ለከተሞች ውበትን ከሚያጎናፀፉ የመሠረተ ልማት ሥራዎችና ተግባራት መካከል የዋና ዋና አውራ ጎዳናዎችን በአረንጓዴ ልማት የማስዋብ ሥራ ሊጠቀስ ይችላል፡፡ በመንገድ አካፋዮች መካከል ያሉ ክፍተቶችን ተጠቅሞ አበቦችን መትከልና የማስዋቢያ ግንባታዎችን ማከናወን ዓይን የሚሞላ፣ መንፈስ የሚያድስ ተግባር ነው፡፡
ለዚህ ዋቢያችን፣ ከቦሌ እስከ መስቀል አደባባይ ድረስ ባለው 4.12 ኪሎ ሜትር መንገድ አካፋይ ላይ የምናየው የማስዋብ ሥራ ነው፡፡ ጅምሩ ሥራ አካባቢውን ምን ያህል እንደለወጠው ማየት ይቻላል፡፡
የቦሌ መንገድ እንደአሁኑ ተስፋፍቶ ከመሠራቱ በፊት፣ የመንገዱን አካፋይ ቦታዎች በመጠቀም ለማስዋብ ሲደረጉ የቆዩ ጥረቶች ዛሬ ላይ ከሚታየው ገጽታ አኳያ የሚወዳደሩ አይደሉም፡፡
ከዚህ ቀደም አካፋይ የመንገዱን ክፍሎች ለማስዋብ በተለያየ ቅርጽ ተስተካክለው የተዘጋጁ የብረት ውጤቶችን እንደ አጥር በመትከልና በአካፋዩ የተተከሉትን ዕፀዋት ለመንከባከብ ሙከራዎች ተደርገዋል፡፡ በየጊዜው የብረትና የአርማታ አጥር ቢተከልም በየጊዜው ሲተከልና ሲነቀል ቆይቷል፡፡ የተተከለው አጥርም ከአጥርነት የዘለለ ትርጉም አልነበረውም፡፡
እንደውም ብረቱ አልበቃ ብሎ የሰንሰለት ማገጃ ተገጥሞ መንገዱን ለማስዋብ ተሞክሮም ነበር፡፡ ይህ ሥራ አንድ አስገራሚ ነገርም ነበረው፡፡ መንገዱን ለማጠር የሚኮናተሩ አካላት በጨረታ ስም በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ወጥቶታባቸው ሲሠሩ እንደነበር ሲታወስ ነው፡፡ መንገዱን ለመሥራት የወጣውን ወጪ የማይተናነስ ገንዘብ ለአጥር ሲውል ታዝበናል፡፡ በብረት ለማጠር በየጊዜው የተበላው ገንዘብም ዛሬ በቦሌ መንገድ እንደምናየው ዓይነት ማራኪ ሥራዎችን በመንገዶቻችን አካፋዮች ሁሉ ሊያሠራ ይችል እንደነበር መገመት አይከብድም፡፡
አዲስና ከቀደሙት የተሻለና ወጪ ቆጣቢ ሥራ እያየን ነው፡፡ የማስዋብ ሥራው ደረጃ በደረጃ እየተሠራና እያማረ፣ የተተከሉት አበባዎችም በብዛት እየፈኩና ውበታቸውን እያሳዩ ነው፡፡ በጥቅሉ ስናየው በተወሰኑ ወራት ውስጥ ያየነው ለውጥ ከተማዋን እንዴት በቀላሉ ማስዋብ እንደሚቻል ትምህርት የሚሰጥ ነው፡፡
የሚታየውን ዓይነ ግቡ ሥራ አለማድነቅ አመል ካልሆነብን በቀር፣ በቦሌ ጎዳና የፈኩት አበቦች ወደ ከተማዋ ለሚገባውም ለሚውጣውም ተጓዥ፣ የአገር ውስጥና የውጭ ዜጋ የሚሰጡትን ስሜት እየተመለከትን ነው፡፡ ከዚህ የተሻለ ማስዋብ እስኪቻል ድረስ በወራት ልዩነት ያየነው ግሩም ሥራ ነው፡፡ በቦሌ ጎዳና የምናየውን ለውጥ በሌሎች የከተማችን ጎዳናዎችም ማየትን እንናፍቃለን፡፡ ይህ ከማድረግ የሚይዘን ምን ነገር ይኖር ይሆን?
የቦሌውን የማስዋብ ተግባር ለየት የሚያደርገው ሌላው ገጽታ፣ ሥራው የአንድ ሰሞን ሞቅታ እንደማይሆን የሚያስረዱ ነገሮችን መኖራቸው ነው፡፡ ዘወትር ክትትል የሚደረግበት በመሆኑ፣ ተጨማሪ የማስዋቢያ ሥራዎችን እየታከሉበትና በየጊዜው እየተሻሻለ ዛሬ ከተደመምንበት በላይ ሊዋብ እንደሚችል እንገምታን፡፡
ከቦሌ እስከ መስቀል አደባባይ ባለው መንገድ የተተከሉት አበቦች ካላቸው የተፈጥሮ ውበት በተጨማሪ፣ በምሽት ደምቀው የበለጠ የሚያደምቃቸውን አጃቢ አግኝተዋል፡፡ የተለያዩ ቀለማትን የሚፈነጥቁ መብራቶች ከመንገዱ ግራና ቀኝ ተሰቅለዋል፡፡ የቦሌ መንገድ ቀን ወጥቶለታል፡፡
በተለይ ከአውሮፕላን ወርዶ አዲስ አበባን ለመርገጥ የመጀመርያው ለሆነ የውጭ ዜጋ ብቻም ሳይሆን፣ ለአገሬውም ጭምር ሸገርን በጥሩ ውበቷና መልካም ገጽታዋ ማየት እንዲችል ያነሳሳዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እንዳመለከቱትም፣ በዚህ ጉዳይ ላይ እየተሠራ ያለው ሥራ አዲስ አበባን በምሽት የሚረግጣት ሰው ከሚቀበለው የተጨላለመ የከተማ ገጽታ በጥቂቱም ቢሆን የተፍካካ ነገር እንዲመለከት የሚያስችለው ስለሚሆን፣ በመጀመርያ የሚያየው የከተማዋ ክፍል ስለኢትዮጵያ በሚኖረው ዕይታ ላይ መልካም ተፅዕኖ እንዲያርፍበትና በጥሩ ጎኗ እንዲያስባት የማድረግ ሥነ ልቦናዊ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡ ኢትዮጵያ የምትሸጠው በቦሌ መንገድ ነውና፡፡ ጠቅላዩ ትክክል ናቸው፡፡ የቦሌን መንገድ ለማስዋብ የታየው ትጋት በሌሎች መንገዶችና በየአካባቢያችንም ቢተገበር የመዲናችንን ገጽታ በአጭር ጊዜ ውስጥ በበጎ ጎኑ ለመለወጥ ያስችለናል፡፡
ክፋቱ ይህንን የመሰለ ሥራ በመጠጥ የደነዘዙ፣ በአግባቡ የማሽከርከር ብቃት የሌላቸው አሽከርካሪዎች በየዕለቱ እየገጩ የተለፋበትን ሥራ መና ሲያደርጉት ማየቱ ነው፡፡ ይህ ያሳዝናል፡፡ እንዲህ ያሉቱ ሞገደኛ አሽከርካሪዎች ለሚያደርሱት ጥፋትና አደጋ ይጠየቁበት ይሆን? ቢቻል የጠፋውን ንብረት በቶሎ መልሶ ለመገንባት አስፈላጊውን ክፍያ እንዲከፍሉ ከማስገደድ ባሻገር፣ አጥፊዎች ላደረሱት ጉዳት ማካካሻ ሌላ መንገድ ላይ እንዲሠሩ ቢገደዱ ይበጃል እላለሁ፡፡
ከልብ የሚሠራ እንዲህም መሥራት እንደሚቻለው አይተናል፡፡ የተሻለና የበለጠ ለመሥራት መጣር የበለጠ ያስመሰግናል፡፡ መሥራት ባንችል ግን የተሠራውን እንንከባከብ፡፡ ይህም ባይሆንልን አናበላሸው፡፡ ከአደጋ መጠበቅ የሁላችንም ኃላፊነት ይሁን፡፡