Sunday, March 3, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊማሳዎችን መና የሚያስቀረው የአንበጣ ወረርሽኝ

ማሳዎችን መና የሚያስቀረው የአንበጣ ወረርሽኝ

ቀን:

ሚሊዮኖችን እንደዋዛ ካረገፉ በታሪክ ከማይዘነጉ የረሀብ ክስተቶች መካከል እ.ኤ.አ ከ1959 እስከ 1961 የዘለቀው ታላቁ የቻይና ረሀብ አንዱ ነው፡፡ አብዛኛው ቻይናዊ በተራበበት በዚህ ወቅት 15 ሚሊዮን ሰዎች እንደሞቱ የአገሪቱ መንግሥት ያምናል፡፡ ሌሎች ግን የሟቾቹን ቁጥር እስከ 43 ሚሊዮን ከፍ ያደርጉታል፡፡ እ.ኤአ. ከ1917 እስከ 1918 በዘለቀው የፋርስ ረሀብ ወቅትም እንዲሁ ከስምንት እስከ አሥር ሚሊዮን የሚሆኑ ኢራናውያን መሞታቸው ተመዝግቧል፡፡  ከ1782 እስከ 1784 በነበረው በቸሊሳ ጠኔም 11 ሚሊዮን ሰዎች አልቀዋል፡፡  ከ1932 እስከ 1933 በታየው የሶቪየት ረሀብም ከሦስት እስከ አሥር ሚሊዮን ዜጎች ማለቃቸው ይገመታል፡፡ ከ250 ዓመታት በፊት በቤንጋል ተከስቶ የነበረው ረሀብም አሥር ሚሊዮን ሰዎችን ከአፈር ቀላቅሏል፡፡ ጠኔው በከፋባቸው በአንዳንድ የዓለም ክፍሎች የሚኖሩ የአይጥ ሥጋ እስከ መብላት ደርሰዋል፣ እንደ ከብት ሳር ግጠዋል፣ ሌሎችም በሰላሙ ጊዜ የሚቀፏቸውን ነገሮች እንደ ምግብ አላምጠዋል፡፡

በኢትዮጵያም በተለያዩ ዘመናት በተለይ በ19ኛውና በ20ኛው ምዕት ዓመት በተከሰቱ ረሀቦች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሞተዋል፡፡ በሌላው ዓለም ታሪክ ሆኖ የቀረ ረሀብ ግን እስከ ቅርብ ጊዜ ኢትዮጵያን ደጋግሞ ጎብኝቷታል፡፡ አሁንም የምግብ ድጋፍ ስለሚደረግላቸው እንጂ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎችን ሊያስርብ የሚችል የምግብ ዋስትና ችግር በአገሪቱ መኖሩ የሚታወቅ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ከ100 ሰዎች መካከል 45ቱ ከድህነት ወለል በታች የሆነ ኑሮ እንደሚገፉ የዓለም ምግብና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) እ.ኤ.አ በ2004 ያወጣው ሪፖርት ያሳያል፡፡ ድርጅቱ ከ40 እስከ 60 በመቶ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን የምግብ ዋስትና ችግር እንዳለባቸውም በወቅቱ አስታውቆ ነበር፡፡ ከ16 ዓመታት በኋላም የምግብ ዋስትና ጉዳይ አሳሳቢ እንደሆነ አለ፡፡ በዚህ አገራዊ ቀውስ ጓዳው የሚጎድለውና የሚራበው ዜጎችን አርሶ የሚያበላው አርሶ አደርና የአርብቶ አደሩ ማኅበረሰብ ነው፡፡

