በተለያዩ የመሪዎች ኮንፈረንሶች ላይ ተገኝተው በሚያደርጉት ወጣ ያለ ንግግርና ድርጊት ይታወቃሉ፡፡ በሰብዓዊ መብት ጥበቃ፣ በኢኮኖሚ ዕድገት፣ በዴሞክራሲ ልቀት ጣራ ነክተናል ብለው የሚመፃደቁ ምዕራባውያንን ማብሸቅ የሚወዱ ይመስላሉ፡፡ በየመድረኩ አወዛጋቢ ነገር ማንሳታቸው አይቀርም ተብሎ ስለሚታሰብም ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ሲናገሩ ወዳጆቻቸውም ሆኑ ባላንጣዎቻቸው በተጠንቀቅ ያደምጣሉ፡፡
በታሪካዊ ፎቶግራፍ ላይ ከፕሮቶኮል ውጪ ፈንጠር ብለው ታይተው ያውቃሉ፡፡ የጀርመኗን ፕሬዚዳንት አንጌላ መርኬልን የሆነ ነገር ተናግረው ‹‹ጀመረው እንግዲህ›› በሚል አተያይ ሲያዩዋቸው በካሜራ ተቀርፀዋል፡፡ ብቻ በተገኙባቸው መድረኮች የተለየ ነገር ማለታቸው ማድረጋቸው አይቀርም፡፡ ባለፈው ሳምንት ይፋ ያደረጉት የሩሲያን የአስተዳደር ምኅዳር የሚለውጥ አዲስ ምክረ ሐሳብ እንዲሁ መነጋገሪያ ሆኖ ነው የሰነበተው፡፡
ፕሬዚዳንት ፑቲን ሩሲያ ከፕሬዚዳንታዊ ወደ ፓርላሜንታዊ የአስተዳደር ሥርዓት የምትሸጋገርበትን ሕገ መንግሥታዊ ለውጥ ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ጥር 5 ቀን አቅርበዋል፡፡ የፑቲንን መግለጫ ተከትሎም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዲምትሪ ሜድቬዴቭ ካቢኔያቸው ሥልጣን መልቀቁን አስታውቀዋል፡፡ የሩሲያ መንግሥት ከሥልጣን መልቀቁን ያስታወቀው ፕሬዚዳንቱ ያቀረቡት ሕገ መንግሥታዊ ለውጥ ተቀባይነትን ያገኝ ዘንድ ነው ብሏል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሥልጣን መልቀቃቸውን ባሳወቁ በሰዓታት ጊዜ ውስጥ ሚካይል ሚሹስቲን የተባሉ ግለሰብ በእግራቸው እንዲተኩ ሆኗል፡፡ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ብዙም የማይታወቁ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተዘጋጀ ስለማንነታቸው የሚገልጽ የዊኪፒዲያ ገጽም የሌላቸው ተብለዋል፡፡ የሩሲያን የአስተዳደር ሥርዓት ወደ ፓርላሜንታዊ የመቀየር ሐሳቡ የቭላድሚር ፑቲንን የሥልጣን ዕድሜ ለማራዘም የመጣ መላ ነው የሚሉ ተንታኞች ሐሳባቸውን እየገለጹ ነው፡፡
እ.ኤ.አ. ማርች 26 ቀን 2000 የሩሲያ ፕሬዚዳንት ሆነው የተሾሙት ቭላድሚሪ ፑቲን እስካሁን ድረስ የአገሪቱ መሪ ሆነው መዝለቅ ችለዋል፡፡ ለ20 ዓመታት የዘለቀውና ለመጠናቀቅ ሌላ ተጨማሪ አራት ዓመታት የሚቀረው የፑቲን የሥልጣን ዘመን በዜጎች ምርጫ የተወሰነ ነው፡፡
ፑቲን እ.ኤ.አ. በ2004 በተካሄደ ምርጫ ሁለተኛ የሥልጣን ጊዜያቸውን አረጋግጠዋል፡፡ በፕሬዚዳንታዊ የአስተዳዳር ሥርዓት መሠረት ሁለተኛ የሥልጣን ምዕራፋቸውን እንዳጠናቀቁ እ.ኤ.አ. በ2008 ሥልጣናቸውን ለዲሚትሪ ሜድቬዴቭ አስረከቡ፡፡ ሜዴቭዴቭ በትረ ሥልጣኑን በተቀበሉ በአፍታ ጊዜ ውስጥ ፑቲን የሩሲያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኑ፡፡
ሜድቬዴቭ የመጀመርያ የሥልጣን ዘመናቸውን እንዳጠናቀቁ እ.ኤ.አ. ማርች 4 2012 ላይ ፑቲን ለሦስተኛ ጊዜ የሩሲያ ፕሬዚዳንት ሆነው ተሾሙ፡፡ ከወር በኋላ ቃለ መሐላ ሲፈጽሙ ምርጫው ተጭበርብሯል ያሉ የአገሬው ተወላጆች ተቃውሞ እያሰሙ ነበር፡፡ በተደጋጋሚ ጊዜ ምርጫ እያሸነፉ የመጡት ፕሬዚዳንት ፑቲን ግን እ.ኤ.አ. በ2018 ሩሲያን ለተጨማሪ ስድስት ዓመታት ለመምራት ቃለ መሐላ ፈጸሙ፡፡
በሕገ መንግሥቱ መሠረት እ.ኤ.አ. ከ2024 በኋላ ግን ለፕሬዚዳንትነት መወዳደር አይችሉም፡፡ የአገሪቱ የፖለቲካ አስተዳዳር የሚለውጠውን ምክረ ሐሳብ ያቀረቡትም እ.ኤ.አ. በ2024 የሚጠናቀቅ የሥልጣን ዘመናቸውን ለማራዘም ነው እየተባለ ነው፡፡
ፑቲን ከፕሬዚዳንታዊ የአስተዳደር ሥርዓት ፓርላሜንታዊ ሥርዓት የሚደረገው ሽግግር በሕዝብ ድምፅ የሚወሰን ይሆናል ብለዋል፡፡ ውሳኔ ሕዝቡ ለፑቲን ምክረ ሐሳብ የሚያደላ ከሆነ የሩሲያ ጠቅላይ ሚኒስትር ከፕሬዚዳንቱ የተሻለ ቦታ ይኖራቸዋል፡፡ በፓርቲ የሚመረጥ ጠቅላይ ሚኒስትር ከፕሬዚዳንት የላቀ ሥልጣን ሲኖረው፣ የሚመረጠው ፕሬዚዳንት ግን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ያህል ወሳኝ አይሆንም፡፡
ፑቲን እ.ኤ.አ. ከ2000 ጀምሮ እስካሁን የሩሲያ መሪ ሆነው በቆዩባቸው ዓመታት የፕሬዚዳንትነት ቦታቸውን የለቀቁት አንድ ጊዜ ብቻ ነበር፡፡ በእግራቸው ተተክተው የተሾሙት ታማኝ አገልጋቸው እንደሆኑ የሚነገርላቸው ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ ስለነበሩም በእነዚያ ጊዜያትም ቢሆን የሥልጣኑ ባለቤት ፑቲን እንደነበሩ ይታሙ ነበር፡፡ ከቀናት በፊት ያቀረቡት የአስተዳደር ለውጥ ሐሳብ ይሳካ ዘንድ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣን መልቀቃቸው የነበረውን ጉምጉምታ የሚያጠናክር ነው፡፡
የሩሲያ ሕገ መንግሥት አንድ ፕሬዚዳንት በተከታታይ ከሁለት ጊዜ በላይ በሥልጣን ላይ መቆየት እንዳይችል ገደብ ያስቀምጣል፡፡ በምክረ ሐሳብ ደረጃ የቀረበው ሕገ መንግሥታዊ ለውጥ ፑቲን እ.ኤ.አ. ከ2024 በኋላም መሪ ሆነው እንዲቆዩ ዕድል የሚሰጥ ነው ተብሏል፡፡
እ.ኤ.አ. በ1952 በሩሲያ ፒተርስበርግ የተወለዱት ቭላድሚር ቭላድሚሮቪች ፑቲን በሌኒንግራድ ስቴት ዩኒቨርሲቲ በሕግ ትምህርት ተመርቀዋል፡፡ ወደ ፖለቲካ ከመግባታቸው በፊት እ.ኤ.አ. በ1975 ኮሚቴ ፎር ስቴት ሲኪዩሪቲ (ኬጂቢ)ን ተቀላቅለው ነበር፡፡
እ.ኤ.አ. 1991 ወደ ፖለቲካው እስኪገቡ ድረስ በተለያዩ ኃላፊነቶች አገልግለዋል፡፡ ፖለቲካውን የተቀላቀሉት አናቶሊ ሶብቻክን (ለሌኒንግራድ ከተማ ከንቲባ ለመሆን የተወዳደሩ) በማማከር ነበር፡፡ አናቶሊ ሶብቻክ ምርጫውን አሸንፈው የሌኒንግራድ ከንቲባ ሲሆኑ፣ ቭላድሚር ፑቲን ደግሞ የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ሊቀመንበር ሆነው ተሾሙ፡፡ በፕሬዚዳንት ቦሪስ የልሲን ዘመን ፑቲን የክሬምሊን ምክትል ዋና አስተዳዳሪ ሆነው ከሠሩ በኋላ እ.ኤ.አ. በ1999 ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል፡፡ በዓመቱ መጨረሻ ላይ ቦሪስ የልሲን ከሥልጣን ሲለቁ ቭላድሚር ፑቲን ነበር በእግራቸው የተተኩት፡፡ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ የሚያዘወትሩት ፑቲን በጁዶ ስፖርት ጥቁር ቀበቶ አላቸው፡፡