን ፈቃድ ለአንድ ዓመት በቆየ ሒደት ውስጥ አልፈው እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት የአክሬዲቴሽን አገልግሎት ተጠቃሚ የሆነበት የሠርተፊኬሽን ዘርፍ የመጀመርያው እንደሆነ በማመልከት፣ ተቋሙ ከአሁን ቀደም በሌሎች ዘርፎች የአክሬዲቴሽን ተጠቃሚ በመሆን በተለይ የኢንስፔክሽን ዘርፍ በግብርና ምርቶች ኢንስፔክሽን የአገሪቱ ምርቶች ወደ ውጭ አገር በሚላኩበት ወቅት ትክክለኛ የኢንስፔክሽን አገልግሎት በመስጠት ምርቶች ወደ ዓለም ገበያ እንዲገቡ ለማስቻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

በኢንስፔክሽን ዘርፍ የአክሬዲቴሽን አገልግሎት ተጠቃሚ የሆነው ኪውአይቲኤስ ድርጅት ሲሆን፣ በኢንስፔክሽን ዘርፍ በአዲስ የፍተሻ ወሰኖች የአክሬዲቴሽን አገልግሎት ተጠቃሚ እንደሆነና ከአሁን ቀደም በኢንስፔክሽን ዘርፍ የአክሬዲቴሽን ተጠቃሚ ከሆኑት ተቋማት በተለየ በጨርቃ ጨርቅ፣ በፕላስቲክና በወረቀት ዘርፍ የአክሬዲቴሽን ተጠቃሚ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ጽሕፈት ቤቱ የተመሠረተበት ዋና ዓላማ የተስማሚነት ምዘና አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ማለትም ለላቦራቶሪ፣ ለኢንስፔክሽንና ለሠርተፊኬሽን ሥራዎች  የአክሬዲቴሽን አገልግሎት መስጠት እንደሆነ የገለጹት፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ አክሬዲቴሽን ጽሕፈት ቤት ምክትል ዳይሬክተር አቶ ጌትነት ጽጌመላክ ናቸው፡፡ ስለአክሬዲቴሽን አገልግሎት ሲገልጹም፣ ‹‹የአክሬዲቴሽን አገልግሎት ማለት በዓለም አቀፍ ደረጃ አንድን የተስማሚነት ምዘና ሰጪ ተቋም የቴክኒክ ብቃቱን በመገምገም የሚሰጥ ምስክርነት ማለት ነው፤›› ብለዋል፡፡

አክሬዲቴሽኑ ለሰባቱ ተቋማት በምን አግባብ እንደተሰጣቸው ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ ‹‹በሕክምና ላቦራቶሪዎች፣ በፍተሻ ላቦራቶሪዎች፣ በሠርተፊኬት እንዲሁም በኢንስፔክሽን ዘርፎች አክሬዲቴሽን የተሰጣቸው እነዚህ ድርጅቶች፣ በየዲስፒሊኑ ባሉ ደረጃዎች መሠረት ሰነዶች አዘጋጅተው፣ ሰነዶቻቸው ታይተውና ተገምግመው ምን ያህል ክፍተት አለባቸው የሚለውን ተፈትሾ ክፍተቶቻቸውን እንዲያስተካክሉ ከተደረገ በኋላ በድጋሚ በመስክ ግምገማ ምን ያህሉን ተግባራዊ አድደርገዋል የሚለው ተመዝኖ አክሬዲቴሽኑ ተሰጥቷቸዋል፤›› ብለዋል፡፡

እንደ አገር ሲታይ የተቋማት ለአክሬዲቴሽን ፍላጎት አነስተኛ ነው የሚሉት ምክትል ዳይሬክተሩ፣ በርካታ የላቦራቶሪ፣ የኢንስፔክሽን፣ እንዲሁም ጥቂት የሠርተፊኬሽን ተቋማት ቢኖሩም የአክሬዲቴሽን ተጠቃሚዎች ግን ከሚጠበቀው ቁጥር አንፃር ብዙም ዕድገት እንደማይታይበት ገልጸዋል፡፡

‹‹የተስማሚነት ምዘና አገልግሎት የሚሰጡ የግል እንዲሁም የመንግሥት ተቋማት፣ አክሬዲቴሽን እንዲያገኙ የበኩላቸውን ጥረት ማድረግ አለባቸው፤›› በማለት አክሬዲቴሽን ከተሰጣቸው ተቋማት በተጨማሪም ሌሎችም ድርጅቶች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በኢትዮጵያ የአክሬዲቴሽን አገልግሎት በአስገዳጅነት መሟላት ከሚጠበቅባቸው አገልግሎቶች ውስጥ ባለመካተቱ፣ የአክሬዲቴሽን አገልግሎት የሚያገኙ ድርጅቶች በራሳቸው ተነሳሽነት አገልግሎት ለማግኘት ወደ ተቋሙ እንደሚመጡና የአገልግሎቱ ተጠቃሚ በመሆናቸውም፣ ከገበያ ጀምሮ ለምርቶቻቸውና አገልግሎቶቻቸው ተዓማሚነትን የሚያረጋግጥ ጠቀሜታ እንደሚያገኙበት አብራርተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ አክሬዲቴሽን ጽሕፈት ቤት ተጠሪነቱ ለንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የሆነ የመንግሥት ተቋም ነው፡፡ አክሬዲቴሽን በምርት፣ አገልግሎት ወይም በሥርዓት ቴክኒካዊ ችግሮችን ለመቀነስና ለማስወገድ ከፍተኛ ዕገዛ ያለው ሲሆን፣ ንግድ እንዲያድግ ሀብት እንዲጨምር እንዲሁም የሥራ ድግግሞሽ በመቀነስ ወጪን መቀነስ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ለተስማሚነት ምዘና ተቋማት፣ ለተጠቃሚዎች፣ ለአክሬዲቴሽን ለተቆጣጣሪ ተቋማት እንዲሁም ለኢንዱስትሪዎች ጠቀሜታው እንደሚጎላ ተብራርቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች