በሔለን ተስፋዬ
መቄዶኒያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል በባህር ዳር ከተማ ለሚገነባው መጠለያ አሥር ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ በስጦታ ማግኘቱ ተገለጸ፡፡ የመሬት ካርታውንም ከአማራ ክልል ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ሙሉነሽ ደበበ (ዶ/ር) እጅ ተረክቧል፡፡ ማዕከሉ ከ3000 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች መጠለያ እንደሚሆን ተነግሯል፡፡
የአማራ ክልል የመቄዶኒያ አስተባባሪ አቶ ማህተመ በቃሉ በደብረ ብርሃን፣ በጎንደር፣ በደሴ ከተሞች በእያንዳንዳቸው አምስት ሺሕ ካሬ ሜትር እንዲሁም በድሬዳዋ፣ በአዳማ፣ በሐረር ሌሎች ማዕከሎች መገንባት የሚያስችሉ ቦታዎች መገኘቱን ገልጸዋል፡፡
በእነዚህ ቦታዎች መቄዶኒያ በጎ ሥራውን ከጀመረ ወደ አዲስ አበባ የሚመጣውን የተረጂዎች ፍሰት ለመቀነስ ጉልህ ሚና ይኖረዋል ያሉት አቶ ማህተመ፣ በደብረ ማርቆስ ከተማ የተገነባውን የመቄዶኒያ ሕንፃ በቅርቡ እንደሚረከቡም አቶ ማህተመ ተናግረዋል፡፡
መቄዶኒያ በአዲስ አበባና ሌሎች ከተሞች ለሚያደርገው ግንባታ 21 ሚሊዮን ብር ወጪ የሚጠበቅበት በመሆኑ፣ በመጪው መጋቢት 6 ቀን 2012 ዓ.ም. በሚሌኒየም አዳራሽ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር እንዳዘጋጀ አስታውቋል፡፡