Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክየሰውን ምስል ለሕዝብ ማሳየትና የሚያስከትለው የሕግ ተጠያቂነት

የሰውን ምስል ለሕዝብ ማሳየትና የሚያስከትለው የሕግ ተጠያቂነት

ቀን:

በውብሸት ሙላት

የሚዲያ ዓይነታውና ወደ ታዳሚዎች የሚደርስበት ሁኔታ እየበዛ መሄድ፣ በተለይም በማኅበራዊ የትስስር ሚዲያዎች አማካይነት በቢሊዮኖች የሚቆጠር የዓለማችን ሕዝብ መልዕክትና መረጃ በቀላሉ መለዋወጥ የሚቻልበት ሥርዓት መፈጠሩ የሰዎችን ፎቶግራፍና ምስል (ተንቀሳቃሽንም ጨምሮ) በስፋት መለጠፍና ማሳየት እንዲጨምር አድርጎታል፡፡ የሚለጠፉበት ምክንያቶች የተለያዩና ብዙ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ የአገራችን ሁኔታ ደግሞ ቅጣምባሩ የጠፋበት ነው፡፡

ጋዜጣው፣ መጽሔቱ፣ ቴሌቪዥኑ፣ ፌስቡክና ዩቲዩቡ፣ ፊልምና የሙዚቃ ሥራዎች ጭምር ሥርዓት በሌለው መልኩ የሰዎችን ምስል ለሕዝብ በማሳየት የግላዊ ነፃነትን (ግላዊነትን) የሚጻረሩ ድርጊቶች አፋጻጸም ሕጋዊ እስኪመስል ድረስ ተንሰራፍቷል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የሰዎችን የግል ገመና፣ ሕዝብ ሊያውቅ የሚችልበትን በጣት የሚቆጠሩ ምክንያቶች በሕግ ቢገለጽም፣ በተግባር ግን የግለሰቦችን ግላዊ ጉዳይ (ገመና) ለአደባባይ የሚያውለው ሰውም የሚውልበትም መንገድም እየበዛ ነው፡፡

በዚህ ጽሑፍ የምንዳስሰው የግለሰቦች ፎቶግራፍ ወይም ሥዕል የግላዊ ነጻነት፣ መብት አካል በመሆናቸው ጥበቃና ዕውናቸው ሕጋዊ ሥርዓታችን ምን እንደሚመስል ማሳየት ነው፡፡ በቅርቡ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የተሰጠ ፍርድንም እንደ ተጨማሪ አስረጂ ከአስተያየት ጋር ቀርቧል፡፡

 

የሰበሩ ውሳኔ

በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ተወስኖ በቅጽ ሃያ ሦስት ታትሞ የወጣ የሰውን ምስል ሳያስፈቅዱ በቴሌቪዥን ማስተላለፍን የሚመለከት አንድ ውሳኔ  አለ፡፡ የሰበር መዝገብ ቁጥሩ 156425 ሲሆን ውሳኔው የተላለፈው ኅዳር 14 ቀን 2011 ዓ.ም. ነው፡፡ ክርክሩ የነበረው በዳሸን ባንክና ድሪና አቫኪያን በሚባሉ የውጭ ዜጋ መካከል ነው፡፡ ድሪና አቫኪያን ከባልተቤታቸው ጋር በመሆን ከዳሸን ባንክ አገልግሎት እያገኙ ሳለ ባንኩ በቪዲዮ ቀርጾ ስለአገልግሎቱ ምቹነት፣ ጥራት፣ ብቃት ወዘተ ማስታወቂያ ሠርቶ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የዓለም እግር ኳስ በብራዚል በሚደረግበት ወቅት በ2006 ዓ.ም. ከሚያዚያ እስከ ሰኔ ድረስ አስተላልፏል፡፡

ባንኩ የከሳሽን ፈቃድ ሳይጠይቅ ቪዲዮ በመቅረጽ ማስታወቂያ ስለሠራበት ካሳ 400,000 ብር ተጠየቀ፡፡ ተከሳሽ በበኩሉ ከሳሽን ዒላማ አድርጌ ስላልቀረጽኩ፣ ምስላቸውም ከአንድ ሴኮንድ የበለጠ ስለማይታይ፣ በምስሉ ምክንያት የተገኘ ገቢ ስለሌለም፣ ከሳሽም ስላላስረዱ ካሳ ልከፍል አይገባም የሚል ምላሽ ሰጥቷል፡፡

አቤታቱታው የቀረበለት የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤትም ጉዳዩን ከመረመረ በኋላ የተከሳሽን መከራከሪያ ምክንያቶች በመቀበል አቤቱታውን ውድቅ አድርጎታል፡፡ ከሳሽ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ በማለት የሥር ፍርድ ቤትን ውሳኔ በማስሻር 100,000 ብር የካሳ ክፍያ አስወሰኑ፡፡ ጠቅላይ ፍርድ ቤትም ይህንኑ አጸናው፡፡ ሰበር ሰሚ ችሎቱም በተመሳሳይ የከፍተኛ ፍርድ ቤቱን ውሳኔ አጽንቶታል፡፡

የከሳሽም መከራከሪያ፣ የከፍተኛ ፍርድ ቤቱም ሆነ የሰበር ሰሚ ችሎቱ ምክንያቶች የቆሙት በዋናነት የፍትሐ ብሔር ሕጉ ከአንቀጽ 27 እስከ 29  ላይ ነው፡፡ እነዚህ ድንጋጌዎች የሰውን ፎቶግራፍ ወይም ምስል ለሕዝብ በአደባባይ ለማሳየት መለጠፍ፣ ማባዛት እንዲሁም መሸጥ ከጥቂት ልዩ ሁኔታዎች በስተቀር ያለፎቶግራፉ ወይም ሥዕሉ ባለቤት ፈቃድ እነዚህ ድርጊቶችን መፈጸም እንደማይቻል በመከለከል ከእነ መፍትሔው ተደንግጓል፡፡

ስለሰው ሥዕል የፍትሐ ብሔር ሕጉ

የፍትሐ ብሔር ሕጉ በአንቀጽ 27 ስለሰው ሥዕል ‹‹ባለፎቶግራፉ ወይም ባለሥዕሉ ካልፈቀደ በቀር የማንም ሰው ፎቶግራፍ ወይም ሥዕል በሕዝብ አደባባይ ሊለጠፍ ሆነ ሊባዛ ወይም ሊሸጥ አይችልም›› ይላል፡፡ በዚህ ድንጋጌ ሊተላለፉ የታሰቡ መልዕክቶች እንዲሁ ጥቂት የሚባሉ አይደሉም፡፡ የአንቀጹ ማጠር ያህል አይደለም መልዕክቱ ብዛት፡፡

ማጠንጠኛው ግላዊነት (ግላዊ ነፃነት) ነው፡፡ የሰው ሰውነቱ ላይ ጣልቃ እንደማይገባ ሁሉ የሰው አምሳያ አልያም በሥዕልም ሆነ በፎቶግራፍ ጥበብ የተዘጋጀ ምስላዊ ውክልናውም ቢሆን ጣልቃ አይገባበትም፡፡ እንደ አካላዊ ሰውነቱ፣ የሰውነቱ አምሳያም የተከበረና የማይደፈር ነው፡፡ የግላዊ ነፃነት አካል ነው፡፡

በዚህ አንቀጽ ጥበቃ የተሰጠው ለሰው ፎቶግራፍ ወይም ሥዕል ነው፡፡ ሥዕል ለሚለው የእንግሊዝኛው ፍትሐ ብሔር ሕግ “Image” ነው የሚለው፡፡ አማርኛው ሥዕል ቢልም አንድን ሰው በካርቱን፣ በቅርጻ ቅርጽ ወይም በሌላ አኳኋን የተዘጋጀ ሊሆን ይችላል፡፡ ተንቀሳቃሽ ምስልንም አያካትትም ማለት አይቻልም፡፡ አገላለጹ ሥዕል (Image) ቢልም የሠዓሊ የእጅ ቅቦችንም ተንቀሳቃሽ ሥዕሎችም (Motion Pictures) ያው ሰው አካል ሰው ሠራሽ አምሳያዎች (Images) ስለሆኑ ከአንቀጹ ዓላማ ጋር ስምሙ ነው፡፡

ዕውቁና ሊቁ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ በ‹‹መጽሐፈ ሰዋሰው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ›› በተሰኘው መጽሐፋቸው ‘ሥዕል’ ለሚለው ቃል የሚከተለውን ብያኔ ሰጥተውታል፡፡ ‹‹በቁሙ›› ይሉና ‹‹መልክ፣ የመልክ ጥላ፣ አምሳል፣ ንድፍ፣ ቢጋር፣ በውኃ፣ በመጽሔት፣ በጥልፍ፣ በስፌት ወይም በቀለም፣ በወረቀት ገዝፎ፣ ተጥፎ፣ ከጽቡር፣ ከእብን፣ ከዕፅ፣ ከማዕድን፣ ታንጦ፣ ተቀርጦ፣ ተሸልሞ፣ አጊጦ፣ የሚታይ፣ የሚዳሰስ ነገር›› በማለት በይነውታል፡፡ (‘መጽሔት’ ማለት መስታወት፣ ’ጽቡር’ ማለት የጭቃ፣ የኖራ ቡኮ ወይም ቁልል፣ ’እብን’ ደግሞ ድንጋይ ማለት ነው፡፡ ሦስቱም ቃላት ግዕዝ ናቸው፡፡)

ሥዕል፣ ‘ሠዐለ’ ከሚለው ግስ የወጣ ቢሆንም በአማርኛም በግዕዝም ተመሳሳይ ትርጓሜ ነው ያላቸው፡፡ ሊቁም ሥዕል አማርኛም ስለሆነ በቁሙ በማለት ጀምረው ማብራሪያቸውን የቀጠሉት፡፡ ከዚህ ብያኔ መረዳት የሚቻለው ሥዕል ቀለም በመቀባት ወይም በንድፍ በሚሠራ ምስል ብቻ የሚወሰን አለመሆኑን ነው፡፡

ፎቶግራፍ የሚለውም ቢሆን ከሚታተመው ባለፈም በቪዲዮ የሚታየውንም ያካትታል ቢባል አንድም ሕጉ ጥበቃ ሊያደርግ ካለመው አንፃር፣ አንድም ቪዲዮም ተንቀሳቃሽና ባለሦስት አቅጣጫ ፎቶግራፍ በመሆኑ፣ አንድም ለፎቶግራፍ ጥበቃ ከተደረገ ለቪዲዮማ በተሻለ ምክንያት ጥበቃ መደረጉን ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡

ፎቶግራፍ ወይም ምስል (ሥዕል) ከማለት ባለፈ በወረቀት ወይም በኤሌክትሮኒክስ ወይም በቴሌቪዥን ወይም በሌላ ቁስ አማካይነት በሚል ለይቶ አላስቀመጠም፡፡ ከዚህ የምንረዳው ፎቶግራፍም ይሁን ምስል (ሥዕል) በማናቸውም ነገር ላይ ቢታይ፣ ቢታተም ወዘተ ለውጥ አይኖረውም፡፡ በጋዜጣ፣ በቴሌቪዥን፣ በፌስቡክ፣ በዩቲዩብ ወዘተ ሊሆን ይችላል፡፡

ባለፎቶግራፉ ወይም ባለምስሉ (ሥዕሉ) ከፈቀደ በማናቸውም መልኩ በሕዝብ ሊታይ ይችላል፡፡ ፎቶውን ወይም ምስሉን ማባዛትም ሆነ መሸጥ ክልክል እንደሆነ መገለጹን ከላይ ተመለክተናል፡፡ በሕዝብ አደባባይ መለጠፍ ለሚለው የእንግሊዝኛው የፍትሐ ብሔር ሕግ “…exhibited in a public place” ነው የሚለው፡፡ በሕዝብ አደባባይ መለጠፍ ወይም ማሳየት ሲባል ባዛርና ኤግዚቢሽን ላይ እንደሚደረገው አልያም በሆነ መንገድ ዳር የሰውን ምስል መስቀል ወይም ማቆም ብቻ ላይ የሚቀር ነው ማለት ሊሆን አይችልም፡፡

ቁምነገሩ ያለው የግል የሆነን ጉዳይ ለሕዝብ በይፋ አለማቅረብ እስከሆነ ድረስ በጋዜጣም፣ በቴሌቪዥንም፣ በዩቲዩብም፣ በፌስቡክም፣ በመካነ ድሮችም (Websites) አማካይነት ለሕዝብ በአደባባይ ለማሳየት አለመለጠፍንም መጨመሩ የሚቀር አይደለም፡፡ ከላይ በአጭሩ የቀረበው የሰበር ውሳኔም ምስሉ የተላለፈው በቴሌቪዥን ቢሆንም (ተንቀሳቃሽ ምስል ስለሆነ) ያው ምስል እንጂ ሌላ ሊባል ስለማይችል፣ በተከራካሪ ወገኖች መካከልም ጭቅጭቅ አላስነሳም፡፡

