Wednesday, February 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

በድንጉዛ የተጀመረው የዲዛይንነት ጉዞ

የኢትዮጵያን የፋሽን ኢንዱስትሪ ለማሳደግ ሌት ከቀን ከሚለፉ የፋሽን ዲዛይነሮች መካከል ዲዛይነር ሰናይት ማሪዎ (ሞዴል) ትገኝበታለች፡፡ ዲዛይነሯ ዋን ፒስ ፋሽን የሚባል ድርጅት በመመሥረት የኢትዮጵያ ባህል አልባሳትን በማሳደግ፣ ለዓለም ገበያ ማቅረብ ዋነኛ ግቧ መሆኑን ትናገራለች፡፡ ስለድርጅቷና ለባህል አልባሳት ዙሪያ ያለውን አስተዋጽኦ አስመልክቶ ሔለን ተስፋዬ እንደሚከተለው አጠናቅራዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ ፋሽን ኢንዱስትሪ እንዴት መግባት ቻልሽ?

ሰናይት፡- ወደ ፋሽን ኢንዱስትሪ የገባሁት ጣሊያን ሳለሁ በሚቀርብልኝ አስተያየት ነው፡፡ አስተያየቱ ዲዛይነር እንድሆን ሳይሆን በቁመቴና ባለኝ ኢትዮጵያዊ ደም ግባት ለምን ሞዴል አትሆኝም? አንዳንዴም ደግሞ ሞዴል ነሽ አይደል? የሚሉኝ ብዙ ሰዎች አስተያየትና ቀና ምኞት ሳቢያ ለተወሰነ ጊዜያት በሞዴሊንግ ሙያ ቆይቻለሁ፡፡ እኔም የተሰጡኝን አስተያየቶች በመቀበል ወደ ሞዴሊንግ ሙያው ተቀላቀልኩኝ፡፡ ብዙዎች ደግሞ የሚወዱትና የሚያደንቁት የኢትዮጵያውያን ደም ግባት፣ መልክ፣ ቁመናና ጥሩ ሰብዕና ስለነበረኝ በብዙዎች ተቀባይነት አግኝቼ ነበር፡፡ ታዲያ ብዙ ሳልቆይ የአንድ ልጅ እናት ከሆንኩ በኋላ ትንሽ ወፈር ስላልኩኝ ከሞዴሊንግ ሕይወት ወደ ዲዛይኒንግ ሙያዬን ቀየርኩ፡፡   

ሰናይት፡- ከሞዴሊንግ ወደ ዲዛይነርነት የገባሁበት ሚላን የጣሊያን የፋሽን ከተማ ነች፡፡ ናይጄሪያ፣ ኬንያ፣ ጋናና ሌሎችም የአፍሪካ አገሮች በብዛት የፋሽን አልባሳት ሥራቸውን ለዓለም ለማሳየት ይመጣሉ፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ እንደ ሌሎች የአፍሪካ አገሮች በሙያው ስትሳተፍ ስላላየሁ መንፈሳዊ ቅናት አድሮብኝ ነው ወደ ዲዛይኒንግ ሙያው የተቀላቀልኩት፡፡ በተጨማሪም በጣም ዕውቅ የሚባሉ ዓለም አቀፍ ዲዛይነሮች ከኢትዮጵያ ጥሬ ዕቃ ወስደው፣ ዲዛይን አድርገው ለራሳችን ሲሸጡ ሳይ ለምን እኛም በራሳችን ሰው፣ በራሳችን የአገር ልብስ ምቹ በሆነ መልኩ ሠርተን አናቀርብም የሚል ሐሳብ ስለመጣልኝ ልቀላቀል ችያለሁ፡፡ ከውጭ የሚገቡ አንዳንድ አልባሳት ከአገሪቱ የአየር ንብረት ብሎም ከጤንነት አንፃር ሲታዩ ከባድ እንደሆኑ ብዙዎች ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ የሆኑ ምርቶች ከጤና፣ ከአየር ንብረቱ ጋር ምቹ ናቸው፡፡ ለዚህ ማድረግ ያለብን የአገራችንን የባህል አልባሳት ቀን በቀን እንዲለበሱ ለማድረግ ምቹ ማድረግ ደግሞ የእኛ ሥራ ስለሆነ በደንብ ለመሥራት ነው ቆርጬ የተነሳሁት፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርቡ ወላይታ፣ አርባ ምንጭ፣ ሐዋሳና ሌሎችም ቦታዎች ላይ ባህላዊ የፋሽን ትርዒት አዘጋጅተሽ ነበር፡፡ ጠቀሜታው ምንድነው?

ሰናይት፡- ፋሽን የሚያድገው በግለሰብ ብቻ አይደለም፡፡ ለዚህም ዕምቅ ችሎታ ያላቸው ወጣት ዲዛይነሮች አሉ፡፡ ለእነርሱ ደግሞ ዕድል መስጠትና መድረክ መፍጠር ኢንዱስትሪውን ከሚያሳድጉት መካከል አንዱና ዋነኛ ነው፡፡ በሌላ በኩል እነዚህ ዲዛይነሮች በየአካባቢው እየዞሩ የአገራቸውን የባህል አልባሳት ምቹ አድርገው ለገበያ በማቅረብና ራሳቸውን ኢንተርናሽናል ዲዛይነር ለማድረግ ነው ጥረት የሚደረገው፡፡ የአገራችን አልባሳት በአብዛኛው የሚሠሩት በጥጥ በመሆኑ ለበጋም ሆነ ለክረምት ምቹና ጤናማ በመሆኑ ቀልብ የሚስብ ነው፡፡ ለዚህም ነው አብዛኛዎቹ የዓለም አገሮች ዲዛይነሮች ጥሬ ዕቃ ከዚህ ወስደው መልሰው የሚሸጡልን፡፡ ታዲያ እንደዚህ ዓይነት መድረኮችን በመፍጠር ዲዛይነሮችን በማበረታታት ከአገራቸው አልፈው አኅጉራቸው፣ ከዚያም ዓለም አቀፍ ብራንድ እንዲኖራቸው ነው የምንሠራው፡፡

ሪፖርተር፡- በትውልድ ኢትዮጵያዊት፣ በዜግነት ደግሞ ጣሊያናዊት ነሽ፡፡ በምትኖሪበት አካባቢ ስለኢትዮጵያ ፋሽን (የአልባሳት) ምን ይላሉ? አለባበስ ላይስ?

ሰናይት፡- እኔ በምኖርባት ከተማ ብቻ ሳይሆን ለሥራ በሄድኩባቸው ቦታዎች በሙሉ በፋሽን ምርት ወደ ኋላ የቀረች አገር እንደሆነች ነው የሚነግሩኝ፡፡ ያ እንዲሆን ያደረገው ደግሞ የሰው ፋሽን ተከታይ እንጂ የአገራችንን የሚለብሱ ባለመኖሩ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም የእነርሱ ዓይነት አለባበስም እዚያው አለላቸው፡፡ ለእነርሱ ፋሽን ለየት ያለና ምቹ፣ ለጤና ተስማሚ እንዲሆን ነው የሚፈልጉት፡፡ በእሱ ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ የታደለ የለም፡፡ ሙሉ ለሙሉ ከጥጥ የተመረቱ ምርቶች አሉ፡፡ ጤናማና ተስማሚ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- እስካሁን በኢትዮጵያ በተለያዩ ዞኖች የባህል አልባሳትን እያሳየሽና ለአዳዲስ ዲዛይነሮች ዕድል እየሰጠሸ ይገኛል፡፡ ብዙዎቹ ደግሞ ደቡብ ክልል ላይ የሚገኙ ዞኖች ላይ ነው እየተካሄዱ የሚገኙት፡፡ በሌሎች ክልሎች ላይ የመሥራት ሐሳብ አለሽ?

ሰናይት፡- እኔ አጀማመሬ ከተወለድኩባትና ከቦረቅኩባት ደቡብ ምድር መነሻዬን አደረግኩ እንጂ፣ እዚሁ ብቻ እሠራለሁ ማለት አይደለም፡፡ ቀስ በቀስ ወደ መቐለ፣ ባህር ዳርና ሌሎችም የክልል ከተሞች ላይ በመሄድ የአገሪቱን የባህል አልባሳት በዘመናዊ መልኩ እንዲቀርቡ ዕድል አመቻቻለሁ፡፡      

ሪፖርተር፡- በዚህ የፋሽን ሥራ ምን ያህል ጊዜ ሆነሽ?

ሰናይት፡- በፋሽን ሥራ የቆየሁት አራት ዓመታት ብቻ ነው፡፡ በነዚህ ዓመታት መሥራት ያለብኝን ሠርቻሁ ብዬ አላስብም፡፡ ነገር ግን ከፊቴ ብዙ የሚጠብቁኝ የቤት ሥራዎች አሉ፡፡ እነርሱን በመሥራትና የአገራችንን የፋሽን ኢንዱስትሪ ከፍ ማድረግ ነው ዓላማዬ፡፡

ሪፖርተር፡- የመጀመርያ የዲዛይን ሥራሽ ምንድነው?

ሰናይት፡- በተለያዩ የሶሻል ሚዲያዎች የተለቀቀውና ነጮች ለብሰው የነበረው በወላይታ ‹‹ድንጉዛ›› የተሠራው የባህል ልብስ የእኔ ሥራ ነው፡፡ ብዙዎች የጀርመን ባንዲራ ይመስላቸው ነበር፡፡ ከዚያም በኋላ ዋን ፒስ ፋሽን መሥርቼ መሥራት ጀመርኩኝ፡፡ ብዙ ጊዜ የማይደገሙ ልብሶችን ነው ዲዛይን የማደርገው፡፡ ሌላ ቦታ ሄደው የተለየ ማንነት ሊገልጹ የሚችሉና የኢትዮጵያውያነት ኩራት የሆኑ ልብሶችን ነው የምሠራው፡፡ ከእንሰት፣ በአልኮል ታጥበው የሚሠሩ ልብሶች፣ ከድንች ጋር በመቀላቀል የሠራኋቸው ብዙ ሥራዎች አሉ፡፡ ነገር ግን አሁን ትኩረት አድርጌ የምሠራው የአገር አልባሳት ላይ ነው፡፡      

ሪፖርተር፡- በሙያሽ ምን ያህል አገሮች ላይ ሥራዎችሽን አሳይተሻል?

ሰናይት፡- ፓሪስ፣ ሚላን፣ ኒውዮርክ፣ ከአፍሪካ ደግሞ ጋና፣ ደቡብ አፍሪካና ናይጄሪያ ላይ ሥራዎቼን አቅርቤያለሁ፡፡ እነዚህን ካየሁ በኋላ ነው ኢትዮጵያ ላይ ዝግጅቶችን ማዘጋጀት ጀምሬ አምስተኛ ዙር ላይ የደረስኩት፡፡ በዚህም አዳዲስና ነባር ዲዛይነሮችን መድረክ እንዲፈጠርላቸውና የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ ያመቻቸሁት በራስ መተማመን እንዲጨምርላቸው ስለሚያግዝ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች አልባሳትን ለዓለም ማስተዋወቅ ነው ትልቁ ግቤ፡፡ በዚህም ኢትዮጵያዊ የሆነውን ዕምቅ የባህል አልባሳታችንን ለዓለም ማሳወቅና በአገሪቱ ኢኮኖሚ ፋሽን የራሱን አስተዋጽኦ እንደኖረው ለማድረግም ጭምር ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ማን ነው ዕገዛ የሚያደረግልሽ?

ሰናይት፡- በተወሰነ መልኩ መተባበር ይኖራል እንጂ አብዛኛውን ጊዜ በራሴ ገንዘብ ነው የምሠራው፡፡ የሚያግዘኝና ስፖንሰር የሚያደርግልኝ ቢገኝ ደስ ይለኛል፡፡ ነገር ግን ለፋሽን ኢንዱስትሪ ያላቸው አመለካከት ዝቅተኛ በመሆኑ አብዛኛው ይሸሻል፡፡ አንዳንዱ ደግሞ ‹‹ምንድነው ይኼ ነገር ለእኛ ምን ይበጃል?›› የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ ይህም የግንዛቤ ማነስ ስለሆነ እነርሱን ማሳወቅ ይጠበቅብኛል፡፡ እኔ ብቻ ሳልሆን መንግሥትም በዘርፉ ትልቅ ለውጥ ለማምጣት የራሱን አስተዋጽኦ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡    

ሪፖርተር፡- ኢንዱስትሪው ለአገር ያለው ጠቀሜታ እስከ ምን ድረስ ነው?

ሰናይት፡- የፋሽን ኢንዱስትሪ ጥቅምን ለማወቅ ያደጉ አገሮችን ማየት ብቻ በቂ ነው፡፡ ለምሳሌ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ምርቶችን ብንመለከትና ያንን እንዳይገባ በአገር ምርት ቢተካ አንደኛው ጥቅም ነው፡፡ በሌላ በኩል ፋሽን እያደገ ሲመጣ የተለያዩ የዓለም ዲዛይነሮች፣ ሞዴሎች፣ ፋሽን ተከታዮች ወደ አገራችን ይዘው የሚመጡት የውጭ ምንዛሪ አለ፡፡ በተጨማሪም በሆቴል ይጠቀማሉ፣ ይዝናናሉ፣ የተለያዩ ዕቃዎችን ይሸምታሉ፣ ከፍ ሲል እዚሁ የመሥራት ፍላጎት ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ስለዚህ የፋሽን ኢንዱስትሪ አገሪቷን በተወሰነ መልኩ ሊደግፍና ሊያቀና የሚችል ኢንዱስትሪ ነው፡፡ ዋናው ግን የቱሪዝም ፍሰት አሁን ካለበት በበለጠ ይጨምራል ማለት ነው፡፡ አክሱም፣ ላሊበላና ሌሎች ታሪካዊ ቦታዎችን ሊጎበኙ የመጡ የውጭ አገሮች ዜጎች ወደ ፋሽኑ ጎራ ብለው ቆይታቸው ሲራዘም የሚያስገኙት ገቢ ከፍ ይላል፡፡      

ሪፖርተር፡- እስካሁን በሄድሽበት የሥራ ሕይወትሽ ምን ችግር ገጠመሽ?

ሰናይት፡- በተለይ ኢትዮጵያ ላይ በእያንዳንዱ ነገር እፈተናለሁ፡፡ ቦታ ለማግኘት፣ ስፖንሰር ለማግኘት፤ ነገር ግን ዓላማዬ ትልቅ በመሆኑ ይህ አያደናቅፈኝም፡፡ ይበልጥ መሥራትና መጠንከር እንደሚገባኝ ነው የማስበው፡፡ የሚገጥመኝን ችግር ካየሁ ከአንድ መድረክ ውጪ የሚያሠራ አይደለም፡፡     

ሪፖርተር፡- በፋሽን ኢንዱስትሪው የሰውን ሥራ መሥራት በኢትዮጵያ የተለመደ ነው፡፡ ሥራዎችሽ በሌሎች ቦታዎች ኮፒ አልተደረጉም?

ሰናይት፡- እንዲያውም አንድ ነገር ትዝ አስባልሽኝ፡፡ ሽሮ ሜዳ ላይ ሥራዎቼን ከነ ሞዴሎች በማስታወቂያ ባነር ላይ አይቼዋለሁ፡፡ ሕጉ ቢኖርም ጠንካራ ባለመሆኑ ይመስለኛል ይህ የሆነው፡፡ ለፋሽኑ ኢንዱስትሪ አለማደግ ትልቁ ማነቆ የሰውን ሥራ ኮፒ አድርጎ መሸጥ አንዱና ዋነኛ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በሥራዎችሽ የተለያዩ ዕውቅና እንደተሰጠሽ ሰምቻለሁ፤

ሰናይት፡- እስካሁን በማደርገው እንቅስቃሴ የተለያዩ ሽልማትን አግኝቻለሁ፡፡ በናይጄሪያ፣ ጋና፣ አሜሪካና በኢትዮጵያ አቢሲኒያ አዋርድ ላይ የተለያዩ ሽልማቶችን አግኝቻለሁ፡፡ ያ ደግሞ እኔን አበርትቶኛል፡፡ ምክንያቱም የሎሬት ማዕረግ ሳገኝ በጣም ነበር የደነገጥኩት እንዲያውም ተጨማሪ እንድሠራ አድርጎኛል፡፡

ሪፖርተር፡- በቀጣይ ከዝግጅቶችሽ ምን እንጠብቅ?

ሰናይት፡- በቀጣይ በተለያዩ ከተሞች እየሄድን ዲዛይነሮች የሠሩትን ሥራ ማስተዋወቅና እንደዚህ ተደርጎ መልበስ ይቻላል የሚለውን ማሳየትና ማሳወቅ ነው፡፡ ከዚያም እያደገና እየተሻሻለ ሲመጣ ኢንተርናሽናል ዝግጅት ላይ ዲዛይነሮች እንዲሳተፉ ማድረግና የኢትዮጵያ የባህል አልባሳት ለዓለም ማሳወቅ ቀጣይ ሥራዬ ይሆናል፡፡ ዋን ፒስ ፋሽን በቅርቡ የቴክስታይል ኢንዱስትሪ ለመክፈት ዝግጅት ላይ እንገኛለን፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

ግዴታን መሠረት ያደረገ የጤና መድኅን ሥርዓት

የኢትዮጵያ ጤና መድኅን ተቋቁሞ ወደ ሥራ ከገባ ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ማኅበረሰብ አቀፍና የማኅበራዊ ጤና መድኅን ሥርዓቶችን መሠረት አድርጎም ይሠራል፡፡ የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን ሥርዓት በኢመደበኛ...

የመሠረተ ልማት ተደራሽነት የሚፈልገው የግብርና ትራንስፎርሜሽን

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ተቋም አርሶ አደሩን የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ በማድረግ የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚውን የማሳደግ ዓላማ ይዞ የተመሠረተ ነው፡፡ ተቋሙ የግብርናውን ዘርፍ ሊያሳድጉ የሚችሉ ጥናቶችን...

‹‹በአሁኑ ሰዓት እየፈተነን ያለው እንደ ልብ ተንቀሳቅሰን መሥራት አለመቻላችን ነው›› አቶ ልዑል ሰገድ መኮንንን፣ አይሲዳ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር

አይሲዳ አገር በቀል የዕርዳታ ድርጅት በኤችአይቪ ሥርጭት ቁጥጥር ላይ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ ከ1998 ዓ.ም. ወዲህ ራሱን እንደ አዲስ አዋቅሮ በተለይ ለሰው ሠራሽና ለተፈጥሮ አደጋዎች ምላሽ...