Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናከምዕራብ ወለጋና ከሌሎች ታጣቂዎች ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ ተጠርጣሪዎች በሽብርተኝነት ተከሰሱ

ከምዕራብ ወለጋና ከሌሎች ታጣቂዎች ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ ተጠርጣሪዎች በሽብርተኝነት ተከሰሱ

ቀን:

የመንግሥት ኃላፊዎችንና የፀጥታ ሠራተኞችን ለማጥቃት ሲዘጋጁ ነበር ተብሏል

ፖለቲካዊና ርዕዮተ ዓለማቸውን በኃይል በመንግሥት ላይ ለመጫን በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ወለጋ ዞን እየተንቀሳቀሰ ከሚገኘው የሸኔ ታጣቂ መሪ ኩምሳ ድሪባ ወይም ጃልመሮ፣ በምዕራብ ሸዋ ዞን ከሚንቀሳቀሰው ያደሳ ነጋሳና ሌሎች ታጣቂዎችና አባ ቶርቤ (ገዳይ ቡድን) ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አላቸው ተብለው በተጠረጠሩ ስድስት ግለሰቦች ላይ፣ የሽብር ድርጊት መፈጸም ወንጀል ክስ ቀረበባቸው፡፡

በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የሽብርተኝነትና በሕገ መንግሥት ሥርዓት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ማስቻያ አንደኛ ችሎት የቀረቡት ተከሳሾች ያዘው ከበበው፣ ፍራኦል እንዳሉት፣ ገላና ወጋሪ፣ ፊጣ ጫላ፣ ኤፍሬም ገለታና ታደሉ ዮናስ ናቸው፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ጥር 14 ቀን 2012 ዓ.ም. በተጠርጣሪዎቹ ላይ ያቀረበው ክስ እንደሚያስረዳው፣ ተከሳሾቹ የሸኔ አመራርና አስተባባሪ ከሆነው ባጫ ቶላ፣ በምዕራብ ወለጋ ዞን የሸኔ አመራር ኩምሳ ድሪባ (ጃልመሮ)፣ በኬንያ ሶሎሎ ማሠልጠኛ ሠልጥኖ የሸኔ አመራር ከሆነው ባትሬ ስሜ ወይም አማን ጋር በመገናኘትና ተልዕኮ በመውሰድ ዕርምጃ ለመውሰድ ሲንቀሳቀሱ እንደነበር ዓቃቤ ሕግ በክሱ አስረድቷል፡፡

ከአመራሮቹ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት በማድረግ የሽብር ድርጊት ለመፈጸም እንዲያመቻቸው፣ ጫካ ለነበሩ ለሸኔ ታጣቂዎችና ለአባ ቶርቤ ዕርምጃ ወሳጅ ቡድን ጥይትና የእጅ ቦምብ መግዣ የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ሲንቀሳቀሱ እንደነበርም አክሏል፡፡ ተከሳሾቹ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በኦሮሚያ የተለያዩ ከተሞች ውስጥ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ በመከታተልና መረጃ በማቀበል፣ ዕርምጃ እንዲወሰድባቸው ለሸኔ ታጣቂዎች ሁኔታዎችን ሲያመቻቹ እንደነበርም ዓቃቤ ሕግ በክሱ ጠቁሟል፡፡

በተለያዩ የዞንና የወረዳ አመራሮች ላይ ታጣቂዎች ወይም የአባ ቶርቤ ዕርምጃ ወሳጅ ቡድን ዕርምጃ እንዲወሰድባቸው መመርያና ተልዕኮ ሲሰጡ እንደነበርም አክሏል፡፡ የጦር መሣሪያና ወታደራዊ ቁሶችን ለቡድኑ በመላክ ድጋፍ ሲያደርጉ እንደነበር፣ ወታደራዊ አልባሳትንና ሽጉጦችን ገዝተው ሲያቀርቡ መቆየታቸውንም ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡

በኬንያ ሶሎሎ ማሠልጠኛ ገብተው ወታደራዊና ፖለቲካዊ ሥልጠና ከወሰዱ በኋላ፣ ከሸኔ አመራሮች ተልዕኮ በመውሰድና ወደ ኢትዮጵያ በመግባት መቀመጫውን አዲስ አበባ ከተማ አየር ጤና ‹‹ኬኒቴር›› በተባለ ቦታ አምስት አባላት ያሉት የሸኔ ዕርምጃ ወሳጅ (አባ ቶርቤ ቡድን) በማደራጀት ሲንቀሳቀሱ እንደነበር በክሱ ተገልጿል፡፡

በምሥራቅ ወለጋ ዞን ከሚሴ አካባቢ ከሚንቀሳቀሰው የሸኔ ታጣቂ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት በማድረግ፣ የመከላከያ ሠራዊት የሚያደርገውን እንቅስቃሴ በመከታተል ቡድኑ ዕርምጃ እንዲወስድበት መረጃ ሲያቀብሉ እንደነበርም ተገልጿል፡፡ ተከሳሾቹ በአምቦና በሆለታ ከተሞች በግለሰቦችና በተለያዩ የመንግሥት ኃላፊዎች ላይ ዕርምጃ ለሚወስዱት የሸኔ ታጣቂዎች ወይም የአባ ቶርቤ ቡድን ሁኔታዎችን ሲያመቻቹ እንደነበር ተገልጿል፡፡ ስናይፐር ጠመንጃ ሲያቀርቡ እንደነበርና በአጠቃላይ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 (1ሀ)፣ 35፣ 38 እና የፀረ ሽብር አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 4 በመተላለፍ፣ የሽብር ወንጀል ለመፈጸም ሲዘጋጁ እንደተደረሰባቸው ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹ ከጠበቆቻቸው ጋር ተመካክረው እንዲቀርቡና ክርክራቸውን በማረሚያ ቤት ሆነው እንዲከታተሉ ትዕዛዝ ሰጥቶ፣ ክስ ለመስማት ለጥር 20 ቀን 2012 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹በየቦታው ምርት እየገዙ የሚያከማቹ ከበርቴ ገበሬዎች ተፈጥረዋል››

አቶ ኡስማን ስሩር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር...

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...