Monday, May 29, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ኢትዮጵያ ከጠባብ ቡድናዊ ፍላጎት በላይ ናት!

ኢትዮጵያን ለምንም ነገር መደራደሪያ ማድረግ አይቻልም፡፡ ህልውናዋን የሚጎዳ ማንኛውም ዓይነት ድርጊት መፈጸምም አይቻልም፡፡ ጠባብ ቡድናዊ ፍላጎትን በማስቀደም ሰላሟን መፈታተን አይፈቀድም፡፡ ከውስጥም ሆነ ከውጭ ሆኖ በማሴር ቀውስ መፍጠርም አይሞከርም፡፡ ኢትዮጵዊያን ፍላጎታቸውን ከኢትዮጵያ ህልውና በታች አድርገው፣ በፈለጉት መንገድ በመደራጀት መንቀሳቀስ ይችላሉ፡፡ በኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች መሳተፍ የሚችሉት፣ ብሔራዊ ደኅንነቷንና ጥቅሞቿን ሳይጎዱ ብቻ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በአገሩ ህልውና ላይ የመጣን ማንኛውንም ጥቃትም ሆነ ሴራ ስለማይታገስ፣ ከአጥፊና ከአውዳሚ ድርጊቶች መታቀብ ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ ህልውና ሲነካ እጁን አጣጥፎ የሚቀመጥ የለምና፡፡ ኢትዮጵያን ከሥልጣን፣ ከጥቅማ ጥቅም፣ ውሉ ከማይታወቅ የታሪክ ትርክት፣ ከክልላዊ ወሰን ጥበትና ስፋት፣ ከማንነትና ከሃይማኖታዊ አጥር፣ ከዓርማዎችና ከምልክቶች ልክፍትና መያዣና መጨበጫ ከሌላቸው ርዕዮተ ዓለማዊና ዕሳቤዎች በላይ ማክበር ይኖርብናል፡፡ አንድነቷ እንደ ብረት የጠነከረ፣ ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም ያላት፣ በኢኮኖሚ የዳበረችና ለሁሉም ሕዝቧ የምትመች ዴሞክራሲያዊት አገር መገንባት የሚቻለው በዚህ ቁመና ላይ መገኘት ሲቻል ብቻ ነው፡፡ አሁን በየቦታው እንደሚታየውና እንደሚሰማው በጠባብ ቡድናዊ ፍላጎት ላይ ብቻ ማተኮር እርባና ቢስ ከመሆኑም በላይ፣ የከሰረ ፖለቲካ ምርኮኛ መሆን ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ የፈራረሰችውን ዩጎዝላቪያ የሚያስታውሱ ምልክቶች ከበቂ በላይ እየታዩ ነውና፡፡

የአገሪቱ ልሂቃን ከዘመናት ድብርት ውስጥ መውጣት አለባቸው፡፡ ፍሬ የማያፈራ ሥርዓተ ትምህርት ይዞ የትም መድረስ እንደማይቻል መገንዘብ ይገባቸዋል፡፡ ትውልድ ገዳይ የሆነው ሥርዓተ ትምህርት እንዲስተካከል ዕገዛ ሊያደርጉ ይገባል፡፡ ለዓመታት የተረጨውን የከፋፋይነት መርዝ ማጥፋት የሚቻለው፣ ትውልዱ ጥራት ባለው ትምህርት ሲታነፅ ብቻ ነው፡፡ የሰጡትን ተቀብሎ በስሜት የሚነዳ ሳይሆን መጠየቅ፣ መመርመርና መሞገት የሚችል ትውልድ የሚፈጠረው፣ ጥራት ባለውና ዘመኑን በዋጀ ትምህርት ብቻ ነው፡፡ በተጨማሪም በትውልዱ ውስጥ የተዘራው ከመጠን ያለፈ ራስ ወዳድነት፣ ስግብግብነት፣ በአቋራጭ የመበልፀግ አባዜ፣ ወገንን መጥላት፣ የአገር ፍቅር ስሜት ማጣት፣ ሐሜትና አሉባልታ፣ ጭካኔና ክፋት መወገድ የሚችሉት ጥራት ባለው ትምህርት መሆኑን መዘንጋት አይገባም፡፡ በሌላ በኩል የአገሪቱ የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ የተሰገሰጉ ሥልጣንና ገንዘብ አምላኪዎች፣ ትውልዱን እየበረዙት መሆኑን ማስተዋል የግድ ይላል፡፡ ገንዘብ እስካገኙ ድረስ አገርን ለጠላት አሳልፈው ከመስጠት የማይመለሱ ሴረኞችን የማጋለጥ ኃላፊነትን ለአፍታም ቢሆን ቸል ማለት አይገባም፡፡ አገርን በማተራመስና ቀውስ ውስጥ በመክተት የታሪካዊ ጠላቶችን ፍላጎት ለማሳካት የሚያደቡ ተላላኪዎች ጉዳይ ከፍተኛ ትኩረት ይሻል፡፡ የእነሱ ጥቅም እስካልተጓደለ ድረስ አገር ፍርክስክሷ ቢወጣ ደንታቸው አይደለም፡፡ እነዚህንና የሚያሰማሯቸውን ጭምር ሕጋዊ ሆኖ መታገል ይገባል፡፡

ኢትዮጵያ በሰላምና በዕድገት ወደፊት መራመድ የምትችለው፣ ከራሳቸው በላይ ለአገራቸው የሚቆረቆሩ ኢትዮጵያዊያን ሲበዙ ነው፡፡ አሁን እንደሚታየው ግን የብዙኃኑ ድምፅ ታፎኖ አየሩን የተቆጣጠሩት፣ ከአገር በፊት የራሳቸውን ጥቅም ብቻ የሚያስቀድሙ መሰሪዎች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ የሚባለውን ስም ለመስማት ከሚቀፋቸው ጀምሮ፣ በኢትዮጵያዊነት ስም እስከሚቆምሩት ድረስ ፍላጎታቸው ዥንጉርጉር ነው፡፡ አገርንና ሕዝብን ማዕከል ማድረግ አይፈልጉም፡፡ በኢትዮጵያዊነት ጣሪያ ሥር ተገድበው ከመፎካከር ይልቅ፣ ጠባብ ቡድናዊ ፍላጎታቸውን አልፋና ኦሜጋ ማድረግ ይሻሉ፡፡ በሰላማዊ መንገድ መነጋገርና መደራደር ሲችሉ አንዱ ሌላውን ለማስገበር ይራኮታሉ፡፡ በትምህርት ገበታ ላይ ያሉ ወጣቶችን በመመልመል ነውጥ ይቀሰቅሳሉ፡፡ ቤተ እምነቶች ድረስ በመዝለቅ የፍላጎታቸው ማስፈጸሚያ ለማድረግ ተግተው ይሠራሉ፡፡ የአገር ሽማግሌዎችን ሳይቀር የጥፋት ተላላኪ ያደርጋሉ፡፡ የማኅበረሰቦችን የሥነ ምግባርና የሞራል እሴቶች በመናድ ሕገወጥነትን ያስፋፋሉ፡፡ የሕግ የበላይነትን በመዳፈር ንፁኃን ይገድላሉ፣ ይዘርፋሉ፣ ያፈናቅላሉ፡፡ ችግር በተፈጠረባቸው አካባቢዎች ሴቶችን አስገድደው ይደፍራሉ፣ ያስደፍራሉ፡፡ ታይቶም ተሰምቶም በማይታወቅ ሁኔታ ዜጎችን በሰብዓዊ ጋሻነት ያግታሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ ድርጊቶች ኢትዮጵያን ከማጥፋት የዘለለ ሚና የላቸውም፡፡ በሕዝብ ላይ የበለጠ ድህነትና ጉስቁልና ከማምጣትና ቀውስ ከመፍጠር ውጪ፣ አንዳችም ዓይነት ጥቅም እንደሌላቸው ግልጽ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ዋና ኮሚሽነር ሰሞኑን በፓርላማ ተገኝተው የስድስት ወራት የአፈጻጸም ሪፖርት ሲያቀርቡ፣ ከዚህ ቀደም የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሲፈጸም የነበረው በመንግሥት እንደነበር፣ አሁን ግን ሁኔታዎች ተለውጠው የፖለቲካ ፍላጎት ባላቸው ኃይሎች እየተፈጸመ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በተወሰኑ ወገኖች የሚመሩ የፖለቲካ አስተሳሰቦች በተለያዩ ሥፍራዎች ለሚስተዋሉ ግጭቶች ዋነኛ ምክንያት መሆናቸውንና ከተለያዩ ፖለቲካዊ ፍላጎቶች፣ ከማንነትና ከወሰን ጋር የሚያያዙ ጥያቄዎች፣ እንዲሁም ሃይማኖታዊ ችግሮች አገሪቱን ቀውስ ውስጥ መክተታቸውን አክለዋል፡፡ ይህ የሚያስገነዝበን ምን ያህል ለሰላምና ለተረጋጋ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ትኩረት እንዳልተደረገና ለቡድናዊ ፍላጎት ብቻ ሲባል የሚፈጸሙ ወንጀሎች መበራከታቸውን መረዳት እያዳግትም፡፡ በሰላማዊ የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ በመሆን በሕዝብ ድምፅ በሚወሰንበት ምርጫ የፖለቲካ ሥልጣን መያዝን የመሰለ የሠለጠነ ተግባር እያለ፣ በሕዝብ ስም እየማሉ መቆመር ከባድ ኪሳራ አድርሷል፡፡ በሌላ በኩል መንግሥት በሕግ የተሰጠውን ሕግ የማስከበር ኃላፊነት ባለመወጣቱ፣ ለሰብዓዊ መብት ጥሰት ቀጥታ ባልሆነ መንገድ ተባባሪ መሆኑን መረዳት የግድ ነው፡፡ ሕገወጦች ሕግ የለም የሚል መልዕክት በግልጽ እያስተላለፉ የፈለጉትን ድርጊት ሲፈጽሙ በስፋት ታይቷል፡፡ በተወሰኑ አካባቢዎች የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ከሕገወጦች ጋር ሲተባበሩም ተስተውሏል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ሥርዓተ አልበኝነት በሕግ የበላይነት ካልመከነ፣ የእርስ በርስ ፍጅት ያስከትላል፡፡ ይህ ደግሞ አገርን ያጠፋል እንጂ አያኗኑርም፡፡

በአሁኑ ጊዜ ሌላው አሳሳቢ ችግር ነገሮችን በኢትዮጵያዊነት ማዕቀፍ ውስጥ ከማየት ይልቅ፣ ለተጠለሉበት የፖለቲካ ጎራ ወገንተኝነት በማሳየት ለአንድነት የሚደረገውን ትግል መገዳደር ነው፡፡ ሥልጣን በዚህም በዚያም ተብሎ ይገኛል ተብሎ በሚገባ ቃል፣ በሚሰጥ ጥቅምና በቡድንተኝነት ኢትዮጵያን ከጊዜ ወደ ጊዜ ቀውስ ውስጥ መክተት ተለምዷል፡፡ አንድን ሐሳብ በምክንያታዊነት መሞገት ሲገባ፣ በአሽሙርና በአሉባልታ ጠቃሚ ሐሳቦችን ማብጠልጠል የዘመኑ ፈሊጥ ሆኗል፡፡ በተለይ በፖለቲካ ፓርቲዎች ዙሪያ የተኮለኮሉ ምንደኛ ደጋፊዎችና አቀንቃኞች ከሐሳብ ጥራት ይልቅ፣ ስም አጥፊነት ላይ ተሰማርተው ኢትዮጵያዊያንን ይከፋፍላሉ፡፡ በዚህ በሠለጠነ ዘመን ልዩነቶቻቸውን ይዘው በአገር ጉዳይ ጎን ለጎን በመቀመጥ መወሰን የሚገባቸው ፖለቲከኞች፣ ልሂቃን፣ ወጣቶች፣ አዛውንቶች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ ወዘተ የበለጠ እንዲራራቁ ያደርጋሉ፡፡ በሐሳብ መለያየት ጠላትነት አይደለም ተብሎ በሚቀነቀንበት ዘመናዊ ዓለም ውስጥ እየኖሩ፣ ከጠባብ ቡድናዊ ፍላጎት መውጣት ያቃታቸው ድምፃቸው ማስገምገሙ ያሳዝናል፡፡ ብዙኃኑ ድምፃቸው ሰልሎ ማየትም ያሳፍራል፡፡ እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ኢትዮጵያ ውስጥ ማንም የማንም ጠላት ሳይሆን፣ ይልቁንም ከእነ ልዩነቱ በአገር ጉዳይ አንድ ላይ መቆም የሚገባው ነበር፡፡ ጠላትነትን በመስበክ ኢትዮጵያዊያንን እርስ በርሳቸው ማላተም ሰይጣናዊ ድርጊት ነው፡፡ ኢትዮጵያ በልጆቿ ትብብር ታላቅ አገር መሆን እንደምትችል እየታወቀ፣ ጠላትነትን ማጉላትና መከፋፈል ደካማነት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከጠባብ ቡድናዊ ፍላጎት በላይ መሆኗን መገንዘብ ይገባል!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ከወለድ ነፃ ባንክ የተሰበሰበውን በመቶ ቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ለምን ሥራ ላይ ማዋል አልተቻለም?

  ባንኮች ከወለድ ነፃ የሚሰበስቡት ተቀማጭ ገንዘብ መጠን ዕድገት እያሳየ...

መንግሥት ባለፈው ዓመት ለማዳበሪያ የደጎመው 15 ቢሊዮን ብር ለአርሶ አደሮች አለመድረሱ ጥያቄ አስነሳ

መንግሥት ለ2014/15 በጀት ዓመት እርሻ በአፈር ማዳበሪያ ላይ ያለውን...

የሁለተኛው አብዮታዊ ሠራዊት ዋና አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ሁሴን አህመድ (1930-2015)

ኢትዮጵያ የሁለተኛውን የፋሺስት ጣሊያን ወረራ (1928-1933) በድል ከተወጣች በኋላ...

የመስጅድ ፈረሳን በመቃወም እንዲቆም ለመጠየቅ በተደረገ ሰላማዊ ሠልፍ ላይ የሰው ሕይወት አለፈ

በ56 የፖሊስ አካላትና አጋዥ ኃይሎች ላይ ጉዳት ደርሷል ‹‹በሕዝበ ሙስሊም...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የመስቀል አደባባይ የመግቢያ ክፍያ ለምን?

ወጣቶች፣ ሕፃናትና አረጋውያን ሳይቀሩ መንፈሳቸውን የሚያድሱበት እንዲሁም ሐሳባቸውን በነፃነት...

በሕገ መንግሥቱ የተዋቀረው ‹‹የብሔር ፖለቲካ›› እና ‹‹ሥርዓቱ›› ያስከተለው መዘዝና መፍትሔው

(ክፍል አራት) በዓቢዩ ብርሌ (ጌራ) ባለፈው ጽሑፌ (በክፍል ሦስት) አሁን ያለው...

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብና የመንግሥት መሪ ምሥል

በበቀለ ሹሜ በ2015 ዓ.ም. መጋቢት ወር ውስጥ ይመስለኛል በ‹ሸገር ካፌ›...

ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ ያደረገው አዋጅ የፍትሐዊነት ጥያቄ አስነሳ

በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ስምንት ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ በማድረግ ተቋማዊና...

ለመጪው ዓመት የሚያስፈልገው 4.3 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ነዳጅ 4.4 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ይጠይቃል

ለመጪው 2016 ዓ.ም. ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ለታቀደው 4.3...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የመኸር እርሻ ተዛብቶ ቀውስ እንዳይከሰት ጥንቃቄ ይደረግ!

ክረምቱ እየተቃረበ ነው፡፡ የክረምት መግቢያ ደግሞ ዋናው የመኸር እርሻ የሚጀመርበት ጊዜ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከእርሻው ክፍለ ኢኮኖሚ 70 በመቶ ያህሉን የሰብል ምርት የምታገኘው በመኸር እርሻ...

የሕዝቡን ኑሮ ማቅለል እንጂ ማክበድ ተገቢ አይደለም!

መንግሥት አገር ሲያስተዳድር ለበርካታ ወጪዎቹ ገንዘብ ስለሚያስፈልጉት አስተማማኝ የገቢ ምንጮች ሊኖሩት ይገባል፡፡ በጀት ሲይዝም ሆነ ወጪዎቹን ሲያቅድ ጠንቃቃ መሆን ይኖርበታል፡፡ ወቅቱ ለመጪው ዓመት በጀት...

ጠንካራና አስተማማኝ ተቋማት በሌሉበት ውጤት መጠበቅ አይቻልም!

በኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ብሔራዊ ጉዳዮች ላይ የሚስተዋሉ መዛነፎችና አለመግባባቶች ዋነኛ ምክንያታቸው፣ ከበፊት ጀምሮ እስካሁን ድረስ ጠንካራና አስተማማኝ ተቋማትን ለመገንባት አለመቻል ነው፡፡ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ፣ በፀጥታ፣...