Monday, July 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በኤክሳይስ ታክስ ምክንያት የኢንሹራንስ ዋጋ ሊጨምር እንደሚችል ይጠበቃል

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኤክሳይስ ታክስ ረቂቅ አዋጅ ከሰሞኑ መነጋገሪያ ሆነው ከሰነበቱ ጉዳዮች አንዱ ነበር፡፡ ከረቂቅ አዋጁ አጠቃላይ ይዘት ይልቅ የበርካቶችን ትኩረት የሳበውና ሲያነጋግር የሰነበተው ባገለገሉ ተሽከርካሪዎች ላይ የተጣለው የኤክሳይስ ታክስ መጠን ነው፡፡

ረቂቅ አዋጁ ባገለገሉ ተሽከርካሪዎች ላይ የጣለው ኤክሳይስ ታክስ ከፍተኛ መሆኑ ብቻም ሳይሆን፣ ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖው በብዙ መልኩ እንደሚገለጽ በተለያዩ ደረጃ ለሚገኙ ተሽከርካሪዎች ሊጣል የታሰበው የኤክሳይዝ ታክስ መጠን እስከ 500 በመቶ መድረሱ የተሽከርካሪ ዋጋን በእጅጉ ያንራል የሚለው ሥጋትና እየታየ ያለው ሁኔታ አጽንኦት እንዲሰጠው አድርጓል፡፡ የመድን ሰጪዎች ሥጋት ጎልቶ እየተደመጠ ነው፡፡ የመድን ኩባንያዎች የታሰበው የታክስ መጠን ያስከትላል ያሉትን ተፅዕኖ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ረቂቁ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከመመራቱ አስቀድሞ እየታየ ቢሆንም፣ ይበልጥ እንዲመከርበት በረቂቁ አዋጁ ዝግጅት ላይ ዋናው ተዋናይ ገንዘብ ሚኒስቴርና አስፈጻሚው የገቢዎች ሚኒስቴር የውይይት መድረክ አዘጋጅተው ስለ ታክሱ አጠቃላይ ይዘት ማብራሪያ መስጠታቸው ይታወሳል፡፡  

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ረቂቅ አዋጁ በተለይ ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ላይ ያስቀመጣቸው ድንጋጌዎች ላይ ለውጥ እንደማይኖር በአጽንኦት መናገራቸው አይዘነጋም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆኑ ሚኒስትሮቻቸው ኢትዮጵያ ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች መጣያ ሆናለች የሚል አቋም ያራምዳሉ፡፡ ረቂቅ አዋጁ ይህንን ለማስቆም መዘጋጀቱንም ይገልጻሉ፡፡ ከዚህ አኳያ በአንድ በኩል ኢትዮጵያ አዳዲስ መኪኖችን ዝቅተኛ የሽያጭ ወይም የአቅርቦት መጠን ሳታሟላ እንዲህ ያለውን አዋጅ ማውጣቷን በመጠየቅ የሚተቹ አካላት፣ በአገር ውስጥ የሚገጣጥሙ ኩባንያዎችም ቢሆኑ ከአገሪቱ የተሽከርካሪ ፍላጎት ውስጥ ምን ያህሉን ማሟላት ችለው ነው ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች እንዳይገቡ ከፍተኛ ታክስ መጣል ያስፈለገው የሚለውም አነጋጋሪ ነው፡፡

ይህም ሆኖ በረቂቅ አዋጁ ላይ በተደረገ ማሻሻያ መሠረት ከ1,300 በታች የፈረስ ጉልበት (ኢንጂን ካፓሲቲ-ሲሲ) ያላቸው አዳዲስ አነስተኛ አውቶሞቢሎች ሊጣልባቸው ታስቦ የነበረው የ30 በመቶ የኤክሳይስ ታክስ፣ ወደ አምስት በመቶ ዝቅ ይደረጋል ተብሏል፡፡ ከዚህ በቀር ባገለገሉ ተሽከርካሪዎች ሊጣል የታሰበው ኤክሳይስ መጠን ለውጥ ሳይደረግበት በታሰበው መጠን ይጸናል ተብሏል፡፡ ይህም ፓርላማው የመንግሥትን ሐሳብ እንዳለ ከተቀበለው ነው፡፡

በረቂቅ አዋጁ ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ላይ እንደ አገልግሎት ዘመናቸውና ሥሪታቸው ለበረዶ አየር ሁኔታ የተሠሩትን ጨምሮ እስከ 500 በመቶ ኤክሳይስ ታክስ ተጥሎባቸዋል፡፡ በአንፃሩ አዳዲስ ተሽከርካሪዎች በተለይም በአገር ውስጥ የሚገጣጠሙም፣ የሚመረቱትም ዝቅተኛ የኤክሳይስ ታክስ ይጣልባቸዋል፡፡   

ባገለገሉ ተሽከርካሪዎች ላይ ሊጣል የታሰበው የኤክሳይስ ታክስ ከየትኛውም የቢዝነስ ዘርፍ በተለየ በኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው ውስጥ ከፍተኛ ተፅዕኖ እንደሚያሳርፍ የዘርፉ ተዋንያን ይገልጻሉ፡፡  

የኢትዮጵያ የመድን ኢንዱስትሪ ዋነኛ የገበያ መሠረት የተሽከርካሪዎች ወይም የሞተር ኢንሹራንስ ከመሆኑ አኳያ፣ የተሽከርካሪዎች ኤክሳይስ ታክስ ላይ ከፍተኛ ጭማሪ መደረጉ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው ላይ የሚኖረውን ተፅዕኖ ባለሙያዎቹ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ይቃኛቸዋል፡፡  

ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኢንሹራንስ ባለሙያዎች እንደገለጹት፣ የተሽከርካሪዎች ዋጋ መጨመር የመድን ኩባንያዎች የሚያስከፍሉትን የዓረቦን ክፍያ መጠን እንዲያሻሽሉና ዋጋ እንዲጨምሩ ያደርጋቸዋል፡፡ ኤክሳይስ ታክሱ ያስከትላል ተብሎ የሚጠበቀው ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች የዋጋ ጭማሪ የኢንሹራንስ ኩባንያዎችን የሚፈታተናቸው በመሆኑ፣ በግዴታ የመድን አገልግሎት ወይም የዓረቦን ዋጋ ጭማሪ ማድረጋቸው እንደማይቀር ይገልጻሉ፡፡ በመሆኑም የተሽከርካሪዎቹን የመሸጫ ዋጋ መሠረት ያደረገ የመድን ዋጋ ጭማሪ ይኖራል ተብሏል፡፡

አብዛኛው የተሽከርካሪ የመድን ሽፋን ዓረቦን የሚተመነው ከተሽከርካሪዎቹ ዋጋ አኳያ በመሆኑም፣ ዋጋቸው በጨመረ ቁጥር የመድን ዋጋ እየጨመረ ይመጣል፡፡ ይህን ሁኔታ ያብራሩት ባለሙያዎቹ፣ በረቂቅ ሕጉ ባለው ሥሌት መሠረት ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ላይ በሚጣለው ኤክሳይስ ታክስ ምክንያት ዋጋቸው በከፍተኛ ደረጃ ስለሚጨምር፣ እስካሁን በነበረው የዓረቦን ዋጋ የመድን ሽፋን መስጠቱ ይቀርና    የዋጋ ማስተካከያ ይደረጋል ብለዋል፡፡

የመድን ዓረቦን ክፍያ በመኪና ዓይነት ዋጋ፣ እንዲሁም በመኪናው የሥሪት ዘመንና የአገልግሎት ዕድሜ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ይህንን መሠረት በማድረግ የዓረቦን ዋጋ ስለሚሰላ፣ የተሽከርካሪ ዋጋ ከፍና ዝቅ ማለቱ የመድን መስጫ ዋጋም እንደሁኔታው ማስተካከያ ይደረግበታል፡፡

የኢትዮጵያ የተሽከርካሪ የመድን ሽፋን ዓረቦን ሽፋን ዋጋ አተማመን አንፃር የኤክሳይስ ታክሱ ሊያስከትል በሚችለው የዋጋ ለውጥ መነሻነት የመድን ኩባንያዎች የተለየና ከፍተኛ ጭማሪ ያደርጋሉ ብሎ መገመት አስቸጋሪ እንደሚሆንባቸው ሪፖርተር ያነጋገራቸው የመድን ዘርፍ ባለሙያ ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡ ለዚህ ግምታቸው ምክንያቱ ደግሞ በአሁኑ ወቅት ከሌሎች የንግድ ዘርፎች ይልቅ የኢንራሹንስ ዓረቦን ዋጋ እየቀነሰ መምጣቱ ነው፡፡ በመድን ኩባንያዎች መካከል የሚታየው ውድድር፣ የገበያውን ዋጋ ያላማከለና ጤናማ ያልሆነ ነው እየተባለ ስለሚተች የአሮጌ ተሽከርካሪዎች ዋጋ መናር በመድን ዋጋ ላይ ለውጥ ሊያስከትል መቻሉን እንጂ ጭማሪው የቱን ያህል ያድጋል በሚለው ላይ እርግጠኛ መሆን እንደማይቻል አስረድተዋል፡፡

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ረቂቅ የኤክሳይስ ታክስ አዋጁ አሁን ባለው ይዘቱ ቢፀድቅ ግን፣ በኢንሹራንስ ኩባንያዎች ላይ ከፍተኛ የጥገና ዋጋቸውንና የካሳ ክፍያቸውን እንደሚያንረው ይገመታል፡፡ እስካሁን በነበረው አካሄድ ለአብነት 500 ሺሕ ብር ዋጋ የነበረው ያገለገ ተሽከርካሪ አሁን 1.2 ሚሊዮን ብር ሊያወጣ ይችላል፡፡ በመሆኑም  የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ይህ ተሽከርካሪ ሙሉ በሙሉ ጉዳት ቢደርስበት፣ በካሳ መልክ በምትኩ የሚከፍሉት 500 ሺሕ ብር መሆኑ ይቀርና ወደ 1.2 ሚሊዮን ብር የሚያሻቅብ በመሆኑ የካሳ ወጪያቸውን ያንረዋል፡፡ ኤክሳይስ ታክሱን ተከትሎ ሊመጣ የሚችለው የመኪና ዋጋ ንረትና በመድን ኢንዱስትሪው ላይ የሚያሳርፈው ጫና በዚህ መልኩ ተብራርቷል፡፡

ለጥገና በሚሰጡት የመድን ሽፋን ረገድም ዋጋቸው ሊንር እንደሚችል ተገምቷል፡፡ የተሽከርካሪዎች ዋጋ ሲጨምር፣ የመለዋወጫ ዕቃዎች ዋጋም ስለሚጨምር የጉዳት ካሳ ጥያቄዎች ዋጋም ከፍተኛ ሆኖ ይቀርባል ያሉት ባለሙያው፣  ይህን ለመተካት የዓረቦን ዋጋ አሁን ካለው የተሽከርካሪዎች የገበያ ዋጋ ጋር ማጣጣም ግድ ይሆንባቸዋል በማለት አብራርተዋል፡፡

አሁን ባለው ሁኔታ የመድን ኩባንያዎችን ውጤታማ ያደረጋቸው የተሽከርካሪዎች አደጋ መብዛትና የመለዋወጫ ዕቃዎች ዋጋ እየጨመር እንደሆነ ያወሱት ባለሙያው፣ አዲሱ ጭማሪ ግን አጠቃላዩን የዓረቦን ተመን ቀመር ለመቀየር እንደሚያስገድድ ይገልጻሉ፡፡

የመድን ሽፋን በአብዛኛው የሚሰጠው ለተሽከርካሪዎች በመሆኑ፣ ከኤክሳይስ ታክስ አዋጁ ትይዩ ከሚመጣ የዋጋ ለውጥ አኳያ የዓረቦን ማስተካከያ ማድረግ የማይቀር መሆኑ ቢገለጽም ይህን በሚያደርጉ ኩባንያዎች ላይ ሥጋት መደቀኑ አልቀረም የሚሉት ባለሙያዎቹ፣ በተለይ ከዜሮ እስከ ሦስት ዓመት ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ለመድን ሽፋን የሚከፍሉት ዓረቦን አነስተኛ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ሊመጣ የሚችል ተዕኖ እንደሚኖርም ይገምታሉ፡፡

አሮጌና ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ከአዲስ ተሽከርካሪዎች አኳያ የመድን ዋጋቸው ከፍ የሚለው አደጋ የማድረስ ዕድላቸው ከፍተኛ በመሆኑ ሲሆን፣ በጥናትም አዳዲስ ተሽከርካሪዎች አደጋ የማድረስ ዕድላቸው ዝቅተኛ በመሆኑ ያገለገሉት ላይ የመድን ዋጋ ይጨምርባቸዋል ብለዋል፡፡

ከሦስት ወይም ከአምስት ዓመት በላይ እስከ 30 ዓመታት ዕድሜ ያስቆጠሩ ተሽከርካሪዎች የመድን ሽፋን እያገኙ ሲሆን፣ በተለይ 20 እና 30 ዓመታት ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች የመድን ሽፋን ግን በተለየ መንገድ ይስተናገዳል፡፡ እንዲያውም በአንዳንድ የመድን ኩባንያዎች ለሦስተኛ ወገን መድን ሽፋን እንጂ ለተሽከርካሪዎች ዋስትና እንደማይሰጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ይህ የሚሆነው ግን ዕቃ የማይገኝላቸውና ለአደጋ ያላቸው ተጋላጭነት ከፍተኛ በመሆኑ ነው፡፡

ይህም ይባል እንጂ በርካታ ባለንብረቶች ከጠቅላላ መድን ይልቅ አስገዳጅ በመሆኑም ምክንያት ለሦስተኛ ወገን ሽፋን ቅድሚያ ስለሚሰጡ፣ የተሽከርካሪዎች የመድን ሽፋን ዋጋ እንደሚገመተው ላይንር እንደሚችል የሚጠቅሱ አሉ፡፡ 

ይህም ሆኖ ረቂቅ አዋጁ በመድን ኢንዱስትሪው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳረፉ እንደማይቀር ሁሉም የሚስማማበት ሲሆን፣ የመኪኖች ዋጋ መጨመሩ፣ የመድን ሽፋኑ ከተሰጠበት ዋጋ ጋር ያለውን ልዩነት ለማጥበብ ለጊዜው ሊደረግ የሚችለው ማስተካከያ፣ ደንበኞች የተሽከርካሪዎቻቸውን የገበያ ዋጋ ቀርበው በማሳወቅ፣ የኢንሹራንስ የሚከፍሉትን ዋጋ ላይ ጭማሪ ማድረግ አንዱ አማራጭ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር ግን የኤክሳይስ ታክስ አዋጁ ተግባራዊ የሚደረግበት የጊዜ እፎይታ ሊኖር እንደሚችል ስለሚታሰብ፣ እስከዚያ ባለው ዋጋ ሊቀጥል እንደሚችልም ይገመታል፡፡

ይሁን እንጂ የተሽከርካሪዎች ዋጋ አዋጁ ከመፅደቁም በፊት እየጨመረ በመምጣቱ፣ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ሊገጥማቸው የሚችለውን አላስፈላጊ ወጪ ለመቅረፍ የዓረቦን ዋጋ ማስተካከል ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡ ደንበኞች የተሽከርካሪዎቻቸውን ወቅታዊ ዋጋ በማስላት የመድን ውላቸውን ቢያስተካክሉ፣ በሁለቱም ወገን ያለውን ሥጋት ሊቀንሱ እንደሚችሉም እየተገለጸ ነው፡፡

በኢትዮጵያ መድን ኢንዱስትሪ ከጠቅላላው ዓመታዊ የዓረቦን ገቢ ውስጥ ለካሳ ጥያቄ ከ60 በመቶ በላይ ከተሽከርካሪዎች አደጋ ጋር በተያያዘ የሚከፈል ነው፡፡ በ2011 ዓ.ም. የመድን ኢንዱስትሪው ያስመዘገበው አጠቃላይ የዓረቦን ገቢ 9.1 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡  

እንደ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መረጃ 17ቱ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች የተጣራ የዓረቦን መጠናቸው ደግሞ 6.53 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ በሒሳብ ዓመቱ ለጉዳት ክፍያ ያዋሉት 3.78 ቢሊዮን ብር መሆኑን ያሳያል፡፡ ከዚህ ክፍያ ውስጥ እስከ 60 በመቶ የሚሆነው ለሞተርና ተያያዥ የኢንሹራንስ ሽፋን ለተሰጣቸው የተከፈለ ካሳ ነው፡፡ በሒሳብ ዓመቱ የመድን ሰጪ ኩባንያዎች አጠቃላይ ሀብት የ23 በመቶ ዕድገት በማስመዝገብ 20.8 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ የኩባንያዎቹ አጠቃላይ ካፒታል የ33 በመቶ ዕድገት በማስመዝገብ 8.1 ቢሊዮን ብር እንደረሰ መረጃው ያመለክታል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች