ከሰኔ 15 ግድያ ጋር በመጠርጠር በአዲስ አበባ የተያዙት ለለውጡ ሲባል እንዲለቀቁ መወሰኑን ገልጿል
ክልሎች ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ምክንያት 1,596 ተጠርጣሪዎችን ለሕግ ማቅረብ አልቻልኩም ብሏል
በርካታ ኢትዮጵያውያንን እያነጋገረና እያስጨነቀ የሚገኘውን የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መታገት አስመልክቶ ማብራሪያ እንዲሰጥ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተጠየቀው የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ፣ የታገቱ ተማሪዎች ጉዳይ ‹‹ተጣርቶ ቢገለጽ ጥሩ ነው፤›› የሚል ምላሽ ሰጠ።
የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አመራሮች ማክሰኞ ጥር 19 ቀን 2012 ዓ.ም. የስድስት ወራት፣ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርታቸውን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅት፣ በምዕራብ ወለጋ የሚገኘው የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መታገትን በተመለከተ ማብራሪያ እንዲሰጡ ከምክር ቤቱ በአባላቱ ጥያቄዎች ቀርበውላቸው ነበር።
ይህንንና ሌሎች ወንጀል ነክ ጉዳዮችን አስመልክቶ የምክር ቤቱ አባላት ላቀረቧቸው ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት በተቋሙ የተደራጁና ድንበር ተሸጋሪ ወንጀሎች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ ፀጋ፣ የታገቱት ተማሪዎችን በተመለከተ ምርመራ መጀመሩንና ይህ ጉዳይ ተጣርቶ ዝርዝር ሁኔታው ቢገለጽ የተሻለ እንደሚሆን አመልክተዋል።
ይህንን የዕገታ ድርጊት አስመልክቶ በተለያየ መንገድ ከሚነገረው ውጪ ምርመራ ተደርጎ ከተጣራ በኋላ ቢገለጽ ጥሩ ነው ብለው እንደ ባለሙያ እንደሚያምኑ፣ አቶ ፍቃዱ ለምክር ቤቱ ምላሽ ሰጥተዋል። ‹‹እነ ማን ናቸው የታገቱት? አጋቾቹ ማን ናቸው፣ እንዴትና መቼ ነው የታገቱት? ስንት ናቸው? የሚለው ጉዳይ ተጣርቶ ለሕዝብ ቢገለጽ ነው ጥሩ የሚሆነው፤›› ሲሉም አክለዋል።
በአሁኑ ወቅትም የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ፣ የኦሮሚያ ክልልና የፌደራል ፖሊስ በጋራ ሆነው ያዋቀሩት ቡድን ምርመራ መጀመሩን አስረድተዋል።
በዩኒቨርሲቲዎች በአጠቃላይ እየተስተዋለ የሚገኘውን የተማሪዎች ሕይወት እየቀጠፈ የሚገኝ ግጭትና የወንጀል ድርጊት በመከላከልና በወንጀል ድርጊቶቹ የተሳተፉትን በሕግ እንዲጠየቁ በማድረግ ረገድ፣ ተቋሙ ያከናወናቸውን ተግባራት እንዲያብራራ ሌላው ከምክር ቤቱ አባላት የተነሳ ጉዳይ ነበር።
አቶ ፍቃዱ በሰጡት ምላሽ በዩኒቨርሲቲዎች የተፈጸሙ ወንጀሎችን በተመለከተ ዓቃቤ ሕግ በአሁኑ ወቅት ምርመራውን አጠናቆ መዝገቦቹን እየገመገመ እንደሚገኝ ገልጸዋል። ነገር ግን በዩኒቨርሲቲዎች በጠረራ ፀሐይ ተማሪዎች ተገድለው ሳለ ወንጀል ፈጻሚዎችን ለይቶ ተጠያቂ እንዲሆኑ በማድረግ ረገድ ተግዳሮት እንደገጠማቸው ጠቁመዋል።
የዓቃቤ ሕግ የምርመራ ሥልት በአመዛኙ በሰው ምስክር ላይ የተመሠረተ መሆኑ፣ ከዚህ ቢያልፍ ኮምፒውተሮችንና አንዳንድ የኤሌክትሮኒክስ ቁሶች ላይ የሚደረግ ምርመራን ጥቅም ላይ የማዋል አቅም ብቻ ያለው በመሆኑ ዋነኛ ወንጀል ጠንሳሾችንና ፈጻሚዎችን በቁጥጥር ሥር አውሎ ተጠያቂ የማድረግ ውስንነት እንዳለበት አስረድተዋል።
ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. በአማራ ክልል አመራሮችና በአዲስ አበባ ደግሞ በጦር ጄኔራሎች ላይ ከተፈጸመው ግድያ ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው በአዲስ አበባ ከተማ ቁጥጥር ሥር ውለው የነበሩ ተጠርጣሪዎች፣ እንዲለቀቁ የተደረገበት ምክንያት እንዲብራራላቸውም የምክር ቤቱ አባላት ባቀረቡት ጠቅለል ያለ ጥያቄ ምላሽ ጠይቀዋል።
በዚህም ጉዳይ ላይም ምላሽ የሰጡት አቶ ፍቃዱ ሲሆኑ፣ ከዚህ ግድያ ጋር ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር የነበሩት የተለቀቁበት ምክንያት በቂ ማስረጃ ስላልነበረ አይደለም ብለዋል። እነዚህ ተጠርጣሪዎች በወቅቱ በነበረው የፀረ ሽብር ወንጀል ሊከሰሱ ይችሉ እንደነበርና በዚህ የወንጀል ድርጊት እንዲጠየቁ ለማድረግ በቂ ማስረጃ ተሰብስቦ እንደነበር ገልጸዋል።
ነገር ግን በወቅቱ የፀረ ሽብር አዋጁን የማሻሻል ሥራ እየተሠራ በመሆኑ፣ እንዲሁም ተጠርጣሪዎቹ በዚህ የወንጀል አዋጅ ሊከሰሱ አይገባም የሚል ቅሬታ ከማኅበረሰቡ በመነሳቱ ለውጡን እንዳያጠለሽ ሲባል እንዲቀር መደረጉን ተናግረዋል።
‹‹አዲስ አበባ ላይ ወንጀል ስላልነበረ ሳይሆን፣ ለውጡን ማስቀጠሉና የሕዝብን ድምፅ መስማቱ ተገቢ ነው ተብሎ በአመራሩ ስለታመነበት ክስ እንዳይመሠረት ተወስኗል። በዚህም ተይዘው የነበሩ እንዲለቀቁ ተደርጓል፤›› ብለዋል።
ዋና ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ ለምክር ቤቱ ባቀረቡት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት፣ በተለያዩ ወንጀሎች ለምርመራና ለክስ ከሚፈለጉ ሦስት ሺሕ ተጠርጣሪዎች ውስጥ 1,596 ገደማ የሚሆኑትን ለሕግ ማቅረብ እንዳልተቻለ ገልጸዋል።
የተገልጋይ አመለካከትና አመኔታ ልኬት የተደረገ መሆኑን፣ በዚህም በተቋሙ ላይ የተገልጋይ አመለካከትና አመኔታ 71 በመቶ እንደሆነም በሪፖርታቸው አቅርበዋል። እንዲሁም የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ፣ የወንጀል ሕጉን ለማስጠበቅና ውጤታማ ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎች ተሠርተዋል ያሉት ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ፣ የወንጀል መከላከል ሥራን ውጤታማ ለማድረግ የወንጀል መከላከል ስትራቴጂ መዘጋጀቱንም ነው ያስታወቁት።
የሁሉም የወንጀል ዓይነቶችን የማጥራት ምጣኔ 100 በመቶ ለማድረግ ታቅዶ፣ የምርመራ ሒደታቸው የተጠናቀቁ 27,959 የክስ መዝገቦች ቀርበው 27,684 መዛግብት ውሳኔ እንደተሰጠባቸው፣ 175 መዛግብት ደግሞ በሒደት ላይ እንደሚገኙ፣ በዚህም የማጥራት ምጣኔው 99.01 በመቶ ደርሷል ብለዋል።
