Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናለሕገ መንግሥቱ ታማኝ መሆን ዳኞችን ለመመዘን እንዳይውል የሚከለክል ረቂቅ አዋጅ ቀረበ

ለሕገ መንግሥቱ ታማኝ መሆን ዳኞችን ለመመዘን እንዳይውል የሚከለክል ረቂቅ አዋጅ ቀረበ

ቀን:

ፓርላማው በዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ውስጥ የነበረው ውክልና ከረቂቅ አዋጁ ተሰርዟል

ለሕገ መንግሥቱ ታማኝ ሆነው አልተገኙም በማለት አንድ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛን በ2008 ዓ.ም. ከዳኝነት ሹመታቸው ያነሳው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ለሕገ መንግሥቱ ታማኝ መሆንን ከመመዘኛ መሥፈርትነት የሚሰርዝና የዳኝነት ነፃነትን ለመጠበቅ ያለሙ ሌሎች ድንጋጌዎችን የያዘ አዲስ ረቂቅ አዋጅ ቀረበለት።

ረቂቅ አዋጁ ላለፉት በርካታ ዓመታት የፌዴራል ዳኞችን ለመመልመልና በፓርላማው ለማሾም ጥቅም ላይ ሲውሉ ከነበሩት መመዘኛዎች መካከል፣ ‹‹ለሕገ መንግሥቱ ታማኝ መሆን›› የሚለውን መመዘኛ የሚያስቀርና በምትኩም ሌሎች አዳዲስ መመዘኛዎችን አካቶ ይዟል።

በሥራ ላይ የሚገኘውን አዋጅ ቁጥር 684/2002 እንደሚተካ የሚጠበቀው ይህ ረቂቅ የሕግ ሰነድ “የዳኝነት አስተዳደር አዋጅ” የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን፣ ከአንድ ሳምንት በፊት ለምክር ቤቱ ቀርቦ የመጀመርያ ውይይት ተደርጎበታል።

በሥራ ላይ ያለው አዋጅ ቁጥር 684/2002 አንቀጽ 11 (1) ሥር ከተቀመጡት ለዳኛነት የሚያበቁ መመዘኛዎች መካከል በንዑስ አንቀጽ (1)(መ) ሥር፣ ‹‹ለሕገ መንግሥቱ ታማኝ የሆነ፣ ለሕገ መንግሥቱ ታማኝ ስለመሆኑና ሕገ መንግሥቱን በሚቃረን ተግባር ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተሳትፎ እንደማያውቅ በጽሑፍ ማረጋገጨ የሚሰጥ›› ሊሆን እንደሚገባ ተደንግጓል።

ይህ ድንጋጌ ዳኞችን ለመመዘን አግባብነት የሌለው በመሆኑ እንዲወጣ ተደርጎ ረቂቅ አዋጁ መቀረፁን የማብራሪያ ሰነዱ ያስረዳል። የሥራ ዘመኑን ሊያጠናቅቅ የጥቂት ወራት ዕድሜ የቀረው የአምስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የሥልጣን ዘመኑን በ2008 ዓ.ም. መስከረም ወር ላይ ከጀመረ ከጥቂት ወራት በኋላ የዲሲፕሊን ጥሰት ፈጽመዋል የተባሉ አንድ ዳኛን፣ ከዳኝነት እንዲያሰናብት የሚጠይቅ የውሳኔ ሐሳብ ቀርቦለት ነበር።

በዳኞች አስተዳደር ጉባዔ የተዘጋጀው ይህ የውሳኔ ሐሳብ ከ2006 ዓ.ም. ጀምሮ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በዳኝነት ሲያገለግሉ የቆዩት ዳኛ አቶ ግዛቸው ምትኩ ለሕገ መንግሥቱ ታማኝ ሆነው እንዳልተገኙ በመጥቀስ፣ ፓርላማው ከሹመት አንስቶ እንዲያሰናብታቸው የሚጠይቅ ነበር፡፡

የውሳኔ ሐሳቡ አራት የዲሲፕሊን ክሶችን በዳኛው ላይ ያቀረበ ሲሆን፣ ሁሉም ክሶች አቶ ግዛቸው ለሕገ መንግሥቱ ታማኝ አለመሆናቸውንና ፖለቲካዊ ወገንተኝነት የሚያንፀባርቁ እንደነበረ የሚያመለክቱ ነበሩ።

ከእነዚህም መካከል አቶ ግዛቸው የዳኞች ሥነ ምግባር ረቂቅ ደንብን በተመለከተ የፍትሕ አካላትን ለማወያየት ተዘጋጅቶ በነበረ መድረክ ላይ፣ ‹‹ዳኛ ሕገ መንግሥቱ ላይ ልዩነት (Reservation) ቢኖረውም ዳኛ ሆኖ መሥራት ይቻላል፤›› የሚል አቋም ማንፀባረቃቸው፣ በ2006 ዓ.ም. ደግሞ ለፌዴራል ዳኞች በተዘጋጀ የሥልጠና መድረክ ላይ፣ ‹‹የሰበር ችሎት ዳኞች የሰጡት ውሳኔ ከሕገ መንግሥቱ የሚቃረን ከሆነ፣ የበታች ፍርድ ቤት ዳኞች መቀበል የለባቸውም በማለት ተከራክረዋል፤›› የሚሉት በዳኛው ላይ ከቀረቡት ክሶች መካከል ዋነኞቹ ነበሩ።

ከዚህ በተጨማሪ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ የማይቀበሏቸው ሐሳቦች መኖራቸውን በሌሎች አጋጣሚዎች ይናገሩ እንደነበር፣ ከሌሎች ዳኞች ጋርም ተግባብቶ የመሥራት ችግር እንዳለባቸው በዳኛው ላይ የቀረቡት ሌሎች ክሶች ነበሩ።

 የውሳኔ ሐሳቡ ዳኛው ለቀረበባቸው ክስ የሰጡትን ምላሽና ክርክር ያካተተ ሲሆን፣ በዚሁ መሠረትም በመልስ ክርክራቸው እንደ አንድ ዳኛና እንደ ዜጋ ሕገ መንግሥቱን በማክበርና ሕገ መንግሥቱን መሠረት በማድረግ የወጡ ሕጐችን፣ ፖሊሲና ስትራቴጂዎችን በማክበር ኃላፊነትን መወጣት ያለባቸው መሆኑን እንደሚያምኑ መግለጻቸውን ያትታል።

‹‹ለፍትሕ አካላት ማሠልጠኛ ማዕከል ካሪኩለም ለማዘጋጀት በተደረገ መድረክ ላይ ዕጩ ዳኞችና ዓቃቤ ሕጎች ወደ ሥልጠና ማዕከሉ ሲመጡ በሕገ መንግሥቱ ላይ ልዩነት ቢኖራቸው እንኳን፣ የሙያ ብቃት ካላቸው ተቀብሎ አመለካከታቸውን በሥልጠና መለወጥ ይገባል የሚል አስተያየት ከመስጠታቸው ውጪ፣ የተሾመ ዳኛ በሕገ መንግሥቱ ላይ ልዩነቱ ሊኖረው ይችላል አለማለታቸውን፣ ቢሉም ሕገ መንግሥቱ ሊሻሻል እንደሚችል ራሱ እንደሚገልጽና ማሻሻል የሚችልባቸውን ድንጋጌዎች የያዘ መሆኑን፣ የእሳቸው ለሕገ መንግሥቱ ታማኝ ከመሆን ወይም ካለመሆን ይልቅ መታየት ያለበት ለሕገ መንግሥቱ ተገዥ መሆናቸው እንደሆነና እሳቸው ለሕገ መንግሥቱ ተገዥ እንደሆኑ መገለጫውም ሕግን መሠረት አድርገው እየሠራሁ ነው፤›› የሚል የመልስ ክርክር ማቅረባቸውን፣ የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ በወቅቱ ለምክር ቤቱ አቅርቦት በነበረው የውሳኔ ሐሳብ ላይ ሰፍሮ ነበር።

ፓርላማው ይህንን ጉዳይ በተመለከተበት ወቅት ጥቂት የምክር ቤቱ አባላት ዳኛው በውይይት መድረክ ያነሱትን ሐሳብ መነሻ አድርጐ እዚህ ድምዳሜ ላይ የመድረስ ተገቢነትን፣ እንዲሁም ዳኛው በውይይት መድረኮች ተሳትፎ ሲያደርጉ ሐሳብ አቀረቡ እንጂ፣ ከተግባር ጋር የተያያዘ የዲሲፕሊን ጥፋት መፈጸማቸውን የሚያሳይ አይደለም የሚል ጥያቄ አቅርበው ነበር፡፡

በወቅቱ በፓርላማ የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትርና የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ አባል የነበሩት አቶ አስመላሽ ወልደ ሥላሴ፣ ለተነሱት ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ ዳኛው ሐሳባቸውን ስለገለጹ ሳይሆን፣ ለዳኛነት ዋነኛ የሆነው ሕገ መንግሥቱን ለማክበርና ለማስከበር ፍፁም ሆኖ የመገኘት መሥፈርት በመጣሳቸው እንደሆነ ተናግረው ነበር።

