የጥር ወር በተለይ የሚታወቅበት ጥንዶች ጎጆ የሚቀልሱበት፣ ትዳር የሚመሠርቱበት፣ ሠርግ የሚደግሱበት በመሆኑ ነው፡፡ በሐውርታዊት (ባለ ብዙ ብሔረሰቦች) በሆነችው ኢትዮጵያ ካሉት ከሚኖሩት ልዩ ልዩ ባህሎች መካከል ሦስት ጉልቻ ሲጎለት የሚፈጸመው ዓይነት ይጠቀሳል፡፡ የተለያዩ የየብሔረሰቡ አሻራ ያረፈባቸው የጋብቻ ሥርዓቶች አሉ፡፡
በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የደቡብ ኦሞ ምርምር ማዕከል በደቡብ ኦሞ ዞን በሚገኙት 16 ብሔረሰቦች ባህላዊ ቅርሶች ዙሪያ ትኩረቱን በባህላዊ የአስተዳደር ሥርዓት፣ የጋብቻ ሥነ ሥርዓት፣ እንዲሁም ባህላዊ ክብረ በዓል ላይ ያደረገ ቅኝት በሀገሬ ሚዲያ አማካይነት በማድረግ ለኅትመት አብቅቷል፡፡
የጋብቻና የሠርግ ቅኝት ከተደረገባቸው መካከልም የሐመርና የበና ብሔረሰቦች ይገኙበታል፡፡ በዚህ መጣጥፍ የሁለቱን ብሔረሰቦች የሦስት ጉልቻ ትውፊት እንደሚከተለው ተቀናብሯል፡፡
ሐመር
የሐመር ብሔረሰብ በዋናነት በሐመር ወረዳ ውስጥ ይኖራል፡፡ “ሐመር” የሚለው የብሔረሰቡ መጠሪያ ቃል በብሔረሰቡ ቋንቋ ‹‹በተራራና በድንጋይ መካከል የሚኖሩ የተዋሃዱና የተቀላቀሉ ሕዝቦች›› የሚል ፍቺ እንዳለውና ይህም ሐመሮች በጥንት ዘመን በትላልቅና ሰንሰለታማ በሆኑ ተራራዎች መካከል በሚገኙ የተቦረቦሩ ቋጥኞች ውስጥ ይኖሩ እንደነበር የሚያመላክት እንደሆነ አፈ ታሪካዊ መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡
ዋነኛ መተዳደሪያቸው ከብት እርባታ ሲሆን ከዚህ ጎን ለጎን ንብ በማነብና በዝቅተኛ ደረጃ ደግሞ በቆሎና ማሽላ ለዕለት ፍጆታ በማምረት ኑሯቸውን ይመራሉ፡፡
በብሔረሰቡ አምስት ዓይነት የጋብቻ ሥርዓቶች አሉ፡፡ እነዚህም በቤተሰብ ስምምነት የሚፈጸም ጋብቻ፣ ‹‹ኪንዳል ቃይስ›› በሁለቱ ተጋቢዎች ስምምነት የሚፈጸም ጋብቻ፣ “የዶት” የጠለፋ ጋብቻ፣ “ኢሽሜና” የውርስ ጋብቻ እና “መርማ” የምትክ ጋብቻ በመባል ይታወቃል፡፡ አንድ ለአቅመ አዳም የደረሰ ወጣት ጋብቻ ከመፈጸሙ በፊት አስቀድሞ ለጥሎሽ የሚሆኑ ከብቶችን በግሉ ማርባት፣ ቀፎ ሰቅሎ ማር መቁረጥ፣ ጎጆ መቀለስ፣ መገረዝ፣ ከብት መዝለል በምንም መልኩ የማይታለፉ ባህላዊ ግዴታዎች ናቸው፡፡ “ኡኩሊ” ለአቅመ አዳም የደረሰና ከብት ለመዝለል ዝግጁ የሆነ የሐመር ወጣት የሚጠራበት የማዕረግ ስም ነው፡፡ አጭር ዱላ ከወገቡ ላይ (ከወደ ጀርባው በኩል) ይሸጉጣል፤ ከወገቡ በላይ ራቆቱን ይሆናል፡፡
“ኡኩሊ” ከብት በሚዘልበት ዕለት ሥርዓቱ በሚፈጸምለት ሥፍራ ላይ በቅርብም ይሁን በሩቅ ያሉ ዘመዶቹ እንዲገኙ የመጥራት ኃላፊነት አለበት፡፡ ይህ ኃላፊነትም የኡኩሊው መንፈሳዊና አካላዊ ጥንካሬ የሚለካበት አንዱ መንገድ እንደሆነ ይነገራል፡፡ በዚህ ጥሪ መሠረትም ዘመዶቹ ሥርዓቱ በሚፈጸምበት ቦታና ዕለት ይገኛሉ፡፡
የከብት መዝለል ባህላዊ ሥርዓት ከመጀመሩ አስቀድሞ በሥርዓቱ ላይ በብሔረሰቡ የተለመደው የግርፋት ሥርዓት ይከናወናል፡፡ የሚገረፉት የከብት ዘላዩ የቅርብ ዘመድ የሆኑ ሴቶች ሲሆኑ ገራፊዎቹ ደግሞ የኡኩሊ ጓደኞች ወይም አጃቢ የሆኑ ወንዶች ናቸው፡፡ ይህን የሚያደርጉትም ወንድማቸው ከብት ለመዝለል በመብቃቱ የተሰማቸውን ከፍተኛ ደስታ ለመግለጽ፣ ዝምድናቸውንና ተቆርቋሪነታቸውን ለማሳየት እንደሆነ ይነገራል፡፡ ይህን ባይፈጽሙ ዘላዩ ዘመድ እንደሌለው ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ እሱም ቢሆን በዚያን ዕለት በሥርዓቱ ላይ ተገኝታ ያልተገረፈችለትን ሴት እንደዘመድ አይቆጥራትም፡፡
የግርፋት ሥርዓቱ እንዳበቃ ዘመድ አዝማዶች በተሰበሰቡበት ከብት የመዝለሉ ሥርዓት ይከናወናል፡፡ ከብት የመዝለሉ ሥርዓት እንደተጠናቀቀ ይጨፍራሉ፡፡ ይህም በሐመርኛ “ኡኩሊ ጋዲ” በመባል ይታወቃል፡፡ የኡኩሊ ጭፈራ ወይም ከብት ለዘለለ ልጅ ክብር የሚደረግ ጭፈራ ማለት ነው፡፡ ጭፈራው የሚከናወነው በምሽት ወቅት በጨረቃ ብርሃን በመታገዝ ነው፡፡ የዘላዩ ወላጆች “ልጃችንን ለቁም ነገር አድርሰናል፤ በዚህም ተደስተናል፡፡” ብለው ደግሰው ልጃቸው ለአካለ መጠን መድረሱንና ጋብቻ ለመፈጸም የሚያስችለውን አስፈላጊ የሆኑ ባህላዊ ግዴታዎችን ማሟላቱን የሚያውጁበት ሥርዓት ነው፡፡
“ኡኩሊው” ከብት ከዘለለ በኋላ “ማዝ” የሚል የማዕረግ ስም ይሰጠዋል፡፡ ማዝ ከኢኩሊ ጋዲ ሥርዓት ማግሥት ጀምሮ ሚስት እስከሚታጭለት ድረስ ከሥጋ፣ ከማርና ከወተት በስተቀር እህል አይበላም ወይም እንዲበላ ባህላዊ ሕጉ አይፈቅድለትም፡፡ በዚህ ሁኔታ እስከ ሦስት ወር ሊቆይ ይችላል፡፡
