Thursday, December 1, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  መንግሥት ዝምታውን ይስበር!

  የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ዕገታ ጉዳይ ሲነሳ የአንድ ክልል ወይም የሌላ፣ የአንድ ብሔር ወይም የሌላ፣ የአንድ ፆታ ወይም የሌላኛው ሆኖ አይደለም፡፡ ይህ እጅግ ነውረኛ የሆነ የዕገታ ድርጊት ሁሉንም የሰው ልጆች የሚመለከት የሰብዓዊ መብት ጉዳይ ነው፡፡ በሰብዓዊ ፍጡራን ላይ የተፈጸመ በደል ስለሆነ ሁላችንንም ሊቆረቁረን፣ ሊከፋን፣ ነግ በእኔ ሊያስብለንና በጋራ እንድናወግዘው አንድ ላይ ሊያቆመን የሚገባ ነው፡፡ አገርን ከሚያስተዳድረው መንግሥት ጀምሮ እስከ እያንዳንዱ ዜጋ ድረስ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር፣ ለአካላዊ ደኅንነትና በሕይወት ለመኖር መብቶች መቆርቆር ያስፈልጋል፡፡ ከደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ግጭት በመሸሽ ላይ ሳሉ ከሃምሳ ቀናት በፊት የታገቱት ተማሪዎች ጉዳይም፣ ለፖለቲካ ፍጆታ ሳይሆን በሰብዓዊ ርህራሔ ነው መታየት ያለበት፡፡ ከማንም በፊት ደግሞ መንግሥት ስለአጋቾቹ ማንነት፣ ታጋቾቹ ስላሉበት ሁኔታና ችግሩ ለምን ከቁጥጥሩ በላይ ሆኖ እነዚህ ሁሉ ቀናት በሰቆቃ እየታለፉ እንዳሉ ለሕዝብ ግልጽ ማድረግ ነበረበት፡፡ ይህ ባለመሆኑ ግን በመንግሥት ዝምታ የተሰላቸው ሕዝብ በነቂስ አደባባይ ወጥቶ ‹‹ልጆቻችን የታሉ?›› ብሎ እየጠየቀ ነው፡፡ የመንግሥት ግልጽነት በመጓደሉ ሕዝብ መያዣና መጨበጪያ ለሌላቸው መረጃዎች ተጋልጧል፡፡ በዚህም ምክንያት ሕዝብ በመንግሥት ላይ ያለው እምነት ተሸርሽሯል፡፡ ሌላው ቀርቶ የመገናኛ ብዙኃን ተገቢውን መረጃ በተገቢው ጊዜ እንዳይሰጡ፣ የተለመደው የመንግሥት ዝምታ እጅና እግራቸውን አስሯል፡፡ የመንግሥት ዝምታ ሕዝቡን ሥጋት ውስጥ በመክተቱ ፈጣን ምላሽ ያስፈልጋል፡፡

  የታገቱት ተማሪዎች ወላጆች የደረሰባቸው ሰቆቃ ከባድ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም መንግሥት አስለቅቄያቸዋለሁ ያላቸው ተማሪዎች የት ናቸው? በአጋቾች ዘንድ አሉ የተባሉትስ በምን ሁኔታ ላይ ናቸው? ወላጆች መንግሥት ልጆቻቸው ተለቀዋል ብሎ ከተናገረ በኋላ የውኃ ሽታ ሆኖ መቅረቱ በጣም አሳዝኗቸዋል፡፡ በሌላ በኩል በመንግሥት የተለያዩ አካላት ጉዳዩን በተመለከተ የሚወጡ መረጃዎች እርስ በርሳቸው የማይጣጣሙ፣ ይመለከታቸዋል የተባሉ አካላትም ወደ ሌላው የመግፋትና አይመለከተኝም የማለት አባዜ መኖሩን፣ የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡ ተለቀዋል ስለተባሉት ተማሪዎች መንግሥት ማረጋገጫ ባለማቅረቡም ሕዝብ በመላምት እንዲያስብ ማድረጉን፣ ይህም በሕዝብና በመንግሥት መካከል ጥርጣሬና አለመተማመን እንዲፈጠር ማድረጉን ገልጿል፡፡ እዚህ ላይ ልብ መባል ያለበት መንግሥትን የሚያህል ግዙፍ ተቋም በዝምታ ሲሸበብ፣ የማኅበራዊ ትስስር ገጾች መላምቶችና ሐሰተኛ መረጃዎች ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያደርሱ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ወላጆችም ሆኑ የወገኖቻቸው ጉዳይ ያሳሰባቸው ወገኖች ግራ ተጋብተዋል፡፡ ጉዳዩ ይመለከተኛል የሚሉ ወገኖችም በተናጠልም ሆነ በመሰባሰብ መንግሥት ዝምታውን ይስበር እያሉ ነው፡፡ የእነዚህ ሁሉ ወገኖች ጥያቄ እየጎረፈ ‹ጆሮ ዳባ ልበስ› ማለት አይቻልም፡፡

  የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ሴኔት፣ አስተዳደር፣ የተማሪዎች ማኅበር፣ የደምቢዶሎ ከተማ፣ ወረዳው፣ ዞኑ፣ የኦሮሚያ ክልል፣ ወዘተ ምን እያደረጉ ነው? ዩኒቨርሲቲው የጠፉበት ተማሪዎች የት ናቸው አይልም ወይ? በየደረጃው ያሉ የአስተዳደርና የፀጥታ መዋቅሮች ምን እየሠሩ ነው? ከማንም በፊት የተማሪዎቹ ጉዳይ ሊያሳስባቸው የሚገባው በአካባቢው ያሉትን ነው፡፡ ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲው ሲገቡ በሽር ጉድ ከመቀበል ጀምሮ አጠናቀው እስኪሰናበቱ ድረስ ኃላፊነት እንዳለባቸው ሲናገሩ ከርመው፣ ከመሀላቸው በዕገታ ምክንያት የተወሰኑት አድራሻቸው ሲጠፋ እንዴት ዝም ይባላል? የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎችን የሚቆጣጠረው መንግሥታዊ አካልም ሆነ የፌዴራል መንግሥት ዝምታም ያስገርማል፡፡ ተማሪዎችን በአጀብ ሲቀበል በመገናኛ ብዙኃን ያስነገረ ዩኒቨርሲቲ፣ ተማሪዎቹ የት እንዳሉም መናገር አለበት፡፡ ካልሆነም አፋልጉኝ ማለት ይኖርበታል፡፡ እንዲያው በደፈናው ዝምታው ራሱ ጩኸት ይመስል ያደናቁራል፡፡ ይህ አልበቃ ብሎ ደግሞ በተለያዩ አካላት የተምታቱ መረጃዎችን መልቀቅም ያደናግራል፡፡ የዕገታ ወንጀል ውስብስብና ከፍተኛ ትዕግሥትና ብልኃት የሚፈልግ ቢሆንም፣ ሕዝብን መረጃ ነፍጎ የመላምቶችና የሐሰተኛ ወሬዎች መጫወቻ ማድረግ ግን አግባብ አይደለም፡፡ በፌዴራል መንግሥትና በክልል መንግሥታት መካከል ያለው ግንኙነት ችግር ያለበት ይመስል፣ ዝምታው ከመቼውም ጊዜ በላይ ሕዝብን እያበሳጨ ነው፡፡

  በዚህ ጊዜ ጥያቄ ከሚቀርብላቸው መካከል የሕዝብ ተወካዮችም ሆኑ የክልል ምክር ቤቶች ተመራጮች ምነው ድምፃቸው ጠፋ? በዚህ የከፋ ጊዜ ወጣ ብለው የታገቱት ተማሪዎች የት እንዳሉ አስፈጻሚው የመንግሥት አካል በምክር ቤቶች መጠየቅ እንዳለበት ረሱ? ወይስ ጉዳዩን እነሱም እንደ ተራ ነገር ተመለከቱት? ከአንዳንድ ሹማምንት እንደሚሰማው የታገቱ ተማሪዎች የሉም? ወይስ ለፖለቲካ ፍጆታ የሚሯሯጠው አደናቀፋቸው? የሕዝብ ተወካይ ነን ካሉ ግን አንድም ለመረጣቸው ሕዝብ ባለባቸው ኃላፊነት፣ በሌላ በኩልም ለህሊናቸው ተጠያቂነት ሲሉ የመንግሥትን ዝምታ መስበር ይጠበቅባቸው ነበር፡፡ እነሱ እውነት እንዲወጣና ሕጋዊ መፍትሔ እንዲፈለግ ተፅዕኖ መፍጠር ሲገባቸው፣ በዝምታ መዋጣቸው ያስተዛዝባል፡፡ ሌላው ቀርቶ በመገናኛ ብዙኃን አማካይነት ሕዝቡ የተጣራ መረጃ እንዲያገኝ መጎትጎት እየቻሉ፣ ድምፃቸው ሲጠፋ የህሊና ዕዳ እንዳለባቸው ሊያውቁት ይገባል፡፡ ይህ ጉዳይ በቀጥታ ከአካባቢው ተወክለው በየምክር ቤቶቹ የሚገኙትን ቢመለከትም፣ ሌሎች የምክር ቤቱ አባላት ዝምታም ያስተዛዝባል፡፡ ቢያንስ ቢያንስ ልጆቻቸው ታግተውባቸው በመገናኛ ብዙኃን እያለቀሱ ያሉ ወላጆችን ማሰብ ነበረባቸው፡፡ ይህ ለፖለቲካ ፍጆታ ተብሎ ሳይሆን በሰብዓዊነት የሚፈጸም ተግባር ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ሰብዓዊነት ሲጓደል ግን ያሳዝናል፡፡

  ለኢትዮጵያዊያን ፈፅሞ እንግዳና ነውረኛ የሆነው የተማሪዎች ዕገታ ብዙዎችን አስቆጥቷል፡፡ ለዕገታው የተሰጠው ትኩረት ከፍተኛ ነው ተብሎ በመንግሥት ባለሥልጣናት ቢነገርም፣ ሕዝቡን በምልዓት አደባባይ አስወጥቶ ‹‹ልጆቻችን የታሉ?›› ብሎ በቁጣ እንዲገነፍል አድርጎታል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አሳሳቢና አሳዛኝ ድርጊት ወደፊት ተስፋፍቶ በአገር ላይ መከራ እንዳያመጣ መጠንቀቅ ይበጃል፡፡ ሕግ ማስከበር ሲያቅት ጉልበተኛ እየተነሳ ሕፃናትን፣ አዋቂዎችን፣ አዛውንቶችንና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ማገት የዘወትር ተግባር ይሆናል፡፡ የሕግ የበላይነት ይከበር ተብሎ የሚለፈፈው ጉልበተኞች ያሻቸውን ነገር እንዳይፈጽሙ ነው፡፡ ሥርዓተ አልበኝነት ደግሞ የሕዝቡን ሕይወት ያመሰቃቅላል፡፡ በተጨማሪም የመንግሥት አሠራር ግልጽነት፣ ኃላፊነትና ተጠያቂነት የሚኖርበት የሕግ የበላይነት ሲኖር ነው፡፡ መንግሥት አሠራሩ ለሕዝብ ግልጽ መሆኑ የሚረጋገጠው መረጃን በአግባቡ ሲያስተላለፍ ነው፡፡ በሕዝብና በመንግሥት መካከል መተማመን የሚፈጠረው በዚህ መንገድ ኃላፊነቱን ሲወጣ ብቻ ነው፡፡ መንግሥት ለሕዝብ የሚሰጠው መረጃ ተዓማኒነት ሲጎድለውና የተድበሰበሰ ሲሆን፣ ሕዝብ ደግሞ ጀርባውን ይሰጠዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገዥው ፓርቲ ስብሰባዎች ሳይቀሩ በቀጥታ ሥርጭት ይተላለፋሉ ማለታቸው ይታወሳል፡፡ ይህ ቃል ግን በተግባር አልታየም፡፡ ይባስ ብሎም የደምቢዶሎ ተማሪዎች ከታገቱ ሃምሳ ቀናት አልፈው፣ ከዚህ ቀደም ከዕገታ ተለቀዋል የተባሉት የት እንደደረሱ በማይታወቅበትና የተምታቱ መረጃዎች ሕዝቡን በአጠቃላይ ውዥንብር ውስጥ በከተቱበት በዚህ ጊዜ፣ መንግሥት ሆይ ዝምታህን ሰብረህ ኃላፊነትህን ተወጣ ማለት የግድ ነው!

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  አዋሽ ባንክ ለሁሉም ኅብረተሰብ የብድር አገልግሎት የሚያስገኙ ሁለት ክሬዲት ካርዶች ይፋ አደረገ

  አዋሽ ባንክ ለሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች በዘመናዊ መንገድ ብድር ማስገኘት...

  ባንኮች እንዲዋሀዱ እስከ ማስገደድ ሊገባ እንደሚችል ብሔራዊ ባንክ ጠቆመ

  በአሁኑ ወቅት የባንኮች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ችግር የሚሆንና የውጭ...

  ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ የሚጓዙ በርካታ ሰዎች ወደ ከተማዋ እንዳይገቡ በፖሊስ መከልከላቸውን ገለጹ

  ‹‹የኦሮሚያ ክልል መፍትሔ እንዲሰጥበት አሳውቀናል›› የአማራ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ‹‹ጉዳዩ...

  ‹‹ከገበሬው እስከ ሸማቹ ያለውን የንግድ ቅብብሎሽ አመቻቻለሁ›› ያለው ፐርፐዝ ብላክ ውጥኑ ከምን ደረሰ?

  ከመቼውም ጊዜ በላይ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ የሚሰማ አንድ...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  [በተቋሙ ሠራተኞች የተወከሉ አንድ ባልደረባ ሚኒስትሩን ለማነጋገር ቀጠሮ ይዘው ወደ ቢሯቸው ገቡ]

  ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም ሰላም ... ተቀመጥ! አመሠግናለሁ ክቡር ሚኒስትር!...

  የጉራጌ ዞን ጥያቄና የክላስተር አደረጃጀት የገጠመው ተቃውሞ

  መንግሥት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አካል የነበሩ ዞኖችንና...

  አዋሽ ባንክ ካፒታሉን ወደ 55 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ያስገደደው ምክንያት ምንድን ነው?

  ባለፈው ቅዳሜ ጠቅላላ ጉባዔውን ያካሄደው አዋሽ ባንክ የ43 ቢሊዮን...

  አቢሲኒያ ባንክ ካለፈው ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው ትርፍ በማግኘት አዲስ ታሪክ አስመዘገበ

  አቢሲኒያ ባንክ ከቀደሚ የሒሳብ ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው...

  የጉድለታችን ብዛቱ!

  ከፒያሳ ወደ ሜክሲኮ ልንጓዝ ነው። ጎዳናውን ትውስታ እየናጠው ሁለትና...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ለዘመኑ የማይመጥን አስተሳሰብ ዋጋ ያስከፍላል!

  በኳታር እየተከናወነ ያለው የዓለም ዋንጫ በእግር ኳስ ጨዋታ ውስጥ ያልተጠበቁ ማራኪ ቴክኒኮችንና ታክቲኮችን ከአስገራሚ ውጤቶች ጋር እያስኮመኮመ፣ ከዚህ ቀደም በነበረ ችሎታና ዝና ላይ ተመሥርቶ...

  መንግሥት ለአገር የሚጠቅሙ ምክረ ሐሳቦችን ያዳምጥ!

  በሕዝብ ድምፅ የተመረጠ መንግሥት ለሕዝብ የሚጠቅሙ ሐሳቦችን የማዳመጥ ኃላፊነት አለበት፡፡ ሥራውን ሲያከናውንም በግልጽነት፣ በተጠያቂነትና በኃላፊነት መርህ መመራት ይኖርበታል፡፡ እያንዳንዱ ዕርምጃው በሕግ ከተሰጠው ኃላፊነት አኳያ...

  የሰላም ስምምነቱ ተግባራዊ ይደረግ!

  የሰላም ስምምነቱ ‹‹ታጥቦ ጭቃ›› ሊሆን የሚችልባቸው ምልክቶች እየተስተዋሉ ነው፡፡ ሚሊዮኖችን ለዕልቂት፣ ለመፈናቀል፣ ለከፍተኛ ሰብዓዊ መብት ጥሰትና መሰል ሰቆቃዎች የዳረገው አውዳሚ ጦርነት በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት...