ምክትል ከንቲባው ያቀረቡት የካቢኔ ሹምሽር በተቃውሞ ፀደቀ
ባለፉት ሁለት ዓመታት ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተመረቁ 20 ሺሕ የአዲስ አበባ ወጣቶችን፣ ከመጪው ሳምንት ጀምሮ በከተማ አስተዳደሩ የመንግሥት መዋቅሮች ውስጥ በቅጥር መመደብ እንደሚጀምር የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ።
ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ከፍተኛ ትምህርታቸውን በ2010 ዓ.ም. እና በ2011 ዓ.ም. ላጠናቀቁ ከ20 ሺሕ በላይ የከተማዋ ወጣቶች የሥራ መስኮችን ማመቻቸቱን፣ የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ለሪፖርተር ባደረሰው መረጃ አስታውቋል።
ከቀጣዩ ሳምንት ጀምሮም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ተማሪዎቹን በውጤት ደረጃቸው በመለየት በተለያዩ የሥራ መስኮች እንዲቀላቀሉ እንደሚያደርግ ያስታወቀው አስተዳደሩ፣ ለወጣቶቹ የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባሻገር ሕዝብን እያገለገሉ ራሳቸውን እንዲያበቁ፣ እንዲሁም የጠንካራ የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ግንባታ አካል እንዲሆኑ ማድረግ የዚህ ዕቅድ ዓላማ መሆኑን ገልጿል። በዚህ ሒደትም ከወረዳ ጀምሮ ባሉ ኃላፊነቶች እየተተኩ የአስተዳደሩን የአመራር መዋቅር እንዲቀላቀሉ እንደሚደረግ አስታውቋል።
የከተማ አስተዳደሩን እየመሩ የሚገኙት ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር)፣ ከዋና ቢሮው አንስቶ እስከ ወረዳ ድረስ የሚገኙ የከተማዋ የመሬት አስተዳደር አመራሮችን ከሥራ ማንሳታቸውን፣ እንዲሁም ሰፊ የሆነ የካቢኔ ሹምሽር እንደሚያደርጉ ባለፈው ዕትም መዘገባችን ይታወሳል።
በዚህ መሠረት ምክትል ከንቲባው ከሞላ ጎደል አዲስ ካቢኔ ሊባል የሚችል የ19 የካቢኔ አባላትን ሹመት፣ ለአስተዳደሩ ምክር ቤት ዓርብ ጥር 15 ቀን 2012 ዓ.ም. አቅርበዋል።
ባቀረቡት አዳዲስ የካቢኔ አባላት ዝርዝር ውስጥ ቀደም ሲል የነበረው ሁለት የምክትል ከንቲባነት (ከእሳቸው ውጪ) ኃላፊነት ወደ አንድ ዝቅ እንዲል ያደረጉ ሲሆን፣ በዚህም መሠረት እስከ ሳምንቱ መጨረሻ ድረስ ምክትል ከንቲባና የትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ የነበሩት ሰለሞን ኪዳኔ (ዶ/ር) ከኃላፊነት ተነስተዋል።
በምክትል ከንቲባነት የማኅበራዊ ዘርፍ ኃላፊ የነበሩት አቶ እንዳወቅ አብጤ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግሥት አገልግሎት ሰጭ ተቋማት አስተባባሪ ሆነው እንዲሾሙላቸው አቅርበዋል። የመሬት አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ የነበሩት ሰናይት ዳምጠው (ኢንጂነር) የቤቶች ልማት ቢሮ ኃላፊ ሆነው እንዲሾሙ አቅርበዋቸዋል።
የአስተዳደሩ ካቢኔን እንደ አዲስ እንዲቀላቀሉ ለሹመት የቀረቡት ከተደረጉት መካለከል ወ/ሮ ነጂባ አክመል የፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ፣ አቶ አብዱልቃድር መሐመድ የአስተዳደሩ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ፣ አቶ ነብዩ ባዬን በመተካት የባህልና ቱሪዝም ኃላፊ ሆነው የቀረቡት ወ/ሮ ኤፍራህ ዓሊ፣ የኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ ሆነው የቀረቡት ደመላሽ ከበደ (ኢንጂነር)፣ የፐብሊክ ሰርቪስ ቢሮ ኃላፊ እንዲሆኑ የቀረቡት አቶ ኃይሉ ሉሌ፣ የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዘለዓለም ሙለታና በትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊነት አቶ ስጦታው ታከለ ይገኙበታል።
በተጨማሪም አቶ ነጋሽ ባጫ የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ኃላፊነት፣ አቶ ይመር ከበደ የሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ቢሮ ኃላፊነት፣ አቶ መኮንን ተፈራ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊነት፣ አቶ አዱኛ ደበላ የሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊነት፣ አቶ አብርሃም ታደሰ የወጣቶች በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ቢሮ ኃላፊነት፣ አቶ ዋቁማ አበበ የፕላን ኮሚሽን ኮሚሽነርነት፣ አቶ ታምራት ዲላ የኢንቨስትመንት ኮሚሽነርነት፣ አቶ ታዜር ገብረ እግዚአብሔር የኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊነት ተመድበዋል፡፡ አቶ ሺሰማ ገብረ ሥላሴ የገቢዎች ቢሮ ኃላፊነት ይዘው እንዲቀጥሉ በምክትል ከንቲባው ለሹመት ቀርበዋል።
በነበሩበት የንግድ ቢሮ ኃላፊነት እንዲቀጥሉ የተደረጉት አቶ አብዱልፈታህ የሱፍ ናቸው፡፡
የአስተዳደሩ ምክር ቤት አንዳንድ አባላት የነበሩት አመራሮች እንዲነሱ የተፈለገበት ምክንያት እንዳላሳመናቸው የገለጹ ሲሆን፣ ምክትል ከንቲባ ታከለ አዲስ ሹመት ለማቅረብ የተገደዱበት ምክንያት የነበሩት አመራሮች የሥራ አፈጻጸም ደካማ በመሆኑ ብቻ እንደሆነና በምንም ዓይነት ከብሔር ማንነት ጋር እንደማይገናኝ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በዚህም መሠረት ምክር ቤቱ በሁለት ተቃውሞና በሰባት ድምፀ ተዓቅቦ የቀረበውን ሹመት በአብላጫ ድምፅ አፅድቆታል።