ደምስ ጫንያለው (ዶ/ር)፣ የኢኮኖሚ ባለሙያ
ደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞው የአለማያ እርሻ ኮሌጅ በግብርና ኢኮኖሚክስ በ1972 ዓ.ም. የመጀመርያ ዲግሪያቸውን ከያዙ በኋላ ወደ አሜሪካ በማቅናት በኦክላሆማ ግዛት ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ፣ በካሳስ ግዛት ዩኒቨርሲቲ ሦስተኛ ዲግሪያቸውን ሠርተዋል፡፡ ከ40 ዓመታት በላይ በውጭና በአገር ውስጥ በዘለቀው የምርምር፣ የማማከር፣ የአካዴሚክና የጽሑፍ ሥራቸው ዛሬም ህያው ሆኖ በየጊዜው ሐሳቦቻቸውንና ሙግቶቻቸውን እያረቀቡ ይገኛሉ፡፡ በርካታ የምርምር ሥራዎችን ከማዘጋጀት አልፈው ዳጎስ ያሉ መጻሕፍትን በኢኮኖሚ መስክ በተለይም በግብርናው ዘርፍ ላይ በማተኮር ለንባብ አብቅተዋል፡፡ ከሰሞኑም ‹‹ኢኮኖሚው ሦስቱ ፖለቲከኞችና ፖሊሲ›› የተሰኘ መጽሐፍ በአማርኛ ቋንቋ ለንባብ አብቅተዋል፡፡ የአገር ውስጥ ፖለቲከኞች፣ ከውጭ ኃይሎች ጋር በሚያደርጉት መመሳጠርና ተላላኪነት ሳቢያ የኢትዮጵያ ፖሊሲ አቅጣጫውን የሚስትበት አካሄድ እንደሚያሠጋቸው የሚገልጹት ደምስ (ዶ/ር)፣ ኢኮኖሚው ለፖለቲከኞች ፍላጎት መጫወቻ ከመሆኑ በቀር ለአገርና ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ተገቢውን ትኩረት ማግኘት እንዳልቻለ ይሞግታሉ፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች በአገር ጉዳይ ላይ የማይደራደር አቋም በመያዝ ለሕዝብ የሚበጅ አገራዊ ፖሊሲ መከተል እስካልቻሉ ድረስ፣ የኢትዮጵያ መጪው ጊዜ አሥጊ እንደሚሆን ያምናሉ፡፡ ፍራቻቸውም ኢትዮጵያ የዴሞክራቲክ ኮንጎ ዕጣ ፈንታ እንዳይርስባት ስለመሆኑም ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በኢኮኖሚ ፖሊሲና በፖለቲከኞች ሚና ላይ የሚያጠነጥነውን መጽሐፍ መነሻ በማድረግ ብርሃኑ ፈቃደ ከደምስ (ዶ/ር) ጋር ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡
ሪፖርተር፡– በአዲሱ መጽሐፍዎ የፖሊሲ ጉዳይ ላይ አተኩረው መነሻዎንም ከመቶ ዓመታት በፊት ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ ባሰፈሩት ቁም ነገር አዋዝተዋል፡፡ በእርስዎ ገለጻ ሦስቱ ፖለቲከኞች ማለትም ገዥና ተቃዋሚ የአገር ውስጥ ፖለቲከኞች፣ እንዲሁም የውጭ ኃይሎች በፖሊሲ ጉዳዮች ላይ ጣልቃ ገብ ናቸው፡፡ ከነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ ትረካ አኳያ ዛሬም ድረስ የውጭ ተፅዕኖ ውስጥ እንገኛለን የሚል ምልከታም አስቀምጠዋል፡፡ ከዚህ አኳያ ክርክርዎ ፖሊሲዎቻችንን እኛ አንቀርፅም፣ የእኛም አይደሉም ነው የሚለው?
ደምስ (ዶ/ር)፡– የነጋድራስ መጽሐፍን ያነበበ ሰው ዛሬ ላይ ሆኖ ሲመለከተው መደነቁ አይቀርም፡፡ ነጋድራስ ከመቶ ዓመታት በፊት ሊነግረን የፈለገው ኢትዮጵያዊ ሆነን እንደ ኢትዮጵያዊ እናስብ፣ ተግተን በመሥራት ከውጭ ተፅዕኖ እንድንወጣ ነው፡፡ የውጭ ኃይሎች በግልጽ በተፅዕኗቸው ሥር እንደምንገኝ እየነገሩን ነው፡፡ እንዳይደርሱብን መከልከል አንችል ይሆናል፡፡ ነገር ግን በሥራና በጥረት አቅማችንን ስናደራጅ መከላከል እንችላለን፡፡ ለዚህ ደግሞ የራሳችን የሆነ የአሠራር ሥርዓት ወይም ፖሊሲ ሊኖረን ይገባል፡፡ ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ከመቶ ዓመታት በፊት ሥጋት ሆኖበት የጻፈልን ችግር ዛሬም አለ፡፡ ከጥያቄው አኳይ ለመነጋገር፣ በንጉሡ ጊዜ ያየን እንደሆነ በትክክልም ጨዋታውን የተረዱ ኢትዮጵያውያን ነበሩ፡፡ ምርጫም አልነበራቸውም፡፡ በአስቸጋሪ ጦርነቶች ውስጥ ያለፈ መንግሥት እንደ መሆኑ መጠን፣ የጦር አጋዦች የነበሩ አገሮችን ፍላጎት የማስተናገድ ግዴታ ነበረበት፡፡ ንጉሡ ይህንን በማድረጋቸው የሚኮንናቸው ካለ ተገቢ አይመስለኝም፡፡ በዚያ ሁኔታ ውስጥ ኢትዮጵያውያንን አገራዊ ስሜት እንዲኖራቸው፣ ስለአገር ብለው እንዲሠሩ ያበረታቱ እንደነበር ከበርካታ ንባቦች ትረዳለህ፡፡ በፖሊሲም ሆነ በስትራቴጂ ረገድ የሚጻፉትን ነገሮች በአብዛኛው የውጭ ኃይሎች ቢያመጧቸውም፣ የአገር ውስጥ ኃይሉ ግን የአገርን ጥቅም ለማስከበር ብዙ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡
ከኢኮኖሚው አኳያ ዛሬ እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድን፣ እንደ ኢትዮ ቴሌኮም ያሉትን ግዙፍ ኩባንያዎች አሳልፈን ለመስጠት ነው የምንጣጣረው፡፡ በንጉሡ ጊዜ እነዚህ ተቋማት በፖሊሲና በስትራቴጂ አግባብ በውጮች ዕገዛ እንዲቋቋሙና ከመነሻውም በእነሱ እንዲመሩ ተደርገው ቀስ በቀስ ወደ ኢትዮጵያን እንዲዛወሩ፣ በኢትዮጵያውያን እንዲመሩ ሲያደርጉ ነበር፡፡ በወታደራዊው መስክም ብናይ፣ በተለይ አየር ኃይላችንን በምናይበት ጊዜ ስዊድኖችን ጠይቀው ባገኙት ድጋፍ ነው ጠንክሮ ወጥቶ በኢትዮጵያውያን ይበልጥ ውጤታማ መሆን የቻለው፡፡ በቴሌኮም መስክ ፈረንሣዮች አግዘውናል፡፡ የንጉሡ ጊዜ የፖሊሲ ትኩረት ከውጭ ወደ ውስጥ ነበር፡፡ ኃያላኑን አገሮች ሳይጋፉ ውስጥ ለውስጥ ግን የኢትዮጵያን ተቋማት በኢትዮጵያውያን እንዴት መመራት እንደሚችሉ ዝግጅት ሲደረግና ኋላም ኢትዮጵውያኑ እንዲረከቧቸው ሲመቻች ነበር፡፡ ይህ አካሄድ እስከ ደርግ ሥርዓት መምጣት ድረስ ቀጥሏል፡፡ የተማረው ኃይል ወደ መጨረሻው አካባቢ ማፈንገጥ ከመጀመሩ ቀደም ብሎ ኢትዮጵያዊ ስሜቱና ማንነቱ ላይ ጠንካራ አመለካከት ነበረው፡፡ ከደርግ መምጣት በኋላ በታየው የፖለቲካ ክፍፍል ውስጥ ውጭ አዳሪውና አገር ተመልካቹ እየተለዩ መጡ፡፡ ውጭ አደሩ የተማረ ኃይል የአገሪቱ ፖሊሲዎች በውጭ ኃይሎች እንዲቀረፁ ድጋፍ ከመስጠት አልፎ፣ መሣሪያ እየሆነ መጣ፡፡ ከደርግ ጋር በፖለቲካ ያደረበትን ቁርሾ የደርግን ሙከራ ሁሉ ከርዕዮተ ዓለም ጽንፈኝነት አኳያ እየቃኘ፣ በምዕራባውያን ጫና እንዲደረግበት ውጭ አደሩ መሣሪያቸው ሆኖ አገልግሏል፡፡
ይህ ሁኔታ ከምን ክስተት ጋር ተዛምዶ እንደነበር ለመመልከት፣ እ.ኤ.አ. በ1960ዎቹ የአፍሪካ አገሮች ከአውሮፓ ቅኝ ገዥዎች ነፃ በወጡ ጊዜ፣ አፍሪካ ምንም ቢደረግ የማያልፍለት አኅጉር ነው የሚል ሥነ ልቦናዊ ዘመቻ ይካሄድ ነበር፡፡ አፍሪካ የራሱን ፖለሲ በራሱ መቅረፅ እስካልቻለ ድረስ እውነትም አያልፍለትም፡፡ እስከ ዛሬም ድረስ በርካታ የአፍሪካ አገሮች ይህንን ማድረግ አልቻሉም፡፡ ኢትዮጵያ እስከተወሰነ ጊዜ ድረስ ዕድሉ ነበራት፡፡ አሁን ግን በውጭ ተፅዕኖ መረብ ውስጥ ገብታለች፡፡ ይህን እርግጥ ከ30 ዓመታት በፊት ጽፌው ታትሟል፡፡ ‹‹ኮሎኒያሊዝም ኢን አብሰንሺያ›› የሚል ርዕስ ያለው ጽሑፍ ነበር፡፡ መነሻዬ ሎርድ ሉጋርድ የተባለ እንግሊዛዊ ያነሳው ሐሳብ ነበር፡፡ ቅኝ የተገዙ አፍሪካውያንንም ሆኑ ሌሎችን አገሮች ለመያዝ እንደ ድሮው ጦር ማዝመትና አገሩን መቆጣጠር እንደማያስፈልግ፣ ይልቁንም የተማረውን ኃይል በመጠቀም በእጅ አዙር የኢኮኖሚና የሌላውንም ፖሊሲ እንደ እንግሊዝ ፍላጎትና ጥቅም እንዲቀርፅ ማድረግ ስለሚቻልበት መንገድ ጽፎ ነበር፡፡ በአጭሩ በአገራችን አሁን ያለው አካሄድ ይሄ ዓይነቱ ጥላ ያንዣበበት ነው፡፡ ፖሊሲዎቻችን በእኛ መንገድና በእኛ አመለካከት መቀረፅ አለባቸው፡፡ በአዲሱ መጽሐፌም እንደ ጠቀስኩት፣ የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት በሰፊው ይታያል፡፡ አቶ ገብሩ አሥራት ስለአቶ መለስ በጻፉት ውስጥ የአሜሪካን ተፅዕኖ ለማሳየት ሞክረዋል፡፡ አቶ በረከት ስምኦን የጻፉትም ምን ያህል ከውጭ ኃይሎች ጋር ትግል እንደነበር፣ እጅ ላለመስጠት ይደረግ ስለነበረው ውጣ ውረድ እንመለከታለን፡፡ አሁን ይህ ኃይል የለም፡፡ በኢሕአዴግ ውስጥ ተመቷል፡፡ አሁን አገር በቀል እየተባለ ስለሚገለጸው ፖሊሲ ከሦስት አራት ዓመታት በፊት የተናገርነውና የጻፍኩበት ነው፡፡ አዲስ ነገር አይደለም፡፡ አርከበ ዕቁባይ (ዶ/ር) አገር በቀል በማለት በመጽሐፋቸው ስለዚሁ በዚያን ወቅት ጽፈው ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት በውጭ ኃይሎች ጫና ሳቢያ ችግር ላይ የወደቅን ይመስለኛል፡፡
ሪፖርተር፡– በፖሊሲ ረገድ የቀድሞዎቹ የኢሕአዴግ ኃይሎች ሲያራምዷቸው የነበሩ ፖሊሲዎችም ቢሆኑ ከእስያ የተቀዱ፣ አንዱ እግራቸው እስያ ሌላኛው ላቲን አሜሪካ እየተባሉ የሚተቹ ነበሩ፡፡ የልማት ፖሊሲዎቹ በእንዲህ ዓይነት መንገድ ስለተቀረፁ ውጤታማ ሊሆኑ አልቻሉም እየተባሉ ነው፡፡ አሁን አገር በቀል፣ ኢትዮጵያ ተኮር የሆነ ፖሊሲ ስለመውጣቱ እየተነገረን ነው፡፡ ከኃያላኑ ተፅዕኖ አኳያስ ስለፖሊሲ ነፃነትና ስለፖሊሲ አገር በቀልነት እንዴት ደረትን ነፍቶ መናገር ይቻላል?
ደምስ (ዶ/ር)፡– እዚህ ላይ ነው መጽሐፌ ትኩረት እንድናደርግ የሚያመላክተው፡፡ ዓውዶችን ግን መለየት አለብን፡፡ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ወዘተ. ጉዳዮችን በየፊናቸው ልንቃኛቸው ይገባል፡፡ ችግራችን ዕሳቤ፣ ፍልስፍና፣ ርዕዮተ ዓለም፣ ንድፈ ሐሳብ፣ ወዘተ. አይደለም፡፡ ልማታዊ መንግሥትነት የነበረና የቆየ ሐሳብ ነው፡፡ ሊበራሊዝም ላይ ብዙ ተብሏል፣ ተጽፏል፡፡ ሁሉ ነገር ፖለቲካዊ ቅኝት ውስጥ መውደቁ ነው ችግር እየሆነ የመጣው፡፡ ኢኮኖሚውና ዕሳቤዎቹ የፖለቲከኞች መጫወቻ ስለሆኑ ነው ችግር የተፈጠረው፡፡ ለኢኮኖሚያዊና ለማኅበራዊ ልማት መምጣት፣ መጀመርያ በርዕዮተ ዓለም ካልታጠርክ የሚልህ አካል ካለ ዕርባና ቢስ ነው፡፡ የአሁኖቹም ሆኑ የበፊቶቹ ኢሕአዴጎች ራሳቸው የጻፉትን ነገር አያውቁትም፡፡ ፖሊሲና ስትራቴጂ ከእስያ ወይም ከሌላ ቦታ መምጣቱ ቁምነገር አይደለም፡፡ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ነው ስለተባለም አይደለም ውጤታማ የሚሆነው፡፡ ለመሆኑ ምንድነው? ለምንስ ይህንን ገለጻ መጠቀም ፈለጉ? አልገባኝም፡፡ ይህንን ወደ ጎን እንተወውና ፖሊሲዎቹና ስትራቴጂዎቹን እንያቸው፡፡ አብዮታዊ ዴሞክራሲ የሚለውን መጽሐፍ ሲያወጡ በውስጡ ያለው ቁምነገርና በየአምስት ዓመቱ የወጡት የኢኮኖሚ ዕቅዶች፣ ማሻሻያ የተደረገባቸው ስትራቴጂዎችና ሌሎችም ሰነዶች ውስጥ የተመለከቱት ሐሳቦች ተለቅመው ሲወጡ መታየት ያለበት ክፍተታቸውና አዳዲስ ጉዳዮች ምንድን ናቸው የሚሉት ናቸው እንጂ፣ ስያሜና መጠሪያቸው መሆን የለበትም፡፡
አገር በቀል የተባለውን የኢኮኖሚ ሪፎርም ሰነድ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) መጽሐፍ ለይቼ ማየት እፈልጋለሁ፡፡ ሁለቱን ለይቶ ማየት ያስፈልጋል፡፡ አገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም የተባለው ሰነድ ምንም አዲስ ነገር እንደሌለው መከራከር እችላለሁ፡፡ አዲስ ሊባል የሚችለው ምናልባት በዝርዝር ተብቶ ሲቀርብ ሊሆን ይችላል፡፡ ስህተት ያለው የሚመስለኝ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ዙሪያም ሆነ በሌሎች መሥሪያ ቤቶች ውስጥ የተሰገሰጉት ወጣት ልጆች፣ ሲመስለኝ አብዮታዊ ዴሞክራሲን ማየት አልፈለጉም፡፡ ይህ በመሆኑም ይመስለኛል የነበረውን መልሰው የሚደግሙት፡፡ ማንበብ ቢችሉ ጥሩ ነበር፡፡ ስያሜው አይደለም ችግሬ፡፡ እኔ ስጽፍ አገራዊ ወይም ‹‹ኢንዲጂኒየስ›› እያልኩ ነው፡፡ በተለይ በግብርና መስክ መሠረት የሆነኝ የኢሕአዴግ የግብርና ልማትና ፖሊሲ መርሆዎች በሚለው ሰነድ ውስጥ፣ ‹‹እግር በመሬት›› ወይም ‹‹ፉት ኦን ዘ ግራውንድ›› የሚለው መርህ ነው፡፡ በሰው ጉልበትና በመሬት ሀብት ላይ ያተኮረ ልማት፣ የተቀናጀ ግብርና መከተል፣ አገሪቱ በሥነ ምኅዳር ሀብቷ የታወቀች በመሆኗ እንዲህ ያሉ የግብርና ሥራዎች ላይ ማተኮር እደሚገባ ይህ ሰነድ ያስቀምጣል፡፡ በአጭሩ በአገር ሀብትና በአገር ተጨባጭ ሁኔታ ላይ የሚንተራስ ይዘት ነበረው፡፡ ይሁን እንጂ አገራዊ ፖሊሲና ስትራቴጂ መነሻው ተጨባጭ ነገር ሳይሆን አስተሳሰብ ነው፡፡ ለምሳሌ በፖሊሲ ረገድ በ21 ክፍሎች ከፋፍዬ ካስቀመጥኳቸው የመንግሥት ፖሊሲ አቅጣጫዎች መካከል ለአገራዊ ባለሀብት የተሰጠውን ትኩረት እንይ፡፡ ትልቅ ችግር ያለው እዚህ ላይ ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት አብዛኛው የመንግሥት ቢሮ ለውጭ ባለሀብት አገልግሎት ለመስጠት ታስቦ የተቋቋመ እስኪመስል ድረስ፣ ትኩረቱ የውጭው ላይ ብቻ እየሆነ ነው፡፡ በእኔ ሥሌት ግን 78 በመቶ የግብር ገቢ ከግብርናው መስክ የሚሰበሰብ ነው፡፡ በመጽሐፌ ጠቅሻለሁ፡፡ የግብርናው አስተዋጽኦ አምስት በመቶ ብቻ ነው የሚሉ አሉ፡፡ ይህ ግን ከየት የመጣ አባባል እንደሆነ አይገባኝም፡፡ መሬቱ፣ ፋይናንሱ፣ ሌላው ሌላው ሁሉ እያደጉ ላሉ ንግድ ተኮር ገበሬዎች ሳይሆን፣ ለውጭው ባለሀብቶች ነው የሚዘጋጀው፡፡ እነዚህ ናቸው መደገፍ የነበረባቸው፡፡ አስተሳሰቡ ይህ ነው፡፡ ማን ነው መጀመርያ መገንባትና መነሳት የሚያስፈልገው የሚለውን አናስብም፡፡ የኢንዱስትሪ ፓርክ መገንባት ቅድሚያ የሚሰጠው ሥራ መሆን የለበትም፡፡ ደግሞም ገንዘቡ እስካለ ድረስ እንዲህ ያለው ግንባታ በማንኛውም ጊዜ መካሄድ ስለሚችል ያለ ጊዜው እሱ ላይ ሀብት ከማባከን ይልቅ፣ የአገር ውስጥ ባለሀብቶችና አምራቾች እንደ አካባቢያቸው ተጨባጭ ሁኔታ ምርታማ እንዲሆኑ ማድረግ ይበጃል፡፡ ምርታማ ለመሆን ማምረቻ ሼድ መገንባት ግዴታ አይደለም፡፡ ኢንዱስትሪ ፓርኮች በደርግ ጊዜም ሲገነቡ ነበር፡፡ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም በመጽሐፋቸው ስለዚህ ሥራ አስፍረዋል፡፡ ችግሩ በደርግ ጊዜ የተሠራውንም መሥራት አለመቻላችን ነው፡፡ በደርግ ጊዜ ትራክተር ማምረት ተጀምሮ ነበር፡፡ ኬሚካል የሚረጩ አነስተኛ አውሮፕላኖችን በመሥራት ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ተሞክሮ ነበር፡፡ ሁሉ ነገር ፖለቲካዊ ይዘት ስለሚሰጠው እንጂ፣ የተሠራውንና በሰነድ ያለውን የሚያነብ የለም፡፡ ይልቅ እዚህ ሲሠራና ሲያሠራ የነበረውን በመተው ለውጭው እንግዳ ነው ሽር ጉድ የሚባለው፡፡ ፖለቲካው የራሳቸው ጉዳይ ነው፡፡ ማንም ቢሆን ግን አገራዊ ዕይታ ሊኖረው ግድ ይለዋል፡፡
ሪፖርተር፡– ፖሊሲ ሲቀረፅ እንደ እርስዎ ያሉ ባለሙያዎች ግብዓት እንድትሰጡ ትጠየቁ ይሆናል፡፡ ለመሆኑ ኢትዮጵያ ፖሊሲ በምትቀርፅበት ጊዜ ከመሠረታዊ ችግሮቿ በመነሳት ነው? ችግሮቿን በሚገባ ትፈትሻለች? ምሁራኑስ ችግራችን ይህ ነው የሚል ሐሳብ ያንሸራሽራሉ?
ደምስ (ዶ/ር)፡– በአጭሩ ፖሊሲ በመቅረፅና በመጻፍ አገር አታድግም፡፡ አዳዲስ ፖሊሲዎች ከመቅረፅ በፊት ያሉትን ችግሮች ማየት ተገቢ ነው፡፡ ለምሳሌ በግብርና ላይ ከዚህ ቀደም የገጠር ልማት ስትራቴጂ ስልቶች የተሰኘ ሰነድ አለ፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እንደጻፉት ይነገራል፡፡ እሳቸው ከየትም አላመጡትም፡፡ አንብበው ካገኙት ተነስተው አገራዊ ዕይታ ሊሰጡት ሞክረዋል፡፡ እንደሰው አመለካከት መለስ ሊወገዙ ይችላሉ፡፡ ስለፖሊሲ ስንነጋገር ግን ያንን ሰነድ ማገላበጥ ያስፈልጋል፡፡ ፖሊሲውን ለማስፈጸም የወጡ አዋጆችና ደንቦችን እንደ ሙያተኛ ማየቱ ተገቢ ነው፡፡ እኔ መለስን ሳይሆን ሥራውን ነው የማየው፡፡ ለምሳሌ አርብቶ አደሩ ከብቶቹን ይዞ የሚዞረው ለምንድነው የሚል መነሻ ቢኖርህ፣ ውኃና ግጦሽ ፍለጋ እንደሆነ ታጠናና የውኃ ልማቱን በዚህ ደረጃ ምላሽ እንዲሰጥ የማድረግ አካሄድ መከተል፣ ችግሮችን በፖሊሲ የመፍታት አካሄድ ነው፡፡ ትግበራ ግን መሠረታዊ ችግር ነው፡፡ የውኃ ልማት በየአካባቢው አርብቶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተባለ ይጀመራል፡፡ ነገር ግን በመንገድ ላይ ይቀራል፡፡ ችግራችን መጻፍና ችግርን ማየት አይደለም፡፡ ትግበራ ነው፡፡ በመጽሐፍ ደረጃ አብዛኞቹ ፖሊሲዎቻችን ጥሩ ዕይታ አላቸው፡፡
ሪፖርተር፡– ፖሊሲዎቹ ችግራችንን በአግባቡ ተገንዝበው ይወጣሉ ወይ የሚለውስ?
ደምስ (ዶ/ር)፡– አንድ ነገር መገንዘብ ያለብን ፖሊሲዎች ከተለዋዋጭ ሁኔታዎች አኳያ የሚታዩ መሆን እንዳለባቸው ነው፡፡ አገራዊም ዓለም አቀፋዊም ሁኔታዎችን እየተከታተሉ መገምገምና ማስተካከል የግድ ይሆናል፡፡ ይህም ይባል እንጂ ፖሊሲዎች በሚወጡበት ወቅት ችግሮችን በሚገባ ይመለከታሉ፡፡ ነገር ግን በተንዳሆ፣ በቆጋ አካባቢና በሌሎችም ትልልቅ ፕሮጀክቶች በፖሊሲ ታግዘው ተጀምረው ነበር፡፡ ብዙዎቹ ፕሮጀክቶች ከፖሊሲው አቅጣጫ ውጪ ሆነዋል፡፡ ሰፋፊ ለምግብ ሰብሎች ልማት የታሰቡ መሬቶች የጫት እርሻ ለመሆን ተገደዋል፡፡ ፖሊሲዎቻችን እንደ አወጣጣቸው አይተገበሩም፡፡ ፖሊሲዎች ከተቋማትና ከትግበራ አቅም አኳያ ተነጣጥለው አይታዩም፡፡ ችግሩ አንዳንዶቹ የውጭ ለጋሾችን ለማስደሰት ሲባል ጭምር የሚወጡ መሆናቸው ነው፡፡ ይህ ‹‹ቴሌ ፖሊሲ›› የሚባለውን ሐሳብ ያስታውሰኛል፡፡ የውጭ አጋሮች ድጋፍ ሲሰጡህ ቅድመ ሁኔታዎችን አብረው በማስቀመጥ ነው፡፡ በዚህ አግባብ የሚጻፈው ፖሊሲ ሁሉ ግን አይተገበርም፡፡ በውስጥ በኩል የማይታወቅ ሌላ ፖሊሲ ነው ወደ ተግባር የሚመጣው፡፡ ይኼ ዓለም አቀፍ መልክ ያለው ነው፡፡ አገሮች የተስማማንበት ፖሊሲ ይህ አይደለም እያሉ በአደባባይ ሲሞግቱ የምንሰማው ለዚህ ነው፡፡ እነሱን ለማስደሰት የሚወጣው ፖሊሲ መድረሻው አይታወቅም፡፡
ሪፖርተር፡– በመጽሐፍዎ በፖለቲከኞች ላይ ቆንጠጥ ያለ ትችትና ወቀሳ አቅርበዋል፡፡ ገዥው ፓርቲ፣ ተቃዋሚዎች ወይም የውጭ ፖለቲከኞች ኢኮኖሚውን ባሻቸው መንገድ ሲጠመዝዙትና ኦኮኖሚያዊ ፖሊሲዎችንም ለዓላማቸው ሲያንሻፍፉ ይታያሉ ብለዋል፡፡ ፖለቲከኞችና ኢኮኖሚስቶች በኢኮኖሚ ጉዳይ ላይ የት ጋ ነው የሚገናኙትና የሚለያዩት?
ደምስ (ዶ/ር)፡– ይህንን በትነን ማየት አለብን፡፡ በመጽሐፌ ፖለቲከኞችን በሦስት እከፍላቸዋለሁ፡፡ ሁለቱ በመጽሐፉ ሽፋን የተቀመጡት የአገር ውስጥ ፖለቲከኞች ናቸው፡፡ ፖለተከኛ ሲባል በየመንደሩ ሻይ ቡና ላይ የሚተርከውን ሳይሆን፣ በፖለቲካ ቡድን ውስጥ ተደራጅተው ወይም ሥልጣን የያዙ ወይም ሥልጣን ለመያዝ የሚሠሩ ፖለቲከኞች ናቸው፡፡ ሦስተኛው ፖለቲከኛ ከውጭ የሚመጣው ኃይል ነው፡፡ እነዚህን ሦስት አካላት ከኢኮኖሚ ዕይታቸው አንፃር ስንመለከት ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎችን ሳይረዱ ሳይሆን፣ ተረድተውም ጭምር ነው ችግር የሚፈጥሩት፡፡ የውጪዎቹ በተለይ ዋና ተልዕኳቸው በፖለቲካ መሣሪያነት ኢኮኖሚያዊ ጥቅማቸውን ማስከበር ነው፡፡ ሌላ ፍላጎት የላቸውም፡፡ የውጪዎቹ ስለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ መሠረትና ከኢትዮጵያ ምን እንደሚፈልጉ ያወቁት ዛሬ አይደለም፡፡ ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ በጻፈበት ጊዜም አይደለም፡፡ ከዚያም በፊት የነበረና የኖረ ፍላጎት አላቸው፡፡ የውጭ አካላት ለምን ወደ እኛ እንደሚመጡ በግልጽ የታወቀ ነው፡፡ ያለህን ሀብት ለመውሰድና የሸቀጣቸው ማራገፊያ እንድንሆን ማድረግ እንደሚፈልጉ ነጋድረስ ገብረ ሕይወት ያኔ ጽፎ ነበር፡፡ ከማዕድን ቀርቶ ከእያንዳንዷ ደቡብ ውስጥ ካለች ዛፍ ከቅርፊቷ ስንት ሚሊዮን ብር ማግኘት እንደሚቻል ያውቃሉ፡፡ ዝም ብዬ ሳይሆን የደን ባለሙያዎች የሚነግሩኝን ነው የምጠቅሰው፡፡ በውኃው ሀብት መስክ ምን ማልማት እንደምንችል ያውቃሉ፡፡ ለምን እንደሚሞግቱንም የታወቀ ነው፡፡
በባህር ዳር የንጉሡ ቤተ መንግሥት ውስጥ የት ቦታ ምን ዓይነት ልማት እንደሚካሄድ የሚያመላክት ካርታ ተሰቅሎ ይታያል፡፡ ንጉሡ የጂኦ ተርማል ኃይል ሳይቀር የመገንባት ዕቅድ ነበራቸው፡፡ ስለዚህ የውጭ ኃይሎች ኢኮኖሚያችንን አላምጠው ያውቁታል፡፡ የቀድሞዎቹ ኢትዮጵያውያን ለአገር ልማት የሚያስቡ ሙያተኞችና ልሂቃን ነበሩ፡፡ የዘንድሮ ፖለቲከኞች ግን ችግር አለባቸው፡፡ ብዥታ ውስጥ የወደቀ ብዙ ነው፡፡ ተማርኩ የሚለውና በዳያስፖራ ስም የሚመጣው አካል ችግር አለበት፡፡ በየመሥሪያ ቤቱ ተሰግስጎ በማያውቀው ኢኮኖሚ ውስጥ ችግር እየፈጠረ ነው፡፡ አብዛኞቹ የግብርናውን ዘርፍ አልተረዱትም፡፡ የምናቀርበውን ሐሳብ ላይ ላዩን ይወስዳሉ ግን አያዘልቁትም፡፡ ግብርና ቢራ ፋብሪካ እንደ መክፈት፣ ጭማቂ ማምረቻ እንደ መገንባት ወይም ደግሞ የቆዳ ቦርሳ ፋብሪካ እንደ መሥራት ቀላል አይደለም፡፡ ክትትልና ያልተቋረጠ ፅናት ይፈልጋል፡፡ የግብርና ኢኮኖሚውን የተረዳው የለም፡፡ ፖለቲከኞች እንዲረዱ የምፈልገው ጉዳይ አለ፡፡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በእግሩ ቆሞና አድጎ ለኢንዱስትሪውና ለአገልግሎት ዘርፉ ሊተርፍ የሚችለው ግብርናው ላይ ከተሠራ ብቻ ነው፡፡ አስናቀ ፍቅሬ (ዶ/ር) የተባሉ ባለሙያ ስለግብርና በጻፉት መጽሐፍ፣ ግብርና በመሬት ስፋትና ጥበት ሳይወሰን ውጤታማ መሆን ስለሚቻልበት አሠራር ይተርካሉ፡፡ ደቡብ ኮሪያዎች ከራሳቸው አልፈው ሌላውንም በአትክትልና ፍራፍሬ የሚመግቡት ግማሽ ሔክታር አርሰው ሳይሆን፣ አሥር ካሬ ሜትር ቦታ አልምተው ነው፡፡ ማሰብ ነው የሚጠበቅብን፡፡ ፖለቲከኞቻችን ብዙ ያልተረዱት ነገር አለ፡፡ እነሱ የሚያነቡትና የሚያወሩት ስለብሔር ብሔረሰብ፣ ስታሊን ስለጻፈው ጉዳይ ወይም ሌላው ምዕራባዊ ስለሚያቀነቅነው አመለካከት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥያቄ ግን የብሔርና ብሔረሰብ ጉዳይ አይደለም፡፡ ከመነሻውም ይህ ችግር አልነበረም፡፡ ጥያቄው የኢኮኖሚ ጉዳይ ነበር፡፡ ጥያቄው ከመሬት ጋር የተያያዘ ነበር፡፡ ድሮም ዛሬም የገበሬው ጥያቄ የብሔር ብሔረሰብ ጉዳይ አይደለም፡፡ ጥያቄው ኢኮኖሚያዊ ነው፡፡ የዘንድሮ ፖለቲከኞች ግን አውቀውም ሆነ ሳያውቁ ጊዜያቸውን በማይገባቸው ጉዳይ ውስጥ እያባከነኑ ነው፡፡
ሪፖርተር፡– በሐሳብ፣ በምርምራቸውና በደረሱባቸው ሳይንሳዊ ውጤቶች የሚጠቀሱ በርካታ ምሁራንና ባለሙያዎች በየመስኩ አሉ፡፡ ፖለቲከኞች ነገሩን ከማበለሻሸታቸው በፊት እንዴት ተፅዕኖ መፍጠር አቃታቸው?
ደምስ (ዶ/ር)፡– ሲጀመር ምሁር የምትለውን አገላለጽ አልቀበለውም፡፡ ከፍተኛ ትምህርት አካባቢ ያለፉትን ለመግለጽ ከሆነም የተሳሳተ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የሚሰለፉት አካላት እንዲያውም አገሪቱ ለደረሰባት ድቀት ተጠያቂዎች ናቸው፡፡ የተማሩ የሚባሉት ሰዎች የሚጽፏቸውን አነባለሁ፡፡ ሙግቶቻቸውን እሰማለሁ፡፡ እንዲሁ መጧጧዝ ነው፡፡ ዋናውን ጉዳይ ረስተውታል፡፡ የተማሩት አካላት ወይም ልሂቃን ተብዬዎቹ ራሳቸውን አይደሉም፡፡ ልሂቃንና ባለሙያዎች በፖለቲከኞች ላይ ተፅዕኖ ለመፍጠር መጀመርያ መግባባትና መነጋገር ሲችሉ ነው የሚመጣ ነው፡፡ አሁን እኮ አገራዊ ዕይታ ይዞ የሚነሳ እየጠፋ ነው፡፡ ከመጻፍና ከውጭ በመጣ ኃይል በሚያገኘው ዳረጎት የሚቀዝፍ ነው የሞላው፡፡ እኔ ውጭ ነው የተማርኩት፡፡ ለአሜሪካ ሕዝብ ከበሬታ አለኝ፡፡ የአሜሪካ ሕዝብና ካፒታሊዝም ግን የተለያዩ ናቸው፡፡ ካፒታሊዝማቸው ለራሱ ሲል ሁሉንም ነገር ጨምድዶ የመያዝ አባዜ አለበት፡፡ እንኳንና የታዳጊ አገሮችን ፖለቲከኞችና ልሂቃን የራሱን አገር አዋቂዎች አንቆ ይዞ እንደሚይዝ፣ ታዋቂው ልሂቅ ጆሴፍ ስቲግሊዝ ጽፈውታል፡፡ የአሜሪካ ምሁር በለው ልሂቅ በጥቂት ሀብታሞችና ባለሥልጣናት ተጨምድዶ የተያዘ ነው፡፡ የእኛ አገር ልሂቅማ እንዳሻህ በጥቂት ዶላሮች ታሽከረክረዋለህ እኮ፡፡ በአሁኑ ወቅት የአገር ውስጥ ፖለቲከኞች የውጭ ኃይል ከጀርባቸው ስላለ እንጂ፣ በራሳቸው ኃይል ቆመዋል ለማለት ይቸግረኛል፡፡
እኔ የኢኮኖሚ ባለሙያ ነኝ፡፡ መላምቶችንና ትንበያዎችን አስቀምጣለሁ፡፡ ሳስተምር የማይጠይቅና የማይጠራጠር ተማሪ ተመራማሪ እንዳልሆነ እነግረዋለሁ፡፡ ፖለቲከኞቻችን በራሳቸው ገቢና ዕውቀት ቆመው ይሄዳሉ ብዬ አላምንም፡፡ በራሳቸው እስካልቆሙ ድረስ ተነጋግረው ሊግባቡ አይችሉም፡፡ የውጭ ቀራጮቻቸውም ተነጋግረው እንዲግባቡ ስለማይፈልጉ፣ አገራዊ ዕይታ እንዲኖራቸው ስለማይሹ የእኛ ፖለቲከኞች በየት በኩል ይነጋገሩ? ቪንሴንት ቶምሰን የተባለ ናይጄሪያዊ እ.ኤ.አ. በ1970ዎቹ ሲጽፍ አንድ ነገር አስቀምጦ ነበር፡፡ በርካታ አገሮች ከቅኝ ግዛት መውጣት ሲጀምሩ እነ ንክሩማ ከኮሎኒያሊዝም ወደ ኒዮ ኮሎኒያሊዝም ተሸጋገርን ብለው ይከራከሩ ነበር፡፡ ይህ ጸሐፊ ግን አንድ ሐሳብ ነበረው፡፡ ኮሎኒያሊስቶች አድብተው እየሠሩ ነው፡፡ የለቀቁትን አገር መልሰው ይይዙታል፡፡ መልሰው የሚይዙትም በ‹‹ማይክሮ ናሽናሊዝም›› ወይም በንዑስ ብሔርተኝነት አካሄድ ነው ብሎ ይከራከር ነበር፡፡ አሁንም እኛ እየሆነ ያለው አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ከቅኝ ግዛት አፍሪካ እንደተላቀቀች ነው ይህን ሴራ ነጮቹ ያዘጋጁት፡፡ በዚህ አስተሳሰብ የተቀረፀ ምሁር ነው እንግዲህ ከውጭ እየመጣ ያለው፡፡ በየሥርቻው ተወሽቆ አገር እንደማያልፍለት እንጂ፣ እንዴት መሥራት እንደሚገባ አይናገርም፡፡ ዳያስፖራው ካፒታሊዝም የሚጠቀምበት መሣሪያ እየሆነ ነው፡፡ በዳያስፖራ ስም የሚመጣው በሽታ ይዞ ከሆነ ሳይመጣ ቢቀር ይሻለናል፡፡ ዳያስፖራውን በሦስት ከፍዬ ነው የማስቀምጠው፡፡ አንደኛው ኢንቨስተር የሚባለው ነው፡፡ ሌላኛው በከፍተኛ ተቋማትና ሌሎችም የምርምር መስኮች ሙያዊ ድጋፍና ግልጋሎት ለመስጠት የሚመጣው ነው፡፡ ሦስተኛው ግን በዳያስፖራ ስም በሁለትዮሽና በባለ ብዙ የትብብር ስምምነቶች ሰበብ እየመጣ በየመሥሪያ ቤቱ ድጋፍ ለመስጠት በሚል የተሰገሰገው ነው፡፡ ፖሊሲ ላይ አማክራለሁ ይላል፡፡ የማያውቀውን ሲሠራ ታየዋለህ፡፡ ሰንጥቆና ጨፍልቆ ሲጥል የምታየው ነገር ያሳምምሃል፡፡ ከሚመጡት ውስጥ ጥሩ ጥሩዎቹን ለይተን ማውጣት አለብን፡፡ ተልዕኮ ተሰጥቶት የውጭ ኃይሎች መሣሪያ ሆኖ የሚመጣውን መጠንቀቅ አለብን፡፡ በእነዚህ ምክንያቶች ተቋሞቻችን እንዲፈርሱ እየተደረገ ነው፡፡ ባለሥልጣናት መጠንቀቅ አለባቸው፡፡ ይህም ሲባል ግን ለአገር የሚበጁ ኢትዮጵያውያን አሉ፡፡
ሪፖርተር፡– በዚህ አካሄድ ታዲያ የት ነው የሚደረሰው?
ደምስ (ዶ/ር)፡– የትም አንደርስም፡፡ ፖለቲከኞች መዘናጋት የለባቸውም፡፡ ይኼ አካሄዳችን እውነተኛውን ችግራችንን እንዳናይ በማድረግ ነገ ገንፍሎ በሚወጣ ጥያቄና ብሶት ሳቢያ፣ አሁን እየተገነባ ያለውም ነገር መልሶ እንዳይጠፋ ነው የምሠጋው፡፡ ካልተጠነቅቅ መድረሻችን ወደዚያ ስለሚሆን ነው የምፈራው፡፡ ገዥውም ተቃዋሚ ፖለቲከኞችም የሚሠሩት ምን እንደሆነ ሁሉም ያውቃል፡፡ እንኳንና ዛሬ በፊትም መሸወድ ከባድ ነበር፡፡ ፖለቲከኞች ሊገባቸው ይገባል፡፡ መንቃት አለባቸው፡፡ ስለዴሞክራሲ በየቦታው መደስኮርና ማነብነብ ችግር አይፈታም፡፡ ለውጥ አያመጣም፡፡ መልዕክቴ ኢኮኖሚው ላይ ትኩረት ይደረግ፣ ይሠራበት የሚል ነው፡፡ ዓመታት የፈጀውን ግንባታ ለመናድ ጥቂት ደቂቃዎች ይበቃሉ፡፡ ኢኮኖሚው ላይ መሥራትና ለውጥ ማምጣት መቻል ነው ለጥያቄዎች መልስ ለመስጠት የሚያስችለው፡፡ ኢኮኖሚው ተዘንግቷል፡፡ ዴሞክራሲ ለአሜሪካም ቢሆን የታይታ እንደሆነ አሁን በግልጽ እያየን ነው፡፡ አሜሪካ ምን ያህል ጨቋኝ እንደሆነች፣ እነ አውስትራሊያ በምን አግባብ እንደተመሠረቱ፣ ወዘተ. ለመማር የሚያበቁ ማሳያዎች አሉን፡፡ መጠንቀቅ አለብን፡፡ ዴሞክራቲክ ኮንጎ ለዓለም የሚበቃ ሀብት ያላት አገር ነች፡፡ ምንም ሳይሠሩ የተፈጥሮ ሀብታቸውን በመሸጥ ብቻ ለአራት ሺሕ ዓመታት መኖር የሚስችላቸው ሀብት ተፈጥሮ ለግሷቸዋል፡፡ ዜጎቿ ተንደላቀው መኖር የሚስያስችላቸው ሀብት በአገራቸው እያለ፣ 78 በመቶ የኮንጎ ሕዝብ ከድህነት በታች እየኖረ ነው፡፡ ወታደር ሳይቀር ለምኖ የሚበላት አገር ሆኗል፡፡ ይኼንን ነው መፍራት ያለብን፡፡ የኮንጎን የማያልቅ ሀብት የውጮቹ የተቆጣጠሩት እኮ በጥቂት ጥቅም አደሮች በኩል ነው፡፡ ካልጠነቀቅን ኢትዮጵያ የኮንጎ ዕጣ ፈንታ ሊደርሳት ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ ኢትዮጵያዊ አገር ወዳድና ለነፃነቱ ሲል በድህነት መኖርን የሚመርጥ ሕዝብ በመሆኑ፣ አገሩን ለባዕዳን እንዲህ እንደ ኮንጎ አሳልፎ ይሰጣል የሚል ግምት ግን የለኝም፡፡ የሚታየው ነገር ግን ጥንቃቄ ይፈልጋል፡፡ በምንሠራው ሁሉ በገዛ አገራቸው ኢትዮጵያውያን ቅድሚያውን ይዘው፣ ራሳቸው እየመሩ ራሳቸው ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ሥራ ማስቀደሙ ነው የሚበጀበው፡፡ ሀብታችንን በእንዲህ ያለው ሁኔታ ላይ ብናፈሰው ነው ለህልውናችን ዋስትና የሚሰጠን፡፡