Tuesday, November 29, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናታክስ አጭበርብሮ ክስ እንዲቋረጥ የሚቀርብ ጥያቄ የሕግ መሠረት እንደሌለው ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ...

  ታክስ አጭበርብሮ ክስ እንዲቋረጥ የሚቀርብ ጥያቄ የሕግ መሠረት እንደሌለው ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አስታወቀ

  ቀን:

  በሕገወጥ መንገድ ሐሰተኛ ደረሰኝ በመጠቀምና በታክስ ማጭበርበር የተከሰሱ ተጠርጣሪዎችን ክስ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ሆነ ሌላ አካል እንዲቋረጥ የሚጠይቅበትም ሆነ የሚያስገድድበት የሕግ መሠረት እንደሌለ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አስታወቀ፡፡

  የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ይህንን ያስታወቀው፣ በሺዎች የሚቆጠሩ የአዲስ አበባ ከተማ ነጋዴዎች በሕገወጥ መንገድ ሐሰተኛ ደረሰኝ በመቁረጥ እንዲሁም ከግብርና ከታክስ ማጭበርበር ጋር በተያያዘ የተመሠረተባቸውን ክስ እንዲቋረጥላቸው የከተማ አስተዳደሩ መጠየቁን እንደ ሕጋዊ አሠራርና ሕጋዊ መሠረት ያለው አድርገው ያቀረቡትን ወቀሳና አቤቱታ አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ ነው፡፡

  የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከ1,900 በላይ የሚሆኑ ሐሰተኛ ደረሰኝ በመቁረጥ፣ ግብርና ታክስ በማጭበርበር ተጠርጥረው የተከሰሱ ነጋዴዎችን፣ ስህተታቸውን አርመውና ያለባቸውንም የመንግሥት ዕዳ ከፍለው የለውጡ አጋዥ እንደሚሆኑ በመግለጽ ክሳቸው እንዲቋረጥ በመጠየቁ፣ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግም ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ በማስገባት ክሳቸው እንዲቋረጥ ማድረጉን የተቋሙ ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ዝናቡ ቱኑ ገልጸዋል፡፡ ዓቃቤ ሕግ ክሳቸው እንዲቋረጥ ያደረገው ተጠርጥረው የተከሰሱትን ሙሉ በሙሉ ሳይሆን፣ ሐሰተኛ ደረሰኝ የቆረጡትንና ተደራራቢ ወንጀሎች ያሉባቸውን በማስቀረት መለስተኛ የወንጀል ባህሪ ላይ በመሳተፍ የተጠረጠሩትን ብቻ መሆኑንም አክለዋል፡፡

  አስተዳደሩ ከሦስት ወራት ቆይታ በኋላ ከ3,000 በላይ የሚሆኑ ግብር ከፋይ ነጋዴዎች በታክስ ማጭበርበር ተጠርጥረው ክስ ተመሥርቶባቸው እያለ ክሳቸው እንዲቋረጥላቸው መጠየቁን ያስታወሱት አቶ ዝናቡ፣ ዓቃቤ ሕግ የመጀመርያውን ጥያቄ ተቀብሎ ያስተናገደው ተጠርጣሪዎቹ ከድርጊታቸው ተቆጥበው ሕግንና ሕግን ብቻ ተከትለው በመሥራት የተጀመረውን አገራዊ ሪፎርም ያግዛሉ ከሚል እንጂ፣ በተደጋጋሚ ጥፋት ሲፈጽሙ ተመሳሳይ ምሕረት ይደረግላቸዋል በሚል አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡

  አስተዳደሩ ክሳቸው እንዲቋረጥላቸው ሲጠይቅ፣ ከቀድሞዎቹ ጋር በተመሳሳይ ወንጀል የተጠረጠሩ መሆናቸውን ከመጠቆም ባለፈ፣ ቀደም ብለው ከተጠረጠሩት ጋር አብረው ተጠርጥረው የነበሩና የተለያየ ማስረጃ ሲያጠናቅር ወይም ሌላ ምክንያት እንኳን በደብዳቤው ላይ አለመግለጹን አክለዋል፡፡ ‹‹የዚህ ዓይነቱ አሠራር የሕግ መሠረት የለውም፤›› ያሉት ዳይሬክተሩ የሕግ የበላይነትን ከማስከበርና የወንጀል ፍትሕ አስተዳደርን ከማስቀጠል አንፃር የራሱ የሆነ ችግር ሊያስከትል ስለሚችል፣ ከዚህ ዓይነት አካሄድ መቆጠቡ የተሻለ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ አንዳንድ ነጋዴዎች ከግንዛቤ ማነስ ወይም መረጃ ከማጣት የተነሳ ሕገወጥ እንቅስቃሴዎችን እንደ ሕጋዊ በመቁጠር፣ ግዴታቸውን ሳያከብሩ መብታቸው እንዲከበር የሚያቀርቡት አቤቱታ የሕግ መሠረት አንደሌለው ልብ ሊሉ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

  ሕገወጥ ንግድን፣ ሐሰተኛ ደረሰኝ መቁረጥን፣ ግብርና ታክስ ማጭበርበርን የሚፀየፍ ነጋዴ እስከሚፈጠር ድረስ የሕግ ማስከበር ሒደቱ ስለሚቀጥል፣ ‹‹የሌላውን ነጋዴ ክስ አቋርጠው እኛን ከለከሉን›› የሚል አቤቱታ በራሱ ሕገወጥ ሆኖ ለመቀጠል ፍላጎት ያለ መሆኑን ስለሚያሳይ፣ ባለበት መቆም እንዳለበትና ሕጋዊ አሠራርን በመከተል መሥራት ብቻ የሚያዋጣ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ የተጠርጣሪዎቹም ጉዳይ ሕጉንና ሕጉን ብቻ ተከትሎ ውሳኔ የሚያገኝ መሆኑንም አክለዋል፡፡

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በችግር የተተበተበው የሲሚንቶ አቅርቦት

  ሲሚንቶን እንደ ግብዓት ተጠቅሞ ቤት ማደስ፣ መገንባት፣ የመቃብር ሐውልት...

  ‹‹የናይል ዓባይ መንፈስ›› በሜልቦርን

  አውስትራሊያ ስሟ ሲነሳ ቀድሞ የሚመጣው በተለይ በቀደመው ዘመን የባህር...

  ‹‹ልብሴን ለእህቴ››

  ለሰው ልጅ መኖር መሠረታዊ ፍላጎት ተብለው ከተዘረዘሩት ውስጥ ልብስ...

  የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች የምርመራ ውጤት እስከምን?

  በፍቅር አበበ የትምህርት ጥራትን፣ ውጤታማነትንና ሥነ ምግባርን ማረጋገጥ ዓላማ አድርጎ...