በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በአመራርነት ለረዥም ዓመታት በማገልገል ላይ የነበሩት አቶ ዱቤ ጅሎ የስፖርት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ሆነው ተሹመዋል፡፡ በእሳቸው ሹመት ዙሪያ የሚደመጡ አስተያየቶች፣ ሙያተኛው በስፖርቱ ከአትሌትነት እስከ አመራርነት እንዲሁም በአካዴሚ ዕውቀታቸውም በስፖርት ሳይንስ ሁለተኛ ዲግሪ ያላቸው እንደመሆናቸው ለቦታው የሚመጥኑ ናቸው ብለዋቸዋል፡፡
የአትሌቶች ተወካይ በመሆን ከ1986 ዓ.ም. ጀምሮ ስፖርቱን በማገልገል ላይ የቆዩት አቶ ዱቤ፣ እስከ ተሾሙበት ቀን ድረስ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የቴክኒክ ዳይሬክተርም ነበሩ፡፡ ከዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር በዚሁ አገልግሎታቸው “ቬትራን ፒን” ተበርክቶላቸዋል፡፡
አቶ ዱቤ በፌዴሬሽኑ በኃላፊነት በነበሩበት ወቅት ለተወሰኑ ወራት ከቦታቸው ተነስተው የነበረ ቢሆንም፣ በቀድሞ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ አማካይነት ወደ ነበሩበት ኃላፊነታቸው እንዲመለሱ የተደረገበት አጋጣሚ የቅርብ ጊዜ ትውስታ መሆኑ አይዘነጋም፡፡ ኃላፊው በፌዴሬሽኑ በአጠቃላይ ከሃያ ዓመታት በላይ አገልግለዋል፡፡
ለብዙ ዓመታት በሙያው ያሳለፉት አቶ ዱቤ ጅሎ ዕውቀትና ልምድ እንዲሁም በተለያዩ ወቅቶች ዓለም አቀፍ ሥልጠናዎችን በመውሰዳቸው አሁን ለተመደቡበት ኃላፊነት የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ያስችላቸዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