በድህነት ከሚጠቀሱ አገሮች በመጀመርያዎቹ ተርታ በምትሰለፈው ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትና ጉዳይ እስካሁን ምላሽ ያላገኘ አገራዊ አጀንዳ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ኋላ ቀር የአስተራረስ ዘዴ፣ የአየር ንብረት ለውጥ (ድርቅ፣ ጎርፍ)፣ የሕዝብ ቁጥር መጨመርና ሌሎችም አገሪቱ ላለባት የምግብ ዋስትና ችግር ምክንያት ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ የበረሃ አንበጣ ወረርሽ የምግብ ዋስትና ላይ የተደቀነ ሌላው ሥጋት ሆኗል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ካለፈው ዓመት ሰኔ 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ኢትዮጵያ እየገባ የሚገኘው የበረሃ አንበጣ ወረርሽኝ ባለድርሻ አካላትን ዕረፍት የነሳ ብሔራዊ ጉዳይ ሆኗል፡፡ የአፍሪካ ቀንድ አገሮችን በስፋት እያጠቃ ሲሆን፣ ወደ ኢትዮጵያ የሚገባውም ኢትዮጵያ በምሥራቅ በምትዋሰናቸው ሶማሊያ፣ ሶማሊላንድ እንዲሁም በኬንያ በኩል በሚገኙ አምስት መግቢያዎች መሆኑን የሚናገሩት በግብርና ሚኒስቴር የዕፀዋት ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ ዘብዴዎስ ሳላቶ ናቸው፡፡ በእያንዳንዱ መግቢያ በትንሹ በቀን አንድ  የበረሃ አንበጣ መንጋ ወደ ኢትዮጵያ ይገባል ይላሉ፡፡

በዚህ ወቅት የታየው የአንበጣ መንጋ በምሥራቅ አፍሪካ በ25 ዓመት ውስጥ ከተከሰቱ ወረርሽኞች ትልቁና አደገኛው ነው ተብሏል፡፡ ወረርሽኙ በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ላይ ከፍተኛ የምግብ ዋስትና ፈተና እንደሚሆን እየተነገረ ነው፡፡ በጎረቤት አገር ኬንያ እጅግ በጣም አደገኛ የተባለው የአንበጣ መንጋ በአንዴ 60 ኪሎ ሜትር ርዝመት፣ 40 ኪሎ ሜትር ስፋት ያለውን ቦታ ሸፍኖ ሲንቀሳቀስ ታይቷል፡፡ አንድ የአንበጣ መንጋ በአንድ ስኩዌር ኪሎ ሜትር ውስጥ 150 ሚሊዮን አንበጣዎችን ይይዛል፡፡ አንድ መንጋ የንፋስ አቅጣጫን ተከትሎ የሚንቀሳቀስ ሲሆን፣ በቀን ከ100 እስከ 150 ኪሎ ሜትር ቦታዎችን ያዳርሳል፡፡

አንድ የአንበጣ መንጋ በአማካይ በቀን 2,500 ሰዎችን መመገብ የሚችል ሰብል ያጠፋል፡፡ ሶማሊያን፣ ሱዳንን፣ ኤርትራን፣ ኢትዮጵያንና የመንን ያጠቃው ይህ የበረሃ አንበጣ መንጋ እስካሁን ሚሊዮኖችን ሊመግብ የሚችል ሰብል ማጥፋቱ እየተነገረ ነው፡፡ የአንበጣ ወረርሽኝ አስከፊ ውጤት እንዳለው የሚናገሩ አካላት ከዚህ ቀደም የታዩ ክስተቶችን በማስረጃነት በማቅረብ አፋጣኝና በቂ ምላሽ እንዲሰጥበት ያስጠነቅቃሉ፡፡ እ.ኤ.አ. በ2003 እና በ2005 በሰሜን አፍሪካ አገሮች ላይ ተከስቶ የነበረውን ወረርሽን ለመቆጣጠር 500 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ወይም 15 ቢሊዮን ብር እንደፈጀ፣ 2.5 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚገመት ሰብል መጥፋቱን ከፋኦ የተገኘ መረጃ ያሳያል፡፡

የአንበጣው ወረርሽኝ መነሻ የሆነችው የመን በጦርነቱ የገባችበትን ከፍተኛ የሰብዓዊ ቀውስ አባብሶታል፡፡ አደጋውን የመከላከል አቅም ያለው መንግሥት አለመኖሩም ወረርሽኙን ለመከላከል የሚደረገውን ትግል የአንድ ወገን ብቻ እንዲሆን አድርጎታል፡፡

አቶ ዘብዴዎስ እንደሚሉት፣ ወረርሽኙን ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር ያልተቻለው አንድም የመን፣ ሶማሊያና ሶማሊላንድ የተቀናጀ የመከላከል ሥራ ባለመሥራታቸው ነው፡፡

እሳቸው እንደሚሉት፣ መንጋው ወደ ኢትዮጵያ መግባት በጀመረባቸው በመጀመርያዎቹ ጊዜያት መንግሥት አንበጦቹ የጣሏቸውን እንቁላሎች በማጥፋት ረገድ ትልቅ ሥራ ሠርቷል፡፡ ይሁን እንጂ ብዙም ጠንካራ መንግሥት በሌለባቸው አዋሳኝ አገሮች ላይ ተመሳሳይ ሥራ ባለመሠራቱ ያደጉና ራሳቸውን ለመተካት ዝግጁ የሆኑ አንበጣዎች ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን ቀጥለዋል፡፡

መንጋዎቹ ለመራቢያ ምቹ ወደ ሆኑ ወደ አፋር፣ አማራ፣ ኦሮሚያና ደቡብ ክልሎች እንዲሁም ድሬዳዋ ከተማ እየገቡ ነው፡፡ ባለፈው ጥቅምት ወር ላይ የግብርና ሚኒስቴር ባወጣው ሪፖርት መሠረት መንጋዎቹ በ56 ወረዳዎች ውስጥ 174 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ቦታ ላይ አርፈው ነበር፡፡ በየቀኑም 8,700 ሜትሪክ ቶን አረንጓዴ ዕፀዋትን ይመገብ እንደነበር ያሳያል፡፡ በወቅቱ በወጣው መረጃ መሠረት በአንድ ኪሎ ሜትር ስኩዌር ቦታ ላይ 30 ሚሊዮን አንበጣዎች ይኖራሉ፡፡ መንጋዎቹ በሚንቀሳቀሱባቸው በተመረጡ 28,671 ሄክታር ቦታዎች ላይ ካለፈው ዓመት ሐምሌ እስከ መስከረም 2012 ዓ.ም. በተደረገ ዳሰሳ 17,370 ሄክታር ቦታ በመንጋው ተይዞ ነበር፡፡ እስከ ጥቅምት ወር ድረስ መንግሥት መቆጣጠር የቻለውም 6,455 ቦታዎችን ብቻ እንደነበር ሪፖርቱ ያሳያል፡፡

መንግሥት ወረርሽኑ ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ 200 ባለሙያዎችን ወደየአካባቢው አሰማርቶ ወረርሸኙን ለመቆጣጠር ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡ አቶ ዘብዴዎስ እንደሚሉት፣ የፌዴራል መንግሥት ካሰማራቸው 200 ባለሙያዎች በተጨማሪ በየክልሎቹ ተመድበው የሚሠሩ ሌሎች በርካቶች አሉ፡፡ እነዚህ ባለሙያዎች መረጃዎችን በኤስኤምኤ (ባጭር መልዕክት) እየተለዋወጡ በየአካባቢው ያለውን እንቅስቃሴ የሚያሳውቁበት የስልክ መተግበሪያ ተጭኖላቸዋል፡፡ ኬሚካሎች፣ የአውሮፕላን ነዳጅ የሚጭኑ ባለሙያዎችም የሚንቀሳቀሱባቸው 17 ተሽከርካሪዎች ተመድበዋል፡፡ ኬሚካል የሚረጩ አራት አውሮፕላኖችም ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡ ይሁንና ወረርሽኙን ለመቆጣጠር በቂ አልሆነም፡፡

መሥሪያ ቤቱ ባለፈው ሳምንት ይፋ ባደረገው ሪፖርት የበረሃ አንበጣው በሶማሌ፣ በአፋር፣ በአማራ፣ በትግራይ፣ በኦሮሚያና ደቡብ ክልሎች በ2,350 ስኩዌር ኪሎ ሜትር  ቦታ ጥቃት አድርሷል፡፡ እስካለፈው ጥቅምት ወር ድረስ ወረርሽኙ 56 ወረዳዎችን ያጠቃ ሲሆን፣ ከዚያ ወዲህ ባሉት ጊዜያት ደግሞ ወደሌሎች 69 ወረዳዎች ተዛምቷል፡፡ 

መጪው የአየር ሁኔታ ደግሞ ለመራባት ምቹ አጋጣሚ ስለሚፈጥር ወረርሽኙ የበለጠ ሊስፋፋ እንደሚችል የፋኦ ሪፖርት ያሳያል፡፡ እስከ ሰኔ ወር ድረስ የተባዮቹ ቁጥር በ500 በመቶ ሊጨምር እንደሚችልም ተነግሯል፡፡

መንጋው እስካሁን ምን ያህል ሰብል እንዳጠፋ የሚገልጽ ጠቅለል ያለ መረጃ በሚኒስቴሩ በኩል በቅርቡ ይፋ እንደሚደረግ ተገልጿል፡፡ ያደረሰው አደጋ በጥቅሉ ሲታይ ግን የወረርሽኙን ያህል እንዳልሆነ ‹‹እግዚአብሔር ጠብቆናል ከባድ የሚባል ጥፋት አልደረሰም፤›› በማለት አቶ ዘብዴዎስ ገልጸዋል፡፡ እንዲህ ያለ የአንባጣ ወረርሽኝ በአንድ አገር ሲከሰት እስከ 30 በመቶ የሚደርስ የሰብል ጥፋት እንደሚያደርስ፣ ነገር ግን በዚህ መጠን የከፋ ጉዳት አለመድረሱን አስረድተዋል፡፡

ለዚህም ወረርሽኙን ለመቆጣጠር በዘመቻ ከሚከናወነው ሥራ ባሻገር የአንበጣዎቹ የዕድገት ደረጃ ዋነኛውን ሚና ተጫውቷል ይላሉ፡፡ በአምስቱ መግቢያዎች ወደ ኢትዮጵያ የሚሻገሩት የአንበጣ መንጋዎች በብዛት ዕድገታቸውን የጨረሱ ናቸው፡፡ ዕድገቱን የጨረሰ አንበጣ ደግሞ የሚበላው በቀን ሲያስፈልገው ብቻ ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ሲበር የሚውል ሲሆን፣ የሚመገበው ከጠዋት እስከ 6 ሰዓት እና ከ10 ሰዓት እስከ ማምሻው ድረስ ብቻ ነው፡፡ እነዚህ መንጋዎች ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡት ለርቢ ምቹ ቦታዎችን እየፈለጉ ራሳቸውን ለመተካት ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት አረንጓዴ ወደ ሚበዛባቸው የአገሪቱ ክፍሎች እየተዛመቱ እንቁላላቸውን እየጣሉ ይገኛሉ፡፡

ወረርሽኙን ለመቆጣጠር የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል እየተጠየቀ ነው፡፡ አቶ ዘብዴዎስ እንደሚሉት፣ በአሁኑ ወቅት ኬሚካል እንዲረጩ የተመደቡ አራት አውሮፕላኖች በድሬዳዋ፣ በጎዴ፣ በባሌና በአርባ ምንጭ ተመድበው በቀን እስከ ሦስት ጊዜ ርጭት ያከናውናሉ፡፡ ነገር ግን ይህ ብቻ በቂ ባለመሆኑ ቢያንስ ሁለት ተጨማሪ አውሮፕላኖች እንዲመደቡ ተጠይቋል፡፡

አውሮፕላኖቹን መንግሥት ከዘመን ፍላይትና አሚባራ ጠቅላላ አቪዬሸን በኪራይ መውሰዱን፣ አውሮፕላኖቹ በበረሩ ቁጥር በሰዓት 1,650  ዶላር እንደሚከፈልባቸው፣ አውሮፕላኖቹ የኬሚካል ርጭት ሲያደርጉ በቀን እስከ አራት ሰዓታት እንደሚበሩ አቶ ዘብዴዎስ ገልጸዋል፡፡ አውሮፕላኖቹ በበረራ የሚያሳልፉት ጊዜ ከአንድ ሰዓት ከበለጠ የሚከፈልባቸው የዋጋ መጠን ከበፊተኛው እያደገ እንደሚሄድ አስረድተዋል፡፡

መንጋውን ለመቆጣጠር የሚደረገው ጥረት ሚሊዮኖችን ከመራብ ኢትዮጵያን ከአስከፊ የሰብአዊ ቀውስ ማዳን ነውና ለነገ የማይባል ጉዳይ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...