ውሳኔ ካገኙት ውስጥ 19,238 መዛግብት ክስ የተመሠረተባቸው መሆኑን፣ 8,446 በተለያዩ ሕጋዊ ምክንያቶች የተዘጉ መሆናቸውንም ነው አቶ ብርሃኑ ያብራሩት። የማስቀጣት ምጣኔን በአማካይ 96.1 በመቶ ለማድረስ ታቅዶ 94.02 ተፈጽሟል ያሉት አቶ ብርሃኑ፣ በዚህም 32,949 መዛግብት በክርክር ሒደት የነበሩ መሆኑን፣ 7,335 መዛግብት ውሳኔ ሲያገኙ፣ ከእነዚህ ውስጥ 6,897 መዛግብት የጥፋተኝነት፣ 438 መዛግብት ደግሞ ነፃ ውሳኔ ያገኙ ናቸው ብለዋል።
ልዩ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን አፈጻጸም ለማሻሻል ባለፈው በጀት ዓመት፣ የተጀመሩና በበጀት ዓመቱ አዲስ የተከፈቱ ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና የሙስና ወንጀሎች ትኩረት በመስጠት ሲሠራ መቆየቱንም አብራርተዋል።
በተለያዩ ወንጀሎች ለምርመራና ለክስ ከሚፈለጉ ሦስት ሺሕ ተጠርጣሪዎች ውስጥ፣ ለሕግ ማቅረብ የተቻለው 1,404 የሚሆኑትን ነው ብለዋል። ከተጠርጣሪዎቹ መካከል 1,600 ገደማ የሚሆኑትን ለሕጉ ማቅረብ አልተቻልም ያሉት ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ፣ ሕግ ፊት እንዲቀርቡ ከሚፈለጉት ተጠርጣሪዎች መካከል በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 827፣ በደቡብ ክልል 655፣ በኦሮሚያ ክልል 50፣ በአማራ ክልል 18፣ በትግራይ ክልል አራት፣ በሶማሌ ክልል 33፣ እንዲሁም በአዲስ አበባ ዘጠኝ ተጠርጣሪዎች መሆናቸውንና ተጠርጣሪዎቹ ላይ ክስ ተመሥርቶባቸው እንዳልቀረቡ በሪፖርታቸው አመልክተዋል።
ተጠርጣሪዎቹን ለሕግ ማቅረብ ያልተቻለው በተለይ ክልሎች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት ባለመቻላቸው እንደሆነ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ተናግረዋል። ይኼንን ጉዳይ በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያ የሰጡት አቶ ፍቃዱ በበኩላቸው፣ በዚህ ጉዳይ ላይ ፖለቲካዊ መፍትሔ ካልተሰጠና ምክር ቤቱም ካላገዘ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግም ሆነ ፌዴራል ፖሊስ ምንም ሊያደርጉ አይችሉም ብለዋል።
እነዚህ ተቋማት የክልል የፀጥታ ተቋማትን ትብብር ይጠይቃሉ እንጂ፣ እነሱን ተክተው እንደማይሠሩ በምክንያትነት ተናግረዋል። ተጠርጣሪዎቹ ተለይተውና እንዲሁም የት እንደሚገኙ ጭምር እየታወቀ፣ የክልል መንግሥታት ለሕግ እንዲያቀርቡ ቢጠየቁም ፈቃደኛ አለመሆናቸውን አቶ ፍቃዱ ገልጸዋል።
‹‹አንዳንድ ክልሎች በወንጀል የሚፈለጉ ናቸው የተባሉ ግለሰቦችን ሹመት ሲሰጧቸው ሁሉ እያየን ነው፡፡ ተጠርጣሪ ሆነው የመንግሥት ደመወዝ እየበሉ ነው፤›› ሲሉም ያለውን ተግዳሮት ገልጸዋል።
ምክር ቤቱ አንዳንድ የሪፎርም ሥራዎችን ያበረታታ ቢሆንም፣ ሕግ በማስከበር ረገድ ተቋሙ ጉድለት እንዳለበት በመግለጽ መስተካከል እንደሚገባው አሳስቧል።