Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርየተሰናሰልንበትን ኢትዮጵያዊነት ማጥበቅ ይበጃናል!

የተሰናሰልንበትን ኢትዮጵያዊነት ማጥበቅ ይበጃናል!

ቀን:

በንጉሥ ወዳጅነው

ኢትዮጵያ ኅብረ ብሔራዊት አገር ናት፡፡ መልከ ብዙና ቀለመ ዥንጉርጉር፡፡ የባህል፣ የእምነት፣ የቋንቋ፣ የመልክአ ምድር ብዝሀነትን የተላበሰች ምድር ናት፡፡ የሰው ልጅ በዓለም ታሪክ ለመጀመሪያ ግዜ የተገኘባትና የኖረባትም ነች፡፡ ኢትዮጵያ ከፊት ዘመን ጀምሮ በድህነት፣ በጉስቁልና  በውስጥ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ዘመናትን ብታልፍም፣  ሕዝቦቿ የሚተባባሩበትና አንድ የሚሆኑበት አገራዊ እሴትም ነበራቸው፣ አላቸው፡፡

በተለይ አገሪቱ ከውጭ ወራሪዎች ጋር በየዘመኑ ጦርነት እየገጠመች በመጡበትም እየመለሰች ነፃነትዋን አስከብራ እንድትኖር ያደረጉዋት በየዘመኑ የነበሩ ጀግኖች ልጆች ነበሩ፡፡  ዘር፣ ፖለቲካና ሃይማኖት ሳይለያያቸው ለዘመናት ሲፋለሙ የነበሩ አያት ቅድመ አያቶቻችን፣ ሌሎች በባርነት ቀንበር ሲማቅቁ እኛ በነፃነትና በኩራት የምንኖርባት፣ የሉዓላዊነት ምሳሌና አርዓያ ሆና የኖረች አገር ባለቤት አድርገውና፡፡ ምንም ያህል ታሪክ መዛባት ቢጀምር፣ እነዚህን የጋራ እውነታዎች ለመካድ የሚስችል አቅም አይኖረውም፡፡ ስለዚህ የሚበጀን ጋራ እሴታችን እየገነቡና የተዘናፈውን እያረሙ መቀጠል ብቻ ነው፡፡

በፌዴራላዊ ዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ረገድ አሳታፊና የተቃና መልካም አስተዳዳር ለማስፈን የተደረጉ ጥረቶች ቢኖሩም፣ በታሪክም ሆነ በሕዝቦች መሰናሰል ዜጎች የሚጋሩዋቸው በጎ እሴቶች ላይ የተሠራው ደካማ በመሆኑ፣ አብሮ ለመቆም የተቸገረ ትውልድ ሊፈጠር ችሏል፡፡ እሱ ብቻ ሳይሆን የተዛባው ትርክትና የጥላቻው ወግ እያካካደን እንደሚገኝ፣ ጥር 13 ቀን 2012 ዓ.ም. በዚሁ ጋዜጣ ልናገር ዓምድ ላይ ከመጣንበት ይልቅ በአብሮነት የምንሄደው መንገድ ረጅም መሆኑን በዳሰስኩበት ጽሑፍ ቃኝቼዋለሁ፡፡

ዛሬም ቢሆን አገራችን የጀመረችው የዳግም ውልደትና የህዳሴ ጉዞ ወጣ ገባውን እያለፈና በተስተካካለ መንገድ  እየተመመ ለመሄድ እያስቸገረው ያለው ደረቅ ሀቅ ይኸው መሆኑን ግን ደጋግሞ ማጤን ይገባል፡፡ ይህ አካሄዳችን አንድ ቦታ ላይ ካልታረመ ደግሞ፣ የዘመናት አብሮነታችንና  አገራችን ተረት ሆና ለማንም መሳቂያ መሳለቂያ እንዳሆን መንቃትም ያስፈልጋል፡፡ የጥላቻ ዘመን ትውልድ አገር ከመበተን እንደማይመለስ እየታየ እንደ መሆኑም እገሌ ከእገሌ ሳይባል ማስተዋልን ሊላበስ ይገባል፡፡

በመሠረቱ እኛ ኢትዮጵያዊያን አንድ መገንዘብ ያለብን እውነት ቢኖር ዓለም ከመነጣጣል፣ ጥላቻና ቁርሾ አትራፊ መሆን እንዳልቻለ ነው፡፡ እንኳንስ እንደኛ ለዘመናት በአንድ ሥርዓተ መንግሥት ለኖረ ሕዝብ አገዛዞች ቢፋለሙምና በሕዝብ ላይ በደል ቢያደርሱም፣ ለሺሕ  ዓመታት በአንድ አገር ወሰን (በየጊዜው መስፋት መጥበቡ እንዳለ ሆኖ) እንደ ዘለቀ ብዝኃነት ተከባብሮና ተደማምጦ በእኩልነት ከመኖር የዘለለ ዕድል ለኖረን እንደማይችል መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ እንደ አገር በተመጣበት መንገድ ክፍተቶች አልነበሩም ባይባልም፣ እነዚህን ብልሽቶች አርሞ ፍትሕ፣ እኩልነትና ርትዕ ብቻ ሳይሆን ሰላም፣ አብሮነትና አንድነትን ማረጋጋጡ ነው ለማንም የሚበጀው፡፡ ለዚህ ደግሞ የኦሮሞ፣ የአማራና የትግራይ ልሂቃን የተጣዱበትን ፉክክር ቤት አለዝበው ሌላውን ሕዝብ ያቀፈ ትግል መጀመር ግድ ይላቻዋል፡፡ በመሠረቱ ኢትዮጵያ ማለት የተናጠል አንድ ብሔር ይቅርና የሦስቱ በአንድ ላይ ብቻም እንዳልሆነች መጨበጥ አለበት ፡፡

በመሠረቱ ኢትዮጵያን ከዳር እስከ መሀል ካናሳው እስከ ብዙኃኑ አብሮነታችን የተሳሰረና ዘመናትን የተሻገረ ነው ሲባል በመላምት አይደለም፡፡ የኢትዮጵያዊንን አብሮነትና ለዘመናት የዘለቀ መሰናሰል ከታሪክ ድርሳናት አጣቅሶ ወደ መዳረሻ ነጥባችን ለመዝለቅ በቀዳሚነት ኃይሌ ወልደ ሚካኤል (ዶ/ር) የተባሉ ምሁር “አብሮነት በኢትዮጵያ” (1994 ዓ.ም.) የሚል አነስ ያለ ታሪካዊ ጥናትን መጥቀስ ይቻላል፡፡

ይህ መጽሐፍ ስለኢትዮጵያ ሕዝቦች ቀደምት ታሪክ፣ አብሮነትና አኩሪ እሴቶች ጠቃሚ ሐሳቦችን የሚያነሳ ብቻ ሳይሆን በዘር እየተራኮተ ያለውን የእኛን መናኛ ትውልድም ወደ ውስጡ እንዲመለከት የሚጎተጉት ነው፡፡ በምንገኝበት ሁኔታ እንዲህ ዓይነት የታሪክ ድርሳናትን እየመረመሩ ከማጉላት ውጪ አማራጭ ሊኖር አይችልም ፡፡

እኔም ከመጽሐፉ በአጭሩ የወሰድኩት የሕዝባችንን የተሳሰረ መስተጋብር በአጭሩ እንዲያሳይልኝ በሚል ነው፡፡ አሁን በአገራችን የጎሳና የብሄር ፖለቲካ ላይ ተጠምዶ ሥር ነቀል ለውጥ ለማምጣት እንደማይቻልም ለማመላከት ነው፡፡ ፖለቲከኞች የማናቆር ትርክትና የተዛባ ሴራ እየጫኑብን እንጂ፣ የአገራችን ሕዝቦች ለዘመናት የገነቡት ትስስር፣ መስተጋብርና ውህደት ሲፈተሽ፣ ኢትዮጵያዊያንን ለአፍታም የማይለያዩና የተሳሳሩ መሆናቸውን ቁልጭ አድርጎ ስለሚያንፀባርቅም ነው፡፡

እንዲህ ይላል  “ስለኢትዮጵያ ሕዝቦች መስተጋብር ስንጠቅስ ጥንት የአክሱም መንግሥት በዮዲትና በቤጃዎች ሲደመሰስ፣ አክሱማውያን ወደ ሰሜንና ወደ መሀል አገር ፈልሰው ኑሮ መመሥረታቸው በቅድሚያ ይወሳል፡፡ የዛጉየ መንግሥትም ሮሃ ላይ ከተመሠረተ በኋላ የአክሱማውያንን ዕደ ጥበበኞችን ስቧል፡፡

“የሸዋ መንግሥት በጀመረው የመስፋፋት ጉዞ ደግሞ ቋሚ የጦር ሠፈሮችና የአካባቢ ጋሻ ጃግሬዎች በሐረር፣ በሶማሌ፣ በአፋር፣ በደዋሮ፣ በባሌ፣ በሃዲያ፣ በከምባታ፣ በወላይታ፣ በጋሞጎፋ፣ በሸዋ፣ በዳሞት፣ በእናርያ፣ በጉራጌ፣ ወዘተ እንደነበሩትና በዚህም ሰፊ መስተጋብር እንደተፈጠረ ይታወቃል (እንግዲህ እዚህ ላይ አንዱ ግዛት ሲስፋፋ የሌላውን እየወገና እያስገበረ መሆኑ ባይካድም፣ የጭሰናና የገዥ መደቡ የብዝበዛ ሥሪት ከፈትሉ ተነጥሎ ባይታይም ውህደቱ ግን ዘመናትን የተሸገረ ለመሆኑ የዓለምን ተሞክሮ መመርመር ብቻ በቂ ነው!!)፡፡

“ዛሬ ድረስ ወላይታ ውስጥ ትግሮ (ትግሬ)፣ ቡልጎ (ቡልጋ)፣ መንዞ (መንዝ )፣ ቄሶ (ቄስ)፣ መራቤቶ (መረሃቤቴ) ወዘተ የሚባሉ ጎሳዎች አሉ፡፡ ከምባታ ውስጥ ኦያ የሚባለው ጎሳ ከጎንደር ከመጣ ሀመልማል ሠራዊት የሚመነጭ መሆኑ ሲታወቅ፣ ሃዲያ ውስጥም ጋስ አማራ (የጥንት አማራ) የሚባል ጎሳ እንደነበር ተመዝግቧል፡፡

“የጉራጌም ሕዝብ በአመዘኙ፣ የእናርያ፣ የሲዳማ፣ የሐረር፣ የኦሮሞና የሃዲያ ሕዝቦች መስተጋብር ውጤት ነው፡፡ በሌላ በኩል በ16ኛው ምዕተ ዓመት መጀመሪያ ሩብ አጋማሽ ግራኝ አህመድ ከሐረር ተነስቶ ከብዙ ሕዝቦች የተውጣጣ ሠራዊት መሥርቶ፤  ኢትዮጵያን  እንዳጥለቀለቀ ይታወሳል ፡፡ በዚህም የብሔረሰብ ስብጥር ብቻ ሳይሆን የሃይማኖት ውርርስና ቦታ መቀየር ተፈጥሯል፡፡

“ከግራኝ ሽንፈት በኋላ የግራኝ ሠራዊት እንደሟሸሸ ቢታወቅም፣ ጦርነቱ የፈጠረው መስተጋብር የኦሮሞ ሉባዎችን ወደ ባሌ፣ ደዋሮ (አርሲ)፣ ሐረር፣ ሸዋ፣ ቤተ አማራ (ወሎ)፣ ጎንደር፣ ከፋና ጎጃም አሰባስቧል፡፡ በዚህ ምክንያት ኦሮሞዎች ከነባር የየአካባቢው ማኅበረሰቦች ጋር ተወራርሰዋል፣ ተዋህደዋል፡፡

“እዚህ ላይ የባሌ፣ የደዋሮ፣  የዳሞት፣ የእናርያ፣ የሃዲያ (በከፊል)፣ የጉራጌ (በከፊል) ሕዝቦች ማንነታቸውን ትተው ኦሮሞዎች ሲሆኑ፣ በተለዋጩ ወደ ቤተ አማራ፣ ጎንደር፣ ትግሬና ጎጃም የዘለቁ ኦሮሞዎች ደግሞ ማንነታቸውን ትተው አማራዎችና ትግሬዎች ሆነዋል፡፡ በሌላ በኩል የማዕከላዊ መንግሥት ግዛት አካል የነበረው ባህረ ነጋሽ (የዛሬው ትግራይና ኤርትራ) ብዙ የጎንደር፣ የጎጃምና የቤተ አማራ ሕዝቦችን ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ ስቧል፡፡ ስለሆነም በኤርትራ ውስጥ ሀማሴን የሚባለው ሕዝብ በአመዛኙ ከጎንደር የፈለሰ ሕዝብ መሆኑ ታውቋል፡፡ . . .” (ዝርዝሩ ብዙ ቢሆንም ገጽ 60 ከተጠቀሰው ይኼው ይበቃል፡፡)

እንግዲህ ላለፉት በርካታ መቶ ዓመታት በጠንካራ አገረ መንግሥትም ሆነ በየአካባቢው በነበሩት መሣፍንት የመስፋፋት አካሄድ የተነሳ ሕዝቡ ሲዋሀድና ሲዋለድ ዘልቋል፡፡ ታዲያ ይህን አብሮነት የመሠረተውን ማኅበረሰብ በዘር ፖለቲካ ለመነጣጣል መጣደፍ ይሻላል? ወይስ ዴሞክራሲንና ፍትሕን እያረጋጋጡ አንድነቱን ማጠናከር? ብሎ መመርመር ያስፈልጋል፡፡ እዚህ ላይ በአንድ ቤተሰብና አንድ ትውልድ ላይ ያነጣጠረ የሚመስለው የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የቅርብ ጊዜ መጽሐፍ፣ “እኛም እንናገር ትውልድ አይደናገር”ን በጥሞና መመርመር የሚያስጨብጠው ብዙ ቁምነገር ይኖራል፡፡

 በመሠረቱ የጥንቱን እንኳን ትተን በዘመነ መሣፍንትም ሆነ ከዚያ ወዲህ ገዥዎች እርስ በርስ ጦር ሰብቀው ሲዘምቱ፣ ዓላማቸው ገባር ማባዛትና ወሰንንን ማስፋት ነበር፡፡ የሚተላላቀው ግን ሕዝብ ነበር፡፡ አፄ ዮሐንስ በአፄ ቴዎድሮስ፣ አፄ ምኒልክ በአፄ ዮሐንስ፣ አፄ ኃይለ ሥላሴ በልጅ እያሱም ሆነ በዘውዲቱ ላይ የፖለቲካ ሴራ እየሰሩ ቢያልፉም፣ ሁሉም ለአገዛዙ እንጂ ጎሳና ዘውጉን ልጥቀም በሚልም አልነበረም፡፡ በአገራቸው አንድነትና ሉዓላዊነት ጉዳይ አለመደራደራቸውም በድምር የሚያስከብራቸው ነው፡፡ የእነ ኮሎኔል መንግሥቱ ከልክ ያለፈ የአገር ፍቅርና የተፅዕኖ አንድነት ሕዝቦችን ዕልቂት የዳረገ መሆኑ ባይዘነጋም፣ የብሔር መሠረት የነበረውና የመድሎ ታሪክ የሚወሳበት አልነበረም፡፡

በእነዚህ የዘመናት ሒደቶች ደግሞ ቢያንስ ጥፋቶችን ለገዥዎችና ለመሪዎች ብንሰጥ፣ ሕዝቡ አብሮነቱንና አገራዊ መስተጋብሮችን ጠብቆ መቆየቱን መካድ ያዳግታል፡፡ ድርብ ጭቆና የወደቀባቸው ዜጎች ሳይቀሩ በኢትዮጵያዊነት ሳይደራደሩ ለዘመናት ለእኩልነትና ለነፃነት የታገሉትም ለዚህ ነበር፡፡

ይህን ለዘመናት የተሰናሰለ ሕዝባዊ አንድነትና ኅብረ ብሔራዊ መስተጋብር ለመበጣጠስና የራሳቸውን የፖለቲካ ፍላጎት በሕዝብ ላይ ለመጫን የሚሹ ኃይሎች፣ ከቅርብ አሠርት ዓመታት ወዲህ በአገሪቱ ተፈጥረዋል፡፡ መነሻቸው ምንም እንኳን የብሔርና የመደብ ጭቆናን ለማስወገድ መሆኑ በጎ ቢመስልም፣ በቀጣፊ አዲስ ትርክት አገዛዞችን ሳይሆን ሕዝቦችንም በጥላቻ አፋጥጠው የአገር አንድነትንና የሕዝቦችን አብሮነትን በግላጭ ለአደጋ አጋልጠዋል፡፡ መዘዙ ዛሬም እንደተደቀነብን ይገኛል፡፡

