Monday, April 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢንቨስትመንት ኮሚሽን በተመድ ሪፖርት ላይ ቅሬታውን አሰማ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ኢቨስትመንት ኮሚሽን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ያወጣውን የኢንቨስትመንት መግለጫ ሪፖርት እንደማይቀበል በመግለጽ፣ ሪፖርቱ ሙሉውን እውነታ አላሳየም ሲል ቅሬታውን አሰማ፡፡

የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ተመስገን ጥላሁን ሰሞኑን ስለወጣው የተመድ ‹‹ኢንቨስትመንት ትሬንድስ ሞኒተር›› የተሰኘውና እ.ኤ.አ. የ2019 ዓመትን የቃኘው ሪፖርት፣ ‹‹እውነታ ቢኖረውም ሙሉ ገጽታውን አያሳይም፤›› በማለት ለሪፖርተር አስታውቀዋል፡፡

እንደ ምክትል ኮሚሽሩ ገለጻ ሪፖርቱ የሙሉ ዓመቱን መረጃ አላካተተም፡፡ ይኸውም ከዓመቱ መካከል የአንድ ሩብ ዓመት የኢንቨስትመንት መረጃን ያላካተተ የተመድ የንግድና የልማት ጉባዔ ያወጣው የኢንቨስትመንት ሪፖርት በመሆኑ፣ እንደማይቀበሉት አቶ ተመስገን ተናግረዋል፡፡ ይህም ይባል እንጂ እውነታ የለውም ማለት እንዳልሆነ አልሸሸጉም፡፡

ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ የተመዘገበው የኢንቨስትመንት ፍሰት እያሽቆለቆለ መምጣቱን ያስታወሱት አቶ ተመስገን፣ በኢትዮጵያ እየታየ ባለው የፀጥታ ችግርና በመሳሰሉት ምክንያቶች እየቀነሰ ቢመጣም፣ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ከ1.6 ቢሊዮን ዶላር ያላነሰ ካፒታል ያስመዘገቡ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች መኖራቸውን ምክትል ኮሚሽነሩ አስረድተዋል፡፡ ይህ የኮሚሽኑን የ70 በመቶ ዕቅድ እንደሚወክልም ገልጸዋል፡፡

ተመድ በሪፖርቱ ባለፉት ሦስት ዓመታት በተከታታይ እየቀነሰ የመጣው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መጠን ከ3.2 ቢሊዮን ዶላር ወደ 2.5 ቢሊዮን ዶላር መውረዱን አመላክቷል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2016 4.2 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በማስመዝገብ ኢትዮጵያ ከዓለም ትልልቅ መዳረሻዎች አንዷ እንደነበረች ቢመዘገብም፣ ከዚያን ጊዜ ወዲህ ግን እየወረደ የመጣው የውጭ ኢንቨስትመንት መጠን ከ1.7 ቢሊዮን ዶላር በላይ ቅናሽ እንዳሳየ አመላክቷል፡፡

የተመድ ሪፖርት በዓለም አቀፍ ደረጃ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መጠን እ.ኤ.አ. በ2019 ለውጥ ሳያሳይ ባለበት ቢቆይም፣ በበርካታ አገሮች ውስጥ የበለጠ ማሽቆልቆል እንደታየበት አስታውቋል፡፡ በኢትዮጵያ የታየው ቅናሽም ከአራት ዓመታት ወዲህ ከፍተኛው ሆኗል ብሏል፡፡

እ.ኤ.አ. ከ2016 በፊት ሲመዘገብ የቆየው የኢንቨስትመንት ፍሰት ከ2.2 ቢሊዮን ዶላር ያነሰ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ እያደገ በመምጣት እስካለፈው ዓመት ድረስ በቅናሽ ውስጥም ሆኖ በአፍሪካ ከፍተኛ የኢንቨስትመንት መጠን ዝርዝር ውስጥ የኢትዮጵያን ስም ያቆየው የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰት፣ እ.ኤ.አ. በ2019 ያስመዘገበው መጠን ወደ 2.5 ቢሊዮን ዶላር ዝቅ ማለቱ ከፍተኛ ቅናሽ ከሚባሉት ውስጥ እንዲካተት አድርጎታል፡፡

... 2016 4.2 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ከአፍሪካ ብቻም ሳይሆን፣ ከዓለም ታዳጊ አገሮች ተርታ ቀዳሚ የነበረችው ኢትዮጵያ፣ ... 2017 ወደ 3.5 ቢሊዮን ዶላር ዝቅ ያለ የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰት ማስተናገዷ አይዘነጋም፡፡ ምንም እንኳ ቅናሽ ቢታይበትም አሁንም ቢሆን በአፍሪካ ደረጃ ከፍተኛ ከሚባሉት ተርታ የሚመደብ ኢንቨስትመንት ፍሰት ስለመሆኑ ተመድ አመላክቶ ነበር፡፡

በአፍሪካ በተለይም በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ከፍተኛውን የኢንቨስትመንት ፍሰት በማስተናገድ ቀዳሚነቱን ይዛ የቆየችው ኢትዮጵያ ከግንባታው ዘርፍ ባሻገር፣ በአውቶሞቢል መገጣጠምና በአነስተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች መስክ የምታደርገው እንቅስቃሴ የቱርክና የቻይና ባለሀብቶችን በመሳብ ደረጃዋን አስጠብቃ መጓዝ እንድትችል እንዳበቋት ይታሰብ ነበር፡፡ የውጭ ኢንቨስትመንት ክምችቷ (በአንድ ዓመት ውስጥ ወይም በየሩብ ዓመቱ የሚገለጽ የወጪና የገቢ ኢንቨስመንት መጠንን ያመላክታል) 18 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደሚሆንም ተገምቶ ነበር፡፡

ይሁን እንጂ በተመድ የዓለም ኢንቨስትመንት ሪፖርት መሠረት፣ እ.ኤ.አ. በ2018 ወደ አፍሪካ ከመጣው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ውስጥ ያስመዘገበችው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ድርሻ 3.2 ቢሊዮን ዶላር ነው፡፡ ይህም ከአንጎላ፣ ከግብፅ፣ ከናይጄሪያና ከጋና በመከተል አምስተኛ ደረጃ በመያዝ ከፍተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት መዳረሻ እንደነበረች ይታወሳል፡፡ ይህ ሁሉ እ.ኤ.አ. በ2019 ወደ 2.5 ቢሊዮን ዶላር ወርዶ ከፍተኛውን ቅናሽ ካስመዘገቡ አገሮች ተርታ አሠልፏታል፡፡

ከዓለም የኢንቨስትመንት መዳረሻ አገሮች ተርታ በተሠለፈችበት አፍታ ከደረጃዋ እየተንሸራተተች የወጣችው ኢትዮጵያ፣ ካስመዘገበችው የ2.5 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት ውስጥ ከ60 በመቶ ያላነሰው በቻይና ኩባንያዎች አማካይነት የሚካሄዱ ፕሮጀክቶች የያዙት ድርሻ እንደሆነ በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡

በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ዋነኛ የውጭ ኢንቨስትመንት ምንጭ ከሆኑ አገሮች መካከል ቻይና ቀዳሚዋ ስትሆን፣ የአውሮፓ ኩባንያዎች በተለይም የኔዘርላንድስ ባለሀብቶች በሁለተኛነት፣ የሱዳን በሦስተኛነት እንደሚከተሉ የኮሚሽኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በአንድ ወቅት የቱርክ ኩባንያዎች በ2.5 ቢሊዮን ዶላር የኢንቨስትመንት ካፒታል ቀዳሚዎቹ እንደነበሩ አይዘነጋም፡፡

በሌላ በኩል መንግሥት በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት መስክ በመካከለኛው ጊዜ ውስጥ ከግሉ ዘርፍ ጋር በሽርክና የሚያስተዳድራቸው ላይ እንደሚያተኩር፣ በሒደትም ሙሉ ለሙሉ በግሉ ዘርፍ የሚመራ ዘርፍ እንዲሆን የማድረግ አቅጣጫ እንደሚከተል አስታውቋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ዘጠኝ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ወደ ሥራ እንደገቡ ሲገለጽ፣ በተለይም የጅማና የባህር ዳር ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ሙሉ በሙሉ የቻይና ኩባንያዎች መረከባቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች