ለአማራ ክልል ሕዝብ ድጋፍ እንዲሰጥ በተቋቋመው ጥረት ኮርፖሬት ሥር ከሚገኙ ዳሸን ቢራ አክሲዮን ማኅበርና ሌሎች ድርጅቶች ጋር በተያያዘ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በእስር ላይ የሚገኙት እነ አቶ በረከት ስምዖን፣ በመከላከያ ምስክርት ቆጥረዋቸው የነበሩትን ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ምስክርነት እንደማይፈልጉ ተናገሩ፡፡
አቶ በረከት ስምዖን፣ አቶ ታደሰ ካሳ (ጥንቅሹ) እና አቶ ዳንኤል ግዛው (የዴቬንተስ ባለድርሻ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸውንና የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝን በመከላከያ ምስክርነት መቁጠራቸው ይታወሳል፡፡
የተከሳሾቹን መከላከያ ምስክሮች ከጥር 4 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ የሰማው የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ በተከሳሾቹ ከተቆጠሩ ዘጠኝ ምስክሮች አምስቱን ሰምቶ እንደጨረሰ ሦስቱ ምስክሮች ግን በፋክስ የላኩትን የመጥሪያ ምላሽ ለችሎቱ አስታውቋል፡፡ ሦስቱም ባለሥልጣናት መጥሪያው እንደ ደረሳቸው አረጋግጠው፣ በሥራ ምክንያት በተጠሩበት ቀን መቅረብ እንደማይችሉ ማስታወቃቸውን ገልጸዋል፡፡
የተከሳሾች ጠበቆችም ያሰሟቸው አምስት መከላከያ ምስክሮች (አንዱ ተመሳሳይ በመሆኑ ትተውታል) በቂ መሆናቸውን ተናግረው፣ የባለሥልጣናቱን ምስክርነት እንደማይፈልጉት በማስረዳት፣ በተሰሙት ምስክሮችና የሰነድ ማስረጃዎች ብቻ ውሳኔ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡ በተለያዩ የክልሉ መንግሥት ተቋማት ያሉ የሰነድ ማስረጃዎች እንዲቀርቡላቸው ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸውም ጠይቀዋል፡፡
የጠበቆቹን ምላሽና አስተያየት የሰማው የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተጠየቁት ማስረጃዎች ለተከሳሾች እንዲደርሱ በማዘዝ፣ ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ በሰነዶቹ ላይ ያለውን አስተያተየት ለየካቲት 10 ቀን 2012 ዓ.ም. እንዲያቀርብ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