እህል መቅመስ የሚችለው ሚስት ሲያጭ ብቻ ነው፡፡ ለእሱ የምትሆነውን የሚያጭለትና የሚመርጥለት ወላጅ አባቱ ነው፡፡ አባቱ ጥሩ ሚስት ትሆነዋለች ብሎ የመረጠለትን ልጃገረድ በይፋ እስከሚነግረው ድረስ ማዝ ወደፊት በሚያገባት በእጮኛው አንገት ላይ በሚያስርላት በድኩላ ቆዳ በተሠራ ቀበቶ ወገቡን በማሰር ረሃቡን ያስታግሳል እንጂ እህል አይቀምስም፡፡
አባት ምርጫውን ይፋ ካደረገ በኋላ የልጅቷን ወላጆች ፈቃድ ለማግኘት ሽማግሌ ይልካል፡፡ የልጅቱ ወላጆች ጋብቻውን ከፈቀዱ ማዝ እና እጮኛው በአንድ ማዕድ ላይ ቀርበው እንዲጎራረሱ ይደረጋል፡፡ ከመጎራረሳቸው በፊት ግን “ቢኛሬ” ውን ከእጮኛው አንገት ላይ በማድረግ ያጫታል ወይም የቃል ኪዳን ማሰሪያ ያደርግላታል፡፡ ይህ ከሆነ በኋላ ከበሬታ ስለሚሰጣት ማንም ወንድ ቀና ብሎ አያያትም፡፡ ማዝ ካጨ በኋላ “ዶንዛ” የሚል ሌላ የማዕረግ መጠሪያ ይሰጠዋል፡፡ በሐመር ብሔረሰብ ከአንድ በላይ ሚስት ማግባት የተለመደ ነው፡፡ ይህን የሚወስነው አግቢው ያለው የከብትና የሀብት መጠንና የመጀመርያ ሚስቱ መልካም ፈቃደኝነት ነው፡፡
ኢቫንጋዲ የሐመር ብሔረሰብ የሚታወቅበት ባህላዊ ጭፈራ ነው፡፡ “ኢቫን” “ጋዲ” ማለት ደግሞ ጭፈራ የሚል ትርጉም አለው፡፡ ኢቫንጋዲ በአዝመራ ወቅት በሥራ የደከመን አዕምሮና አካል ለማዝናናት ሲባል የሚደረግ ባህላዊ ጭፈራ ሲሆን የሐመር ወጣት ወንዶችና ልጃገረዶች ብቻ የሚሳተፉበት ከማኅበራዊ ሕይወት ጋር የሚተዋወቁበት አዳዲስ ባህላዊ ዘፈኖችንና የአጨፋፈር ሥልቶችን የሚቀስሙበት አጋጣሚ ነው፡፡ ጭፈራውም በየሦስት ቀን አንዴ በሐመር መንደሮች በምሽት ጨረቃ ይካሄዳል፡፡
በና
የበና ብሔረሰብ በበና ፀማይ ወረዳ ውስጥ ከሚገኙት ብሔረሰቦች መካከል አንዱ ሲሆን በቦሪ፣ አልዱባ፣ ሻባ፣ አረጎ፣ ቃቆ፣ በፎ፣ አንሶንዳ፣ ኡሩሪና ሙቀጫ ተብለው በሚታወቁ ቀበሌዎች ውስጥ በዋናነት ይገኛል፡፡
በበና ብሔረሰብ ጋብቻ ለመፈጸም በመጀመርያ መሟላት ያለበት ቅድመ ሁኔታ አለ፡፡ ለአካለ መጠን የደረሰ ወንድ ልጅ የትዳር ጓደኛ ከመምረጡ በፊት ማኅበራዊ ደንቡ የሚያዘውን የከብት ዝላይ ማከናወን ግዴታው ነው፡፡ ወጣቱ ይህን ከማከናወኑ በፊት ለመዝለል መዘጋጀቱን ለዘመድ አዝማድ እየዞረ ይናገራል፡፡ የከብት ዝላዩን በአግባቡ ዘሎ ካጠናቀቀ መዝለሉን ለማሳየት በወገቡ ላይ ከቆዳ የተሾረበ ጠፍር ያስራል፡፡ ጠፍሩም ከዝላይ በኋላ በምትታጭለት ልጃገረድ አንገት ላይ የሚያደርገው ነው፡፡
የከብት ዝላዩ ከተከናወነ በኋላ የማጨቱ ሒደት ይቀጥላል፡፡ ዘላዩ ከብቶችን ዘሎ ካጠናቀቀ በኋላ እስከሚያጭ ወይም እስከሚታጭለት ድረስ ከወተት፣ ከማርና ከሥጋ በስተቀር እህል አይቀምስም፡፡ ከመዝለሉ በፊት በአግቢው ቤተሰብ የታሰበች /የተመረጠች/ ልጅ ካለች ሽማግሌ ተልኮ ይጠየቃል፡፡
በቤተሰብ የተመረጠች ልጅ ከሌለችም የሚያጫትን ልጅ እስከሚያገኝ ድረስ ከራሱ ጎሳ ውጪ የሆነችን ሴት ይፈልጋል፡፡ የሚፈልጋትን ልጅ እንዳገኘም በኃይል በመያዝ በጉልበት እህል ያቀምሳታል፡፡ እህል ካቀመሳት አጭቷታል ተብሎ ስለሚታመን ከርሱ ውጭ ለማንም አትሰጥም፡፡ እህል ባቀመሳት ወቅት ልጅቱ ሕፃን ልትሆን ስለምትችል ከ15 እስከ 20 ዓመት ድረስ ከቤተሰቦቿ ጋር ልትቆይ ትችላለች፡፡ ከዚህ በኋላ ሽማግሌ በመላክ፣ በጉልበት ወይም በሠርግ ሊወስዳት ይችላል፡፡ በዚህ መልኩ ከብት በመዝለል የሚያገቧት የመጀመርያ ሚስት “ብኛሬ” የሚል ስያሜ የሚሰጣት ሲሆን የምትለይ አንገት ላይ የሚታሰር ጌጥ ታደርጋለች፡፡ ከብኛሬ በኋላ የሚያገቧት ሚስት ደግሞ “ማሪ” በመባል ትታወቃለች፡፡
በከብት ዝላይ ወቅት የተለየ ባህላዊ የጭፈራ ሥርዓት ይከናወናል፡፡ የጭፈራው ሥርዓት እሸት ሊደርስ ሲል ጀምሮ እስከ በጋ ወቅት መግቢያ ድረስ የሚዘልቅ ነው፡፡ የከብት ዘላዩ ያገቡ ሴት ዘመዶች በከብት ዝላዩ ወቅት በአዳራሽ ውስጥ ቁጭ ብለው “ይሳሮ” /አዳጎይኖ/ የሚባል ጨዋታ ይጫወታሉ፡፡ በጨዋታው ወቅት የዘላዩ የአባት ወገን ያገቡ ሴቶችና ልጃገረዶች እንዲሁም የእናት ወገን አክስቶች ይገረፋሉ፡፡ በሚገረፉበት ወቅት የዘላይ ዘመዳቸውን ጀግንነት ያለውን የከብት ብዛትና ሌሎች ነገሮች እየጠቀሱ ይፎክራሉ፡፡
ከእናት ወገን ያገቡ ሴቶች ግን በዝላዩ ወቅት በአዳራሽ ውስጥ ይጨፍራሉ እንጂ የግርፊያው ሰለባ አይሆኑም፡፡ በሌላ ወገን በከብት ዝላይ ወቅት ወጣት ወንዶችና ልጃገረዶች ከምሽቱ ሦስት ሰዓት አካባቢ ጀምሮ ‹‹ኢቫንጋዲ›› የሚባል ባህላዊ ጨዋታ በጋራ ይጫወታሉ፡፡ በጨዋታው ወቅት ጨዋታውን ለማድመቅ “ዋርዋራ” ተብሎ የሚጠራ እንደቃጭል የሚጮህ ነገር በእግራቸው ላይ ያስራሉ፡፡ “ቃቃ” የሚባል ከእንጨት የሚሠራ ነገር ለጭብጨባ ማድመቂያነት ይጠቀማሉ፡፡