Thursday, June 20, 2024

በትርምስ ማትረፍ አይቻልም!

የተልከሰከሰው ፖለቲካ ራሱን መቻል አቅቶት ሕዝብን በማንነት፣ በሃይማኖትና በተለያዩ ጉዳዮች ማጋጨቱን ቀጥሏል፡፡ ያልበሰሉ የፖለቲካ ተዋናዮችም ራሳቸውን መቻል አቅቷቸው፣ አጀንዳ እየመዘዙ ሕዝቡን እያጋጩ ነው፡፡ የሕዝብ ድምፅ በሴራና በአሻጥር የሚገኝ ይመስል፣ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ሕዝብን አለመተማመንና ጥርጣሬ ውስጥ መክተት የዘመኑ ብልጠት ሆኗል፡፡ የብሔር አልሳካ ያለ ሲመስል ወደ ቤተ እምነቶች መዝመት፣ እሱም አዋጭ አልመስል ሲል የሰንደቅ ዓላማ ንትርክ መፍጠር፣ የአዘቦቱ እንደ ልብ አልመች ሲልም በዓላትን የጦርነት አውድማ ለማድረግ ጥረቱ ቀጥሏል፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች እየታየ ያለው ይኸው ነው፡፡ የትርምስ አውሎ ንፋስ እየቀሰቀሱ ሰላማዊ ከባቢን ነውጥ ውስጥ መክተት እንዲቆም ካልተደረገ፣ የውድቀትን መንገድ ማስቆም ያዳግታል፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ በሥርዓተ አልበኞች ቁጥጥር ሥር እየዋለ ሕግ ማስከበር ካቃተ፣ መጪው ጊዜ ብሩህ ይሆናል ብሎ መጠበቅ ሞኝነት ነው፡፡ ከሥልጣኔ ጋር የተራራቁ በጥባጭ ፖለቲከኞች ትክክለኛውን መስመር ካልያዙ በስተቀር፣ አገሪቱ የሕገወጦችና የሥርዓተ አልበኞች መፈንጪያ መሆኗ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ የመንግሥት አስተዳደራዊ መዋቅሮችና የፀጥታ አካላት ኃላፊነታቸውን መወጣት ባቃታቸው ክልሎች ውስጥ የሚታየው አጉራ ዘለልነት፣ ለአገር ህልውና ጠንቅ እየሆነ ስለሆነ የመፍትሔ ያለህ መባል አለበት፡፡ ከአገር ህልውና የሚቀድም ምንም ነገር ስለሌለም፣ መንግሥት ሕግ የማስከበር ተግባሩን በሥርዓት መወጣት ይኖርበታል፡፡ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖችም ትርምሱን ለማስቆም በጋራ ሊነሱ የግድ ይላል፡፡

ኢትዮጵያ በዚህ የታሪክ አጋጣሚ ላይ ሆና በሰላማዊ መንገድ ሽግግር ማድረግ አለባት፡፡ ይህንን ሽግግር በሕዝቡ ፍላጎት መሠረት የማስቀጠል ኃላፊነት፣ በመንግሥት ላይ ብቻ የተጫነ አለመሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ እርግጥ ነው መንግሥት በሕግ የተሰጠውን ኃላፊነት ሥርዓት ባለው መንገድ መወጣት ይጠበቅበታል፡፡ እያንዳንዱ ዕርምጃውም በሕግ መቃኘት አለበት፡፡ ከአድሎአዊነትና ከአግላይነት አስተሳሰብ በመላቀቅ፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ በእኩልነት ማገልገል ኃላፊነቱ ነው፡፡ በአስተዳደርም ሆነ በፀጥታ ማስከበር ሥራዎች ላይ የተሰማሩ ሹማምንቱንም ሆነ የበታች ሠራተኞችን በሕግ መግራት አለበት፡፡ በተቻለ መጠን ለብልሹ አሠራሮች በር መክፈት የለበትም፡፡ መጪው ምርጫም በሥርዓት እንዲከናወን የሚጠበቅበትን ሁሉ ማድረግ ይኖርበታል፡፡ በሌላ በኩል በተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተደራጁ ወገኖችም ትልቅ ኃላፊት አለባቸው፡፡ የመጀመርያው ትልቁ ኃላፊነት ለሕግ መገዛት ነው፡፡ ራስን ለሕግ አለማስገዛት ለሕገወጥነት ጥብቅና መቆም ነው፡፡ ሌላው ትልቁ ጉዳይ ሕዝብ ማክበር አለባቸው፡፡ ለሰላሙና ለደኅንነቱ ጠንክረው መሥራት አለባቸው፡፡ ሐሰተኛ መረጃዎችን ከማሠራጨት መቆጠብ ግዴታቸው ነው፡፡ መጪው ምርጫ ያማረ እንዲሆን አስተዋጽኦ ማድረግ አለባቸው፡፡ ሌሎች የአገር ጉዳይ ይመለከተናል የሚሉም በዚህ መንፈስ መመራት ይኖርባቸዋል፡፡ ይህንን የተቀደሰ ኃላፊነትን ሳይወጡ መተናነቅ ተያይዞ መጥፋት ነው፡፡ ይኼ ደግሞ ለማንም አይበጅም፡፡

በተደጋጋሚ ለማስገንዘብ እንደሞከርነው ኢትዮጵያ ያጋጠማትን መልካም ዕድል ማበላሸት አይገባም፡፡ አንዴ ከእጅ ያመለጠን ዕድል ዳግም ለማግኘት ያስቸግራል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በዚህ ዘመን እያስቸገሩ ያሉት ደግሞ ማገናዘብ ይችላሉ ተብለው የሚታሰቡ ናቸው፡፡ ቢያንስ በታሪክ ውጣ ውረዶች ውስጥ ያጋጠሙ ችግሮችን ተገንዝበዋል ማለት ይቻላል፡፡ ነገር ግን ከታሪካዊ ስህተቶች ለመማር ፈቃደኛ የሆኑ አይመስሉም፡፡ አንዳንዶቹ በነጭና በቀይ ሽብሮች ዘመን ዋነኛ ተሳታፊና ግብረ አበር የነበሩ ሲሆን፣ የሚከተሉዋቸው ደግሞ ያንን አሳፋሪ ታሪክ በሚገባ የሚያውቁ ናቸው፡፡ የተቀሩት ደግሞ በቅርቡ ዘመን የግፍ እስራትና ስደት ሰለባ ከመሆን አልፈው፣ በዚህ በለውጡ ዘመን ዕፎይታ ያገኙ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ ወቅቱ ይዞት የመጣውን መልካም አጋጣሚ በጋራ ከመንከባከብና ወደ ተሻለ ደረጃ ከማድረስ ይልቅ፣ ጎራ ለይተው ሕዝብን ለማፋጀትና አገርን መቀመቅ ለመክተት የቆረጡ ይመስላሉ፡፡ በመገናኛ ብዙኃን ብቅ ባሉ ቁጥር መርዝ ይተፋሉ፡፡ ደጋፊዎቻቸውን ለነውጥ ያነሳሳሉ፡፡ አንድም ቀን ስለሕግ የበላይነት፣ ስለእኩልነት፣ ስለፍትሐዊነት፣ ስለነፃነት፣ ወዘተ ሲያቀነቅኑ አይሰሙም፡፡ ሁልጊዜም ብሶት፣ ምሬት፣ አሉባልታ፣ ሐሜት፣ ጥላቻና አገር ስለማተራመስ ነው የሚያወሩት፡፡ በሰላማዊ የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ ሆነው የጦርነት ነጋሪት ይጎስማሉ፡፡ እንዲህ ተሁኖ ነው ወይ ዴሞክራሲ ሥርዓት የሚሆነው? መልሱን ለባለቤቶቹ መተው ይሻላል፡፡  

በአሁኑ ጊዜ በየቦታው የሚሰማው ሁሉ ከችግር ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ሰርጎ በመግባት ተማሪዎችን ማሸበር፣ መግደልና ማሳደድ ዓላማው ምን እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ በዓላት በመጡ ቁጥር ማንነትን፣ እምነትንና ሰንደቅ ዓላማን እየታከኩ ነውጥ መፍጠር የሚፈለገው በምክንያት ነው፡፡ በግለሰቦች መካከል የተፈጠሩ ዕለታዊ ጠቦችን ወደ ብሔርና እምነት በመቀየር፣ ዜጎችን እርስ በርስ ማፋጀት ራሱን የቻለ ዓላማ አለው፡፡ ሐሰተኛ መረጃዎችን እያሠራጩ በኢትዮጵያውያን መካከል አለመተማመን መፍጠር ግቡ ምን እንደሆነ ይታወቃል፡፡ አንድም ትርምስ በመፍጠር ሥልጣን ላይ በአቋራጭ መንጠላጠል፣ ካልሆነም የጠላት መሣሪያ በመሆን አገርን መበታተን ነው፡፡ በዚህ ትርምስ የመፍጠር ሩጫ ውስጥ የግጭት አውሎ ንፋስ አንዴ ከተነሳ፣ ሁሉንም ጠራርጎ ነው የሚወስደው፡፡ አውሎ ንፋስ እየተግለበለበ የሰዎች ዓይን ውስጥ ጉድፍ እንደሚሞጅረው ሁሉ፣ ነውጠኞች የሚቀሰቅሱት የትርምስ አውሎ ንፋስ የራሳቸውን ሕይወት ጭምር ዋጋ ያስከፍላል፡፡ ለሕግ መገዛት፣ በሕግ መጠየቅና ማስጠየቅ ነውር እየተደረገ በየአካባቢው ትናንሽ ጉልበተኞች ሲፈጠሩ፣ ዳፋው ለሚያሰማሯቸው ጭምር ነው፡፡ አስተዳደራዊ መዋቅሮችና የፀጥታ አካላት ሥራቸውን ማከናወን ሲያቅታቸው፣ ታይቶም ተሰምቶም የማያውቅ አምባገነንነት በአቋራጭ ይመጣና የሁሉም ነገር ፍፃሜ ይሆናል፡፡ ይህ እንዳይሆን ግን በሥርዓት ኃላፊነትን መወጣት ይሻላል፡፡ ያለው ብቸኛ አማራጭ እሱ ብቻ ነው፡፡

የፖለቲካ ፓርቲ የመሠረታችሁ፣ ጥምረትም ሆነ ውህደት የፈጸማችሁ፣ በፖለቲካ ፓርቲዎች ወይም በስብስቦች ዙሪያ ያላችሁ፣ የአገር ጉዳይ ያገባናል የምትሉ፣ ወዘተ ከምንም ነገር በፊት የአገር ህልውና ያስጨንቃችሁ፡፡ በታሪክ አጋጣሚ የተገኙ ዕድሎች እንዴት እንደተበላሹ መርምሩ፣ ስህተትን በስህተት የመድገም ስብራቶችን አስወግዱ፣ ከአጉል እልህና ግትርነት ተላቀቁ፣ ሥልጡን ለሆኑት የዴሞክራሲ ሕግጋት ተገዙ፣ በሰጥቶ መቀበል መርህ ተባበሩ፣ ለልዩነቶቻችሁ ዕውቅና ተሰጣጡ፣ በመጨረሻም ሥልጣን የሕዝብ አንጡራ ሀብት መሆኑን ተገንዝባችሁ ሰላማዊና ዴሞራሲያዊ ምርጫ እንዲኖር በትጋት ሥሩ፡፡ ሕዝብና አገሩን የማያከብር ፖለቲከኛም ሆነ ሌላው ፋይዳ ቢስ ነው፡፡ ጊዜው ተመችቶኛል በማለት የሕገወጥነትንና የሥርዓተ አልበኝነትን ዓርማ ማውለብለብ አያዋጣም፡፡ ለጊዜው ገንዘብ፣ ክብርና ዝና የተገኘ ቢመስልም ረጋፊ ነው፡፡ ሕዝብ ትናንት አምኖ ከፍ አድርጎ የሰቀለውን እንዴት ፈጥፍጦ እንደሚጥል ያውቅበታል፡፡ ፍሬውን ከገለባ መለየት ይችልበታል፡፡ ሕዝብ እንደ ረጋ የኩሬ ውኃ ነው፡፡ የተንቀሳቀሰ ዕለት እንደ ማዕበል ማቆሚያ የለውም፡፡ ትናንት በስሙ ስትቆምሩ የነበራችሁም ሆነ ዛሬ በአፍላነት ስሜት ደማችሁ የሚንተከተክ ስከኑ፡፡ ሕዝብ ወንፊቱን ይዞ ሲነሳ ፍሬውን ከዕብቁ እንዴት እንደሚለይ ያሳያችኋል፡፡ አገር በማተራመስ ሥልጣን ለመያዝ ከመቅበጥበጥ፣ ለሕዝብ ፈቃድ መገዛት ያስከብራል፡፡ በስሜት እየተነዱ ማንንም እንደፈለጉ የመንዳት ፍላጎት የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ተረት ይሆናል፡፡ በማተራመስ ማትረፍ እንደማይቻል በሕዝብ ድምፅ ይረጋገጣል!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...

ብሔራዊ ባንክ ጥርስ እያወጣ ይሆን እንዴ?

በአመሐ ኃይለ ማርያም ‹‹Better late than never›› (ከቀረ የዘገየ ይሻላል) የኢትዮጵያ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ የተንሰራፋው ሌብነት ልዩ ትኩረት ይሻል!

በየዓመቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከበጀት ረቂቅ በፊት መቅረብ የነበረበት የፌዴራል ዋና ኦዲተር ግኝት ሪፖርት ማክሰኞ ሰኔ 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ዘግይቶ ሲቀርብ፣ እንደተለመደው...

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች መካከል አንዱ፣ የዋጋ ንረትን ለመቀነስ ምን ታስቧል የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ በጀት ለተለያዩ መንግሥታዊ ወጪዎች ሲደለደል...

ባለሥልጣናት የሚቀስሙት ልምድ በጥናት ይታገዝ!

ሰሞኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተመራ የከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ልዑክ፣ ከሲንጋፖር ጉብኝት መልስ በሁለት ክፍሎች በቴሌቪዥን የተገኘውን ልምድ በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡ ለአገር...