Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበለውጥ ጅማሮ ወቅት የተገቡ ቃል ኪዳኖች መዘንጋት እንደሌለባቸው የሰብዓዊ መብቶች ዋና ኮሚሽነር...

በለውጥ ጅማሮ ወቅት የተገቡ ቃል ኪዳኖች መዘንጋት እንደሌለባቸው የሰብዓዊ መብቶች ዋና ኮሚሽነር አሳሰቡ

ቀን:

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ለውጥ ምዕራፍን በማብሰር ወደ ሥልጣን የመጣው መንግሥት በወቅቱ ለሕዝብ የገባቸውን የማይረሱ ቃል ኪዳኖች ሳይዘነጋ ሊተገብር እንደሚገባ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) አሳሰቡ።

በሐምሌ ወር 2011 ዓ.ም በኮሚሽነርነት የተሾሙት ዳንኤል (ዶ/ር)፣ የመጀመርያ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርታቸውን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሐሙስ ጥር 14 ቀን 2012 ዓ.ም. ባቀረቡበት ወቅት ነው ይህንን የተናገሩት፡፡ የተጀመረው የፖለቲካ ለውጥ ምዕራፍ በብሔር ማንነትና በሃይማኖት መካረር የተወሳሰበ ተግዳሮት እንደገጠመው ዋና ኮሚሽነሩ ለምክር ቤቱ አስረድተው፣ አሁን ለሚታዩት የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችና ውስብስብ ተያያዥ ተግዳሮቶች መንግሥትን ጨምሮ መላው ማኅበረሰብ ተጠያቂነትና ኃላፊነት አለባቸው ብለዋል።

ባቀረቡት ሪፖርት የለውጥ ምዕራፉን በኃላፊነት ለመምራት መንግሥት ኃላፊነቱን በተቀበለበት ወቅት፣ ለሕዝብ ለገባቸው የማይረሱ ቃል ኪዳኖች ሊታመንና ሊተገብራቸው እንደሚገባ አሳስበዋል። ከእነዚህ የማይረሱ ቃል ኪዳኖች መካከል አንዱ ‹‹ሳያጣሩ ማሰር የለም›› የተባለው ትክክለኛ የሰብዓዊነትና የሕጋዊነት መርህ እንደሆነ የተናገሩት ዋና ኮሚሽነሩ፣ የተገባው ቃል ኪዳን አልፎ አልፎ እየተሸራረፈ በመሆኑ የለውጥ አመራሩ ማስተካከያ እንዲያደርግ አሳስበዋል፡፡

ከአንዳንድ የወንጀል ዓይነቶችና ሕጎች በስተቀር ምርመራ ሳይደረግ ተጠርጣሪዎች መታሰር እንደሌለባቸው የገለጹት ዋና ኮሚሽነሩ፣ ከዚህ አኳያ አልፎ አልፎ ጉድለቶች መኖራቸውን እንደታዘቡ አመልከተዋል። ሐሳብን በነፃነት የማራመድና የመደራጀት መብቶችን የነፈጉ ተግባራት ዋና ከተማ በሆነችው አዲስ አበባን ጨምሮ፣ በተለያዩ አካባቢዎች ባላፉት ስድስት ወራት መፈጸማቸውንና ይህም በፍጥነት ሊታረም የሚገባ ድርጊት እንደሆነ ለምክር ቤቱ ገልጸዋል።

በአገሪቱ የተጀመረው የፖለቲካ ለውጥ ምዕራፍ ውስብስብ ተግዳሮቶች እየገጠሙት መሆኑን፣ በዚህም በርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን ሪፖርት አድርገዋል። ‹‹ዜጎች በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል፣ ተደፍረዋል፣ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፣ ታግተዋል፣ ከቀዬአቸው፣ ከሥራቸውና ከትምህርት ገበታቸው ጭምር ተፈናቅለዋል፤›› ያሉት ዋና ኮሚሽነሩ፣ ለዚህም ሥር የሰደደ የፖለቲካ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሥርዓት ችግርን በመሠረታዊ ምክንያትነት ጠቅሰዋል፡፡ የብሔር ማንነትን መሠረት ያደረጉ፣ እንዲሁም አልፎ አልፎ የሚታይ የሃይማኖት መካረርን በተጨማሪ ምክንያትነት አቅርበዋል፡፡  

በአገሪቱ የተጀመረው አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍ የተወሰኑ ቡድኖች ብቻቸውን የፈጠሩትና ብቻቸውን ባለቤት የሚሆኑበት ሳይሆን፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን የፈጠሩት እንደ መሆኑ መጠን ድሉንና ዕድሉንም ሁሉም ሊጠብቁት እንደሚገባም አሳስበዋል። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኃላፊነቱን መወጣት የማይችል፣ እጅግ በጣም ውስን የሆነ አቅም ያለው ተቋም ሆኖ እንዳገኙት የተናገሩት ዋና ኮሚሽነሩ፣ ይህንን ሁኔታ ለመቀየር ዓለም አቀፍ መመዘኛዎችን የሚያሟላና ተልዕኮውን መወጣት የሚችል ተቋም ለማድረግ የሪፎርም ሥራ በማከናወን ላይ መሆኑን ገልጸዋል። ተቋሙ ሙሉ በሙሉ በመንግሥት ተፅዕኖ ሥር የወደቀ እንደነበር የተናገሩት ዋና ኮሚሽነሩ፣ ተቋሙን ከፋይናንስም ሆነ ከፖለቲካ ተፅዕኖ ነፃና ገለልተኛ፣ እንዲሁም ብቃት ያለውና ለሕዝብ ተደራሽ ለማድረግ ከሕግ ማሻሻያ አንስቶ የአደረጃጀት ለወጥን ያካተተ የሪፎርም ሒደት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የምክር ቤቱ አባላት ዋና ኮሚሽነሩ ባቀረቡት ሪፖርት ላይ ትችቶችን ያቀረቡ ሲሆን፣ የቀረበው ሪፖርት የዓመቱን ዕቅድና አፈጻጸም በቁጥራዊ አኃዞች የማያሳይ በመሆኑ የአፈጻጸሙን ውጤታማነት ለመለካት አያስችልም የሚለው በዋናነት የተነሳ ነበር። ዋና ኮሚሽነሩ በሰጡት ምላሽ ሰብዓዊ መብቶችን የማረጋገጥ ተግባር እንደ ሌሎች ተቋማት የሥራ አፈጻጸም በቁጥር እንደማይለካ፣ ይህ ቢሆንም ለምክር ቤቱ ባቀረቡት ዝርዝር ሪፖርት ላይ በቁጥር የተደገፉ መረጃዎች መኖራቸውን አስረድተዋል።

ከዚህ በኃላ የአገሪቱን የሰብዓዊ መብት ሁኔታ የሚያሳይ ሪፖርት ኮሚሽኑ ለምክር ቤቱ እንዲያቀርብ ቢደረግ፣ ለምክር ቤቱ መንግሥትን የመቆጣጠር ተግባር እንደሚበጅም ሐሳባቸውን አቅርበዋል። ምክር ቤቱ በዚሁ ቀን ውሎው በሰው የመነገድና በሕገወጥ መንገድ ሰዎችን የማዘዋወር ወንጀልን ለመከላከል የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ አፅድቋል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...