Wednesday, May 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊየውጭ ሪል ስቴት ኩባንያዎች ከፍተኛ ዋጋ ማቅረባቸው እያነጋገረ ነው

የውጭ ሪል ስቴት ኩባንያዎች ከፍተኛ ዋጋ ማቅረባቸው እያነጋገረ ነው

ቀን:

መንግሥት 27 በመቶ ድርሻ በያዘበት ሪል ስቴት ለስቱዲዮ ከስድስት ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ቀርቧል

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰፊው ሕዝብ ተጠቃሚ ያደርጋል ያለውን የቤት ልማት መርሐ ግብር በመንግሥትና በግል ባለሀብቶቹ የጋራ ልማት ማስኬድ መጀመሩን በማስመልከት ከውጭ አልሚዎች ጋር እየሠራ ቢሆንም፣ በሪል ስቴት ኩባንያዎች የሚቀርበው ከፍተኛ ዋጋ ግን አሳሳቢ መሆኑ እየተገለጸ ነው፡፡ 

 በቅርቡ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ የግል ተቋራጮች፣ አልሚዎችና ባለሀብቶች ጋር በተደረገ ስብሰባ ወቅት ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) እንዳስታወቁት፣ መንግሥት ባለድርሻ በመሆን ከባለሀብቶች ጋር በጋራ ቤቶችን በመገንባት ሥራዎች ውስጥ በሰፊው ይሳተፋል፡፡ ለዚህም መንግሥት መሬት ከማቅረብ አልፎ የግንባታውን ሒደት ከጅምሩ እስከ ፍፃሜው የሚከታተል አካል መዋቀሩን አስታውቀው ነበር፡፡

- Advertisement -

 ይሁን እንጂ አንዳንዶቹ የውጭ ሪል ስቴት አልሚዎች ለሚገነቧቸው ቤቶች የሚያወጧቸው የሽያጭ ዋጋዎች መጋነናቸው፣ በመንግሥት ላይ ጥያቄ እንዲነሳበት ማድረጋቸው እየተገለጸ ነው፡፡ ለአብነትም በቅርቡ ሽያጭ መጀመሩን እያስተዋወቀ የሚገኘውና ኢግል ሒልስ የተሰኘው የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ሪል ስቴት ኩባንያ፣ ቤቶቹን መገንባት ሳይጀምር ሽያጭ መጀመሩን እያስተዋቀ ነው፡፡ ለስቱዲዮ ያቀረበው የመሸጫ ዋጋ በዱባይ ከተማ ከሚጠየቀውም በላይ የተጋነነ መሆኑን የሪፖርተር ምንጮች ይገልጻሉ፡፡

ሽያጭ የጀመረው ኢግል ሒልስ ሪል ስቴት ኩባንያ ቦታ መያዣ ቅድመ ክፍያን ጨምሮ፣ እ.ኤ.አ. በ2023 እንደሚያጠናቅቃቸው ለሚጠበቁ ቤቶች የዋጋ ዝርዝር በማውጣት ሽያጭ ጀምሯል፡፡ በዚሁ መሠረት ለስቱዲዮ የሚጠይቀው የመሸጫ ዋጋ 202 ሺሕ ዶላር ወይም ከስድስት ሚሊዮን ብር በላይ፣ ባለ አንድ መኝታ ከ230 ሺሕ ዶላር፣ ባለሁለት መኝታ ከ320 ሺሕ ዶላር ጀምሮ፣ ባለ ሦስት መኝታ ከ450 ሺሕ ዶላር ጀምሮ ዋጋ ሲወጣለት፣ ባለ አራት መኝታ ከ550 ሺሕ ዶላር ጀምሮ እንደሆነ በሪል ስቴት ኩባንያው እየተዋወቀ ነው፡፡

በአንፃሩ ኢትዮጵያውያን በዱባይ ከተማ አፓርታማዎችን እንዲገዙ በአዲስ አበባ የሚያስተዋውቁ ኩባንያዎች ባለ አንድ መኝታ አፓርታማዎች የሚሸጡበት ዋጋ፣ በአዲስ አበባ ኢግል ሒልስ ለስቱዲዮ ቤት ካቀረበው ዋጋ በታች ናቸው፡፡ ለአብነት አንድ ስቱዲዮ አፓርትመንት በኢግል ሒልስ የሚሸጥበት የአዲስ አበባ ዋጋ በዱባይ ለባለ አንድ መኝታ ከቀረበው ዋጋ ያነሰ ሆኖ መገኘቱን በማመላከት፣ የሪል ስቴት አልሚው አካሄድ የሌሎች አልሚዎችን ዋጋ ሊያንር ይችላል የሚል ፍራቻ እንዳደረባቸው የኩባንያውን የሽያጭ ሒደት በሐያት ሬጀንሲ ሆቴል የተከታተሉ ይናገራሉ፡፡ ከሁሉ በላይ መንግሥት 27 በመቶ ባለድርሻ የሆነበት ይህ የለገሃር ፕሮጀክት በዚህ ደረጃ ከፍተኛ ዋጋ ያላቸውን አፓርታማዎች ማስተዋወቁም አስገራሚ እንደሆነባቸው አስረድተዋል፡፡

ምክትል ከንቲባ ታከለ በበኩላቸው መንግሥት በጋራ ማልማት ሥራ በሰፊው እንደሚሳተፍ ከማስታወቅ ባሻገር፣ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ወይም አልሚዎችና አቅሙ ያላቸው ተቋራጮች ከመንግሥት ጋር በአጋርነት ከላይ እንደተጠቀሰው የዱባይ ሪል ስቴት አቅም ፈጥረው አብረው እንዲሠሩ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡ በዚህ መንገድ ከነዋሪዎች አቅም ጋር የተመጣጠኑ በርካታ ቤቶችን ገንብቶ ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚቻል መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

‹‹አዲስ አበባ ለሁሉም የምትመች የመኖሪያ ከተማ ትሆናለች፤›› ያሉት ምክትል ከንቲባው፣ መንግሥት በሊዝ መሬት ለጥቂት ግለሰቦች ከማስተላለፍ ይልቅ በወል አልምተው ብዙዎችን ተጠቃሚ ለሚያደርጉ አልሚዎች ቢሰጥ እንደሚጠቅምም አስታውቀው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ከጅምሩ ከፍተኛ ዋጋ የሚጠየቅባቸው የሪል ስቴት ግንባታዎችና አፓርታማዎች፣ ፕሮጀክቱ ይፋ በተደረገበት ወቅት በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሲገለጽ ከነበረው ይልቅ ከፍተኛ ሀብት ላካበቱ የሚውሉ እንጂ ከመካከለኛ ደረጃ ጀምሮ ጥሪት ላላቸው ቤት ፈላጊዎች የማይቀመሱ እየሆኑ መገኘታቸው ከወዲሁ እንደሚያሳስብ እየተገለጸ ነው፡፡ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ቤት ፈላጊዎች ይህን ይበሉ እንጂ፣ በአብዛኛው ቤቶቹ ‹‹ሌግዠሪ›› በሚባል ደረጃ የሚገነቡ መሆናቸውንም ኩባንያው በሚለቃቸው ማስታወቂያዎች እየተገለጸ ነው፡፡

ኢግል ሒልስ በአዲስ አበባ ከ4,000 ሺሕ በላይ መኖሪያ አፓርታማዎችን ጨምሮ በ360 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ለንግድ፣ ለሆቴል፣ ለመዝናኛና ለመሳሰሉት አገልግሎቶች የሚውሉ ቅይጥ ግንባታዎችን በማካሄድ እንደሚሳተፍ ማስታወቁና የግንባታ እንቅስቃሴ መጀመሩ ይታወሳል፡፡ ኢትዮጵያን ስድስተኛው መዳረሻው ያደረገው ኢግል ሒልስ በሰርቢያ፣ በባህሬን፣ በሞሮኮ፣ በኦማን፣ እንዲሁም በዮርዳኖስ ልዩ ልዩ የሪል ስቴት ፕሮጀክቶች ያሉት፣ እ.ኤ.አ. በ2014 በአቡ ዳቢ ከተማ ዋና መሥሪያ ቤቱን ያደረገ የግል ሪል ስቴት አልሚ ኩባንያ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...