በሌሎች አገሮች ተግባራዊ ሆኖ የተገልጋዮች ዕርካታ ማስፈኑ የሚነገርለትና በኢትዮጵያም ተግባራዊ ለማድረግ ውይይት እየተደረገበት የሚገኘው ‹‹የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የጉዳዮች ሒደት አስተዳደር መተግበሪያ መመርያ››፣ የወንጀል ወይም የፍትሐ ብሔር ክርክሮችን ተገማችና ግልጽ እንደሚደርግ ተገለጸ፡፡
በተለያዩ ችሎቶች የሚሠሩ ዳኞችና ባለሙያዎች ተደጋጋሚ ውይይቶች አድርገው ለአጠቃላይ የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ፣ ከፍተኛና ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች ዳኞች ለውይይት የቀረበውን መመርያ ረቂቅ፣ በቅርቡ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ጉዳዮች ሒደት አስተዳደር ኃላፊ ወ/ሮ ሰላማዊት ግርማይ፣ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞች ገለጻ አድርገዋል፡፡
የጉዳዮች ሒደት አስተዳደር (Case Flow Management)፣ የፍርድ ቤቶች ጉዳዮችን (ክርክሮች) ውጤታማነት ከማረጋገጥና ሳይዘገዩ ምክንያታዊ በሆነ ጊዜ ውስጥ እንዲጠናቀቁ፣ ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ የአሠራር መርሆዎችን በመጠቆም፣ የተሻለ የአሠራር ሥርዓት መዘርጋት ማለት መሆኑን ትርጉሙን (Definition) በመግለጽ ስለረቂቁ ኃላፊዋ ገልጸዋል፡፡
ነፃና ገለልተኛ ሆኖ በተቋቋመ ፍርድ ቤት ለመገልገል የሚመጣን ባለጉዳይ፣ ሕጉን በተከተለ (Due Process of Law) መንገድ ያልዘገየ ፍትሕ እንዲያገኝ ለማድረግ፣ ሥርዓት መዘርጋት ግድ እንደሚል የተናገሩት ዳኛዋ፣ መመርያው ምክንያታዊ በሆነ ጊዜ (ሰዓት) የተሻለ ጥራት ያለው ሥራ መሥራት፣ ፍርድ ቤቶችን ውጤታማ፣ ተገማችና ግልጽ እንዲሆኑ ለማድረግ እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡ ይኼ ሥራ የአመራሮችና የጉዳዩ ባለቤቶችን (ዳኞችን) ቁርጠኝነት እንደሚፈልግም አክለዋል፡፡
አሠራሩ ዓለም አቀፋዊ በመሆኑ እንደየአገሩ ሁኔታ ተርጉሞ መተግበር እንደሚያስፈልግ፣ ከተጠቃሚዎች ጋር ማለትም ከጠበቆች፣ ከፖሊስ፣ ከዓቃቤ ሕግና ከሌሎች ተገልጋዮች ጋርም በአንድነት ተቀናጅተው የሚሠሩበት መድረክ እንደሚያስፈልግም አክለዋል፡፡
ጉዳዮች የሚመሩበት ሁለት መርሆዎች እንዳሉ የጠቆሙት ወ/ሮ ሰላማዊት፣ የመጀመርያው ጊዜ ሲሆን፣ ‹‹ተገልጋዮች የሚጠብቁት ምንድነው?›› ብለን፣ እንደ አገሩ ነባራዊ ሁኔታ፣ ሕዝቦች ምን ዓይነት አገልግሎት እንደሚፈልጉ ማወቅ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡ ደረጃውን የጠበቀ አሠራር ለመከተል የሚከለክለን ልማዳዊ አሠራር መቀየር እንደሚያስፈልግም አስታውቀዋል፡፡ ሁለት ሦስት ጉዳዮችን በተመሳሳይ ሰዓት መተግበር ስለማይቻል መቀየር ግድ እንደሆነም አክለዋል፡፡
ይህን ለማድረግ አራት ዘዴዎች እንዳሉ የጠቆሙት ኃላፊዋ፣ የመጀመርያው ቅድመ ምርመራ (Pre Trial Conference) ሲሆን፣ ቁርጠኛና ተገማች የሆነ አሠራርን መፍጠር ማለትም፣ ተገልጋዩ በቀጠሮ ቀን ውሳኔ እንደሚያገኝ ተማምኖ እንዲቀርብ ማድረግ ሁለተኛው ዘዴ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ሦስተኛው ዘዴ የጉዳዮች አስተዳደር (Trial Management) ማለትም አንድ ዳኛ ባለጉዳዩን፣ ፖሊስን፣ ዓቃቤ ሕግን፣ ጠበቆችንና ታዳሚውን ይዞ ችሎቱን እንዴት እንደሚመራ ነው፡፡ የመጨረሻው ዘዴ አፈጻጸም (Post Desposition) መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የሥራ ዕቅድና የአሠራር ሥርዓት መዘርጋት ውጤታማ እንደሚደርግም በንግድ ችሎቶች ላይ በተደረገ የሙከራ ሥራ ውጤታማነቱ መታየቱን አክለዋል፡፡ ጉዳዮቹን በዓይነት ከፍሎ ማየት (Differenciate the Case) እንጂ ጠቅልሎ እንዳይቆጠር ማድረግ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ዳኛው በሥነ ሥርዓት ሕጉ መሠረት መሥራት እንዳለበትና መቀነስም መጨመርም እንደሌለበት አስረድተዋል፡፡ ሆኖም ተግዳሮቶች እንደሚኖሩት ጠቁመው፣ ሌሎች አገሮችም ለምሳሌ አሜሪካም ይኼንን ተግዳሮት አልፋ ነው ውጤታማ የሆነችው ብለዋል፡፡
በመሆኑም ፍሰቱን በትክክል መፈተሽና በቴክኖሎጂ ተደግፎ ውጤታማ መሆን እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡ የጉዳዩ ባለቤት (ሥራ አስኪያጅ) ዳኛው በመሆኑ አንድ መዝገብ በስንት ሰዓት (ጊዜ) መጨረስ እንደሚችል ሪፖርት ማድርግ እንዳለበትም አሳውቀዋል፡፡ መመርያው ከፀደቀ በኋላ ወዲያውኑ ወደ ሥራ እንደማይገባ የገለጹት ወ/ሮ ሰላማዊት፣ ውዝፍ መዝገቦች ከተጠናቀቁ በኋላ፣ አዲሱ የአሠራር ሥርዓት እንደሚጀመርም ተናግረዋል፡፡ ይህም በሚቀጥለው ዓመት የሚተገበር መሆኑንም አክለዋል፡፡
ስለረቂቅ መመርያው ወ/ሮ ሰላማዊት ገለጻ አድርገው እንደ ጨረሱ፣ የውይይቱ ታዳሚ ዳኞች ጥያቄና አስተያየት ሰንዝረዋል፡፡ መመርያውን መተግበር ሲጀመር የተፋጠነ፣ ተገማችና ግልጽ ውሳኔ ለመስጠት እንደሚችል ከመግለጽ ባለፈ፣ ስለጥራት ጉዳይ ለምን በመመርያው እንዳልተካተተ ጠይቀዋል፡፡ የጉዳዮች ሒደት አስተዳደር ጽንሰ ሐሳብ ከመሆኑ አንፃር፣ በዳኝነት አሠራር ውስጥ ገብቶ ስለአሠራሩ ለመወሰን ሕጋዊ ሥልጣን ስለመኖሩም የውይይቱ ተሳታፊ ዳኞች ማብራሪያ ጠይቀዋል፡፡ መመርያው የተዘጋጀው የውጭ ልምድ ወይም ተሞክሮ ስለታየ ብቻ ሳይሆን፣ በአገሪቱ መሬት ላይ ያለው ውስብስብ አሠራርና ውዝፍ ፋይል ስለመታየቱ ጥርጣሬ እንዳላቸውም ተናግረዋል፡፡
በጥናቱ ወደ ፍርድ ቤት ስለሚመጡ ጉዳዮች ቅድመ ምርመራ (Pre Trial Conference) መደረጉ መገለጹን ጠቁመው፣ ይኼ አሠራር ‹ኮመን ሎው› ለሚከተሉ አገሮች እንጂ፣ ‹‹ሰብስታንቲቭ ወይም ‹ኮንቲኔንታል ሎው›› ለሚከተሉ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገሮች እንደማይሠራ ወይም እንደማይጠቅም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
የጉዳዮች ፍሰትን በሚከተሉ አገሮች ወደ ችሎት (ፍርድ ቤት) የሚሄዱት ጉዳዮች አምስት በመቶ የሚሆኑት ብቻ መሆናቸውን የገለጹት ዳኞቹ፣ ሌሎች 95 በመቶ የሚሆኑት በአማራጭ የችግሮች መፍቻ ዘዴዎች የሚፈቱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች ጥናት ባይኖርም ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑ ጉዳዮች የሚስተናገዱት በችሎቶች (ፍርድ ቤቶች) ከመሆኑ አንፃር፣ ገና መስተካከል ያለባቸው መሠረታዊ ፍላጎቶች ብዙ መሆናቸውንም አስረድተዋል፡፡ ከትንንሾቹ ቢጀመር መቅረፀ ድምፅ፣ መብራትና የሠለጠነ ባለሙያን በምሳሌነት ጠቅሰዋል፡፡
በረቂቁ ውዝፍ መዝገቦች ቅድሚያ መጠናቀቅ እንዳለባቸው መጠቀሱን አስታውሰው፣ በተባለው ጊዜ ሥርዓቱን ለመጠቀም (በሚቀጥለው ዓመት መጀመርያ) ያለውን ውዝፍ ፋይል ለመጨረስ እንደማይቻል ሊታሰብበት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ውዝፉን ለማጠናቀቅ ሲሠራ አዳዲስ እየተጨመረበት ስለሚሄድና ሁለቱን በአንድ ጊዜ ማጠናቀቅ የሰው ኃይል ስለሚያስፈልግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በፍርድ ቤቶች አሠራር ዙሪያ ለበርካታ ዓመታት (በ27 ዓመታት ውስጥ) የተለያዩ ጥናቶች መደረጋቸውን ያስታወሱት ዳኞቹ፣ አዲሱ ረቂቅ መመርያ የተዘጋጀው ለምን ጥናቶቹን መተግበር እንዳልተቻለ ጥናት ተደርጎ ስለመሆኑ ወይም ስላለመሆኑ ማብራሪያ ጠይቀዋል፡፡ ‹‹ሪል ታይም ዲስፓች›› (RTD) ወይም የተፋጠነ ውሳኔ መስጫ ችሎት ተቋቁሞ እየሠሩበት ቢሆንም፣ አሁን እየወሰደ ያለው ጊዜ ከመደበኛ ችሎቶች የተለየ ባለመሆኑ፣ ችግሩ መጠናት እንዳለበትና ረቂቁ ሁኔታዎችን ያገናዘበ እንዲሆን ጠይቀዋል፡፡ አንድ ጉዳይ ፍርድ ቤት ከመጣ በኋላ ምስክር መጥራት፣ ማሰማት፣ ሰነድ ማሰባሰብና ክርክሮችን በአግባቡ ለመምራት ጊዜ እንደሚያስፈልግ ግምት ውስጥ እንዲገባም አሳስበዋል፡፡
መመርያውን ማውጣት የሚችለው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሳይሆን የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ጉባዔ መሆኑን፣ በረቂቁ አንቀጽ ሦስት የመመርያው ተፈጻሚነትን በሚመለከት፣ ተመሳሳይ ሐሳቦች መቅረባቸውን በመጠቆም እንዲስተካከሉ ዳኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ በተፋጠነ ሥነ ሥርዓት ሲባል በ‹አክሰለሬትድ› እና ‹ሰመሪ ፕሮሲጀር› የሚታዩ ጉዳዮች እንደ ሌሉም ዳኞቹ አክለዋል፡፡ ረቂቁ በአንቀጽ አራት ለተናጠል ጉዳዮች የተፋጠነና ፍትሐዊ ዳኝነት መስጠት የሚያስችል አሠራር እንዲፈጠር ቢገልጽም፣ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 130 (2ረ) ድንጋጌ መሠረት፣ አንዳንድ ጉዳዮች ሳይወሰኑ ሌሎች መዝገቦች እንደማይወሰኑ፣ እንዲሁም በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 36፣ 37፣ 197 እና 377 ጉዳዮች እንዳይወሰኑ ዕግድ እንደሚሰጥም ዳኞቹ ተናግረው፣ ረቂቁ በደንብ እንዲታይ ጠይቀዋል፡፡
ዜጎች በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ ያላቸው ዕርካታና አመኔታ እየጨመረ እንዲሄድ በሚል በረቂቁ መገለጹን የጠቆሙት ዳኞቹ፣ ‹‹አንድ ጉዳይ በ90 ቀናትና በ170 ቀናት ውሳኔ ስላገኘ ዕርካታ ይገኛል?›› በማለት ጠይቀው፣ አንድ ጉዳይ መነሻና መድረሻ ስለተቀመጠለት ብቻ ሳይሆን፣ በሚሰጠው ጥራት ያለው ውሳኔ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ ረቂቁ በጥቅሉ ‹‹ባለድርሻ አካላት›› የሚላቸው እነማን እንደሆኑ፣ የመተባበር ግዴታን እንጂ መተባበር ባይኖር የሚከተለው ነገር ምንም ያለው ነገር እንለዴለ ጠቁመው፣ በዝርዝር መቀመጥ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ መዝገቦች የሚቆዩት በዳኛ እጅ ብቻ ሳይሆን ችሎት ጸሐፊዎችም ጋር እንደሚቆዩ አክለዋል፡፡
በረቂቁ ስለጭብጥ አወጣጥ የተጠቀሰ ቢሆንም፣ የፍትሐ ብሔር ወይም የወንጀል ስለመሆኑ አለመገለጹንም ጠቁመዋል፡፡ የይግባኝ ጉዳዮች ቅድሚያ ተሰጥቷቸው መታየት አለባቸው መባሉ በምን መሥፈርት እንደሆነ እንዲብራራና ለይግባኙ ቅድሚያ ሲሰጥ ሌላ ውዝፍ መዝገብ ስለመፈጠሩም እንዲታሰብበት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ መጥሪያን በሚመለከት ከደረሰው ቀን ጀምሮ 30 ቀናት የተባለው እሑድና ቅዳሜ ተቆጥሮ ስለመሆኑ፣ በቂ ቀነ ቀጠሮ ማለት ምን ማለት እንደሆነ፣ የዕርምት ዕርምጃዎች ምን እንደሆኑና መመርያውን ለማዘጋጀት አጥኚው ቡድን የተከተለው ‹ሌጋል ሪሰርች ሜቶዶሎጂ› እንዲገለጽላቸው ጠይቀዋል፡፡
ከአሜሪካ ወይም ከሩዋንዳ የተገኙ አሠራሮችና አደረጃጀቶች በቀጥታ መውሰድ ሳይሆን የዳኞችን ብዛት፣ የአሠራር ሥርዓታቸውን፣ ብቃታቸውንና ሌሎች መሥፈርቶችንም ማነፃፀር ተገቢ መሆኑን ዳኞቹ በአስተያየታቸው ጠቁመዋል፡፡ ይህ አሠራር ‹‹ለሳንባና ለጥርስ ሕመም ተመሳሳይ መድኃኒት ከመውሰድ ያድናል፤›› ሲሉም ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች ዳኞች አስተያየታቸውን ሰጥተው እንደጨረሱ አስተያየትና ምላሽ የሰጡት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሰለሞን አረዳ ናቸው፡፡ የጉዳዮች ሒደት አስተዳደር በሌሎች አገሮች በ1980ዎቹ ተጀምሮ ብዙ ተግዳሮቶችን ካለፈ በኋላ፣ አሁን በአግባቡ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጭምር ዕውቅና ተሰጥቶት፣ አሁን የሪፎርም አንዱ ግብዓት ለመሆን መብቃቱን አክለዋል፡፡ ወደፊት የሚያሸጋግር ሥርዓት በመሆኑ፣ ‹‹እንዴት እንሄድበታለን›› የሚለውን ማየት አስፈላጊ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ በጊዜ ለመጠቀም ወሳኝ ሥርዓት በመሆኑ መተግበሩ አይቀሬ መሆኑን አስረግጠው ተናግረዋል፡፡
ስለረቂቅ መመርያው ማብራሪያ የሰጡት ወ/ሮ ሰላማዊት ከውይይቱ ተሳታፊ ዳኞች ስለተነሳው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ እንደገለጹት፣ ጥራት ጥያቄ የለውም ብለዋል፡፡ ጥራት የሌለው ውሳኔ ስለማይሆን ለቁጥር ብቻ የሚሠራ ዳኛ ይኖራል ብለው እንደማያምኑ ገልጸዋል፡፡ የሥራው ከባቢ ሳይስተካከል እንዴት ይሠራል ለሚለው፣ ሁሉም ነገር ሲጀመር የሚያስቸግር ቢመስልም፣ ቀስ በቀስ እየተስተካከለ እንደሚሄድ ጠቁመው፣ መጀመርያ ግን ራዕይ ሊኖር እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡ በረቂቁ ላይ ያሉ ችግሮች በሒደት በውይይት እንደሚፈቱና በሒደት ላይ ባሉ የኢንፎርሜሽንና ቴክኖሎጂ፣ እንዲሁም ሌሎች ጥናቶች ሲጠናቀቁ ብዙዎቹ ችግሮች መፍትሔ እንደሚያገኙም ገልጸዋል፡፡ ሲስተሙ እንዲፈጠር ግን የጉዳዩ ሥራ አስኪያጆች ዳኞችና ሥርዓቱን የሚያስተካክሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ በጋራ በቁርጠኝነት መሥራት እንዳለባቸው ወ/ሮ ሰላማዊት አሳስበዋል፡፡
በተቋማት የሚታዩ መሟላት ያለባቸው የዳኞችና የረዳት ዳኞች ቅጥር፣ የችሎት ግብዓቶች መሟላትና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮች እንዲሟሉ እየተደረገና ውሳኔ ላይ መደረሱንም፣ ውይይቱን የመሩት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ አቶ ብርሃነ መስቀል ዋቅጋሪ ተናግረዋል፡፡ ዳኞች በቡድን ሆነው በየችሎቶቻቸው በረቂቅ መመርያው ላይ ውይይት እንደሚደርጉበት፣ ሐሳባቸውን በማቅረብ አንድ መደምደሚያ ላይ እንደሚደረስም ወ/ሮ ሰላማዊት አስታውቀዋል፡፡