Saturday, May 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

እኔ የምለዉከአሜሪካና ከኢራን ግጭት ጀርባ በጨረፍታ. . .

ከአሜሪካና ከኢራን ግጭት ጀርባ በጨረፍታ. . .

ቀን:

እስክንድር ከበደ

በኢራቅ ወደ ኪርኩክ የሚወስደው መንገድ ተደጋጋሚ የተኩስና የግድያ ትዕይንቶች ይዘወተርበታል:: ኢራቃዊው ታክሲ ነጂው ዓሊ፣ ‹‹የኪርኩክ መንገድ የሲኦል መንገድ ነው፤›› ይላል:: በመካከለኛው ምሥራቅ ነዳጅ ከዚህ በፊት የተገኘ ቢሆንምእ.ኤ.አ. 1928 በኪርኩክ የወጣውን ያህል አይሆንም ነበር፡፡ በወቅቱ በድንገት በወጣው መጠነ ብዙ ነዳጅ በተፈጠረ የእሳት ነበልባል አምስት ሰዎች ሞተዋል፡፡

የነዳጅ ዘይት ታሪክ የሚጀመረው ሌላ ቦታ ነው፡፡ በሦስት የነዳጅና ጋዝ ነጋዴዎች የዓለምን ነዳጅ ለመቆጣጠር የተሸረበ ሚስጥራዊ ስምምነት መኖሩ ይነገራል፡፡ በስኮትላንድ ቤተ መንግሥት ኢንካሪከ የአደን ሥፍራ በሚስጥር የተዶለተ ታሪክ ይዟል፡፡ ሦስት ሰዎች እዚያ ሥፍራ ቀጠሮ ነበራቸው፡፡ የደቹ ሰው፣አሜሪካኑ ሰውና የእንግሊዙ ሰው በሚስጥር ተገናኙ፡፡ የደቹ ሰውዬ ሄነሪ ዲተጅን ነው፡፡ የነዳጅ ዘይትናፖሊዮንበመባል ይጠራል፡፡ ከመርከብ ቱጃሩ ሱማትራ ጋር ሽርክና በመፍጠር በመርከቦቹ የሼል ዓርማን ቀልሞ ወደ ገበያ በስፋት መግባቱ ይነገርለታል፡፡ ሌላው ደግሞ አሜሪካዊው ስቲግል ነበር፡፡ ስታንዳርድ ኦይል ኩባንያን በመወከል በሚስጥራዊው ስብሰባ ተገኝቷል፡፡ በጆን ሮክፌለር 31 ዓመቱ የተመሠረተውን የስታንደርድ ኦይል ኩባንያ አባል ነበር፡፡ እንግሊዛዊው ጆን ካትረን የቢፒ ነዳጅ ኩባንያን ባለቤት ነበር፡፡

- Advertisement -

ሦስቱ የግዙፍ ነዳጅ ኩባንያዎች ሚስጥራዊ ዱለታ የዓለም ነዳጅ ማምረቻ ዞኖችን ማጣራት፣ ሽያጭ፣ ትራንስፖርት፣ ሥርጭት፣ ዋጋ ትመናና ሁሉንም በጋራ ለመጋራት ለማካሄድ የወሰኑበት ነበር፡፡ በኋላ ሌሎች ኩባንያዎችም በዚህ ሚስጥራዊ ዱለታ ውስጥ ተካተቱ፡፡ “ ሰቨን ሲስተርስ” (ሰባቱ እህትማማቾች) በመባል የሚጠሩት ኤክሶን፣ ሞቢል፣ ቼቭሮን፣ ገልፍ፣ ቴክሶን፣ ቢፒና ሼል የነዳጅ ኩባንያዎች እዚህ ስብስብ ውስጥ መግባታቸው ይነገራል፡፡

የሰባቱ እህትማማቾች ታሪክ ወደ ቴህራን ይወስደናል፡፡ 20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ የነዳጅ ዘይት ኩባንያዎች በፐርሺያ ነዳጅ ዘይት ለመቆጣጠር ይፋለማሉ፡፡ የመጀመርያው የዓለም ጦርነት ማብቃቱን ተከትሎ በሳንሪሞ ውል መነሻ ፈረንሣይና ብሪታኒያ የመካከለኛ ምሥራቅ የነዳጅ ሀብት ተከፋፍለውታል፡፡ በዚህ የአሜሪካ የነዳጅ ዘይት ኩባንያዎችን አስቆጥቷል፡፡ ምን ይደረግ? ከአርሜኒያዊው ዘመን አይሽሬ የነዳጅ ዘይት ደላላው ኩባንኪን መፍትሔ ይዞ መጣላቸው፡፡ ኩባንኪን ቀይ መስመር አሰመረ፡፡ የወደፊት የነዳጅ ዘይት መገኛ ዞን በመከለል በካርታ ላይ ቀይ መስመር ተሰመረ፡፡ በዞኑ ፉክክር ተከልክሎ በትብብር ለመሥራት ተስማሙ፡፡ የኢራቅ ፔትሮሊየም ኩባንያ ተመሠረተ፡፡ በኢራቅ ፔትሮሊየም ቢፒ፣ ሼል፣ ኤክሶንና ኤስኤፍፒ የወደፊቱ ቶታል ድርሻ ነበራቸው፡፡ 

ለብሪታኒያ የኢራኑ አብዳን የነዳጅ ማጣሪያ የማይነጥፍ ሀብት ምንጭ ሆነላት፡፡ በዓለም ግዙፉ የነዳጅ ማጣሪያ ነበር፡፡ ኢራን ከነዳጅ ኩባንያው የምታገኘው ሮያሊቲ ገቢ እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም፡፡ የኢራን መንግሥት የኩባንያውን የባንክ ሒሳብ የማየት ሥልጣንም የለውም፡፡ ብሪቲሽ ፔትሮሊየም (ቢፒ) ኩባንያ በመንግሥት ውስጥ ያለ መንግሥት ነበር፡፡

ይህ የብሪታኒያ ኩባንያ ለኢራን ንጉሣዊ ቤተሰቦች ድሎት የሚበቃ ክፍያ ቢሰጥምለአብዛኛው ኢራናዊያን የሚጠቅም አልሆነም፡፡ የብሪታኒያው የነዳጅ ዘይት ኩባንያ ከኢራን የሚያጓጉዘው የነዳጅ ዘይት ሳይቋረጥ ወደ አውሮፓና አሜሪካ ይገባል፡፡ የትኛውም የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የአሜሪካውያንን የአኗኗር ዘይቤ የሚጠይቀውንነዳጅ ኃይል ማሟላት ላይ በትጋት መሥራት ይጠበቅበታል፡፡

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሩዝቬልት ..አ. የካቲት 14 ቀን 1945 ከያልታ ኮንፈረንስ ሲመለሱ መርከባቸው (ዩኤስኤ ኪዊንስ) ስዊዝ ካናል ቦይ አጠገብ መልህቋን ጣለች፡፡ ሩዝቬልት ከሳዑዲ ዓረቢያው ንጉሥ አብዱለዚዝ ኢብን ሳዑድ ጋር ስዊዝ ካናል አቅራቢያ መልህቋን የጣለችው መርከብ ውስጥ በሚስጥር ተነጋገሩ፡፡ ምንም አልተፈራረሙም፡፡ ግን ታላቅ ስምምነት አደረጉ፡፡

አሜሪካና ሳዑዲ ዓረቢያ ..አ. 1936 የጀመሩትን ስምምነት ለመቀጠል ተግባቡ፡፡ ሳዑዲ ዓረቢያ ለአሜሪካ የነዳጅ ኩባንያዎች በሯን እንድትከፍትበሌላ በኩል የሳዑዲ ዓረቢያ ንጉሥ አገራቸው ጥበቃ እንዲደረግላትና ከፍ ያለ ወርቅ እንዲሰጣት መግባባት ላይ ደረሱ፡፡ የሳዑዲ ዓረቢያ ሀብት በእንግሊዛዊው አሳሽ፣ ሰላይና ጸሐፊ ሃሪሰን ሴንት ጆን ፊሊፕ ተይዞ ነበር፡፡ ሃሪሰን ጆን ፍሊፕ የዓረብ አብዮት በመቀስቀስና የሳዑዲ ዓረቢያ ንጉሣዊ ምክር ቤት እንዲመሠረት በማድረግ ይታወቃል፡፡ ሃሪሰን ..አ. በ1930 ሃይማኖቱን ወደ እስልምና በመቀየር የንጉሥ ኢብን ሳዑድ አማካሪ ሆነ፡፡

..አ. 1936 በሃሪሰን ጆን አማካሪነት ሳዑዲ ዓረቢያ የነዳጅ ዘይት መብቷን ለአሜሪካ እንድትሸጥ አደረገ፡፡ ዓረቢያን አሜሪካን ኦይል ካምፓኒ (ARAMCO) የተባለው ግዙፍ የነዳጅ ዘይት ኩባንያ ተመሠረተ፡፡ አራምኮ ግዙፍ የነዳጅ ዘይት ኩባንያዎች ኅብረት የፈጠሩት ኩባንያ ሆነ፡፡ በኤክሶን፣ ቴክሶን፣ ቼቭሮንና ሞቢል ኩባንያዎች ስብስብ አራምኮ ተመሠረተ፡፡

የአሜሪካ ኩባንያዎች በኅብረት የመሠረቱት አራምኮ የሳዑዲ ዓረቢያ የነዳጅ ዘይትን ጠቅልሎ ያዘ፡፡ በድሮ አጠራሩ አራምኮን የመሠረቱት ኩባንያዎቹ በመንግሥት ውስጥ ያሉ መንግሥት እስከመሆን ደረሱ፡፡ ሳዑዲ ዓረቢያ በእነዚህ ኩባንያዎች ቁጥጥር የሚሆን ሕግ ማውጣት አትችልም ነበር፡፡ አራምኮ ነዳጅና ዘይት የማምረት፣ ኤክስፖርት የማድረግና ዋጋ የመወሰን ሥልጣን ነበረው፡፡ ሳዑዲ ዓረቢያ በራሷ ሀብት የሚጣልላትን እርጥባን ከመጠበቅ በስተቀር አማራጭ አልነበራትም፡፡

ከፕሬዚዳንት ሩዝቬልት ጋር ስምምነት ከተደረገ በአጭር ጊዜ ውስጥ የዓረቢያ ነዳጅ ዘይት ማምረት ..አ. በ1946 ተጀመረ፡፡ ሃያ ሺሕ አሜሪካውያን በምሥራቃዊ ዓረቢያ ቴህራን ሠፈሩ፡፡ የንጉሥ ሳዑድ ወዳጅ የሆነችው ኢራን የንጉሡ እንግዶች በግዛቷ ውስጥ እንዲሠፍሩ የተደረጉት ቅዱስ ሥፍራ ስለማይሸጥ ነበር፡፡ ኢራን ስምምነቱ እንዲፈጸም ንጉሡን በመርዳት የንጉሡን እንግዶች ማረፊያ አዘጋጀች፡፡ የአሜሪካ ግዴታ ለንጉሡና 3‚000 ንጉሣዊ ቤተሰቦች የወርቅ ስጦታ ማጉረፍ ሆነ፡፡ የበረሃው ነዳጅ ዘይት ክምችት እጅግ የበዛ ነበር፡፡ 

..አ. 1952 በአሜሪካ ዋሽንግተን ሰባቱ እህትማማች ነዳጅ ኩባንያዎችሚስጥራዊ የንግድ ሻጥር ለመጀመርያ ጊዜ ተጠርጥረው ለጠቅላይ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ታዘዙ፡፡ የፌዴራል ንግድ ኮሚሽን ሕገወጥ የንግድ ሴራቸውንና ኢፍትሐዊ የንግድ ውድድርና ሥውር ትብብር እየመረመረ ነበር፡፡ ፕሬዚዳንት ሃሪ ትሩማን ለመጀመርያ ጊዜ የኩባንያዎቹን የንግድ ሻጥር በተመለከተ ከአሜሪካ ማዕከላዊ ምርመራ ቢሮ (ኤፍቢአይ) ዳይሬክተር ኤድ ጉሁቫ ሚስጥራዊ ማስታወሻ ደረሳቸው፡፡ ምርመራው ታገደ፡፡ የክስ ሒደቱም ተቋረጠ፡፡ ምክንያቱ ሰባቱ እህትማማች የነዳጅ ኩባንያዎች የሚጠቅም ሁሉ አሜሪካን ስለሚጠቅም ተዳፍኖ ቀረ፡፡

በኢራን ዋና ከተማ ቴህራን ሰፋፊ የገበያ ሥፍራዎች የልብና የትርታ ሥፍራዎች ናቸው፡፡ ..አ. በ1951 በእነዚህ ባዛሪ በሚሏቸው ክፍት የገበያ ሥፍራዎች በብሪታኒያ ፔትሮሊየም ኩባንያ (ቢፒ) ላይ የተቃውሞ ዓድማ ተደረገ፡፡ የኩባንያው ሠራተኞች የደመወዝ ጭማሪ ጠይቀው በመከልከላቸው ዓድማ መቱ፡፡ በዚህም አገር አቀፍ ዓድማ መላ ኢራንን አጥለቀለቃት፡፡ የኩባንያው ሠራተኞች ብቻ ሳይሆኑ የንግድ ማኅበረሰቡ፣ መካከለኛ መደብ ክፍሉ፣ ሶሻሊስቶችና የሺዓ ሃይማኖት መሪዎች ተቃውሞ አሰሙ፡፡

በብሪታኒያ ፔትሮሊየም ኩባንያ ሠራተኞች ዓድማ የዓለማችን ትልቁ የነዳጅ ዘይት ማጣሪያ አበዳን ተሽመደመደ፡፡ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የብሪታኒያ ኢምፓየር ታላቁ የሀብት ምንጭ ተዘጋ፡፡ ኩባንያው የአንግሎ ሳክሰን የነጭ የበላይነት ማሳያ ሲሆን፣ ኢራናውያን በገዛ አገራቸው ሦስተኛ ዜጋ ሆነው እንደ ጥቁር የሚቆጠሩበት የገነገነ ጭቆና ነበረባቸው፡፡ በኢራን ተቃውሞው በረታ፡፡ የንቅናቄው መሪ ደግሞ የኢራን ፓርላማ አባሉ ዶ/ር ሞሳዴቅ ነበሩ፡፡ ዶ/ር ሞሳዴቅ በፓርላማው አባላት ዘንድ ̎ሀቀኛ ሰው̎ የሚባሉና ከፍ ያለ የሞራል ደረጃ የሚጠቀሱ ነበሩ፡፡ የዶ/ር ሞሳዴቅ ፕሮግራም ቀላል ነበር፡፡ ይኸውም የነዳጅ ዘይት ማጣሪያውን መውረስ፡፡ በፓርላማው ግፊት ዶ/ር ሞሳዴቅ ጠቅላይ ሚኒስተር ተደርገውሾሙ፡፡

ሞሳዴቅ ጠቅላይ ሚኒስትር በሆኑ ማግሥት ማለትም ..አ. ሜይ 1 ቀን 1951 የብሪታኒያ የፔትሮሊየም ኩባንያ የያዘው የኢራን ነዳጅ ዘይት ማጣሪያ እንዲወረስ ድምፅ አሰጡበት፡፡ የኢራን ጦር ሠራዊት የነዳጅ ዘይት ጉድጓዶችን ተቆጣጠረ፡፡ ኢራናውያን ግን ያንን ግዙፍ የነዳጅ ዘይት ማምረቻ ማስቀጠል የሚችሉ ባለሙያዎች አልነበሯቸውም፡፡

በማግሥቱ ሦስት ሺሕ እንግሊዛውያን ቴክኒሻኖችና ቤተሰቦቻቸው ቴህራንን ለቀው ወጡ፡፡ የብሪታኒያ መርከቦች የኢራን ወደቦችን ዘጉ፡፡  ምዕራባውያን ከኢራን ነዳጅ ዘይት እንዳይገዛ አስተባበሩ፡፡ ከኢራን ነዳጅ ዘይት የሚገዛ አገር በፍርድ ቤት እንደሚከሰስ አስጠነቀቁ፡፡ ከቴህራን ነዳጅ ዘይት ጭና የምትጓዝ መርከብም ትወረስ ጀመር፡፡ ኢራን ነዳጅ ዘይቱን እንዳትሸጥ አገዷት፡፡ ለዚህ ደግሞ ኢራንና ሞሳዴቅ መቀጣት ነበረባቸው፡፡

የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዊኒስተን ቸርችል የአሜሪካን ዕገዛ ጠየቁ፡፡ የአሜሪካ ማዕከላዊ የስለላ ኤጀንሲ (ሲአይኤ) እጁን አስገባ፡፡ ቁጥሩ በውል የማይታወቅ ዶላር ለፓርላማ አባላትና ለቁልፍ ወታደራዊ መኮንኖች ተሠራጨ፡፡ የመፈንቅለ መንግሥቱ ዘመቻ ሚስጥራዊ ስያሜ ደግሞ ̎አጃክስ̎ ነበር፡፡ የመፈንቅለ መንግሥቱ አቀነባባሪዎች ደግሞ የፕሬዚዳንት ሩዝቬልት ወንድም ልጅ ኮሎኔል ሩዝቬልት የሲአይኤ ወኪል ሆኖ መፈንቅለ መንግሥቱን አስተባባሪ ነበር፡፡ በዚህ መፈንቅለ መንግሥት ዘመቻ ዴሞክራት ጀነራሎች፣ ኮሙዩኒስቶችና አገር ወዳዶች እንደተገደሉ ይነገራል፡፡

አምስት ሺሕ የሚሆኑ የመፈንቅለ መንግሥቱ ተቃዋሚዎች ተገደሉ፡፡ ዶ/ር ሞሳዴቅ ሞት ከተፈረደባቸው በኋላ ፍርዱ ተሻሽሎ ወደ ውጭ አገር እንዲሰደዱ ተደረገ፡፡ ኢራን ፍርኃት ውስጥ ተዘፈቀች፡፡ ሲአይኤ ለመጀመርያ ጊዜ በሌላ አገር መፈንቅለ መንግሥት በቀጥታ ተሳትፎ ያሳካው የኢራን መንግሥትን በመጣል ነበር፡፡ ..አ. ኦገስት 24 ቀን 1953 የሻህ ንጉሣዊ ሥርዓት ወደ አገር በድል መንፈስ ተመልሶ ሥልጣኑን ተቆጣጠረ፡፡ ቢፒም ዳግም የኢራንን ነዳጅ ዘይት መልሶ ተረከበ፡፡ አሜሪካ መፈንቅለ መንግሥቱን ማሳካቷን ተከትሎ፣ የብሪታኒያ የፔትሮሊየም ኩባንያ ለአሜሪካ የነዳጅ ዘይት ኩባንያዎች የኢራንን የነዳጅ ዘይት ኢንዱስትሪ መጋራት ቻለ፡፡ በዚህም አሜሪካ በፕላኔታችን ላይሁለቱ ግዙፍ የነዳጅ አምራቾች ሀብት በእጇ ገባ፡፡

በዘመኑ አሜሪካመጠገንም ሆነመስበር ኃይሏ ይታወቃል፡፡ ማንም ያልደፈራትን ዶ/ር ሞሳዴቅ ሞክረውት ነበር፡፡ የእሳቸው ከሥልጣን መወገድ በአካባቢው ፍርኃት አነገሠ፡፡ የዶ/ር ሞሳዴቅ ሙከራ እርግብግቢት ግብፅ ደረሰ፡፡ ከስዊዝ ካናል የሚገኘውን ገቢ ፈረንሣይና እንግሊዝ ይጋሩታል፡፡ ግብፅ ከስዊዝ ካናል ተጠቃሚ አይደለሁም በሚል ቦዩን ከእንግሊዝና ከፈረንሣይ በመንጠቅ ወረሰች፡፡

የግብፅ ፕሬዚዳንት ናስር ..አ. ጁላይ 26 ቀን 1956 ስዊዝ ካናል መወረሱን አወጁ፡፡ በፈረንሣይ፣ በብሪታኒያና በእስራኤል ጥምር ጦር ግብፅ ጦርነት ተከፈተባት፡፡ ወደ ካናሉ የሚያስገባው ፖርት ሳይድ በጥምር ጦሩ የጦር ጄቶች ቦምብ ተደበደበ፡፡ የግብፅ ጦር ተንኮታኮተ፡፡ ናስር በስዊዝ ካናል መርከቦች በማስመጥና መተላለፊያ ግንባታዎችን አፍርሰው መንገዱ ተዘጋ፡፡አሜሪካናሶቪዬት ኅብረት ግፊት አንግሎ ፍሬንች ጥምር ጦር ጥቃቱን እንዲያቆም ሆነ፡፡ የናስር ወታደራዊ ሽንፈት በዓረቡ ዓለም ናስሪዝምንና አዲስዓረባዊነት መንፈስ እንዲወለድ አደረገ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...