ከአንድነት ፓርክ መግቢያ 6.8 ሚሊዮን ብር ሰብስቧል
ሞባይል መኒ አገልግሎት ለመጀመር ፈቃድ ጠይቋል
ኢትዮ ቴሌኮም ለደንበኞቹ ከሰጠው የሞባይል ብድር የአየር ሰዓት ሽያጭ አገልግሎት 6.5 ቢሊዮን ብር ገቢ እንዳገኘ አስታወቀ፡፡
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሪት ፍሬሕይወት ታምሩ ባለፈው ሳምንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደተናገሩት፣ ድርጅቱ የሞባይል የአየር ሰዓት በብድር መስጠት ከጀመረ 17 ወራት ተቆጥረዋል፡፡ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ 20 ሚሊዮን ደንበኞች በአገልግሎቱ እንደተጠቀሙና 6.5 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን ወይዘሪት ፍሬሕይወት ተናግረዋል፡፡
በተመሳሳይ በቅርቡ አገልግሎት መስጠት ከጀመረው በአፄ ምኒልክ ቤተ መንግሥት የተገነባው የአንድነት ፓርክ የመግቢያ ክፍያ 6.8 ሚሊዮን ብር በኦንላይን ክፍያ እንደሰበሰበ ተገልጿል፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም 23,000 የፓርኩን ጎብኚዎች በኦንላይን የክፍያ ዘዴ በማስተናገድ 6.8 ሚሊዮን ብር ገቢ እንደሰበሰበ ወይዘሪት ፍሬሕይወት ተናግረዋል፡፡
ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ እንደተናገሩት መንግሥት የጀመረውን የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ለማገዝ ኢትዮ ቴሌኮም መንገድ በመጥረግ ላይ ይገኛል፡፡ ‹‹ኅብረተሰባችን የወረቀት ገንዘብ ተጠቃሚ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ኅብረተሰባችንን የዲጂታል ክፍያ ተጠቃሚ በማድረግ ቀስ በቀስ የወረቀት ገንዘብ አልባ የሆነ ማኅበረሰብ ለመፍጠር ኢትዮ ቴሌኮም የበኩሉን ሚና እየጫወተ ነው፤›› ያሉት ወይዘሪት ፍሬሕይወት፣ የሞባይል መኒ አገልግሎት ለመጀመር የሚያስችለውን ጥናት አጠናቆ የሥራ ፈቃድ ጥያቄ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እንዳቀረበ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም በሞባይል መኒ አገልግሎት ላይ ያቀረበው የአዋጭነት ጥናት በመንግሥት ተቀባይነት ማግኘቱን ገልጸው፣ ብሔራዊ ባንክ የፈቃድ ጥያቄውን ተቀብሎ በፖሊሲና የፈቃድ አሰጣጥ ሥርዓቱ ላይ እየሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ የሞባይል መኒ አገልግሎቱ ኅብረተሰቡን ወደ ዲጂታል ክፍያ ዘዴ በማስገባት ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ከብሔራዊ ባንክ ምላሽ እየጠበቅን ነው፤›› ብለዋል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም ባካሄደው ጥናት አገሪቱ ከሞባይል መኒ አገልግሎትት 13 ቢሊዮን ዶላር ማመንጨት እንደሚቻል ይጠቁማል፡፡