Monday, April 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰት ወደ 2.5 ቢሊዮን ዶላር አሽቆለቆለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ላለፉት ሦስት ዓመታት በተከታታይ እየቀነሰ የመጣው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መጠን ከ3.2 ቢሊዮን ዶላር ወደ 2.5 ቢሊዮን ዶላር መውረዱን፣ የተመድ ሪፖርት ይፋ አደረገ፡፡ እ.ኤ.አ. በ2016 4.2 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በማስመዝገብ፣ ኢትዮጵያ ከዓለም ትልልቅ መዳረሻዎች አንዷ  ነበረች፡፡

የተመድ የንግድና የልማት ጉባዔ ባለፈው ሳምንት ይፋ ያደረገው ‹‹ኢንቨስትመንት ትሬንድስ ሞኒተር›› የተሰኘ አጭር ሪፖርት፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መጠን እ.ኤ.አ. በ2019 ለውጥ ሳያሳይ ባለበት ቢቆይም፣ በበርካታ አገሮች ውስጥ ግን አሽቆልቁሏል ብሏል፡፡ በኢትዮጵያ የታየው ቅናሽ ግን ከአራት ዓመታት ወዲህ ከፍተኛው ሆኗል፡፡

እ.ኤ.አ. ከ2016 በፊት ሲመዘገብ የቆየው የኢንቨስትመንት ፍሰት ከ2.2 ቢሊዮን ዶላር ያነሰ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ እያደገ በመምጣት እስካለፈው ዓመት ድረስ በቅናሽ ውስጥም ሆኖ በአፍሪካ ከፍተኛ የኢንቨስትመንት መጠን ዝርዝር ውስጥ የኢትዮጵያን ስም ያቆየው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰት፣ እ.ኤ.አ. በ2019 ያስመዘገበው መጠን ወደ 2.5 ቢሊዮን ዶላር ዝቅ ማለቱ ከፍተኛ ቅናሽ ከሚባሉት ውስጥ እንዲካተት አድርጎታል፡፡

... 2016 4.2 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ከአፍሪካ ብቻም ሳይሆን፣ ከዓለም ታዳጊ አገሮች ተርታ ቀዳሚ የነበረችው ኢትዮጵያ፣ ... 2017 ወደ 3.5 ቢሊዮን ዶላር ዝቅ ያለ የውጭ ኢንቨስተመንት ፍሰት ማስተናገዷ አይዘነጋም፡፡ ምንም እንኳ ቅናሽ ቢታይበትም አሁንም ቢሆን በአፍሪካ ደረጃ ከፍተኛው የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰት ሊባል የሚችል ስለመሆኑ ተመድ አመላክቶ ነበር፡፡

በአፍሪካ በተለይም በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ከፍተኛውን የኢንቨስትመንት ፍሰት በማስተናገድ ቀዳሚነቱን ይዛ የቆየችው ኢትዮጵያ ከግንባታው ዘርፍ ባሻገር፣ በአውቶሞቢል መገጣጠምና በአነስተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች መስክ የምታደርገው እንቅስቃሴ የቱርክና የቻይና ባለሀብቶችን በመሳብ ደረጃዋን አስጠብቃ መጓዝ እንድትችል ያበቋታል ተብሎ ይታሰብ ነበር፡፡ የውጭ ኢንቨስትመንት ክምችቷ (በአንድ ዓመት ውስጥ ወይም በየሩብ ዓመቱ የሚገለጽ የወጪና የገቢ ኢንቨስመንት መጠንን ያመላክታል) 18 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደሚሆንም ተገምቶ ነበር፡፡

ይሁን እንጂ በተመድ የዓለም ኢንቨስትመንት ሪፖርት መሠረት፣ እ.ኤ.አ. በ2018 ወደ አፍሪካ ከመጣው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ውስጥ ያስመዘገበችው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስተመንት ድርሻ 3.2 ቢሊዮን ዶላር ነው፡፡ ይህም ከአንጎላ፣ ከግብፅ፣ ከናይጄሪያና ከጋና በመከተል አምስተኛ ደረጃ በመያዝ ከፍተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት መዳረሻ እንደነበረች ይታወሳል፡፡ ይህ ሁሉ እ.ኤ.አ. በ2019 ወደ 2.5 ቢሊዮን ዶላር ወርዶ ከፍተኛውን ቅናሽ ካስመዘገቡ አገሮች ተርታ አሠልፏታል፡፡

ከዓለም የኢንቨስትመንት መዳረሻ አገሮች ተርታ በተሠለፈችበት አፍታ ከደረጃዋ እየተንሸራተተች የወጣችው ኢትዮጵያ፣ ካስመዘገበችው የ2.5 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት ውስጥ ከ60 በመቶ ያላነሰው በቻይና ኩባንያዎች አማካይነት የሚካሄዱ ፕሮጀክቶች የያዙት ድርሻ እንደሆነ በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡

እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ በአንድ ወቅት በአፍሪካ ቀዳሚ ከሚባሉት ተርታ የነበረችው ሞሮኮም፣ ካቻምና ያስመዘገበችው የ3.6 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰት ወደ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ዝቅ ማለቱን የተመድ ሪፖርት ያሳያል፡፡ ይህም ሆኖ እንደ ግብፅ ያሉ አገሮች ዕድገት በማስመዝገብ ዓመቱን ማጠናቀቃቸው ሲታይ፣ በተለይ ግብፅ ከአፍሪካ ከፍተኛ የሆነውን የኢንቨስትመንት ፍሰት መጠን አስመዝግባለች፡፡ የአምስት በመቶ ዕድገት በማስመዝገብ ወደ 8.5 ቢሊዮን ዶላር ያሻቀበ ለውጥ በማሳየት በቁንጮነት ተቀምጣለች፡፡ ለግብፅ የኢንቨስትመንት መጨመር በአገሪቱ የተካሄዱ የለውጥ ዕርምጃዎች ያስገኙት ውጤት፣ እንዲሁም ባለሀብቶች ያደረባቸው አመኔታ፣ ግብፅ በውጭ ኢንቨስትመንት ረገድ የበላይነቱን ተቆናጣ እንድትዘልቅ አስችለዋታል፡፡

በአፍሪካ የተመዘገበው አጠቃላይ የውጭ ኢንቨስተመንት መጠን የሦስት በመቶ አጠቃላይ ዕድገት በማሳየት፣ ወደ 49 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ብሏል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ መጠነኛ ቅናሽ የታየበት የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰት፣ እ.ኤ.አ. በ2019 የ1.4 ትሪሊዮን ዶላር ገደማ እንቅስቃሴ በማስመዝገብ ከካቻምናው ብዙም ለውጥ ያልታየበት፣ ምናልባትም የአንድ በመቶ ቅናሽ የታየበት አፈጻጸም አሳይቷል፡፡ ለዚህ አስተዋጽኦ ካደረጉት ክስተቶች መካከል በቻይናና በአሜሪካ መካከል የሚታየው የንግድ ፍጥጫና ውጥረት አንዱ ሲሆን፣ የእንግሊዝ ከአውሮፓ ኅብረት የመውጣት እንቅስቃሴም በበርካታ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች ላይ መተማመንን ያሳጣ ክስተት ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች