54 አብራሪዎችን አስመረቀ
የተመሠረተበትን 20ኛ ዓመት በማክበር የሚገኘው አቢሲኒያ የበረራ አገልግሎትና አቪዬሽን አካዳሚ፣ በአዲስ አበባ ለዋና መሥሪያ ቤትነትና ለፓይለት ማሠልጠኛ ተቋሙ የሚጠቀምበት ሕንፃ ለመገንባት በዝግጅት ላይ እንደሆነ አስታወቀ፡፡
የአቢሲኒያ የበረራ አገልግሎትና አቪዬሽን አካዳሚ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ካፒቴን ሰለሞን ግዛው ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ኩባንያው በዋና መሥሪያ ቤትነት የሚጠቀምበትን ባለ አሥራ አንድ ፎቅ ሕንፃ ቦሌ አካባቢ በሚገኘው የድርጅቱ ንብረት በሆነ 500 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ለመገንባት ዝግጅት በማድረግ ላይ ነው፡፡ የሕንፃው አጠቃላይ ወጪ ገና ተሰልቶ ያላለቀ መሆኑን የገለጹት ካፒቴን ሰለሞን፣ የሕንፃውን ንድፍና ግንባታ ሥራ የሚያከናውን ተቋራጭ ለመቅጠር በቅርቡ ጨረታ እንደሚወጣ ተናግረዋል፡፡
በ1992 ዓ.ም. የተመሠረተው አቢሲኒያ የበረራ አገልግሎት የቻርተር በረራ አገልግሎት በመስጠት ቀዳሚ የግል አየር መንገድ ሲሆን፣ በ2000 ዓ.ም. በኢትዮጵያ የመጀመርያው የግል ፓይለት ማሠልጠኛ ተቋም መሥርቷል፡፡
ካፒቴን ሰለሞን አቢሲኒያ የበረራ አገልግሎት ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት የበኩሉን አስተዋጽኦ ሲያደርግ መቆየቱንና ለተለያዩ አገሮች መሪዎች፣ ለሚኒስትሮች፣ ለታዋቂ የፊልም ተዋንያን፣ ለሙዚቀኞች፣ ለቱሪስቶችና ባለሀብቶች የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡ ከኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣንና ከኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት የተለያዩ ድጋፍ ሲደረግለት የቆየ ቢሆንም፣ የአውሮፕላን ጥገና ሃንጋር በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ለመገንባት ላለፉት 20 ዓመታት ያደረገው ጥረት ሊሳካለት እንዳልቻለ አስረድተዋል፡፡ ‹‹የጥገና ሃንጋር ለመገንባት አቅሙና ችሎታው ቢኖረንም፣ ለ20 ዓመታት ያቀረብነው የግንባታ ቦታ ጥያቄ አጥጋቢ ምላሽ ባለማግኘቱ በሥራችን ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥሯል፡፡ በዚህ ምክንያት አዲስ አበባ መጠገን የምንችላቸውን አውሮፕላኖች ናይሮቢ እየወሰድን ለጥገና በውጭ ምንዛሪ ከፍተኛ ወጪ እያወጣን ነው፤›› ብለዋል፡፡
በተጨማሪም የአዲስ አበባ ኤርፖርት በመጣበቡ ምክንያት የበረራ ትምህርት ቤቱ በየክልሉ ኤርፖርቶች ለመንከራተት መገደዱን ተናግረዋል፡፡ ‹‹በቀጣይ የዋና መሥሪያ ቤቱ ግንባታ ሲጠናቀቅ የበረራ ንድፈ ሐሳብ ትምህርቱን አዲስ አበባ አድርገን የተግባር በረራ ልምምዱን ባህር ዳር ኤርፖርት ለማድረግ አቅደናል፤›› ብለዋል፡፡ እስካሁን የበረራ ልምምዱ በሐዋሳ፣ በአርባ ምንጭ፣ በጅማና በባህር ዳር ሲሰጥ ቆይቷል፡፡
አቢሲኒያ የበረራ ትምህርት ቤት ለሰባተኛ ጊዜ ያሠለጠናቸውን 54 ፓይለቶች እሑድ ጥር 17 ቀን 2012 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ስካይ ላይት ሆቴል አስመርቋል፡፡ ከተመራቂዎቹ መካከል 22 የንግድ አውሮፕላን አብራሪዎች ሲሆኑ፣ 30 የግል አውሮፕላን አብራሪዎች፣ ሁለት ኢንስትራክተር ፓይለቶች ናቸው፡፡
ከ22 የንግድ አውሮፕላን አብራሪዎች መካከል 15 ኢትዮጵያውያን፣ ሦስት ከደቡብ ሱዳን፣ አንድ ከሱዳን ሪፐብሊክ፣ አንድ ከየመን፣ አንድ ከሶሪያና አንድ ከጋቦን እንደሆኑ ተገልጿል፡፡ ከ30 የግል አውሮፕላን አብራሪዎች መካከል 15 ከኢትዮጵያ፣ አሥር ከሱዳን ሪፐብሊክ፣ አንድ ከደቡብ ሱዳን፣ አንድ ከዩክሬን፣ አንድ ከአሜሪካ፣ አንድ ከሩዋንዳና አንድ ከየመን እንደሆኑ ታውቋል፡፡
በምርቃት ሥነ ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የአቢሲኒያ የበረራ አገልግሎትና አቪዬሽን አካዳሚ ምክትል ማኔጂንግ ዳይሬክተር ካፒቴን አማረ ገብረሃና በአሁኑ ወቅት 38 ተማሪ አብራሪዎች ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ እንደሆኑ ገልጸው፣ ትምህርት ቤቱ ከተቋቋመ ጀምሮ ከ15 አገሮች የተውጣጡ 186 ፓይለቶችን አሠልጥኖ ማስመረቁን አስረድተዋል፡፡
ተመራቂ ፓይለቶች የበረራ ደኅንነትን ተቀዳሚ ዓላማቸው አድርገው እንዲሠሩ ካፒቴን አማረ አሳስበዋል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተፈጠረውን የአቪዬሽን ባለሙያዎች እጥረት ለመቅረፍ፣ አቢሲኒያ አቪዬሽን አካዳሚ የበኩሉን ጥረት እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡
ካፒቴን ሰለሞን በበኩላቸው የቦይንግ ኩባንያ ጥናትን በመጥቀስ፣ የዓለም አቀፉ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ በመጪው 20 ዓመት 800,000 ፓይለቶች (በዓመት 41,000 ፓይለቶች) እንደሚፈልግ ገልጸው ይህ ለበረራ ትምህርት ቤቶች መልካም አጋጣሚ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያ ይህን መልካም አጋጣሚ ተጠቅማ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ማግኛ ምንጭ ለማድረግ እንደምትችል ተናግረዋል፡፡ አንድ የንግድ አውሮፕላን አብራሪ ለማሠልጠን አንድ ዓመት ተኩል ያህል ጊዜና 60,000 ዶላር ወጪ እንደሚፈጅ፣ አንድ የግል አውሮፕላን አብራሪ ለማስተማር አራት ወርና 17,000 ዶላር ያህል ወጪ እንደሚጠይቅ ለማወቅ ተችሏል፡፡
በ1992 ዓ.ም. በአንድ ሴስና አውሮፕላንና በስድስት ሠራተኞች ሥራ የጀመረው አቢሲንያ የበረራ አገልግሎት የ17 አውሮፕላኖች፣ የአንድ ሔሊኮፕተር ባለቤትና ከ100 በላይ ሠራተኞች እንዳሉት ታውቋል፡፡