አገር በቀል የነዳጅ ኩባንያ የሆነው ታፍ ኦይል ኢትዮጵያ በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት በ450 ሚሊዮን ብር ወጪ ያስገነባውን የአውሮፕላን ነዳጅ ዲፖ፣ ማክሰኞ ጥር 19 ቀን 2012 ዓ.ም. አስመረቀ፡፡
ሚኒስትሮችና የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ኃላፊዎች በተገኙበት የተመረቀው የአውሮፕላን ነዳጅ ዲፖ፣ ስድስት ሚሊዮን ሊትር ነዳጅ የማጠራቀም አቅም እንዳለው ተገልጿል፡፡
የታፍ ኦይል ኢትዮጵያ መሥራችና ፕሬዚዳንት አቶ ትንሳዔ አክሊሉ እንደተናገሩት፣ ዘመናዊ የሆነውን የአውሮፕላን ነዳጅ ዲፖ ለመገንባት 450 ሚሊዮን ብር ወጪና የሁለት ዓመት ጊዜ ፈጅቷል፡፡ እያንዳንዳቸው ሁለት ሚሊዮን ሊትር የአውሮፕላን ነዳጅ የሚይዙ ሦስት የነዳጅ ማጠራቀሚያ ዲፖዎችና 300 ሺሕ ሊትር የእሳት አደጋ ማጥፊያ ውኃ ማጠራቀሚያ ጋን ግንባታ እንደተከናወነ ተገልጿል፡፡
በተጨማሪም ኩባንያው እያንዳንዳቸው በሃያ ሚሊዮን ብር ወጪ የተገዙ አምስት ዘመናዊ የአውሮፕላን ነዳጅ መሙያ ተሽከርካሪዎች በማስመጣት፣ ለኢትዮጵያ አየር መንገድና ለሌሎች አየር መንገዶች ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ ማድረጉን አስረድተዋል፡፡
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተካ ገብረ ኢየሱስ፣ የአቪየሽን ዲፖ መገንባቱ ለአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ዕድገት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ገልጸው፣ ሚኒስቴሩ ለዘርፉ ዕድገት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የትራንስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ሙሉ ገብረ እግዚአብሔር፣ ታፍ ኦይል ገንብቶ ያስመረቀው የአቪየሽን ዲፖ ለአገሪቱ የአየር ትራንስፖርት ዕድገት ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው ገልጸው፣ በመስኩ የሚፈጠሩ ችግሮች ቢኖሩ ተባብሮ ለመፍታት የሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸውን ቁርጠኝነት ተናግረዋል፡፡
ታፍ ኦይል የአቪየሽን ነዳጅ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙትን ቶታል ኢትዮጵያ፣ ኦይል ሊቢያና ናሽናል ኦይል ካምፓኒ (ኖክ) ኩባንያዎችን ተቀላቅሏል፡፡
የታፍ ኦይል ኢትዮጵያ ኩባንያ ባለቤቶች እንደ ቤተሰብ ቢዝነስ ላለፉት 45 ዓመታት የነዳጅ ማደያ ሥራ ሲያከናውኑ ቆይተው፣ በ2004 ዓ.ም. የነዳጅና ዘይት አከፋፋይ ኩባንያ (ታፍ ኦይል ኢትዮጵያ) በ56 ሚሊዮን ብር ካፒታል መሥርተዋል፡፡ በ2004 ዓ.ም. በሁለት የነዳጅ ማደያዎች ሥራ የጀመረው ታፍ ኦይል የማደያዎቹን ብዛት ወደ 74 አሳድጓል፡፡
እስከ መስከረም 2013 ዓ.ም. በታፍ ኦይል ሥር የሚተዳደሩትን የማደያዎች ቁጥር ወደ 105 እንደሚያሳድግ አቶ ትንሳዔ ተናግረዋል፡፡ ኩባንያው ለ3‚400 ዜጎች የሥራ ዕድል እንደፈጠረ ተገልጿል፡፡