በዚህ ወንዝ የማያሻግር ወልካፋ ሐሳብ ዛሬም ድረስ ተጠምደው እየባዘኑ ያሉት ደግሞ፣ አብዛኞቹ በብሔር የፖለቲካ አጀንዳ የሚያንቀሳቅሱ፣ ነገን ከሚያሳይ የጋራ ፕሮግራምና ማኒፌስቶ ይልቅ በቁጭትና በጥላቻ ትርክት ላይ የማተኮር አዝማሚያ የሚታይባቸው ናቸው፡፡ እነዚህን ኃይሎች በሰላማዊና ከጥላቻ በፀዳ መንገድ ማረምና በድምፅ ከማሸነፍ በላይ የዚህ ትውልድ ኃላፊነት የለም፡፡

እርግጥ በእነዚህ ኃይሎች እየተመራ ያለ አንድ የአገራችን ትውልድ ከጊዜ ወደ ጊዜ የዘር ሀረግ እየቆጠረ፣ ማንነትና ሃይማኖት ሳይነጣጥለው ለዘመናት አብሮ የኖረውን ማኅበረሰብ (እያወቀም፣ ሳያውቅም ) እያፈላቀቀ ፣ አለፍ ሲልም በኃይል እያተራመሰ መቀጠሉ አልቀረም፡፡ ከዚያም አልፎ ለውጥ መጣ ከተባለም በኋላ የዘር ፖለቲካን ብቻ በማቀንቀንና በጥላቻ ትርክት ላይ በመጠመድ፣ አብሮነትን የሚያፈራረስ ድርጊት የተቀበለ እንደመሰለ ነው፡፡ ይህ እውነታ ግን  በተፅዕኖና በሁከት ካልሆነ የብዙኃኑን ሕዝብ ቀልብ በሰላማዊና የምርጫ መንገድ ያገኛል ብሎ መገመት አዳጋች ነው፡፡ ወቅቱ ሲደርስ የሚታይ ቢሆንም!!

ዛሬም ቢሆን በአገራችን በርካታ አካባቢዎችና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተረጋጋ ፖለቲካዊ ሁኔታና ሰላም እንዳይሰፍን የታወኩት፣ በቅርቡ እንዳየነው ጥምቀትን በመሰሉ ሃይማኖታዊ በዓላት ላይ ሁከትና ግጭት ለመፍጠር እየተሞከረ ያለው መንስዔው የብሔር ንትርኩ ነው፡፡ መንግሥትም እንደ ሽግግር ወቅት አገር የሚመራ ኃይል፣ በኖረው አስተሳሳብ የሚነዳውን ትኩስ ኃይል የሚገራበት ፋታ ባለማግኘቱና እስከ ምርጫ ጊዜ መታገስ የፈለገ በመምሰሉ ነው፡፡ በዚህ መዘዝ የንፁኃን ሞት፣ መቁሰል፣ መፈናቀልና ዕገታ መታየቱና  አለመቆሙ ካላስቆጨን ምን ሊያንገበግበን ይሆን ብሎ መጠየቅ ግን የሁሉም ኃላፊነት መሆን አለበት፡፡

እርግጥ መቼም ሆነ የት የሰላሙና የአብሮነቱ ባለቤት ሕዝቡ ነው። ሕዝቡ በሚያየውና በሚሰማው ነገር ሲያምንበት ብቻ ሰላም፣ አንድነትና ልማት  ባሉበት ይቀጥላሉ ብቻ ሳይሆን ይበልጥ ይጎለብታሉ። ሰላምም ሆነ መቻቻልና አብሮነት  ከሌሉ ደግሞ አይደለም ሠርቶ ኑሮን ማሸነፍ ወጥቶ መግባትም ቢሆን የሚታሰብ አይደለም፡፡ በእውነቱ የሰላምን ዕጦትና አለመከባበር ገና በእንጭጩ ስንጋፈጥ፣ እየሆነ ያለውንም ችግር እንደ ማንቂያ ደውል መቁጠርም የዜጎች ኃላፊነት ሊሆን ይገባል፡፡  

አንድ የማይካድ ጭብጥ በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር በተለይ ባለፉት ሦስት አሠርት ዓመታት የብሔር ብሔረሰቦች የተናጠል ባህል፣ ታሪክ፣ ቋንቋና ሃይማኖት ይበልጥ ተዋውቀዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ያልተዋወቁ እነዚህ ፀጋዎችም ከራሱ ከየብሔረሰቡ አልፈው፣ በሌላው ማኅበረሰብ ዘንድ መተዋወቃቸውም የሚዘነጋ አይደለም፡፡ እነዚህ ተግባራት መልካም አጋጣሚዎች ናቸው፡፡

ይሁንና አገራዊ አንድነትና የኖረው አብሮነት ላይ በቂ ሥራ አልተሠራም፡፡ በዚህም የእርስ በርስ መስተጋብራችን እየተዳከመ፣ የክፉም ሆነ የደግ የጋራ ታሪካችን እየሳሳ መምጣቱ አይካድም ፡፡ እንዲያውም የአገዛዞች ጥፋት እንደ ሕዝብ በደል እየተቆጠረ፣ አንዳችን ለሌላችን አጋርና መከታ ሳንሆን፣  አጥፊና በዳይ እንደሆንን መቀንቀኑ፣ ብሎም ታሪክ ለፖለቲካ ዓላማ ከሚያመቸው ጥግ ብቻ እየተወሰደና እየተጣመመ መተረኩ፣ እነሆ ዛሬ የጉዟችን ሁሉ ፈተና የሆነው ችግር ዋነኛ ማጠንጠኛ ለመሆን በቅቷል፡፡ ከዚህ መውጣት ለሁሉችንም ግዴታ መሆን አለበት፡፡

በመሠረቱ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ይህንኑ የሕዝቦች መለያያትና ፀረ ዴሞክራሲያዊ የዘውግ ፖለቲካ አዙሪትን ለኢፍትሐዊነትና ለብዝበዛ የተጠቀመበት ኢሕአዴግ መራሹ የአገሪቱ መንግሥት፣ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጣ ተቀስቅሶበትም ዓይተናል፡፡ በተለይ ወጣቱ ኃይል በሥርዓቱ የመልካም አስተዳዳርና የዴሞክራሲ መጓደል፣ በልማትና ዕድገት መለያየት የተነሳ  በሚያየውና በሚሰማው ነገር ደስታን ለማጣት መገደዱ ነበር “ለውጥ ወይም ሞት!!“ ብሎ እንዲነሳ ያደረገው፡፡ ታዲያ ፖለቲከኛው እንዴት ከዚህ ተግዳሮት ተምሮ የተሻለ መንገድ መቀየስ ያዳግታዋል?

 እሱ ብቻ ሳይሆን በግራ ዘመም ዕሳቤ በተጠመደውና በቡድን (የብሔረሰብ) መብት ስም መቆሚያ መቀመጫ ያጣው ኅብረ ብሔራዊ ማንነት ያለውና የግል መብት የሚሻው ወገን፣ ሥርዓቱን ክፉኛ እንዳናጋውስ ተዘንግቶ ነው እንዴ እዚያው ላይ መቸከል የተፈለገው? የዜግነት እርካታውን በመነፈጉና ተስፋው እየተሟጠጠ በመምጣቱ ተቃውሞውን ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ (ከአገር ውስጥ እስከ ባህር ማዶ) በመግለጽ፣  የብሔር አገዛዙን  ከሥር ነቀል ለውጥ በመለስ እስከ መዋቅራዊ ለውጥ ድረስ ገፍቶ ያፈራረሰው፣ የሕዝብ አብሮነትና አንድነትን መሻት አልነበረም እንዴ?

ሕዝቡ ሰላሙን አጥብቆ ቢፈልገውም ደርሶብኛል ካለው በደል (ነጣጥሎ የመግዛትና ኢፍትሐዊ አስተዳዳር) እና የመልካም አስተዳደር ዕጦት አንፃር ተመልክቶ መንግሥትን በሕጋዊም፣ በሕገወጥም መንገድ መሞገቱስ ለምን ይዘነጋል? ይህን መመለስ ያልቻለ የኢትዮጵያዊያን ፖለቲከኞች ጉዞ ሄዶ ሄዶ መውደቁ የማይቀር ነው መባሉም ለዚህ ነው፡፡

ለውጥ በመሻት ስም በሕዝብና በአገር ሀብት ላይ ሁሉ የተፈጸመው ተግባር በሙሉ በየትኛውም አመክንዮ ልክ ነው ሊባል ባይቻልም፣ ሕዝቦችን በተለይም ወጣቶችን ገፍቶ እዚህ ደረጃ ላይ ያደረሳቸው በቂ ገፊ ምክንያት ነበራቸው። ከብዙዎቹ ምክንያቶች ተነጥሎ የማይታየው ፌዴራሊዝሙ በተሞላ መንገድ እየተተገበረ አለመሆኑና የሕዝቦችን አብሮነትና የአገር አንድነትን እየሸረሸረ የኖረው ትርክት ጎልቶ የሚታይ እንቅፋት ስለነበር መሆኑን መካድም ነውረኝነት ነው ፡፡

በእርግጥ መንግሥትም (ገዥው ፓርቲ) ችግሩን በአግባቡ ተረድቶ ጥልቅ ተሀድሶ በማድረግ፣ ለሕዝቡ እርካታ ጠንክሮ እንደሚሠራ በተለያዩ ጊዜያትና አጋጣሚዎች ከመግለጹ ባሻገር፣ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን የተሾሙት ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በበዓለ ሲመታቸው ዕለት ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያዊነትንና የጋራ ታሪካችንን በማጉላታቸው ሕዝቡ ከዳ እስከ ዳር በእምባ ከመራጨቱም በላይ፣ በሙሉ ድጋፍ ከጎናቸው መቆሙ የሚታወስ ነው፡፡ ለአብሮነትና ለፍትሐዊ እኩልነት ሕዝባዊ ቀናዒነት እንዳለውም አሳይቷል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ እንዳሉት ኢትዮጵያዊያን ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ አጥንታቸውን ከስክሰውና ደማቸውን አፍስሰው ሉዓላዊነቷን ያስከበሯትን አገር፣ የዛሬው ትውልድ ልዩነትን በማራገብና በጥላቻ ሊያፈርሳት አይገባም፡፡ “አገር የጋራ ናት!” ከተባለም የገዥው ፓርቲ አባሉም፣ አባል ያልሆነውም፣ የተቃዋሚውም ጭምር በመሆኗ ሁሉም በሰላም ሠርቶ፣ ውሎ የሚያድርባትና መብቱን የሚያስከብርባት፣  ግዴታውንም ያለ ጎትጓች የሚወጣባት ማድረግ ይኖርብናል ነበር ያሉት፡፡ ይህን ደግሞ ያለ አገራዊ አንድነት ማድረግ አንችልም በማለት፡፡

የተንደረደርበትን ስናጠቃልል ምንም ቢሆን ለአገር አብሮነትና ሰላም የሚበጀን  ከተካረረ ዘውጌ የፓርቲዎች ፖለቲካ ትግል ይልቅ ሰብሰብ ብለው፣ የተቀናጁና የተዋሀዱ የፖለቲካ ሰላማዊ ትግሎች መጀማመራቸው ነው፡፡ ጥላቻና ቂም እንዲሁም ቁርሾና ዕርቅ አልባ ትግልም ምናልባት በፅንፈኛ ወጣቶች የተደገፈ ቢመስልም፣ አዋኪና ብዙኃኑን የማያማልል መሆኑ ተገማች ነው፡፡ ስለሆነም ከእነ ጉድለቱም ቢሆን አገራዊ አብሮነትና አንድነትን በእኩልነትና በፍትሐዊ ተጠቃሚነት አጅቦ መከተልና መንከባከብ ነው ለማንም የሚበጀው፡፡  የተሰናሰልንበትን አገራዊ ማንነት ያጠበቀ የፖለቲካ ትግል መንደፉ አዋጭ ነው መባሉም ለዚህ ብቻ ነው፡፡

 ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