ከላይ በተገለጹት አኳኋን፣ በማናቸውም ቅርጽ ፎቶግራፍን ወይም ሥዕልን ማባዛት እንዲሁ ለግላዊ ነፃነት ተጻራሪ ነው፡፡ በአንድ ጋዜጣ ታትሞ የወጣን ምስል በሌላ ጋዜጣ፣ ፌስቡክ ገጽ፣ መጽሔት ወዘተ ማራባትን ሕጉ ከልክሏል፡፡ ከማራባትና ማባዛት አልፎ በማናቸውም መልኩ ሰውን ምስል መሸጥ ይህ አንቀጽ ማዕቀብ ማድረጉን ቀድሞ አሳውቋል፡፡

የሰበሩ ውሳኔም የማስታወቂያ አካል ሆኖ በቴሌቪዥን የተላለፈውን የከሳሽን ምስል ሽያጭ ነው ወይስ ማባዛት ይባልም ወይም አይባልም ዞሮ ዞሮ በቴሌቪዥን አማካይነት ለሕዝብ እንዲታይ በመደረጉ የባንኩ አድራጎት የከሳሽን የግላዊ ነፃነት ስለጣሰና ሕግን የተላለፈ በመሆኑ ነው ባንኩ ላይ የወሰነው፡፡

የሰውን ፎቶግራፍም ሆነ ምስል በአደባባይ ለሕዝብ አቅርቦ ለማሳየት ወይም ለማባዛት ወይም ለመሸጥ የባለፎቶግራፉ ወይም ባለሥዕሉ ፈቃድ አስፈላጊ ነው ማለት ነው፡፡ በአደባባይ ለማሳየት እንጂ በግል በቤት፣ በኮምፒውተር ወይም በሞባይል ስልክ መያዝን አይከለክልም፡፡

ያለፈቃድ ሥዕልን ለሕዝብ ማቅረብ

በመርህ ደረጃ የማንንም ሰው ፎቶግራፍ ወይም ምስል በሕዝብ አደባባይ ማዋል፣ ማባዛት ወይም መሸጥ ክልክል ነው፡፡ ይሁን እንጂ ጥቂት በስተቀሮች (exceptions) አልጠፉትም፡፡ እነዚህ በስተቀሮች በፍትሐ ብሔር ሕጉ አንቀጽ 28፣ ከመርሁ ለጥቆ ተዘርዝረዋል፡፡

ባለፎቶግራፉን ወይም ባለሥዕሉን ማስፈቀድ ሳያስፈልግ ፎቶግራፍን ወይም ምስልን ማባዛት የሚቻልባቸውን ሁኔታዎችና ሰዎች ተገልጸዋል፡፡ እነዚህ ምክንያቶች የሚከተሉት ናቸው፡፡ እነዚህም  ታዋቂነት፣ ሕዝባዊ አገልግሎት መስጠት፣ በፖሊስና በፍርድ ቤት አስፈላጊነቱ የተረጋገጠ መሆን፣ ለኪነ ጥበብ (ለሳይንስ)፣ ለሥልጣኔ ዕድገት ወይም ለትምህርት ማስፈለጉ፣ እንዲሁም በክብረ በዓል ወይም በሕዝባዊ ስብሰባ ላይ መገኘት ምክንያት ፎቶው አብሮ መውጣት የሚሉት ናቸው፡፡

ይህ አንቀጽ በግልጽ ያስቀመጠው በተጠቀሱት ምክንያቶች እስከሆነ ድረስ ለማባዛት የባለፎቶግራፉ ወይም ሥዕሉ ፈቃድ የማያስፈልግ መሆኑን ነው፡፡ በአንቀጽ 27 የተዘረዘሩት ማባዛት፣ ለሕዝብ ማሳየትና መሸጥ የሚሉ ስለሆኑና በአንቀጽ 28 ግን ማባዛትን ብቻ መጠቀሱ፤ ሕጉ ፈቃድ የማያስፈልገው ለማባዛት ብቻ እንጂ ለመሸጥና ለሕዝብ በአደባባይ ለጥፎ ለማሳየት ከሆነ ፈቃድ ያስፈልጋል የሚል ይመስላል፡፡

ጃክ ቫንደርሊንደንም “Commentaries upon the Ethiopia Civil Code: The Law of Physical Persons” በሚለው መጽሐፋቸው ለመሸጥና ለሕዝብ ለማሳየት ከሆነ መቼም ይሁን መቼ የባለፎቶግራፉ ወይም ሥዕሉ ፈቃድ አስፈላጊ እንደሆነ ሙግት አቅርበዋል፡፡ ይሁን እንጂ ከቫንደርሊንደን መከራከሪያ በተጻራሪ በሚቆም ምክንያት በአንቀጽ 28 የተዘረዘሩት በስተቀሮች ለሕዝብ በአደባባይ ለማሳየትም ሆነ ለመሸጥም ፈቃድ አያስፈልግም፡፡

ወረድ ብሎ፣ በአንቀጽ 29 እንደተገለጸው በአንቀጽ 28 ከተገለጹት በስተቀሮች ውጭ የአንድን ሰው ምስልም ሆነ ፎቶግራፍ ለሕዝብ ማሳየት፣ መሸጥ ወይም ማባዘት በመከልከል ይህ መብቱ የተጣሰበት ሰው ድርጊቱ እንዲቆምለት፣ እንደነገሩ ሁኔታ የጉዳት ወይም የኅሊና ካሳ ጭምር መጠየቅ እንደሚችል ተደንግጓል፡፡

ከዚህ መረዳት የሚቻለው በልዩ ሁኔታ በስተቀር በተዘረዘሩት ምክንያቶች ፈቃድ የማያስፈልገው በማባዛት ለሕዝብ ማሳየትም መሸጥም ጭምር ነው፡፡ በመሆኑም ቫንደርሊንደን ካሉት በተቃራኒው በክብረ በዓል ወይም በሕዝባዊ ስብሰባ አልያም አንድ ታዋቂ ወይም ባለሥልጣን ሰው ዜናና ሌሎች ጭብጥ ያላቸውን ጽሑፎች አሰናድቶ አብሮ ፎቶውን በጋዜጣ ወይም በመጽሔት አውጥቶ አሳታሚው ቢሸጥ የሚያስጠይቀው አይሆንም፡፡

ከላይ የተገለጸው የሰበር ውሳኔ ላይ የተገለጸው ምክንያትም ቢሆን ከአንቀጽ 29 ጋር አገናኝቶ በማብራራት ‹‹በዚህ ድንጋጌ በተጠቀሱት ሁኔታዎች የሰው ፎቶ (ምስል) ማባዛት የተፈቀዱ ሲሆን፣ በሕዝብ አደባባይ መለጠፍ ወይም ማሳየት ወይም መሸጥ ግን ያለባለቤቱ ፈቃድና ዕውቅና የማይቻል መሆኑን በሕጉ በግልጽ ተመልክቷል፤›› በማለት ፍርድ ቤቱ በማብራራት የባንኩ አድራጎት በልዩ ሁኔታው የማይሸፈን ከመሆኑም ባሻገር እግረ መንገዱንም ለሦስቱም ሁኔታዎች በአንቀጽ 28 የተዘረዘሩት ልዩ ሁኔታዎች ተፈጻሚ እንደሆኑ ገልጿል፡፡

መፍትሔዎቹ

በልዩ ሁኔታ ከተፈቀደው በቀር ፎቶግራፍ ወይም ምስልን ለሕዝብ እንዲታይ ከቀረበ፣ ከተሸጠ ወይም ከተባዛ ባለመብቱ ይህ ድርጊት እንዲቆምለት መጠየቅ መብት አለው፡፡ በአደባባይ በመታየቱ ወይም በመሸጡ ጥቅም ከተገኘ በርትዕ የሚወሰን ካሳ የማግኘት መብት ይኖረዋል፡፡ የተለያዩ ሁኔታዎችን ከግምት በማስገባት የካሳውን መጠን የመወሰን ሥልጣን ለዳኞች ተሰጥቷል፡፡

በአደባባይ መታየቱ እንዲቆም ባለመብቱ ጠይቆ ወዲያውኑ ካልቆመም የኅሊና ጉዳት ካሳ (የሞራል ካሳ) ማገኘትንም በዚሁ በአንቀጽ 29 ተገልጿል፡፡ በዚህ አንቀጽ መሠረት፣ ምስሉ ለሕዝብ የቀረበበት ሰው ድርጊቱን የሚፈጸመው አካል አድራጎቱን እንዲያቆም መጠየቅ፣ ካላቆመ በፍርድ ኃይል የማስቆም፣ ካሳ መጠየቅም እንደሚችልም ሕጉ ዕውቅና ሰጥቷል፡፡

ከላይ ታሪኩ የቀረበው የሰበር ውሳኔም የከፍተኛ ፍርድ ቤቱን ውሳኔ ሲያጸና  ምስሉ በቴሌቪዥን በማስታወቂያነት ባንኩ ፈቃድ ሳይጠይቅ መጠቀሙ የከተረጋገጠ፣ የሰውን ፎቶግራፍ ወይም ሥዕል በልዩ ሁኔታ በሕጉ በአንቀጽ 28 ከተገለጹት ውጭ ለሕዝብ ማሳየት፣ ማባዛት ወይም መሸጥ ክልክል ሆኖ ሳለ ባንኩ ይህን ድርጊት መፈጸሙ የከሳሽን መብት የሚጥስ ድርጊት እንደሆነ በማተት፣ ማስታወቂ ከሠራበት ካሳ የመክፈል ግዴታ እንዳለበት በይኗል፡፡

የካሳ ጉዳይ

የሰውን ምስል ለሕዝብ ያቀረበ ሰው ዳኞች በርትዕ ካሳ እንዲከፍል ሊወስኑበት ይችላሉ፡፡ በርትዕ የሚወሰነው የካሳው መጠን ነው፡፡ ካሳ ለመጠየቅ ግን ጉዳት የደረሰ መሆኑን ማሳየት አስፈላጊ ነው፡፡ ጉዳት መድረሱን ማሳየት ባይቻል እንኳን ምስሉን በመለጠፍ ወይም በመሸጥ ጥቅም ተገኝቶ ከሆነና ይህንን ማሳየት (ማስረዳት) ከተቻለ የዳኞቹ ሚና ካሳውን በርትዕ መወሰን ነው፡፡ በሰበር የታየው ጉዳይም የከፍተኛ ፍርድ ቤቱ በከሳሽ የተጠየቀውን የካሳ መጠን ቀንሶ በርትዕ አንድ መቶ ሺሕ በማድረግ የወሰነውን አጽንቶታል፡፡ በዚህ ጉዳይ በፍርድ ቤቶቹ ከግምት የገባው ጉዳይ ለማስታወቂያነት ባንኩ መጠቀሙ ከተረጋገጠ፣ ምንም እንኳን በፍትሐ ብሔር ሕጉ፣ በአንቀጽ 2141 መሠረት የጉዳቱን መጠን በትክክል ማረጋገጥ ወይም ማስረዳት ስላስቸገረ ነው በርትዕ ውሳኔ የተሰጠው፡፡ 

ግላዊ ነፃነት ብዙ ፈርጅና ዓይነት ያለው መብት ነው፡፡ በጥቅል አንድ ስም ይኑረው እንጂ በሕግ ጥበቃ የተሰጠውና የመብትነት አቋም ያላቸው ብዙ ናቸው፡፡ የሰውን ግላዊ ጉዳይ ወይም ገመና ሕዝብ ማወቅ ያለበት በጥቂት ሁኔታዎች አማካይነት ብቻ ነው፡፡ ያውም ተገቢ የሆነ ማኅበራዊ ጥቅም ሲኖር፡፡ በቀረ አንድ ግለሰብ ሕዝብ ስለእሱ እንዲያውቅ የማይፈልጋቸውን ግላዊ ጉዳዮች መከበር እንዳለባቸው በሕገ መንግሥቱም፣ በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶችም በሌሎች ብሔራዊ ሕጎችም ጥበቃ አላቸው፡፡

ግላዊ የሆኑ ጉዳዮች ለሕዝብ ይፋ ሲደረጉ የግለሰቡን አዕምሮ ሊያውኩም ጭምር ስለሚችሉ ነው፡፡ በዚህ መልኩ ያለ ግለሰቡ ፈቃድ ለሕዝብ መቅረብ የሌለባቸው ምስሎች ናቸው፡፡ የሰውን ምስል በሕግ ከተፈቀደው ውጭ ለሕዝብ ማቅረብ በሕግ ክልክል ነው፡፡ ዜግነት ላይ ሳይወሰን ይህ መብቱ የተጣሰበት ሰው ድርጊቱን ከማስቆም ጀምሮ ካሳ ማግኘት የሚደርስ መብት አለው፡፡ ፌስቡክን ጨምሮ ድርጊቱ የተፈጸመው በማናቸውም ዓይነት ሚዲያ ቢሆንም፡፡

አዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...