Monday, December 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ማዕድን ሚኒስቴር ለአራት ኩባንያዎች የማዕድን ምርመራ ፈቃድ ሰጠ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር አምስት የማዕድን ምርመራ ፈቃዶችን ለአራት የአገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች ሰጠ፡፡

ወርቅ፣ ብረትና ራዮላይት የተሰኘ ድንጋይ ማዕድናት ፍለጋ በአማራና በደቡብ ክልሎች ለማካሄድ ፈቃድ የተሰጣቸው ኩባንያዎች አለታ ላንድ ኮፊ፣ ሮዝ ኢትዮጵያ፣ አጎዳዩ ሜታልስና ኤዋን ማርብል ኤንድ ግራናይት ናቸው፡፡ የማዕድን ፍለጋ ስምምነቱን የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትሩ ከኩባንያዎቹ ኃላፊዎች ጋር ዓርብ ጥር 15 ቀን 2012 ዓ.ም. በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ተፈራርመዋል፡፡

የውሉ ስምምነት ፊርማው ከተፈረመበት ቀን ጀምሮ ለሦስት ዓመታት እንደሚፀና፣ የፈቃድ ዘመኑ ሲጠናቀቅ በባለፈቃዱ ጥያቄ መሠረትና ሚኒስቴሩ ሲያምንበት ሊታደስ እንደሚችል ተገልጿል፡፡

ኩባንያዎቹ ፈቃድ ያገኙት በአማራና በደቡብ ክልሎች ሲሆን በወርቅ፣ ብረትና ብረት ነክ ማዕድናትና ራዮላይት (ዳይሜንሽን ስቶን) ማዕድናት ላይ ምርመራ እንደሚያካሂዱ ተገልጿል፡፡

ኩባንያዎቹ ለኢንቨስትመንት ወጪ በአጠቃላይ 44.9 ሚሊዮን ብር እንደመደቡ፣ በፍለጋው ምዕራፍ ለ57 ኢትዮጵያውያን የሥራ ዕድል እንደሚፈጥሩ ተነግሯል፡፡

የምርመራ ሒደታቸውን በስኬት አጠናቀው ወደ ሥራ ሲገቡ ከሥራ ዕድል ፈጠራ በተጨማሪ፣ የውጭ ምንዛሪ ግኝትና ማዳን ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ተገልጿል፡፡

በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትሩ ሳሙኤል ኡርካቶ (ዶ/ር)፣ መንግሥት የማዕድን ዘርፉን ለመለወጥ በከፍተኛ ቁርጠኝነት እየሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ተቋማዊና የፖሊሲ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ በመሥራት ላይ እንደሆነ የገለጹት ሚኒስትሩ፣ በዘርፉ የሚስተዋሉ ማነቆዎችን ለመፍታት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ የተለያዩ ማዕድናት ባለቤት በመሆኗ የግሉን ዘርፍ አስተባብሮ በመሥራት ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ መፍጠር እንደሚቻል ገልጸው፣ የማዕድናት ዘርፍ አሁን ባለው ሁኔታ እንደማይቀጥልና በመጪው ዓመት ወደ ከፍተኛ ገቢ አመንጪነት እንደሚሸጋገር አስታውቀዋል፡፡

ኩባንያዎቹ ከአካባቢ ማኅበረሰቦችና የክልል መንግሥታት ጋር ተባብረው እንዲሠሩ፣ በቀረቡት የሥራ ዕቅድ መሠረት ተግተው ሥራቸውን እንዲያከናውኑ አሳስበዋል፡፡

ሚኒስቴሩ ከአንድ ዓመት በላይ በሆነ ጊዜ ከ200 በላይ የማዕድን ፈቃዶችን መመርመሩን ገልጸው አብዛኞቹ ወደ ሥራ እንዲገቡ አቅጣጫ እንደተቀመጠላቸው፣ የተቀሩት ቦታ ይዘው የሚቀመጡ ኩባንያዎች ላይ ዕርምጃ እየተወሰደ በምትካቸው የሚሠሩ ኩባንያዎች እንዲገቡ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡ ሥራ እንዲያቆሙ ስለተደረጉት የሚድሮክ ጎልድ ለገደምቢ ወርቅ ማምረቻና የቀንጢቻ ታንታለም ማምረቻ ጉዳይ ተጠይቀው፣ በማዕድን ማምረቻዎቹ ላይ ጥናቶች መካሄዳቸውን ገልጸዋል፡፡ ቀሪ ሥራዎች እንዳሉም አክለዋል፡፡ ከዚህ በኋላ የአካባቢ ማኅበረሰብ ተጠቃሚነትና የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መንገድ መካሄድ እንደሚኖርበት አስረድተዋል፡፡

‹‹ከዚህ በኋላ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የማዕድን ልማት አሠራር እንዲኖረን ነው የምንፈልገው፤›› ያሉት ሚኒስትሩ፣ ኩባንያዎች የአካባቢ ኅብረተሰብ በማሳተፍ ከሠሩ ችግር እንደማይገጥማቸው ተናግረዋል፡፡

የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር የለውጥ ትግበራ ከጀመረ በኋላ ባለፈው በጀት ዓመት 30 የማዕድን ምርመራና ምርት ፈቃድ እንደሰጠ ታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች