በአሰፋ አደፍርስ
በጥንቱ ዘመን ለመማር ብዙ ውጣ ውረድ ነበረበት፣ ደበሎ ለብሶ በየደጃፉ እየዞሩ መለመኑ፣ በየቤተ ክርስቲያኑ ዘኬ መልቀሙና የመሳሰሉት፣ ዛሬ ግን የዕለት ጉርስና የዓመት ልብስ ከተገኘና ሰው ለዕውቀት ጓጉቶ ቆርጦ ከተነሳ መማር፣ ማስተማርና ወገንን ከችግርና ከመከራ ማዳን ይቻላል። ግን የአገሬ ምሁራን ትምህርትን ለስም መጠሪያና ማጌጪያ ያደርጉት እንደሆን (ክቡር፣ (ዶ/ር)፣ ኢንጂነር፣ ሌላም ማዕረግ ይጨመራል)፣ ለአገር ጥቅም ለማዋልና አገሬ ለምን ተቸገረ ማለት ነበረባቸው፡፡ ሁሉም የተትረፈረፈባት ደሃ ልትባል የማይገባት ነች ብሎ የመነሳት ወኔ የከዳው ምሁር የተሰበሰበባት አገር መሆኗ እጅግ ያሳዝናል። ምሁራን ወገኖቼ ጦራችሁን ሰብቃችሁ ጋሻችሁን መክታችሁ ይህ ጥጋበኛ የተዳፈረን ማነው ብላችሁ ብትመጡ እኔ ደግሞ በጦር ሳይሆን፣ በተመረመረና በተጠና መንገድ በመጣችሁበት መንገድ ልመልሳችሁ ተዘጋጅቼያለሁ፡፡
በጥንቃቄ ቁምነገሩን ብትከታተሉና ተወያይተን አገራችንን ከችግር ለማዳን ብንነሳ፣ የየድርሻችንን ውጤት ልናመጣ ስለምንችል ተባብረን እንነሳ ለማለት ነው፡፡ ከምን ተነስቼ ለዚህ ምክርም ሆነ ወቀሳ እንደተነሳሁ ይገርማችሁ ይሆናልና በየተራው አመላክቼ እቀጥላለሁ። አገራችን ለም አፈር ያላት፣ ወራጅ ወንዞች የሞሏትና ወጣት ኢትዮጵያዊያን ምን እንሥራ ብለው የሥራ ያለህ፣ የወገን አሠሪ ያለህ እያሉ ታች ላይ ይላሉ፡፡ ትንሽ ሶልዲ ካገኙም የሻይ ቤቶችን ሲያሟሙቁ የሚውሉ ናቸው፡፡ በየመንገዱ ሲንገላወዱ ጊዜያቸውን በከንቱ የሚያጠፉ፣ የተማሩትም የሚቀጠሩበት ቦታ ወይም አሠሪ አጥተው በከንቱ ጊዜ የሚያቃጥሉበት ሁኔታ እንዳለ አንባቢያን ሁሉ ሊመሰክሩ የሚችሉት ጉዳይ ነው። በየጊዜው የጻፍኩትን መላልሼ ስጽፍ ይህ ሰው ያለዚህ አያውቅ የሚሉኝ ቢኖሩም፣ ችግሩን መስመር ለማስያዝ ስለሆነ መደጋገሙን አትጥሉት።
ኢትዮጵያ በቀንድ ከብት ሀብት ከአፍሪካ አንደኛ ከዓለም አምስተኛ ስትባል እንሰማለን፡፡ ግን የዱቄት ወተት ለተቻላቸው እናስገባለን፣ ለታላላቅ ሆቴሎች ሥጋ እናስገባለን፣ በሌላ በኩል መከራውን ዓይቶ በቦረና፣ በባሌ፣ አልፎ አልፎ በፎገራና በሐረር እንደ ልጁ ሥር ሥሩን እየጎተተ ያደለበውን ወይፈንም ሆነ በሬ በአነስተኛ ዋጋ ገዝተን፣ ሦስት ወራት ቀልበን ካደለብን በኋላ ለዓረብ አገሮች መሸጥ የተቻለ ቢመስልም፣ በጥሩነቱ ተወዶ ሳይሆን ለማሟያ እንደሆነ የምናውቀው ታሪክ ነው። ሁሉንም ዘርዘር አድርጌ እንዳላወጣው ራስን ማጋለጥ እንዳይሆንብኝ የአገሬን ከፍታ እንጂ፣ የማንም መዛበቻ ለመሆን ስለማልፈልግ ልለፈው ብዬ ነው። አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ብቻ 600,000 ሊትር ወተት በቀን ሲፈለግ፣ ዛሬ ያለው የምርት ብዛት 60,000 ሊትር ወተት ብቻ መሆኑን የኢንተርናሽናል ላይቭ ስቶክ ሪሰርች ኢንስቲትዩት ባወጣው መረጃ አስታውቋል፡፡ እንግዲህ በአዲስ አበባ ብቻ ይህንን ያህል ወተትና ተዋፅዖ ከተፈለገና ገበያ ካለው፣ መላውን የኢትዮጵያ ከተሞች ለማዳረስ እጥፍ ድርብ ያስፈልገናል ማለት ነው፡፡ ታዲያ ምን ይሆን የጎደለን? ሠራተኛ፣ መሬት፣ ውኃ ወይስ ዕውቀት ያለው አሠሪ ይሆን ያጣነው? ይህንን ለመመለስ በመስኩ የተሾሙት ሚኒስትሮችና በመስኩ የሠለጠኑ ምሁራን መሆን አለባቸው።
ይህንን በምጽፍበት ሰዓት እጅግ በረሃማ የሆነችውን ሳዑዲ ዓረቢያን በጥናቴ አስገብቼ ለመመልከት ሞከርኩ። ሳዑዲ ዓረቢያ ውኃ የሌላት፣ የከብት መኖ ማብቀልም ሆነ ማቅረብ የማትችል በረሃማ አገር ናት፡፡ ከሕዝቧ ቁጥር እጅግ የላቀ የወተት ተዋፅኦ ብዛት ያላት፣ ከብቶቹ በሙቀት እንዳያልቁ በኤር ኮንዲሽን የምታቀዘቅዛቸው፣ ሣር አገሯ ውስጥ ማብቀል ባለመቻሏ እ.ኤ.አ. በ2014 አሪዞና ውስጥ 9,600 ኤከርስ መሬት ገዝታ ሣር ከዚያ በማመላለስ ስትቀልብ ነበር፡፡ አሁንም መሬቱ አልበቃ ስላላት በካሊፎርኒያ ፓሎ ቨርደ ቫሊ ውስጥ 14,000 ኤከርስ መሬት ገዝታ ከዚያ በማመላለስ፣ የወተት ተዋፅኦ አበርክታ ለራሷ ብቻም ሳይሆን ለኤክስፖርት ትጠቀማለች። ይህ ከኢኮኖሚ አንፃር አዋጭ ነው? ወይስ ከማን አንሼ በማለት እንደሆነ የምናውቀውን ለመዘክዘክ አንሻም።
እግዜር ያሳያችሁ በመስኩ ልሂቃን የተባሉት በብዛት አሜሪካኖች ናቸው፡፡ ተራ ሠራተኞች ከእስያ አገሮች ሲሆኑ፣ ኢትዮጵያዊያንም እንደማይጠፉ አምናለሁ። ታዲያ ሁሉም ያለን እኛ ‘ኒዶ ያጠነክራል’ እያለ አንዱ ታዋቂ ወንድማችን ሲያስተዋውቅልን ማየቱ ምን ያህል እንዳስከፋኝ ልነግራችሁ አልችልም። ምክንያቱም ይህ ታዋቂ ወንድማችን ራሱ ዓለምን በሚያስደንቅ ሁኔታ ለወገኑና ለአገሩ ሰውን አሰባስቦ ከምሁራኑ ተመካክሮ መሥራት ሲችል፣ የዓረብን ወተት ማስተዋወቁ እጅግ አስከፍቶኛል፡፡ ይህንን ወገኔንም ሆነ ሌሎች የአገራችንን ምሁራን ከማየት ያለ ማየትን በመምረጥ፣ ካለሁበት ሆቴልም ሆነ ቤት ሳልወጣ የምውልበት ቀናት በርክተዋል።
ባለፈው ዓመት ሚያዚያ 22 ቀን 2011 ዓ.ም. ይህንን ጉዳይ ተነጋግሬ አስፈላጊውን ጥናት ካስጠኑና በነገሩ ከተስማማን በኋላ፣ መንግሥት በቂ መሬት እንዲሰጠንና በሥራው ላይ በቀደምትነት የሚሳተፉ ኢትዮጵያዊያን ከተገኙ ገንዘብ ለማምጣት እችላለሁ ብዬ ከእርሻ ሚኒስትሩ ቀጠሮ ተቀበልኩ፡፡ በቀጠሮዬ መሠረት ቢሮዋቸው ሦስት ታላላቅ የእርሻ ምሁራንን ይዤ ሄድኩ፡፡ ጸሐፊያቸውን ብንጠይቅ አልገቡም ተባልን፡፡ በስንት ጉትጎታ ሁለት ሚኒስትር ዴታዎች ቀርበው በሚኒስትሩ ቢሮ አነጋግረውን፣ በጉዳዩ የተደሰቱ መሆናቸውን ገልጸው ተለያየን። ሁሉም ነገር የውኃ ሽታ ሆኖ ቀረ። እኔም ሳላቋርጥ በውጭም በአገር ውስጥም በነበርኩበት ጊዜ ደጋግሜ በኢሜልና በስልክ ብከታተል ‘የዝሆን ጆሮ ስጠን’ ብለው ዝም ተባለ።
ታዲያ እንዴት ነው አገር ሊለማ የሚችለው? ልብ በሉ ሳዑዲ ዓረቢያ በአንድ ባላፀጋ የወተት ላም ዕርባታ ብቻ 6‚980 ሠራተኞች ቀጥራ ስታሠራ፣ በሌላት ሣርና ውኃ ከውጭ በማስመጣት በአንድ ሊትር ወተት ሦስት ሊትር ውኃ በማጠጣት በቀን ለአንድ ላም 150 ሊትር ውኃ እያቀረበች፣ እነዚያን ሁሉ የወተት ላሞች መያዝና እንደ ልብ ወተት ማደል ስትችል፣ ከላይ ያመለከትኳችሁ ከፍተኛ ሠራተኞች ከአሜሪካ ሲሆኑ የበታች ሠራተኞች ከእስያ አገሮች የሄዱ ናቸው።
ሁሉም ነገር ያለን የበሬ ግንባር የምታህል መሬት ለአፍ መዝጊያ ለወገናችን ሰጥተን፣ ራሱም ሳይጠቀም አገሪቱም ከልመና እንዳትወጣ በልጆቿ የተፈረደባት ይመስል ስትሰቃይ እያየን በዝምታ ማለፍን መፍቀዱ የጨዋነት ምልክት አድርገን ኖረናል። አሁን ግን ይብቃን! ለሥራ፣ ለልማትና ለአንድነት ተባብረን እንነሳ! 100 ሚሊዮን ሕዝብ ያላት ኢትዮጵያ 100 ሰው የሚይዝ ዕርባታ የላትም። የእኔ ቢጤው ኩባያና ብርጭቆ ሲይዝ ወሬው ያምርለታል፡፡ ከዚያ ከወጣ በኋላ ወሬውም ቁምነገሩም ይረሳል። ወገኖቼ እባካችሁ ተበረታትተን አገራችንን ከልመና እናውጣት፡፡ ፖለቲካ ብቻውን አገር ሊያኖር እንደማይችልም ሁላችንም የምናውቀው ጉዳይ ነው፡፡ ለልማትም ትኩረት ብትሰጡ ሁሉም የተቃና ይሆንላችኋል፡፡ አሁን የሚታየው ትርምስ ያላቸው የሌላቸውን የሚገዙበት አቅም በማግኘታቸውና በቀላሉ ለማታለል ስለሚችሉ ይመስለኛል፡፡ ፖለቲካ እጅግም ስለማላውቅ መላምት ነውና አትቀየሙኝ።
ያለሁበት አገር ሰውን እጅ ሰንዝሮ ያለ መድፈር እንጂ የተሰማውን ተናግሮ ሲያልፍ ተነገረብኝ ባዩ ደግሞ፣ ከፈለገ አፀፋውን ይመልሳል እንጂ ጦርነት የለም። ይህ ነው እንግዲህ አንዱ የዴሞክራሲ መሠረተ ሐሳብ፡፡ የፈለገ በፈለገው መንገድ ያልኩትን ሁሉ የሚያፈስበትን በጥናት በተደገፈም ሆነ ባሻው መንገድ ሊመልስልኝ ይችላል። ዱላ ብቻ ነው የማይፈቀደው። በሉ ልቦና ለሁላችንም ይስጠን፡፡ ለአገር ልማትና ብልፅግና ተባብረን እንሥራ ነው መልዕክቴ።
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