Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊለተሽከርካሪ ብልሽቶች የቆመው መተግበሪያ

ለተሽከርካሪ ብልሽቶች የቆመው መተግበሪያ

ቀን:

ለሰዓታት ተሰልፈው፣ አልያም ተጋፍተው ወድቀው ተነስተው የሚሳፈሩት ታክሲ የረባ መቀመጫ እንኳ የሌለው እንኩቶ ሆኖ ሊያገኙት ይችላሉ፡፡ የወላለቀና የከረከሰ መዝጊያውን እንደ ኩሽና በገመድ የታሰረ፣ በመወርወሪያ የሚቀረቀርም ሆኖ አይተዋል፡፡ በየመንገዱ እየቆመ በግፊት ተመንጨቆ እየተነሳ የሚነዳ ታክሲም ተሳፍረዋል፡፡ ሰው በሰው ላይ ጭነው የሚበሩት የከተማዋ ታክሲዎች ከማጣት ይሻላሉ የሚባሉ ዓይነት ናቸው፡፡

‹‹ምቾቴ ተጠብቆ በኮንትራት ታክሲ እሄዳለሁ›› ቢሉም እስከ 40 ዓመታት የተነዱና የቆረቆዙ ታክሲዎች አሁንም ድረስ በገበያ ላይ ናቸውና ለከፈሉት ተመጣጣኝ አገልግሎት ማግኘት ከባድ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ዕድሜ የተጫኛቸው፣ መንገድ ላይ መውጣት የሌለባቸው ተሸከርካሪዎች በብዛት የአዲስ አበባን ጎዳናዎች ተቆጣጥረው ይታያሉ፡፡

በሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ብቻ ሳይሆን ለግል ጥቅም የሚውሉ የቤት መኪኖችም እንዲሁ ከችግር የፀዱ አይደሉም፡፡ የሚኩራሩበት መኪናዎ በማንኛውም ሁኔታና ቦታ ቀጥ ብሎ ደሞን ሊያፈላ ይችላል፡፡ አደባባይ እየዞሩ ድንገት ሞተሩ ጠፍቶ የትራፊክ ፍሰቱን ሊያስተጓጉሉና ሊደናበሩ ይችላሉ፡፡ ጠዋት ሥራ ለመግባት ቸኩለው ተነስ ቢሉት ወይ ፍንክች ብሎም ያውቅ ይሆናል፡፡

ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡት አብዛኞቹ ተሽከርካሪዎች ያገለገሉና ያረጁ በመሆናቸው ችግሩን ብዙዎች የሚጋሩት ነው፡፡ እንዲህ እየተበላሹ በየመንገዱ ለሚገተሩ ተሽከርካሪዎች ቦታው ላይ ፈጥኖ በመድረስ አስፈላጊውን የመጀመሪያ እርዳታ መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ይዞ ብቅ ያለው ‹‹ኬች ሮድ ሳይድ ኤመርጀንሲ ሰርቪስ›› ግን ‹‹አይዞኝ›› እያለ ነው፡፡

የከች ሮድ ሳይድ ኤመርጀንሲ መሥራች አባልና የፋይናንስ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ      አቶ ዋሲሁን ጌታቸው፣ ከተቋቋመ የወራት ዕድሜ ያለው ድርጅቱ መንገድ ላይ ለሚያጋጥሙ ድንገተኛ የተሽከርካሪ ብልሽቶች አገልግሎት እንደሚሰጥ ይናገራሉ፡፡ ከች ሮድ ሳይድ ኤመርጀንሲ ተበላሽተው መንገድ ላይ በሚቆሙ ተሽከርካሪዎች ላይ እስትንፋስ ይዘራል፡፡ የቆሙት በጎማ ችግር ከሆነ ፈጥነው የሚደርሱት የከች ሮድ ሞተረኞች ለዕርዳታ ያሉበት ከተፍ ይላሉ፡፡ የተበላሸ ጎማን አሽከርካሪው በያዘው ተቀያሪ ጎማ የመቀየር ወይም የተነፈሰ ጎማን በንፋስ የመሙላት አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ በነዳጅ እጥረትም እንደሆነ መኪናዎ ቀጥ ያለው ለአንድ አፍታ የሚሆን ነዳጅ እነሆ ይላሉ፡፡ ዋናው ነገር ለአጣዳፊ ችግር መፍትሔ የሚሆን ነገር ማቅረብ ነው፡፡ ቀሪውን ነዳጅ ማደያ ደርሶ መሙላት ነው፡፡

የመኪናው ችግር ከባትሪ ጋር የተያያዘም እንደሆነ ለጊዜው መኪናው የቆመበት ቦታ ደርሰው የደከመ የተሽከርካሪን ባትሪ በፍጥነት የማስነሳት አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ የመኪናቸው ቁልፉ ጠፍቷቸው ለተቸገሩም መዝጊያውን በጥንቃቄ የመክፈት አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ ጊዜያዊ መፍትሔ የማይመልሳቸው ችግር ያሉባቸውን ተሽከርካሪዎች ወይም በግጭት ለቆሙ ተሽከርካሪዎች የትራፊክና ኢንሹራንስ በሚፈቅደው መሠረት መኪናውን አንስተው አብረዋቸው ለሚሠሩ በአቅራቢያ ወደ ሚገኙ ጋራዦች እንደሚያደርሱ ይናገራሉ፡፡   

ድርጅቱ ከደንበኞች ጋር የሚገናኝበት የስልክ መተግበሪያ እንዲሁም አጭር የስልክ ጥሪ መስመር አዘጋጅቷል፡፡ ችግሩ ያጋጠመው አንድ ሰው በስልክ ኦፐሬተሮቹ በኩል የሚፈልገውን አገልግሎት ይጠይቃል፡፡ ወይም መተግበሪያውን ከፍቶ ድርጅቱ ከሚሰጣቸው የአገልግሎት ዝርዝሮች መካከል የሚፈልገውን መርጦ በመጫን ድጋፍ ያለበት ቦታ እንዲደርስለት መጥራት ይችላል፡፡

ከች ሮድ ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች ውስጥ ለአጭር ጊዜ የሚያገለግሉ ሹፌሮችን ማቅረብም አንዱ ነው፡፡ መጠጥ ቤት አምሽቶ ሞቅ ያለውና ቢያሽከረክር አደጋ ሊገጥመው እንደሚችል ያሰበ፣  ኤርፖርት ለመድረስ የቸኮለና በሌሎችም ምክንያቶች መኪናውን የሚይዝለት ሹፌር የሚፈልግም ከከች ሮድ ‹‹ሹም ሹፌሮች››ን ማግኘት ይችላል፡፡ ሹፌሮቹ ደንበኛውን የሚፈልግበት ቦታ አድርሰው መኪናውን ፓርክ አድርጉ በተባሉበት ቦታ ፓርክ አድርገው ይመለሳሉ፡፡

ከች ሮድ ለሚሰጣቸው አገልግሎቶች የሚያስከፍለው ገንዘብ ተሽከርካሪው እንደሚሰጣቸው አገልግሎቶችና አገልግሎቱን የሚፈልግበት መጠን የተለያየ ነው፡፡ የኬች ሮድን አገልግሎት ለዓመት ለሚገዙ ኮድ ሁለት የቤት መኪናዎች 995 ብር  የዋጋ ተመን ተዘጋጅቶላቸዋል፡፡ ኮድ 3 እና 4 የንግድ ድርጅቶችና የመንግሥት ተሽከርካሪዎች ከድርጅቱ በዓመት ለሚሸምቱት አገልግሎት 1500 ብር ይከፍላሉ፡፡ ኮድ 3 የሕዝብ አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች ደግሞ በዓመት 2000 ብር ይጠየቃሉ፡፡ ኮድ አንድ ታክሲዎች፣ የዕርዳታና ዲፕሎማቲክ ተሽከርካሪዎችም 2500 ብር ለዓመት ይጠየቃሉ፡፡ ከአንድ ዓመት በላይ ለሆኑ ጊዜያት አገልግሎቱን የሚፈልጉም በዓመት የሚከፍሉት ዋጋ ከመደበኛው እየቀነሰ ይሄዳል፡፡ ኬች ያቀረባቸውን የጥቅል አገልግሎቶች ገዝተው ከሚጠቀሙ ደንበኞች ውጪ ያሉም ለሚያስፈልጓቸው ልዩ ልዩ አገልግሎቶች ከ150 እስከ 1500 ብር እየከፈሉ ይስተናገዳሉ፡፡

ድርጅቱ ከተለያዩ የተሽከርካሪ ባለንብረቶች፣ ሞተረኞች፣ ጋራዦች በጋራ እንደሚሠራ የሚናገሩት አቶ ዋሲሁን፣ በተዘጋጁት የስልክ መተግበሪያና የቀጥታ የስልክ ጥሪ ማዕከል አገልግሎቶች ደንበኞችን ከገበያው ጋር የማገናኘት ሥራ እንደሚሠራ ገልፀዋል፡፡ በከተማዋ የሚገኙ መልዕክት ተቀብለው የሚያደርሱ ሞተሮችን፣ የቆሙ መኪኖችን ከሚያነሱ ከባድ ተሽከርካሪዎች ጋር ተቀናጅቶ አገልግሎት የሚሰጠው ከች ሮድ የተወሰኑ የራሱን ሞተረኞች ማዘጋጀቱን አቶ ዋሲሁን ገልፀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...