Tuesday, October 3, 2023

የታገቱት ተማሪዎች የት ነው ያሉት? መልስ ያጣው የዜጎች ጥያቄ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህም ሆነ በፊት በአብዛኛው የኅብረተሰብ ክፍል ዘንድ ከሚነሱ መሠረታዊ ከጥያቄዎች መካል አንዱና ዋነኛው፣ ‹‹መንግሥት በሚፈለገው መጠንና ጊዜ ለአገሪቱ ዜጎች መረጃን በአግባቡ ለምን አያቀርብም?›› የሚለው ነው፡፡

በተለይ አንድ ዓመት ከስድስት ወራት ዕድሜ ያስቆጠረው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የአስተዳደር ዘመን በኩነቶች የተሞላ ከመሆኑ አንፃር፣ አፋጣኝ ዝርዝር መረጃና ማብራሪያ የሚሹ በርካታ ክስተቶች ተስተናግደዋል፡፡

በእነዚህ ሁሉ ጊዜያት ውስጥ ግን መንግሥት ዝምታን መምረጡ፣ ወይም ደግሞ የቢሆን መረጃዎች በተለያዩ ማኅበራዊ የትስስር ገጾች ተነዝተው ዜጎችን ውዥንብር ውስጥ ከከተቱ በኋላ በሚሰጡ መረጃዎች ነገሮችን ለመመከት ይሞከር ነበር፡፡

እንዲህ ያለው አካሄድ እንደማያወጣና መረጃ በጊዜውና በተገቢው መንገድ ለኅብረተሰቡ ማድረስ አገርን ከማረጋጋትና የችግሩን ምክንያትና መፍትሔ ለመረዳት ከሚጫወተው ሚና ባለፈ እያንዳንዱ ዜጋ መረጃን በወቅቱ ማግኘት መብቱ ሲሆን፣ መንግሥት ደግሞ ኅብረተሰቡን የተመለከቱ ማንኛውንም መረጃ የመስጠት ግዴታ አለበት የሚለውን የሕገ መንግሥት አንቀጽ በመጥቀስ መንግሥት ሚናውን እንዲወጣ ሲወተውቱ የሰነበቱ በርካቶች ናቸው፡፡

መገናኛ ብዙኃን በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መረጃ ለማግኘት የሚሄዱበት ርቀት ከቀን ወደ ቀን እየራቀና እየሰፋ መሄዱን በመጥቀስ፣ በርካታ የኅትመትም ሆኑ የብሮድካስት መገናኛ ብዙኃን ‹‹የመረጃ ያለህ!›› ማለት የዕለት ተዕለት ሥራቸው ሆኗል፡፡ የሚሰጥ መረጃ ካለም የግሉን የመገናኛ ብዙኃን ማግለሉ ተጠናክሮ የቀጠለ ይመስላል፡፡

በተለያዩ አንገብጋቢ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ለመስጠት ፈቃደኛ የማይሆኑ የመንግሥት ኃላፊዎች ማብራሪያ ለመስጠት ከፈቀዱም፣ የሚያገኙት የመንግሥት መገናኛ ብዙኃንን መሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ይህም የመገናኛ ብዙኃንን የሥራ፣ እንዲሁም የዜጎች መረጃ የማግኘት መብት መጣስ በመሆኑ በአስቸኳይ መፍትሔ ሊፈለግለት የሚገባ ጉዳይ መሆኑን የሚጠይቁ በርካቶች ናቸው፡፡

ዓመት ከመንፈቅ በሞላው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የአስተዳደር ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ የሚነሳውና መንግሥትን የሚያስተቸው ሌላው ጉዳይ ደግሞ፣ የመንግሥት ሰላምና ደኅንነትን ከማስከበር አንፃር የሚያሳየው የተለሳለሰ አቋም ነው፡፡

ከዚህ አንፃር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተደጋጋሚ የኃይል ዕርምጃ በመውሰድ የተፈጠሩና የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት መሞከር የተለመደ አካሄድ በመሆኑ፣ መንግሥት ትዕግሥትን መምረጡን በተለያዩ መድረኮች ሲገልጹ ተስተውሏል፡፡

ሆኖም ‹‹የመንግሥት ትዕግሥት የሚያልቀው መቼ ነው?››፣ ‹‹ዜጎች የመኖርና የመንቀሳቀስ መብታቸው ተገድቦ የመንግሥት በትዕግሥት ስም ሥርዓተ አልበኝነትን የሚፈቅደው እስከ መቼ ነው?›› እና ‹‹መንግሥት ሰላምና ደኅንነትን ማስጠበቅ ቀዳሚ ሥራው ሆኖ ሳለ፣ በትዕግሥት ስም ዜጎች የሚሰቃዩት ለምንድነው?›› የሚሉትና የመሳሰሉት ጥያቄዎች በአብዛኛው ኅብረተሰብ፣ የፖለቲካ ልሂቃን፣ እንዲሁም የሲቪል ማኅበራት መሪዎች መደመጥ ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡

መረጃ መስጠት ላይ እምብዛም የሆነው መንግሥት ግን ለእነዚህ ጥያቄዎች አጥጋቢ ምላሽ ሳይሰጥ በደል በበደል ላይ እየተከመረ፣ ያልተፈቱ ችግሮች እየተባባሱ፣ እንዲሁም ያልተመለሱ ጥያቄዎች እየጠነከሩ አሁን የተደረሰበት ደረጃ ላይ መገኘት ቅሬታዎች እየፈጠረ ነው፡፡

ከዚህ አንፃር የመንግሥት መረጃ አለመስጠትና ሰላምና ደኅንነትን አለማስከበር ኃላፊነቱን ካለመወጣቱ ባሻገር፣ አሁን የመንግሥትን ህላዌ ወደ መጠየቅ ተሸጋግሯል፡፡   

ተማሪዎቹ የት ነው ያሉት?

ሁለት ወራት ለሚጠጋ ጊዜ የደረሱበት ያልታወቀው የደምቢዶሎ ተማሪዎች ጉዳይ የመንግሥትን የደኅንነት መጠበቅ አቅም ጥያቄ ምልክት ውስጥ ያስገባ ሲሆን፣ በጉዳዩ ላይ መረጃ የሚሰጡ የመንግሥት ኃላፊዎች መረጃ መጣረስም ኅብረተሰቡን ውዥንብር ውስጥ ከቶታል፡፡

በዚህም ምክንያት፣ ‹‹ስለእህቶቻችን መጠየቅ አናቆምም››፣ ‹‹ተማሪዎቻችንን መልሱ››፣ ‹‹መንግሥታዊ ውንብድና ይብቃ›› እና ‹‹ተማሪዎቹ የት ገቡ?›› የሚሉና ተመሳሳይ ሐሳብ ያላቸውን መልዕክቶች ያዘሉ ጥያቄዎች ያነገበ የማኅበራዊ ትስስር ገጾች ዘመቻ ተጀምሮ፣ መንግሥት አስፈላጊውን መረጃ እንዲሰጥ በመወትወት ላይ ይገኛሉ፡፡

ከዚህ የማኅበራዊ ትስስር ገጾች ዘመቻ ከተነሱት አንኳርና መሠረታዊ ጥያቄዎች ባለፈም፣ የፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ እንዲሁም የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊን ስም በተደጋጋሚ በመጥቀስ፣ የተማሪዎቹን ሁኔታ አስመልክቶ መንግሥት መረጃ እንዲሰጥ ግፊት እንዲያደርጉ የሚጠይቁ ድምፆችም በርካቶች ናቸው፡፡

በዚህ ሁሉ ከፍተኛ የኅብረተሰቡ የመረጃ የማግኘት ጥያቄና መንግሥት ምን እያደረገ ነው የሚል ውትወታ ዝምታን የመረጠው የፌዴራል መንግሥት፣ የሰጠው መረጃም ጥያቄ ውስጥ የሚስገባውና የአቅሙንም ደካማነት ማሳያ እንደሆነ በመጥቀስ፣ ተስፋ የሚቆርጡ ዜጎች ቁጥር ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ ሲሄድ እየተስተዋለ ነው፡፡

በጥያቄዎቹ ማየልና መበርከት ልክ ግን የመንግሥት ምላሽ ምንም ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ በተለይ መንግሥት 21 ተማሪዎችን ማስለቀቁን የገለጹት የፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊው አቶ ንጉሡ ጥላሁን፣ ተለቀዋል ስለተባሉት ተማሪዎች ምንም ዓይነት ቀጣይ መግለጫዎች ወይም መረጃዎች አለማቅረባቸው በዜጎችና በመንግሥት መካከል ያለውን የጥርጣሬና ያለ መተማመን ደረጃ አጉኖታል፡፡

ከዚህ አንፃር በጉዳዩ ውስብስብነት የተነሳ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈጉት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር በሰጡት አስተያየት፣ ‹‹በመንግሥት በኩል የተሄደበት የድብብቆሽ ጨዋታ የመንግሥትን መታመን ጥርጣሬ ውስጥ ከመክተት ባለፈ፣ የፖለቲካ ቀውስ ምንጭም ሊሆን ይችላል፤›› ብለዋል፡፡ መንግሥት አስፈላጊውን መረጃ በወቅቱ መስጠቱ ችግሩን ከመቅረፉ ባለፈ፣ ሊከሰቱ የሚችሉ የፖለቲካ ቀውሶችንም ለመቆጣጠር ዓይነተኛ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡

እኚሁ ምሁር አክለውም፣ ‹‹መንግሥት ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የመረጠው የዝምታ መንገድ ዜጎችን ውዥንብር ውስጥ ከመክተት ባለፈ ለተለያዩ መላምታዊ ማብራሪያዎች በር እየከፈተ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ስለተፈጠረው ችግር ብቻ ሳይሆን፣ ስለአጠቃላይ የመንግሥት መረጃ የመስጠት ግዴታን በመጥቀስ የጥያቄዎቹን ዓይነትና ብዛት ዘርፈ ብዙ ያደርገዋል፤›› በማለት፣ በታገቱት ተማሪዎች አማካይነት የመንግሥት መረጃ የመስጠት ብቃትም ተያይዞ ጥያቄ ውስጥ መግባቱን ያወሳሉ፡፡

የተለያዩ ወቀሳዎችና ትችቶች እየተሰነዘሩበት የሚገኘው መንግሥት ግን፣ አሁንም ቢሆን በታገቱት ተማሪዎች ጉዳይ ይህ ነው የሚባል ተጨባጭ መረጃ አልሰጠም፡፡

ከዚህ አንፃር የመንግሥትን ጥንካሬ ጥያቄ ውስጥ የሚከቱ ግለሰቦች መንግሥት መረጃ አልሰጠም ከማለት፣ መንግሥት መረጃ አለውን? ወደሚል ጥያቄ ተሸጋግረዋል፡፡ እየተፈጠረ ካለው ማኅበራዊ ግፊት አንፃር የመንግሥት ዝምታን መምረጥ የግለሰቦቹን ጥያቄ ቆም ብሎ ለማሰብ የሚያስገድድ ነው፡፡

በማኅበራዊ ትስስር ገጾች የጀመረው፣ የ‹‹ተማሪዎቻችንን መልሱ›› ዘመቻን በሰብዓዊ መብቶች ላይ የሚሠሩ በርካታ ተቋማት በመቀላቀልና ጥያቄያቸውን በማስተጋባት ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችም በጉዳዩ ላይ ያላቸውን አቋም ማሰማት ጀምረዋል፡፡

ለአብነት ያህልም የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የ2012 ዓ.ም. የበጀት ዓመት የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸምና ወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፣ የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ ቁጥር 590/2000ን በመጥቀስ መንግሥት የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ዕገታን አስመልክቶ ዝርዝር መረጃ እንዲሰጥ አሳስቧል፡፡

በዚህም መሠረት የታገቱ የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን አስመልክቶ፣ ስለአጋቾቹ ማንነትና በመንግሥት ስለተወሰደው ዕርምጃ ለሕዝብ የተሰጠው መረጃ ምልዑነት የጎደለውና እጅግ የዘገየ መሆኑን በመጥቀስ፣ መዘግየቱ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ የመንግሥት አካላት የሚሰጡ መረጃዎች እርስ በርሳቸው የማይጣጣሙና ይመለከታቸዋል የተባሉ አካላት ወደ ሌላው የመግፋትና እኔን አይመለከትም የሚለው የበዛበት ችግር ሆኗል በማለት ስላለው የመረጃ ክፍተት አብራርቷል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ተለቀቁ ስለተባሉ ተማሪዎች መንግሥት ለማሳያነት ያቀረባቸው ማረጋገጫዎች አለመኖራቸውን በመጥቀስ በዚህም ምክንያት ሕዝብ፣ ‹‹በመላምት እንዲያስብና በመንግሥትና በሕዝብ መካከል ጥርጣሬ እንዲፈጠርና አለመተማመን እንዲጠናከር አድርጓል፤›› በማለት የመረጃ ዕጦት የፈጠረውን ችግር ለማሳየት ሞክሯል፡፡  

ስለሆነም አሁንም ቢሆን የሚመለከተው የመንግሥት አካል በጉዳዩ ላይ ግልጽ መረጃ ሊሰጥ እንደሚገባ ጠይቋል፡፡

‹‹ተማሪዎቹን ለማስለቀቅ እየተደረገ ያለውን ጥረት አስመልክቶ ምንም ዓይነት መረጃ ስለሌለ በዜጎች ያውም በሴቶች ላይ የደረሰን በደል ለማስቆም መንግሥት ተለሳላሽነት እንዳሳየ አብዛኛው ሕዝብ መደምደሚያ ላይ እየደረሰ በመሆኑ፣ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት መረጃ በመስጠትም ይሁን ችግሩን ለመፍታት ረገድ የተፋጠነ ምላሽ ይስጡ፤›› በማለት፣ ተቋሙ ማሳሰቢያ አዘል ጥሪውን አስተላልፏል፡፡

ከዕንባ ጠባቂ ተቋም ባለፈም አምስት በሰብዓዊ መብቶች ላይ የሚሠሩ ተቋማትም የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎቹ ዕገታ ጉዳይ እንዳሳሰባቸው በመጥቀስ፣ መንግሥት የዜጎችን የመንቀሳቀስ መብት እንዲያስከብር፣ እንዲሁም የታገቱት ተማሪዎች ስላሉበት ሁኔታ ለሕዝቡ በአስቸኳይ መረጃ እንዲሰጥ አሳስበዋል፡፡

ከእነዚህ ተቋማት ውትወታ ባለፈም በተለያዩ የአማራ ክልል ከተሞች ማክሰኞ ጥር 19 ቀን 2012 ዓ.ም. ተማሪዎቹ በአስቸኳይ እንዲለቀቁ የሚጠይቁ ትዕይንት ሕዝቦች ተካሄደዋል፡፡ በቀጣይም በተለያዩ የክልሉ ከተሞች ተመሳሳይ ሠልፎች እንደሚካሄዱ ታውቋል፡፡

ከዚህ አንፃር የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ሠልፉን እንደሚደግፍ በማስታወቅ፣ ‹‹የአማራ ክልል መንግሥትና ማዕከላዊ መንግሥቱ ላሳዩት የበዛ ቸልተኝነት ተጠያቂነታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ድርጊቱን ላልተገባ የፖለቲካ ቁማር ከማዋል ተቆጥበው ኃላፊነታቸውን ይወጡ፤›› የሚል ጥብቅ ማሳሰቢያ ሰጥቷል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም፣ ‹‹መላው የአማራ ሕዝብ ቀጣይ በልጆቹ ዙሪያ መንግሥት የሚሰጠውን ምላሽ እየተከታተለ ለቀጣይ ትግሎችም ራሱን ያዘጋጅ፤›› በማለት ጥሪ አስተላልፏል፡፡

ከአብን በተጨማሪም የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ማክሰኞ ጥር 19 ቀን 2012 ዓ.ም. ‹‹ዘርን መሠረት ያደረገ ጥቃት በአስቸኳይ ይቁም›› በሚል ርዕስ ባወጣው መግለጫ፣ መንግሥት በጉዳዩ ላይ መረጃ ከመስጠት አንፃር የሄደበት አካሄድ እጅግ እንዳሳዘነው አስታውቋል፡፡

‹‹በደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ይማሩ የነበሩ ንፁኃን ተማሪዎችን ከ50 ቀናት በላይ አግቶ ደብዛቸውን በማጥፋትና ስለሁኔታው የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት እውነታውን ለሕዝብ ማሳወቅና ከድራማው በተስተጀርባ እየተወኑ ባሉ ቡድኖች ላይ አስፈላጊውን ዕርምጃ ወስዶ እውነታውን ለሕዝብ ማሳወቅ ሲገባው፣ በየጊዜው እርስ በርስ የሚጣረስና የሚምታታ፣ እንዲሁም የተድበሰበሰ መረጃ ሲሰጥ መስማታችን እጅግ አሳዝኖናል፤›› በማለት፣ መንግሥት በአስቸኳይ ዝርዝር መረጃ ለሕዝቡ እንዲያቀርብ አሳስቧል፡፡

በደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ የታገቱ ተማሪዎች ጉዳይ አጠቃላይ አገሪቱ የምትገኝበትን የፖለቲካ ሁኔታ ማሳያ አድርገው የሚያቀርቡት በርካቶች ሲሆኑ፣ መንግሥት የዜጎችን ደኅንነትና ከቦታ ቦታ መዘዋወር መብትን፣ እንዲሁም መረጃ የመስጠት ግዴታው በቅጡ እንዲወጣ የሚጠይቁ ድምፆች በርክተዋል፡፡ መንግሥትም ዝምታውን መርጧል፡፡ ዝምታው በረዘመ ቁጥር ግን የሚፈጥረው አገራዊ ቀውስ ከፍተኛ እንደሚሆን የሚገልጹ በርካቶች ናቸው፡፡ መንግሥት በጉዳዩ ላይ የሚሰጠው ምላሽና ማብራሪያ እየተጠበቀ ነው፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -