Friday, April 19, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ክቡር ሚኒስትሩ ለአንድ ባለሀብት ስልክ ደወሉ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚስታቸው ጋር ቁርስ እየበሉ ነው]

 • ብላ እንጂ?
 • በቃኝ እባክሽ፡፡
 • መቼ በላኸው?
 • ዘግቶኛል፡፡
 • አልጣፈጠህም እንዴ?
 • እሱስ አሪፍ ነበር፡፡
 • ታዲያ ለምን አትበላም?
 • አልወርድልህ አለኝ፡፡
 • ምን ሆነሃል?
 • ምን አልሆንኩም ብለሽ ነው?
 • ምነው?
 • የአገራችን ጉዳይ ነዋ፡፡
 • የሚያሳስብ ነገር ተፈጠረ እንዴ?
 • አገራችን አሳሳቢ ከሆነች እኮ ሰነባበተች፡፡
 • አንተ ደግሞ የማያስጨንቅ ነገር ያስጨንቅሃል፡፡
 • እንዴት?
 • አሁን ስንት የሚያስጨንቅ ነገር እያለ ስለአገር ትጨነቃለህ?
 • ከአገር በላይ ምን የሚያስጨንቅ ነገር አለ?
 • ስለራስህ ነዋ መጨነቅ ያለብህ፡፡
 • እ…
 • ተመልከተን እስቲ?
 • ማንን ነው የምመለከተው?
 • እኛን ነዋ፡፡
 • ምን ሆንን?
 • አንተ ምን አለብህ?
 • እንዴት?
 • እኔ እኮ ሁሉንም ነገር ሳጣራ ነበር፡፡
 • ምንድነው የምታጣሪው?
 • ስለበፊቶቹ ባለሥልጣናት ሕይወት ነዋ፡፡
 • ማለት?
 • ለምሳሌ በጥምቀት የሚያደርጉትን ልንገርህ፡፡
 • ምን ያደርጋሉ?
 • እንደ ጥምቀት የሚወዱት በዓል አልነበረም አሉ፡፡
 • ለምን?
 • ብዙ ነገር የሚወራወሩበት በዓል ነዋ፡፡
 • አልገባኝም?
 • መቼም በጥምቀት ሎሚ እንደሚወረወር ታውቃለህ?
 • እንዴት ማለት?
 • በቃ ከባለሀብቶች ጋር የሚተጫጩበት በዓል ነው፡፡
 • እ…
 • አያንዳንዱ ባለሀብት መኪና ይወረውራል አሉ፡፡
 • ለማን?
 • ለክቡር ሚኒስትሩ ነዋ፡፡
 • እሺ፡፡
 • ሌላው ደግሞ ቪላ አሉ፡፡
 • እ…
 • ሙሉ የቤት ዕቃ የሚወረውርም አለ አሉ፡፡
 • ወይ ጣጣ፡፡
 • እሱ ብቻ መሰለህ እንዴ?
 • ሌላ ደግሞ ምን አለ?
 • የባንክ ሼር በለው ኧረ ስንቱን ልጥራው?
 • እ…
 • ባለሥልጣናቱም ግን በተራቸው ይወረውራሉ፡፡
 • ምንድነው የሚወረውሩት?
 • መሬት!

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቃዋሚ መሪ ጋር ተገናኝተው እያወሩ ነው]

 • ምንድነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ምኑ?
 • አገሪቱ ወዴት እያመራች ነው?
 • ወደ ብልፅግና ነዋ፡፡
 • ፅድቁ ቀርቶብኝ በቅጡ በኮነነኝ አሉ፡፡
 • ተረት ትችላለህ እንዴ?
 • ምን ለማለት ፈልገው ነው?
 • ማለቴ ያው ዳያስፖራ ነህ ብዬ ነው፡፡
 • ወድጄ አይደለም እኮ ዳያስፖራ የሆንኩት፡፡
 • ደግሞ ማን አስገደደህ?
 • አላታግል ሲሉኝ እኮ ነው ከአገር የሸሸሁት፡፡
 • ታዲያ ምን አጠፉ?
 • ምን አሉኝ?
 • ምንም፡፡
 • ልታባርሩን አስባችኋል እንዴ?
 • መቼ ይቀራል?
 • እ…
 • ምነው?
 • እኛ እኮ መንግሥትን አምነን ነው የመጣነው፡፡
 • መንግሥትም አምኖ ነበር የጠራችሁ፡፡
 • ምን አምኖ?
 • አገሪቱ ሰላም ትሆናለች ብሎ ነዋ፡፡
 • እ…
 • አተርፍ ባይ አጉዳይ አሉ፡፡
 • ማን ነው እሱ?
 • መንግሥት ነዋ፡፡
 • እንዴት?
 • ይኸው የአገሪቱ ሰላም በየጊዜ እየደፈረሰ ነዋ፡፡
 • እኛ እጃችን የለበትም፡፡
 • እሱን ስትጠየቅ ታወራለህ፡፡
 • ማን ነው የሚጠይቀኝ?
 • ምን አስቸኮለህ?
 • እያስፈራሩኝ ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ዓላማህ ለመሆኑ ምንድነው?
 • ሕዝቤን ማገልገል ነዋ፡፡
 • ማጋደል ነው ያልከኝ?
 • ተው እንጂ ክቡር ሚኒስትር?
 • ትንሽ ግን አያሳዝናችሁም፡፡
 • ማን ነው የሚያሳዝነን?
 • ሕዝቡ ነዋ፡፡
 • ትግል፣ ትግል ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ይኼ ሕዝብ መቼ ይሆን የሚያልፍለት?
 • አሁን በእኛ ያልፍለታል፡፡
 • በእናንተማ ሕይወቱ እያለፈ ነው፡፡
 • ምን አሉኝ?
 • ለማንኛውም ደርሰንበታል፡፡
 • ምኑን?
 • ዓላማህን፡፡
 • ምንድነው?
 • ማተራመስ!

[ለክቡር ሚኒስትሩ የቀድሞ ሚኒስትር ስልክ ደወሉላቸው]

 • ምን አለ ብታምኑ ክቡር ሚኒስትር?
 • ምኑን?
 • ሁሉም ነገር እያፈሰሰባችሁ እኮ ነው፡፡
 • አልገባኝም?
 • ፖለቲካውን ስትሉት ኢኮኖሚው እያለ አስቸገራችኋ?
 • እ…
 • ለምን አትለቁልንም?
 • ለእናንተ?
 • የውጭዎቹም መቼ ቻሉት?
 • ምን?
 • የእነሱን ምክር መስማት እንደማያዋጣ ተናግረን ነበር፡፡
 • የምነግርህ ነገር የእነሱ ምክር ቢያንስ ከእናንተ ይሻላል፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር የሁሉም ነገር መፍቻ በእጃችን ነው፡፡
 • እናንተ ማጥፊያ እንጂ መፍቻ የላችሁም፡፡
 • እ…
 • ተስፋ እንዴት አትቆርጡም?
 • እኛማ መመለሻ ትኬታችንን ነው መቁረጥ የምንፈልገው፡፡
 • የት ነው የምትመለሱት?
 • አራት ኪሎ፡፡
 • ወደዚህ ከተመለሳችሁም የምትመለሱት አንድ ቦታ ነው፡፡
 • የት?
 • ቂሊንጦ፡፡
 • እንግዲያው እንቀጥላለን፡፡
 • ምኑን?
 • ትግላችንን ነዋ፡፡
 • ትግል እኮ ድሮ ቀረ፡፡
 • እንዴት?
 • በዚህ ዘመን ምርጫ ነው ያለው፡፡
 • እ…
 • እናንተ ደግሞ ተመራጭ አለመሆናችሁን መቼም ታውቁታላችሁ?
 • ክቡር ሚኒስትር እኛ ተመራጭም ተደማጭም ነን፡፡
 • ደፍጣጭ ነን ብትል ነው የሚያምርብህ፡፡
 • ሥልጣን የያዝነው በምርጫ መስሎኝ?
 • እኔ ለዚህ አይደል እንዴ ደፍጣጮች ናችሁ የምልህ?
 • ክቡር ሚኒስትር እርስዎንም ለዚህ ያበቃንዎት እኛ መሆናችንን አይርሱት፡፡
 • ወዳችሁ ሳይሆን ተገዳችሁ ነው እባክህ?
 • እ…
 • ለማንኛውም አደብ ብትገዙ ይሻላችኋል፡፡
 • እናንተም አገሩን በሥርዓቱ ብታስተዳድሩት ይሻላችኋል ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እናንተ እያላችሁ እንዴት አድርገን?
 • ታዲያ አንድ ላይ እናስተዳድረዋ?
 • እሱ የማይታሰብ ነው፡፡
 • በቃ?
 • አዎ በቃ፡፡
 • እንግዲያው ተከታታይ ድግሶች አዘጋጅተንላችኋል፡፡
 • የምን ድግስ?
 • የብጥብጥ!

[ክቡር ሚኒስትሩ ለአንድ ባለሀብት ስልክ ደወሉ]

 • እንኳን አደረሰዎት ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ለምኑ?
 • ለጥምቀት ነዋ፡፡
 • በደረቁ ምን ያደርጋል ብለህ ነው?
 • በምን ላርጥብልዎት ክቡር ሚኒስትር?
 • ለበፊቶቹ ሚኒስትሮች በምን ነበር የምታረጥብላቸው?
 • እ…
 • የማላውቅ መሰለህ እንዴ?
 • ምኑን ክቡር ሚኒስትር?
 • ለበፊቶቹ ምን ታደርግ እንደነበር ነዋ፡፡
 • ምን እያሉኝ ነው?
 • አሁን ምነው በደረቁ እያልኩህ ነዋ፡፡
 • አልታወቀም ብዬ ነው፡፡
 • ምኑ?
 • መቀመጫችሁ ነዋ፡፡
 • ከአሁን በኋላ ማን ይነቀንቀናል?
 • ክቡር ሚኒስትር ከየአቅጣጫው እየተወዘወዛችሁ እኮ ነው፡፡
 • እ…
 • ባይሆን ቀልጣፋ ከሆኑ ያቀላጥፉኝ፡፡
 • ምን?
 • አንድ አሪፍ ፕሮጀክት ነበረኝ፡፡
 • ታዲያ ምን ገጠመህ?
 • ፕሮጀክቱን ለመተግበር ዋነኛ እንቅፋት የሆነብኝ ነገር አለ፡፡
 • ምንድነው?
 • መሬት፡፡
 • እ…
 • በቃ እሱን ከቀረፉልኝ የፈለጉትን ነገር እወረውርልዎታለሁ፡፡
 • እውነት?
 • ምን ጥያቄ አለው፡፡
 • እንግዲያው ወርውርልኝ፡፡
 • ምን?
 • ቪላ!                                                                                         

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...

እጥረትና ውጥረት!

ጉዞ ከስድስት ኪሎ ወደ ቃሊቲ፡፡ ‹‹ይገርማል ቀኑ እንዴት ይሄዳል?››...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

[የኢኮኖሚ ጉዳዮች አማካሪው ቅሬታ የቀረበባቸው አንዳንድ ጉዳዮችን ክቡር ሚኒስትሩ ተመልክተው ምላሽና ውሳኔ እንዲሰጡባቸው ለማድረግ ከክቡር ሚኒስትሩ ጋር እየተወያዩ ነው] 

ክቡር ሚኒስትር ተቋማችን በሚሰጣቸው አንዳንድ አገልግሎቶች ላይ ጥያቄ እየተነሳ በመሆኑ ነው ዛሬ ከእርስዎ ጋር ለመወያየት የፈለግኩት። የምን ጥያቄ? ማነው ጥያቄውን ያቀረበው? ጥያቄውን ያቀረቡት የተቋማችን ተገልጋዮች ናቸው። እሺ፣...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባላት ጋር በአገራዊ ጉዳዮች ላይ እየመከሩ ነው]

ክቡር ሚኒስትር ባለፈው ሊያወያዩን ሲመጡ ለአገራችን የፖለቲካ ችግር መፍትሔው አንድና አንድ እንደሆነ ነግረንዎት ነበር፣ ያስታውሳሉ? አላስታውስም። ባለፈው የተገናኘን ጊዜ ይህችን አገር ከችግር የሚያወጣው መፍትሔ አንድና አንድ...

[ክቡር ሚኒስትሩ በዕረፍት ቀናቸው በመኖሪያ ቤታቸው ሆነው ከባለቤታቸው ጋር ከውጭ እንዳይገቡ ስለተከለከሉ ምርቶች እያወሩ ነው]

እኔ እምልህ ...ኤል ሲ እንዳይከፈት ተከልክሏል ሲባል አልነበረም እንዴ? ኤል ሲ ደግሞ ምንድነው? ሌተር ኦፍ ክሬዲት ነዋ!? አልገባኝም? አስመጪዎች ከውጭ ለሚያስገቡት ዕቃ የሚያስፈልጋቸውን የውጭ ምንዛሪ ከባንኮች አይደል የሚያገኙት? አዎ። ኤል...