መሰንበቻውን የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲን የጎበኙት የሕዝብ እንደራሴዎች ዩኒቨርሲቲው በኅዋ ሳይንስና አዳዲስ የመማሪያ ሶፍትዌሮችን በማበልፀግ ረገድ እያከናወነ ያለውን ተግባር አድንቀዋል፡፡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት ልማትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አመራሮችና አባላት የዩኒቨርሲቲውን የልህቀት ማዕከል በጎበኙበት ወቅት እንደተገለጸው፣ ዩኒቨርሲቲው ያደራጀው የልህቀት ማዕከል አገሪቷ ለጀመረችው የሳይንስ፣ የኢንጂነሪንግ፣ የምርምርና ጥናት ሥራዎች በተግባር እንዲደገፉ ለማድረግ የአይሲቲና የኅዋ ሳይንስ ፕሮግራሞች ትልቅ ልምድ የሚቀሰምባቸው ናቸው። ዩኒቨርሲቲው የምድር ሳተላይት መቆጣጠሪያ ጣቢያ ከመገንባት ጀምሮ በራሱ ተማሪዎችና መምህራን የሳተላይት ግንባታ እያከናወነ መሆኑም ተገልጿል፡፡ የዩኒቨርሲቲው ማኅበራዊ ገጽ እንደዘገበው፣ በጉብኝቱ አጋጣሚ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሎሚ ጉቱ በግዥ አፈጻጸም ዙርያ ያለውን ውጣ ውረድ በመጠቆም ፓርላማው የሕግ ማሻሻያ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የግዥ አፈፃፀም ሁኔታን ለማሻሻል ለፓርላማው የቀረበውን ሕግ ይሁንታ እንዲሰጡት የሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) ጠይቀዋል፡፡