Wednesday, March 22, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የሸገርን “ያልበላትን ከማከክ” ሁለንተናዊ ተግዳሮቶቿን መቅረፍ ይቅደም!

በገለታ ገብረ ወልድ

አዲስ አበባ 133 ዓመታት ዕድሜ ያስቆጠረች የአገራችን ዋነኛና ታሪካዊት ከተማ ነች፡፡ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ወደ ደቡብ ምዕራብና ምሥራቅ እየተስፋፉ ሲመጡ ከመንበራቸው እንጦጦ ይልቅ ወደታች የታየው ደልዳላ ሜዳ ለከተማነት አመቺ ሆኖ በመመረጡ አዲስ አበባን ለመዲናነት አበቃት፡፡ በባህሩ ዘውዴ ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ ከ1847 እስከ 1983›› መጽሐፍ እንደተጻፈው፣ ‹‹ይበልጡንም  ንጉሡ ወደ ሐረር ዘመቻ በሄዱበት ወቅት እቴጌ ጣይቱ ፍልውኃ ያለበትና ለኑሮ ተስማሚ የሆነውን ሥፍራ መርጠው ድንኳን በማስጣላቸው ለከተማዋ መመሥረት ከፍተኛውን ድርሻ መጫወታቸው ይነገራል፡፡››

አዲስ አበባ በዚህ ረጅም ዕድሜዋ ውስጥ መዲናዋ ምንም እንኳን የዕድሜዋን ያህል ያደገችና በፕላን የምትመራ ሆና ባትቆይም፣ ባለፉት ሁለት አሠርታት ፈጣን ለውጥ በማምጣት ላይ ትገኛለች፡፡ ከተማዋ በግርድፍ መረጃ ከ5.9 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ የሚኖርባት ከዚህ ውስጥም ሁለት ሚሊዮን የሚደርሰው በየዕለቱ ከአጎራባች አካባቢዎች የሚወጣባትና የሚገባባት መሆን ችላለች፡፡ በዚህም ምክንያት ቁጥሩ ይብዛም ይነስም የመላው አገሪቱ ሕዝቦች ጥቅምና ውክልና ያለበት በመቶ ምናምን ዓመታት ጊዜ ውስጥ እርስ በርስ ተጋብተውና ተዋልደው የአዲስ አበባ ማንነት ያላቸው ሚሊዮን አዲስ አበቤዎች የከተሙባት ነች፡፡

‹‹ከተማዋ እንደ ዕድሜዋ በፍጥነት ያደገች ነች›› ባትባልም የአገሪቱ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማዕከልነቷ የፈጠረላት ሁለንተናዊ መስተጋብር ቀላል አይደለም፡፡ የአኅጉሩ ትልቁን ገበያ ጨምሮ፣ የተለያዩ አብያተ መንግሥት፣ ሚኒስቴሮች፣ ተቋማት ዕድሜ ጠገቡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ አነስተኛና ከፍተኛ ትምህርት ቤቶች፣ አብያተ ክርስቲያንና መስጊዶች ሁሉ ሕዝቦችን በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡

ሸገር ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ ከከፍተኛ እስከ መካከለኛና አነስተኛ ደረጃ ያላቸው ኢንዱስትሪዎችና ፋብሪካዎች፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ባለኮኮብ ሆቴሎች፣ ትልልቅ ሞሎችና የገበያ ማዕከላት፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዓለም አቀፍ የንግድ ድርጅቶችና ኩባንያዎች ብሎም የምርምር ማዕከላት፣ የኪነ ጥበብና የባህል ማዕከላት፣ ዎርክሾፖችና በርካታ የመዝናኛ ቦታዎች የሞሉባት ነች፡፡ እነዚህ ተቋማት ከሚሰጡት ሕዝባዊ አገልግሎት ባሻገር፣ ለመቶ ሺዎች የሥራ ዕድል ስለመፍጠራችው ጥርጥር የለውም፡፡ በአጭሩ ፈጣንና ተለዋዋጭ (ዳይናሚክ) የነዋሪዎቹ ማኅበራዊ ሽግግር እንዲፈጠርም አድርገዋል፡፡ ኢትኖግራፉም ቢሆን በፍጥነት የመቀየሩ ሁነት ከዚሁ ይመነጫል፡፡