‹‹አቶ ግዛቸው የሕግ ምሁር ናቸው፡፡ ስለዚህ ሕግ ተምረዋል፡፡ ሕግ ሲማሩ ደግሞ ሕገ መንግሥቱን ተምረዋል፡፡ ከዚያም አልፎ ወደ ዳኝነት ከመምጣታቸው በፊት የሕገ መንግሥት ሥልጠና ወስደዋል፡፡ አሁን ግን በየመድረኩ ነው በሕገ መንግሥቱ ላይ ያላቸውን ልዩነት የሚገለጹት፤›› ሲሉ አቶ አስመላሽ ምላሽ ሰጥተው ነበር። አንድ ዳኛ ከኃላፊነት የሚነሳው በተግባር ሕግ ሲጥስ ነው የሚል ድንጋጌ በሕገ መንግሥቱም ሆነ በዳኞች አስተዳደር ጉባዔ አዋጅ ላይ አለመኖሩን በመጥቀስ፣ አቶ አስመላሽ ያቀረቡትን ምላሽ ካዳመጠ በኋላ ወደ ድምፅ የገባው ፓርላማው የውሳኔ ሐሳቡን በሙሉ ድምፅ በማፅደቅ አቶ ግዛቸውን ጥር 28 ቀን 2008 ዓ.ም. ከዳኝነት አሰናብቷል።

በዚህ ውሳኔ ምክንያትም ቀጣይ ሕይወታቸውን በጥብቅና ሙያ ለመምራት ወይም በሕግ መምህርነት ለመቀጠር ከፍተኛ ችግር የገጠማቸው አቶ ግዛቸው፣  ከጥቂት ቆይታ በኋላ ከአገር ለመሰደድ እንደተገደዱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ይህ ከሆነ ከአራት ዓመታት በኋላ የዳኝነት አስተዳደር አዋጅ የሚል ስያሜ ተሰጥቶት ከሳምንት በፊት ለምክር ቤቱ የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ዳኛን፣ ለሹመት ከሚያበቁ መመዘኛዎች አንዱ የነበረውን ለሕገ መንግሥት ታማኝ የመሆን መሥፈርት ተገቢ ስላልሆነ እንዲወጣ አድርጎታል።

የተገለጸው መመዘኛ ተገቢነት የሌለው በመሆኑ እንዲወጣ ያስፈለገበትን አመክንዮ የረቂቅ አዋጁ ማብራሪያ ሰነድ አካቶ አቅርቧል። ‹‹ዳኛ ሕግን የሚተረጉመው ስለ ሕጉ ካለው የግል ስሜት አኳያ ሳይሆን፣ የሕጉን ይዘት መሠረት በማድረግ ነው፤›› የሚለው ማብራሪያ ሰነዱ፣ አንድ የሕግ ባለሙያ የተወሰነ የሕግ አንቀጽ እንዲሻሻል ሐሳብ የሚያቀርብ ቢሆን እንኳ፣ ድንጋጌው ሳይሻሻል ፀንቶ የሚቆይ እስከሆነ ድረስ ይህንን ድንጋጌ ያከብራል።

‹‹ሕግን የማክበር ጉዳይ የዜግነት ግዴታ (Civic Duty) በመሆኑና ይህም ከማንኛውም ዳኛ የሚጠበቅ መሆኑ ስለሚታወቅ፣ ይህንን እንደ መመዘኛ መደንገግ አስፈላጊነት የለውም፤›› በማለት፣ ለሕገ መንግሥቱ ታማኝ መሆን ዳኞችን ለመሾም በመመዘኛነት ጥቅም ላይ መዋል እንደሌለበት ይገልጻል።

ከዚህ ይልቅ፣ ‹‹ከፍ ያለ የፍትሕ ስሜት ያለውና ለሕግ የበላይነት መከበር ቁርጠኛ የሆነ›› የሚል መመዘኛነት በረቂቅ አዋጁ እንዲካተት የተደረገ ሲሆን፣ ይህ ድንጋጌ ማንኛውም ዳኛ ለሕገ መንግሥቱም ሆነ ለሁሉም ሕጎች ሊኖረው የሚገባውን ተገዥነት የሚገልጽ እንደሆነ ማብራሪያው ያስረዳል።

ረቂቅ አዋጁ የፌዴራል ዳኛ ሆኖ ለመሾም በመመዘኛነት ጥቅም ላይ ሲውሉ የነበሩ መሠረታዊ መሥፈርቶችን፣ ማለትም ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያለው፣ ዕውቅና ካለው ከፍተኛ የትምህርት ተቋም በሕግ ትምህርት ቢያንስ የመጀመርያ ዲግሪ ያለውና ዳኛ ሆኖ ለመሥራት ፈቃደኛ መሆን ከሚሉት በተጨማሪ፣ የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ በሚያደርግለት ቃለ መጠይቅ፣ የማጣሪያ ፈተናና ሌሎች የባህርይ ምርመራዎች ብቁ ሆኖ መገኘትን አካቶ ይዟል።

በተጨማሪም የፌዴራል ፍርድ ቤቶች በሆኑት የመጀመርያ፣ የከፍተኛና የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ ሆኖ ለመሾም አሁን ባለው አሠራር የሚጠየቀውን መነሻ ዕድሜና የልምድ መሥፈርቶችን ከፍ እንዲሉ ተደርጎ በረቂቁ ድንጋጌዎች ቀርቧል።

በዚህም መሠረት ለፌዴራል ፍርድ ቤት ይጠየቅ የነበረውን መነሻ ዕድሜ ከ25 ዓመት ወደ 30 ዓመት ከፍ እንዲል ያደረገ ሲሆን፣ ለመጀመርያ ፍርድ ቤት ዳኛ ሆኖ ለመሾም ከሚያበቁ የሥራ ልምድ መመዘኛዎች መካከል ቢያንስ ለሦስት ዓመት በረዳት ዳኛነት ወይም በክልል ፍርድ ቤቶች ቢያንስ ለሦስት ዓመት በዳኝነት ያገለገለ ሊሆን እንደሚገባ በረቂቁ ተካቷል።

የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ ሆኖ ለመሾም ከሚያበቁ የሥራ ልምድ መመዘኛዎች መካከል ደግሞ፣ በፌዴራል ፍርድ ቤት ወይም በክልል ፍርድ ቤት ቢያንስ ለሰባት ዓመት በዳኝነት ማገልገል እንደሚገባ በረቂቅ ድንጋጌው ተካቷል።

 የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ ሆኖ ለመሾም ደግሞ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወይም በክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ቢያንስ አሥር ዓመት ያገለገለ መሆን ይጠበቅበታል። በቋሚነት ከሚሾሙ ዳኞች በተጨማሪ በሌላ ሥራ ላይ የተሰማሩ ልምድ ያላቸው የሕግ ባለሙያዎች ለሦስት ዓመት የጊዜ ገደብ በጊዜያዊ ዳኝነት የሚሾሙበትን አሠራርም ረቂቅ አዋጁ አካቶ ይዟል። ጊዜያዊ ዳኞችን የመሾም ዋነኛው ዓላማ በሕግ ሙያ ላቅ ያሉ ሰዎችን በጊዜያዊነት ወደ ዳኝነት ሥራ እንዲገቡ በማድረግ፣ የፍርድ ቤቶችን መዝገብ ክምችት መቀነሰና በቋሚነት የሚሾሙ ዳኞች በሕግ ሙያ ከላቁትና ረዥም ልምድ ካካበቱ እንዲማሩ ማድረግ ናቸው።

ዳኞችን የመመልመልና የማስተዳደር ኃላፊነት የሚሰጠው የዳኝነት አስተዳደር ጉባዔ ሙሉ በሙሉ ነፃነቱ የተጠበቀ እንዲሆን ለማድረግ፣ የመንግሥት አካላት በጉባዔው የነበራቸው ውክልና እንዲቀንስ የሚያደርግ ድንጋጌ በረቂቅ አዋጁ ቀርቧል። አሁን ባለው አሠራር ከጉባዔው ዘጠኝ አባላት መካከል ሦስቱ ከፓርላማ የሚወከሉ የሕዝብ ተወካዮች ሲሆኑ፣ በረቂቅ አዋጁ የፓርላማ አባላት ውክልና ሙሉ በሙሉ እንዲወጣ ተደርጓል።

ዘጠኝ የነበረውን የጉባዔው አባላት ቁጥር ወደ 15 ከፍ ያደረገ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ብቻ ከሥራ አስፈጻሚው መንግሥት የሚወከል ነው። የተቀሩት በሙሉ ከፌዴራል ፍርድ ቤቶችና ከጠበቆች ማኅበር የሚወከሉ ከሰባት ዓመት በላይ በጥብቅና ያገለገሉ ሁለት አባላት፣ ዕውቅና ካላቸው ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሕግ ትምህርት ቤቶች ማኅበር ወይም የጋራ መድረክ ተመርጠው የሚወከሉ ከአሥር ዓመት በላይ ልምድ ያላቸው ሁለት መምህራንና አንድ ስመ ጥር ግለሰብ እንደሚሆኑ ረቂቁ ያመለክታል።

ፓርላማው ይህንን ረቂቅ በመጀመርያ ንባብ ከተመለከተ በኋላ ለዝርዝር ዕይታ ለፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የመራው ሲሆን፣ ቋሚ ኮሚቴውም ረቂቅ አዋጁን በመመልከት ሕዝባዊ ውይይት ለማድረግ የሚያስችሉትን ዝግጅቶች እያደረገ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...