እነዚህ ብቻ ሳይሆኑ አዲስ አበባን ከ115 በላይ ኤምባሲዎችና ቆንስላዎች የተለያዩ ዓለም አቀፍና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የተለያዩ በውጭ ባለቤትነትና የሙያ አጋርነት የሚሠሩ ድርጅቶችና ኩባንያዎች በሺዎች የሚቆጠሩ የውጭ አገር ሰዎችን በመያዝ እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡ አሁን አሁን በተለያዩ የሥራ መስኮች በብዛት የተሰማሩ እንደቻይና፣ ቱርክና የተለያዩ የአውሮፓ ሰዎችን የመሰሉ አካላትን የሚያስተናግዱ የየአገራቱ ሆቴሎችና ሬስቶራንቶችም የመዲናዋ ድምቀት ሆነዋል፡፡ እነዚህና ሌሎቸ የአዲስ አበባ መልኮች ደግሞ መዲናዋን፣ ከአገሪቱ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ባለቤትነት ባሻገር፣ የውጭ አገሮችና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ይዞታም ባለድርሻ አድርጎታል፡፡ በዚህ መነሻ በታሪካ አጋጣሚ ያረፈችበትን ቦታ ውዝግብ (በረራ፣ ፊንፊኔ ወይም ሸዋና ኦሮሚያ ዙሪያ) እንኳን ወደጎን ብለን በፈጠረችው ሁለንተናዊ ውህደትና ስብጥር ብቻ “የእኔ ነች”  “ያንተ ነች” ብሎ ማሰብና መወዛገብ ፍፁም ስህተትና “ያልበላትን የማከክ” ውጤት ነው፡፡

 ሸገር በጋራና በፍትሐዊነት ከምታመነጨው ኢኮኖሚያዊ ጥቅም፣ በፍትሐዊነት ለመከፋፈል ከማሰብ ይልቅ በስግብግብ አስተሳሰብ ሕዝብን ለማጋጨትና አገርን ለማወክ የሚዳርግ አሳፋሪ የፖለቲካ ትግል ለማካሄድ በከተማዋ ላይ መዶለትም ነውር ነው፡፡ የዛሬዎቹ ሁሉም ፖለቲከኞች እንደ ነውር ሊቆጥሩት የሚገባው ችግርም ነው፡፡ ይልቁንም ይቺ የአገር ብቻ ሳትሆን፣ የአኅጉርና የዓለም አቀፍ መቀመጫ የሆነች ምድር ለዓለምም በሚያኮራ መንገድ እንድትመነደግና ችግሯ እንዲቀረፍ ነው መታቀድ ያለበት፡፡ በጋራ እንዴት ልማቷን እናፋጥን? የሰላምና መረጋጋት አውድማስ እንዴት እናድርጋት? በማኅበራዊ ቀውስ (ሱስና ወንጀል) ውስጥ የተዘፈቁ በርካታ ወጣቶችንም በምን እንታደጋቸው? ሕዝቡስ በፍትሐዊነት ከከተማዋ ሀብት እንዴት ይጠቀም. . . ብሎ ነው መሥራት የሚያስፈልገው፡፡ ይህ ሳይደረግ ዋነኛ አጀንዳ ባልሆነው የባለቤትነት ጥያቄ ላይ ጉልበት ማባከንም ሆነ የምርጫ ፖለቲካ መሥራት ሊገታ የሚገባውና የማይበጅ ነው፡፡

ሸገር  ባለፉት ሁለት አሠርታት ሰፋፊ መንገዶች፣ ማሳለጫ፣ የባቡር መስመር፣ በርካታ የጋራ መኖሪያ ቤቶችና ሪል ስቴቶችን ብትገነባም ዛሬም ድረስ የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መሠረተ ልማት መሟላት የሚቀራት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በዚያው ልክ ከተማዋ የምታመነጨው በየዓመቱ እስከ 50 ቢሊዮን ብር የሚደርስ ሀብት ሲሆን፣ ይህ የሚሰበሰብ ገንዘብ ግን ለልማትና ለሕዝቦች ጥቅም በፍትሐዊነት የሚውልባት እንድትሆን መትጋት የዚህ ትውልድ ኃላፊነት መሆን አለበት፡፡

በእርግጥ አዲስ አበባ ባለፉት ዓመታት በሚወጣ ይፋዊ መረጃ፣ በአገሪቱ ካሉ ከተሞች ብቻ ሳይሆን፣ ከአፍሪካም ፈጣን አዳጊ ከተሞች ተርታ ተሠልፋም ነበር፡፡ ነገር ግን ይህ ተስፋ ሰጪ ጅምር እንዴት ይቀጥል እንደ መሬት፣ ግብር እና ቱሪዝም ያሉትን ወሳኝ ሀብት አመንጪ መስኮችስ እንዴት ከዘረፋና ሌብነት አፅድቶ ማስተዳደር ይቻላል ብሎ መትጋት የአስተዳደሩም ሆነ የፖለቲካ ኢሊቱ አጀንዳ መሆን ይኖርበታል፡፡

ይህን ነባራዊ ሀቅ ዕውን ለማድረግ ደግሞ የሚያስፈልገው “የእኛ እና “ኬኛ” ውዝግብ ሳይሆን፣ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተዋቀረ ጠንካራ አስተዳደርና በብቃታቸውና በሥነ ምግባራቸው የተመረጡ የአስተዳደር አካላት በየደረጃው መሰማራታቸው ነው፡፡ ከዚህ አንፃር አዲስ አበባ የራሷ ተወላጅ የሆነ ምሁርና የፖለቲካ ኤሊት የሌላት ይመስል፣ ወይም ኅብረ ብሔራዊ ማንነት ያላቸው ዜጎች የሚኖሩባት መሆኗ እየተዘነጋ በብሔር ፓርቲዎች በተደራጁ ዜጎች (በተለይ ከኦሮሚያ፣ አማራና ትግራይ) ብቻ ተመርጦ እንድትመራ የፖለቲካ ተፅዕኖ ማድረግም በአግባቡ ሊጤን የሚገባው ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱም ሆነ ራሱ የከተማዋ ቻርተር ተፈትሾ ዓለም አቀፍ ተሞክሮን ባገናዘበ መንገድ ሥራ ላይ መዋልም ይኖርበታል፡፡

እርግጥ አዲስ አበባ ካላት ተስፋ ባሻገር፣ የታጨቁባት ዋና ዋና ፈተናዎች ተለይተው ለመሠረታዊ ለውጥ መታገልም እየተዘናጋ መሆኑ ሁሉንም የሚያስቆጭ ሊሆን ሲገባ በሌላ አጀንዳ እየተድበሰበሰ ነው፡፡ ከነዚህ እውነታዎች አንዱ፣ ማኅበራዊ ህፀፆቻችንን (ሱሰኝነት፣ ሴተኛ አዳሪነት፣ ሌብነት፣ ካለሥራ መቀመጥና መሰል ችግሮች) ብንመለከት እጅጉን እየተባባሱ ከመጡ ሰነባብተዋል፡፡ በሃይማኖትና ማኅበራዊ መስተጋብር ለመቅረፍ የሚደረግ ሙከራ ቢኖርም፣ በፀጥታ ኃይልና ሕግ ማስከበር ወይም የሥራ ዕድልን በማስፋፋት ለማረም ጥረት ቢደረግም የመጣው ለውጥ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡

የፖለቲካ ኢሊቱ ግን መዲናዋን ያልበላትን በመፎከት፣ ትውልድ ባልተገባ መንገድ እንዲመክን በዝምታ እየታለፈ ነው፡፡ ሌላው የአዲስ አበባ ቀዳሚው ችግር ዘረፋ፣ ወረራና ሌብነት ነው፡፡ አንዳንዴ ይህ ዓይነቱ የማኅበራዊ ቀውስ አልፎ አልፎ መንግሥታዊ መዋቅሩን (በተለይ ፖሊስና ደንቦችን) ይዘው በነበሩ አንዳንድ መርህ አልባ ሰዎች እየታገዘ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ጉልበትና ሀብት ያለው ደካማውንና አናሳውን እየጨፈለቀ የሚፈጸመው እንደሆነ የሚታወቅ ነው፡፡ በውንብድናና ዘረፋ ረገድ ሕዝብን ይጠብቃል የተባለው የፖሊስና ፀጥታ ኃይል ሲዳከም ወይም ጥንካሬ ሲያጣ እየደረሰ ባለው የተደራጀ ዘረፋና ቅሚያ፣ የአዲስ አበባ ሕዝብ በጣም ተቸግሯል ቢባል ግነት የለውም፡፡ 

የነዋሪው ምሬትም ከሌብነት ጋር በተያያዘው ችግር ብቻ ሳይሆን በጉልበት በሚያስፈራሩ አውጪ አውራጅ፣ ሕገወጥ የመሬት ወራሪዎች ጭምር ሲሆን፣ ሠፈር ወቅትና ሁኔታ ሳይለይ እየተባባሰ ይገኛል፡፡ ወጣቱና የማኅበራዊ ድረ ገጽ አርበኛው ግን ያልበላውን በማከክ በአዲስ አበባ/ፊንፊኔ ውዝግብ ውስጥ ለመስመጥ ይቋምጣል፡፡ በጥፋት ላይ ሌላ ጥፋት እየጋበዘ  የጋራ  መዲናውን ለጉልበተኛና  ለቀማኛ አሳልፎ እየሰጠም ይገኛል፡፡

ዛሬ ላይ በሌብነት ውስጥ ሊከተቱ የሚችሉት ማታለል፣ ዘረፋ፣ ማጅራት መችነትና አስገድዶ መቀበል የመሳሰሉት ሥርዓት አልበኝነቶች ናቸው፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች አይደለም ለነዋሪው ለፖሊስና ለፀጥታ ኃይሉም የማይገዙ የቡድን ጉልበተኞችና ተደባዳቢዎችን (በቦሌ፣ በካራ፣ በመርካቶ፣ በሽሮሜዳ፣ በፈረንሣይ፣ በቃሊቲ፣ በአቃቂ፣ በልደታ፣ በፒያሳና በካዛንችስ፣ የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል፡፡) እንደሌሉ መቁጠርም መንግሥታዊ ድክመት ነው፡፡ በመቼውም ጊዜ ያልታየ በጦር መሣሪያ የታገዘ ዘረፋ፣ የተሽከርካሪ ስርቆት፣ የባንክ ዘረፋና መሰል አደጋዎች የመጪውን ጊዜ የአዲስ አበባ ፈተናዎች አመላካች ናቸው፡፡

 ከዚህ አንፃር በግልጽ መመልከት እንደሚቻለው አሁን ላይ በየመንደሩ “ውሻ በሠፈሩ አንበሳ ነው”ን የሚያስተርቱ የመንደር አለቆችን ለመታገል መትጋት ነው ቀዳሚው አጀንዳ መሆን ያለበት፡፡ የወንጀል ሥምሪቱ ምንጭም ሊለይ የሚችለው በዚሁ አቅጣጫ ትግል ማድረግ ሲቻል ብቻ ነው፡፡ ቀን እየተኙና እየተሠወሩ፣ ሌሊት ለሥራ የሚወጡ አፋኞች በተሽከርካሪና በጦር መሣሪያ (ጩቤ፣ አሲድ፣ ሚጥሚጣ. . . ሁሉ በኪስ ይያዛል) ጭምር እየታገዙ የውንብድና ሥራ ላይ መሰማራታቸውን ሕዝቡ ዋስትና ባጣ መንፈስ እየተናገረ እንደመሆኑ መንግሥት ይንኑ ለማረም መትጋትም ይጠበቅበታል፡፡

አንድ ሰሞን በከተማው ኮሚኒቲ ፖሊሲ የሚባል ሕዝብን ያሳተፈ የፖሊስ ሥራ የተጀመረ እንደነበር ባይካድም ቢጫና ጥቁር ከተቀቡ ቤቶቹ በስተቀር የቀረው እዚህ ግባ የሚባል ሥራ አለመኖሩ ቀዳሚው ድክመት ሆኗል፡፡ (ቢያንስ የለሊት ተረኞች የሉትም፣ ችግር ሲፈጠር ተደውሎ እንኳን ፈጥኖ የሚደርስ ፖሊስ ቀንሷል፣ ጥቅማጥቅም የሚያስቀድመው የፀጥታ አካል እየበዛ ነው፣ ቅንጅታዊ አሠራሩም የተዳከመ እንዳይሆን መፈተሽ ያለበት ጉዳይ ነው!!)

ከዚሁ ተነጥሎ የማይታየው ሌላው የመዲናችን ፈተና ከላይም እንደተጠቆመው የመሬትና የመንግሥት ቤትን መውረርና መስበር ነው፡፡ ከተማዋ ገና በሕዝብ አብላጫ ድምፅ የተመረጠ አስተዳደር ባላገኘችበት በዚህ የሽግግር ሊባል በሚችል ጊዜ፣ ከዚህ ቀደምም ሲታይ እንደነበረው ሁሉ ከፍተኛ የመሬት ወረራ፣ የኮንዶሚኒየምና የቀበሌ ቤቶች ብሎም ሙስናና ሕገወጥ ንግድን ለመግታት አበክሮ መታገል የአስተዳደሩ ኃላፊነት ሊሆን ይገባል፡፡ 

ይህ ድርጊት ደግሞ በአንድ በኩል በዚሁ በተበላሸው የብሔር ፖለቲካ እየተደናበረ በሌላ በኩል በሕገወጡና ሙሰኛው የበታች አመራርና ሙያተኛ (ወረዳና ክፍለ ከተማ ባለው) እየታገዘ እንደመሆኑ ሊያስተካክለው የሚችለው በዋናነት መንግሥት ነው፡፡ ዛሬም እንደትናንቱ ጥገኛው አመራርና ሙሰኛው ሕገወጥ ሀብት እያከማቸ፣ የአገር ሀብት ዘራፊውም መሬትን የመሰሉ የጋራ ሀብቶችን እየወረረና ባለይዞታውን እያፈናቀለ ጥቂቶች ሲበለፅጉ ማየት ለውጥን ከማክሸፍ ባሻገር አገርን የሚበድልና አመኔታን የሚያሳጣ ነው፡፡

 ለዚህ ደግሞ አገራችን  በጅምር ለውጥና ሽግግር ላይ መሆኗ ብቻ ሳይሆን፣ በዴሞክራሲ ማጠናከር ስም ሁሉ ነገር ለቀቅ መደረጉም አስተዋጽኦ ሳያበረክት አይቀርም፡፡ አንዳንድ በፖሊስና ፀጥታ ዘርፍ ላይ የነበሩና ያሉ የሌባ ተባባሪዎችም ችግሩ እንዲባባስ እያደረጉ መሆናቸውን ራሱ የፖሊስ መዋቅሩ በሰሞኑ ሕዝባዊ ስብሰባዎች ላይ ማስታወቁ እንደ ግብዓት ተቆጥሮ እርምት ሊያገኝ ይገባዋል፡፡

  በመሠረቱ ለውጡን ማደናቀፍ የሚሻው የቀቢፀ ተስፋ ኃይልም ሆነ መጪውን ምርጫ በፖለቲካ አሻጥር ለማጨናገፍ የሚቋምጠው ወገን ወረራ፣ ውንብድናና ሌባነት ወይም ሕጋዊ ሽፋን ያለውም ሆነ የሌለው ወሮበላነት እንዲስፋፋ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ማጤን የብልህ መንግሥት ብቻ ሳይሆን፣ የሩቅ አሳቢ የፖለቲካ ኤሊት ድርሻ ሊሆን  ይገባል፡፡ ስለዚህ እንዲህ ዓይነቱ ውጥንቅጥ እንዲወገድ ወይም እንዲቀንስ ሁላችንም ካልተባበርን የተጀመረው ተስፋ እስከ መጨለም ሊደርስ  እንዳይችል ያሳስባል፡፡

እንደ ሕዝብ ሌባው መጥቶ የአንዱን ዜጋ ኪስ ሲያወልቅ/በር ሲፈለቅቅ/መንገድ ሲዘጋ ወይም በነውጥ ሠፈር ሲያውክ፣ መሬት ሲወር የወል ሀብት (ቤት) ሰብሮ ሲገባ   በቅርብ ያለው ዜጋ መተጋገዝ እንዳለበት መግባባት ያስፈልጋል፡፡ የመክት አደረጃጀትም መፈጠር አለበት፡፡ ይህ ማኅበራዊ ትስስርም በትልልቁ ወንጀል ብቻ ሳይሆን፣ በጉልበት ሳይሠራ ዕቃ በማውረድ/መጫን ስም በአፀዳሁና መንገድ ጠገንኩ ሰበብ እያስገደደና እያስፈራራ ሊቀበል የሚሞክረውንም ዋልጌ  አደብ ለማስያዝ መሆን አለበት፡፡

ከዚህ አንፃር የከተማዋ ነዋሪዎችና ሰላም ወዳዱ ዜጋ ከጠባቂነት ወጥተን  በትጋት መደጋገፍ አለብን፡፡ ከተዘናጋን ግን መኖሪያና ሰላማዊ አካባቢ የሚያሳጣን ብቻ ሳይሆን ተያይዘን የምንወድቅ መሆናችንን መርሳት አይገባም፡፡ ለዚህም በሮንድ በዕድር፣ በማኅበር፣ በመኖሪያ አካባቢና መሰል አደረጃጀቶች ጭምር ኅብረትን ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ላይ የመንግሥትና የፀጥታ ኃይሉ ጥረትም የጎላ ሚና መጫወት ይኖርበታል፡፡

 በእርግጥ መንግሥት የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥና የዜጎች የመኖር ዋስትና እንዳይሸረሸር ከፍ ባለ የፖለቲካ ተነሳሽነት መሥራት ይኖርበታል፡፡ ሌብነትና ውንብድና የልማት የሰላምም ሆነ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እንቅፋት መሆኑ የታወቀ ስለሆነ በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን፣ በአገር አቀፍ ደረጃም ሊሠራበት ይገባል፡፡ ስለሆነም በቀዳሚነት በሕገወጥነት ላይ በተናጠል ብቻ ሳይሆን ማኅበራዊ ተቋማት የእምነት ተቋማት፣ የትምህርት ቤቶችና ሚዲያዎችንም አስተባብሮና አደራጅቶ እንደግሪሳ እየተሰማራ ላለው ሕገወጥ ኃይል የሥራ ዕድልን በማስፋፋትና ሕጋዊ ሥርዓት በማስፈን ችግሩን ማዳከም ያስፈልጋል፡፡ ይኖርበታልም፡፡

ሲቀጥል ከዘረኝነትና መበላላት እየወጡ፣ ዜጎች በየትኛውም አካባቢ ተንቀሳቅሰው መሥራትና መኖር እንዲችሉ ለመሥራትም አዲስ አበባን ሞዴል ለማድረግ መታገል የግድ ነው፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ለዘለቄታው የሞራልና ሥነ ምግባር ትምህርትን ማስፋፋትና ማጠናከር አገር ለመዳንና ሕዝብን ከችግር ለማውጣት ይረዳል፡፡ ለዚህ ደግሞ ሸገርን “ያልበላትን ከማከክ!” ሁለንተናዊ ዕድገቷንና ደኅንነቷን ማረጋገጥ ይቅደም እንላለን!! 

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles