Wednesday, July 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ንግድ ምክር ቤት ለፖለቲካ ትኩረት የሰጠበት ጅምር

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በወቅታዊ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ባዘጋጀው የፓናል ውይይት የኢትዮጵያ ገጽታዎች በሰፊው ተቃኝተዋል፡፡ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የሰላም ጉዳይ በርካቶችን እያሳሰበና እጅጉን እያሠጋ እንደመጣ በትንታኔ ታይቷል፡፡

የንግድ ሥራ ማከናወን ያልተቻለበት፣ በተለይም ከገቢና ወጪ ንግድ ጋር የተያያዙ እንቅስቃሴዎች እየተስተጓጎሉ፣ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ችግር እየባሰበት መምጣቱ ተደጋግመው የሚወሱ ችግሮች ለመሆናቸው የንግድ ምክር ቤቱ ዋና ጸሐፊ አቶ ጌታቸው ረጋሳ በውይይት መድረኩ ወቅት ገልጸዋል፡፡ ፖለቲካዊ አለመረጋጋቶች ኢኮኖሚውን እንደሚገባው እንዳይንቀሳቀስ ሳንካ እየሆኑበት መምጣታቸውን አቶ ጌታቸው አውስተዋል፡፡

በሌላ በኩል የግሉ ዘርፍ አመጣጥ የዕዝ የኢኮኖሚ ሥርዓትን ሲከተል በነበረ ፖለቲካዊ ሥርዓት ውስጥ አልፎ በመሆኑ፣ ዕድገቱም ሆነ ህልውናው በአብዛኛው ፖለቲካዊ ጥገኝነት ውስጥ የሚወድቅበት አዝማሚያ እንደሚበረክት በስብሰባው ተመልክቷል፡፡ በመሆኑም በአዲስ አስተሳሰብና ለውጥ ከወቅቱ ሁኔታ ጋር መጓዝ የሚችልበትን አካሄድ ዘርፉ በማዘጋጀት በአኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ መድረኮች ተወዳዳሪ ለመሆን መዘጋጀት የግሉ ዘርፍ ግዴታ እንደሆነ ዋና ጸሐፊው ገልጸዋል፡፡

‹‹የግሉ ዘርፍ የአንድ ፖለቲካ ሥርዓት፣ ፓርቲ ወይም ብሔር ላይ ጥገኛ  መሆን የለበትም፤›› ያሉት አቶ ጌታቸው፣ በውድድር የሚያምን፣ የአገርን ጥቅም የሚያስቀድም፣ ሥነ ምግባር ያለው፣ ዘመናዊ የግል ዘርፍ በዚህ ወቅት እጅጉን እንደሚያስፈልግ በማሳሰብ፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ማስፈንም አሌ እንደማይባል አስታውቀዋል፡፡

የፖለቲካና የግሉ ዘርፍ

የግሉ ዘርፍ ዕድገት ከአገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ ጋር በእጅጉ የተሳሰረ እንደሆነ በመግለጽ፣ ንግድ ምክር ቤቱ ከኢኮኖሚ ባሻገር በፖለቲካዊ ሐሳቦች ላይ የውይይት መድረክ መዘርጋት እንደሚያስፈልግ በማመኑ ያካሄደው ጅምር የውይይት መድረክ እንደሆነ ወደፊትም እንደሚዘጋጅ ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹በፖለቲካው መስክ ያልተመለሱ በርካታ ጉዳዮች እንዳሉ ለሁላችንም ግልጽ ነው፡፡ ይልቁንም በሕዝባዊ እንቅስቃሴና በፖለቲካ መረጋጋት፣ በጠንካራ መንግሥትና በሕግ የበላይነት፣ በዴሞክራሲና በመልካም አስተዳደር፣ በዴሞክራሲና በአገራዊ ማንነት መካከል ያሉ መስተጋብሮች ወሳኝ ጉዳዮች ናቸው፤›› ያሉት አቶ ጌታቸው፣ በዚህ ረገድ ነጋዴው ማኅበረሰብ በፖለቲካውም መስክ ቀጥተኛ ተሳታፊ እንዲሆን ንግድ ምክር ቤቱ መድረኩን እንዳመቻቸ ተናግረዋል፡፡

የንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መሰንበት ሸንቁጥ በበኩላቸው፣ ለሚታዩ ችግሮች መፍትሔ ለመስጠት ሲባል ምክር ቤቱ ፖለቲካ ቀመስ ውይይቶች ግፊት እንዲያደርጉ አስቦ ማሰናዳቱን አስታውቀዋል፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ለዓመታት ካለው የሁለት አኃዝ ዕድገት ባሻገር፣ በአሁኑ ወቅት በማክሮ ኢኮኖሚው ላይ ተግዳሮትና ጥላ አጥልቶበታል፤›› ያሉት ወ/ሮ መሰንበት፣ በሰላም ዕጦት ምክንያት ነጋዴው ማኅበረሰብ ተጎጂ እንደሆነና በሚከሰቱ ችግሮች ውስጥም ይኼው ሲታይ እንደቆየ አስታውሰዋል፡፡ ሰላም ለንግድና ለኢንቨስትመንት እስትንፋስ  በመሆኑ፣ ንግድ ምክር ቤቱ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ አሳታፊ ውይይቶችን ወደፊት እንደሚያዘጋጅ አስታውቀዋል፡፡  

‹‹በአገራችን እዚህም እዚያም በሚከሰተው የሰላም ዕጦት ምክንያት የተስተጓጎሉ የልማት ሥራዎች ከዚህ በኋላ እንዳይከሰቱ ለማድረግና መጪው አገራዊ ምርጫ ሰላማዊ እንዲሆን የንግዱ ማኅበረሰብ በራሱ ተነሳሽነት ከባለድርሻ አካላት ጋር መተባበር አለበት፤›› ያሉት ፕሬዚዳንቷ፣ ስለሰላም አበክሮ መሥራት ቸል የማይባል ሥራ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡

የግል ዘርፉን ከወቅቱ የኢኮኖሚው ፈተናዎችና ዕድሎቹ ጋር ያቆራኙ ሐሳቦች በተንሸራሸሩበት የምክክር መድረክ ላይ የመወያያ ጽሑፍ ያቀረቡት የግጭት አፈታትና ትንተና የሕግ ባለሙያው አቶ ሰይፈ አያሌው፣ ከኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ የፖለቲካ መፍትሔ የሚጠይቁ ጥያቄዎች እንዳሉ በመግለጽ ስለሰላም አብራርተዋል፡፡ ለሚነሱት ጥያቄዎች የመጨረሻ ምላሽ ባይሰጥ እንኳን የተወሰነ የፖለቲካ ስምምነት እንደሚያስፈልግ በማስገንዘብ፣ ለሰላም መሥፈን አስፈላጊ ያሏቸውን ሐሳቦች ጠቅሰዋል፡፡ ልማት ለሰላም ወሳኝ ሚና እንዳለው ያወሱት አቶ ሰይፈ፣ የረሃብና የድህነት  ችግሮች በተንሰራፋበት ሁኔታ ሰላም ሊመጣ እንደማይችል ሞግተዋል፡፡

የንግድ ሚዛን ጉድለት፣ የዋጋ ንረት፣ ከፍተኛ የዕዳ ጫና፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ ኢፍትሐዊ የንግድ ውድድርና የመሳሰሉት ችግሮች ኢኮኖሚውን አላላውስ ያሉ መሠረታዊ ችግሮች እንደሆኑ የገለጹት ወ/ሮ መሰንበት በበኩላቸው፣ የበጀት አጠቃቀምና የገንዘብ ፖሊሲ ትግበራዎች ላይ የታዩ መሠረታዊ ክፍተቶችና ችግሮች በርካታ እንደሆኑ በማብራራት ለሰላም መታጣት አስተዋጽኦ ስለማድረጋቸው ተናግረዋል፡፡ የተዛባ የገንዘብ አቅራቦት፣ ከውጭ ምንዛሪ ገንዘቦች አንፃር የብር የመግዛት አቅምና የምንዛሪ ምጣኔው ማቀሽቆልቆል፣ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት መመናመን፣ የሸቀጦችና የአገልግሎቶች ዋጋ ንረትና ግሽበት አገሪቱን እየተፈታተኑ ከሚገኙ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ውስጥ ጎልተው የሚታዩት ናቸው፡፡

‹‹ንግድ ዓለም አቀፋዊ በመሆኑ ዘርና ጎሳን መሠረት አያደርግም፡፡ ዴሞክራሲ፣ ሰላም፣ ሰላም ስለተባለ ለውጥ አይመጣም፡፡ ዴሞክራሲ ስለተቀነቀነም ዴሞክራሲ አይመጣም፡፡ ነፃ ገበያ ወይም ካፒታል ሥርዓትን እንከተላለን ስላልን አናመጣውም፤›› የሚሉት አቶ ሰይፈ፣ ይህንን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠየቅ የሚበዛበትን ቁርኝት በፖሊሲ ምላሽ ሊያገኝ ስለሚችልበት አግባብ ያብራራሉ፡፡ በሰላም አስፈላጊነት ላይ ስምምነት ካለ የመጀመርያው ዕርምጃ ምን ይሁን የሚለው ጥያቄ ላይ መግባባት እንደሚያስፈልግ በማውሳት፣ ሰላም በጦር ሠራዊት ብዛት ሊረጋገጥ እንደማይችል በከርሞ ብሒል ሙግታቸውን ያሟሻሉ፡፡

ሰላምና የሕግ የበላይነት

ለሰላም መሥፈን ወሳኝ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል የሕግ የበላይነት እንደሆነ  የሚጠቅሱት አቶ ሰይፈ፣ መንግሥት ሕግ እንዲያስከብር መጠየቅ ብቻም ሳይሆን፣ ዜጎች በተለይም ደግሞ የግሉ ዘርፍ ተዋንያንም በሕግ የሚዳኝ ግንኙነት ሊኖራቸው እንደሚገባ ይጠይቃሉ፡፡ ሲያብራሩም ገበያው ሕግ ከገዛው፣ ሕገወጥነትን መግታት የሚችልበት የዲሲፕሊን ሥርዓት ካለው ሕግ ማክበርም ማስከበርም ተቋማዊ ገጽታ እንደሚላበስ በመአክንዮ ሐሳባቸውን ያያይዙታል፡፡

የፖለቲካ ፍጥጫ ጉዳይ ሲነሳ፣ በኢትዮጵያ በርካታ የጦርነት ታሪኮች እንደሚተረኩ፣ ከድህነትና ከእርስ በርስ ግጭት ጋር የተያያዙ፣ ከማንነት ወይም ከብሔር ጥያቄ አኳያም ላለፉት 27 ዓመታት ውስጥም ሲታዩ እንደቆዩ አቶ ሰይፈ፣ በ1950 እና በ1960ዎቹ የኢትዮጵያ ሁኔታ በተማሪዎች ተጀምሮ በአብዛኛው አርሶ አደርና በሠራተኛው ሲነሳ የቆየው ጥያቄ ኢኮኖሚያዊ ገጽታ እንደነበረው፣ በፖለቲካ ጎኑ ግን ከኢትዮጵያ የሥርዓተ መንግሥት ግንባታ ጋር እንደሚገናኝ፣ የማንነት ጥያቄ በምን አግባብና መንገድ መፈታት እንዳለበት ማየት እንደሚያስፈልግ አውስተዋል፡፡ አቶ ሰይፈ፣ ‹‹እንዲህ ያሉ ጥያቄዎች ገለል መደረግ የለባቸውም፡፡ በተነሱ ቁጥር ማንኳሰስም አያዋጣም፤›› ይላሉ፡፡  

በአቶ ሰይፈ ሙግት የፌዴራሊዝ ሥርዓት ሙከራ ኢሕአዴግ ሥልጣን ስለያዘ ብሎም ሥልጣን ስለፈለገ ብቻ ሲያደርገው የቆየ ጉዳይ አይደለም፡፡ ቀድሞም የነበረ ግፊትና ጥያቄ እንደሆነ አውስተዋል፡፡ በፌዴራሊዝም ሥርዓት የብሔር ወይም የማንነት ጥያቄ ላይ ምላሽ ለመስጠት ተሞክሮ በተወሰነ ደረጃ ጥያቄው መመለሱን የሚያምኑት አቶ ሰይፈ፣ በሌላ ጎኑ ግን የግጭት መንስዔ ሆኖ እንደሚታይም ያምናሉ፡፡ ይሁን እንጂ በብሔር ወይም በማምነት ፖለቲካ ምክንያት አሁን እየመጣ ያለው አደገኛ ሁኔታና በተለያዩ አካባቢዎች የሚታዩ ግጭቶች ኢከኖሚያዊ ቀውስም እያስከተሉ እንደሚገኙ፣ የነጋዴውን ህልውናም እየጎዱ እንደሚገኙ በማስታወስ ችግሩ እንዴት ይፈታ ለሚለው ምላሹ ‹‹በአሳታፊነትና በአቃፊነት›› በሚደረግ ጥረት እንደሆነ አመላክተዋል፡፡

‹‹በየቦታው የተከሰቱትን ግጭቶች ካስተዋልናቸው የብሔር ወይም የዘር ጥያቄ ቢመስሉም ውስጣቸው ያለው ግን የተጠቃሚነት ጥያቄ ነው፤›› የሚሉት አቶ ሰይፈ፣  የተጠቃሚነት ጥያቄ አፍጥጦ መውጣቱ በየአደባባዩ እንደሚታይ አስታውቀዋል፡፡ በመሆኑም የግጭቶቹ መሠረታዊ መነሻ የኢኮኖሚ ጥያቄ ከሆነ ምላሹና ዋቢው የግሉ ዘርፍ ሚና እንደሆነ ለማሳየት ሞክረዋል፡፡

ንግድ በማንነት መታወቂያ ሳይሆን በኢኮኖሚ ጥቅምና ትርፍ እንደሚመራ የሚገልጹት አቶ ሰይፈ፣ በኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ዙሪያ ጥያቄዎች እንዲነሱ ግፊት ማድረግና ጥያቄው መልስ የሚያገኝበትን መፍትሔ ማፈላለግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ከኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለመሆን ምላሹ ገበያ መር የኢኮኖሚ ሥርዓትን መከተል ነው ወይ? በማለት ይጠይቃሉ፡፡ ይሁን እንጂ ገበያው ያሉበትን ችግሮች ራሱ እያረመና ችግሮቹን እያሻሽለ አቅርቦትና ፍላጎትን እያጣጣመ የገበያ ውድቀትን ያርቃል የሚለው ርዕዮተ ዓለም ለታዳጊ አገሮች እንደማይሠራ ጥናቶች እንደሚደግፏቸው አቶ ሰይፈ ይሞግታሉ፡፡

ጽሑፍ አቅራቢው የኢኮኖሚ ጥናቶች የገበያ ኃይሎች ራሳቸውን በራሳቸው ያርማሉ የሚባለው ጉዳይ ለሦስተኛው ዓለም አገሮች ስለማይሠራ ‹‹አንዳንድ ጊዜ መራር የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ይታያል፤›› ይላሉ፡፡ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት በኢትዮጵያ ብቻም ሳይሆን፣ በበርካታ የአፍሪካና የእስያ አገሮች ውስጥ እንደሚንፀባርቅም ያወሳሉ፡፡

ይሁን እንጂ በጣልቃ ገብነትና በገበያ የበላይነት መካከል ሦስተኛ መንገድ እንዳለ ሲያብራሩም፣ ‹‹ሙሉ ለሙሉ መንግሥት መር ያይደለ፣ ሙሉ ለሙሉም ገበያ መር ያልሆነ፣ ሦስተኛው መንገድ የሁለቱ ቅይጥ ወደሆነ የኢኮኖሚ ሥርዓት ያመዘነ፤›› አካሄድ በዓለም በሰፊው እንደሚታይ ያብራሩት ባለሙያው፣ ይህም ለአብዛኛው ደሃ ሕዝብ በጥቂቱም ቢሆን ከፍ ከፍ የሚልበትን ዕድል እንደሚፈጥርለት ይገልጻሉ፡፡ ይህ እንዲሆን ግን መንግሥት ከግሉ ዘርፍ ጋር በሚኖረው ስትራቴጂካዊ ቁርኝት ነው ይላሉ፡፡ ‹‹መንግሥት ይደግፈዋል፡፡ ማበረታቻ ይሰጠዋል፡፡ በጣም ተከላካይ የሆነው ፖሊሲ ይህ ነው፡፡ ስለሊበራሊዝም ሲወራ የሚነሱ ሥጋቶችም እነዚህ ናቸው፡፡ ለማነው ኢኮኖሚውን ክፍት የምናደርገው የሚለው ጥያቄ መታየት አለበት፤›› በማለት፣ የመንግሥትን የሰሞንኛ አካሄድ በአጽንኦት ያሳሰቡት አቶ ሰይፈ፣ የውጭ ኩባንያዎች ገብተው እንዳሻቸው የሚሆኑበት ሥርዓት ተዘርግቶ አገር በቀል የንግድ ተቋማት እንዲከስሙ የሚያደርግ አካሄድ እንዳይፈጠር አሳስበዋል፡፡

ከዚህ በመነሳትም፣ ‹‹የኢንቨስመንት ፖሊሲዎች ለአገር ውስጥ ያደሉ ቢሆኑ ምክንያታዊ ነው፤›› የሚል እምነትም አላቸው፡፡ ‹‹በውጭ ኢንቨስትመንት ብቻ ያደገ አገር የለም፡፡ አገርን ማሳደግ የሚችለው አገር በቀል ባለሀብት ብቻ ነው፤›› የሚለውን አመለካከትም አንፀባርቋል፡፡

ለኢኮኖሚው ውጤታማነት አንገብጋቢ እንደሆነ የጠቀሱት የሕግ የበላይነትን ማሥፈን ነው፡፡ በዚህ ረገድ ብዙ ለውጥ እንዳልታየ ጠቅሰዋል፡፡ የሕግ ወይም የፍትሕ ተቋማት የመንግሥት ተቋማት በመሆናቸው ከፓርቲ ወገንተኝነት በመውጣት በመጣውም፣ በሄደውም፣ የማይለዋወጡ የተቋም ማንነት ሊኖራቸው እንደሚገባ ጠይቀዋል፡፡ ‹‹በእኛ አገር ታሪክ ተቋማቱ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የተሳሰሩ ናቸው፡፡ በጥቅምና በአፈጻጸም ትስስር አላቸው፡፡ ስለዚህ ፖለቲካ ፓርቲ ሲታመም ሁሉም ነገር አብሮ ይታመማል፤›› በማለት የፓርቲዎችና የፍትሕ ተቋማት ከመንገድ የወጣ ግንኙነት ሊስተካከል እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡ ተቋማት በነፃነት መሥራት የሚችሉበት  አቅም እንዲኖራቸው፣ ፓርቲዎችም ከፍትሕና ከሌሎች ተቋማት ተፅዕኖ ነፃ ሆነው በመሥራት፣ ለግል ዘርፉ ማደግ ለኢንቨስትንት ተገማች ሥርዓት መሥፈን ሚናቸውን እንዲወጡ ባለሙያው ጠይቀዋል፡፡

የግሉ ዘርፍ ለፖለቲካ መረጋጋት እንዴት መንቀሳቀስ አለበት? ለሚለው ጥያቄ ዘርፉ ለጥቅሙ መንቀሳቀስና መረዳዳት እንደሚጠበቅበት ተወስቷል፡፡ በተዋረድ ተደራጅቶና ይመለከቱኛል በሚላቸው ጉዳዮች ሁሉ ላይ ንቁ ተሳትፎ እንደሚጠበቅበት ተወስቷል፡፡ ነጋዴዎች ከፖለቲካ እጃቸውን ሰብሰብ ማድረግ በአሁኑ ወቅት የማያስኬድ ምርጫ እንደሆነ፣ ይልቁንም ወደ ፖለቲካው መድረክ ቀርቦ ጉልህ ሚና መጫወት እንደሚያስፈልግ አቶ ሰይፈ ይሞግታሉ፡፡ ‹‹አሁን ባለንበት ሁኔታ በጣም የተካረረ የማንነት ጥያቄ እየተነሳ ነው፡፡ ከዚህ በፊትም ሲነሳ ነበር፡፡ ከአሁን በኋላም ስለሚኖር ይህንን በመፍታቱ ረገድ የግል ዘርፉ ሚና አለው፤›› በማለት ነጋዴው በፖለቲካዊ መድረኮች ላይ ተሠላፊ እንዲሆን ጠይቀዋል፡፡

አገር በቀል ባለሀብት

እንዲህ ያሉ ሐሳቦችን ከምክር ቤቱ ኃላፊዎችና ከጽሑፍ አቅራቢው ከተሰነዘሩ በኋላ ተሳታፊዎችም ጥያቄዎችን አንስተው ነበር፡፡ በኢንዱስትሪ መስክ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ገሸሽ እየተደረጉ ነው የሚለውን ጨምሮ፣ ለውጭ ኢንቨስትመንት ከሚገባው በላይ ቦታም ድጋፍም እንደሚሰጠው፣ በዚህም አገር በቀሉ ትኩረት እያጣ መምጣቱን ያነሱ ነበሩ፡፡ በዚህ ጉዳይ ምላሽ የሰጡት አቶ ሰይፈ፣ ለአገር በቀል አምራቾች መንግሥት ድጋፍ መስጠት ግዴታው እንደሆነ ገልጸው፣ እንዲህ ያለው ጥያቄ በአግባቡ እንዲመለስላቸው ግን የዘርፉ ተዋንያን ተደራጅተው ለጥቅማቸው መቆም እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል፡፡

የመንግሥት ትኩረት ለውጭ ኩባንያዎች ሆኗል ለሚለው ጥያቄም፣ ‹‹መንግሥት ይህንን አድርጓል? አላደረገም? ማለት ብቻ ሳይሆን፣ በማስረጃ  በጥናት አስደግፎ ይህ ችግር እየታየ ነው ብሎ በማሳየት መንግሥት ፖሊሲውን እንዲያስተካክል ለማድረግ ተራጅቶ መቅረብ ያስፈልጋል፤›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

በመድረኩ ‹‹ኢኮኖሚው ፖለቲካውን ሊመራው ሲገባ፣ ፖለቲካው ኢኮኖሚውን እየመራው ነው፣››፣ ‹‹የመንግሥት የበላይነት ያለበት የኢኮኖሚ ሥርዓት አሁንም አልቀረም፤›› የሚሉ ሐሳቦችም ተሰንዝረዋል፡፡

በፖለቲካውም በመንግሥትም በኩል ነጋዴው ላይ ከሚደርሱበት ጫናዎች ጠንካራ የንግድ ምክር ቤት አለመኖሩ አንዱ ምክንያት እንደሆነ አስተያየት የሰጡም ነበሩ፡፡ በሚወጡ ሕጎችና ፖሊሲዎች ላይ ንግድ ምክር ቤቱ የበኩሉን እየተወጣ አይደለም የሚሉ ሐሳቦች ቢሰነዘሩም ወ/ሮ መሰንበት ግን ነገሩ ወዲህ ነው ይላሉ፡፡ ችግሩ የንግድ ምክር ቤቱ ብቻ እንዳልሆነ፣ እንዲያውም ተደራጅቶ መፍትሔ ከመፈለግ በተናጠል ከመንግሥት አካላት ጋር ‹‹በመሞዳሞድ ጉዳይ ከማስፈጸም›› ጋር የሚያያዙ የነጋዴው ብቻ ችግሮች እንደሚታዩ በማውሳት ነጋዴዎቹን ወርፈዋል፡፡

‹‹የሚገርመው ነገር በሌላው አገር ንግድ ምክር ቤት ማለት የፖለቲካ ፓርቲዎችን የሚጥልና የሚያነሳ ነው፡፡ የንግድ ምክር ቤት አወቃቀርና አደረጃጀት ያለው አቅምና መብት በሕግ የተቀመጠና መንግሥትም የሚፈራው ነው፤›› ያሉት ፕሬዚዳንቷ፣ የንግዱ ማኅበረሰብ መደራጀት አለበት በሚለው ሐሳብ እንደሚስማሙ፣ ነገር ግን በኢትዮጵያ ሁኔታ ከመደራጀትና መብትን በጋራ ከማስጠበቅ ይልቅ  ጉዳያቸውን በግልና በተናጠል፣ በእግርም በእጅም የማስፈጸም አካሄድ ሰፊ እንደሆነ በማንሳት ምክር ቤቱ በዚህ ረገድ ከሚወክላቸው አባላት ሳይቀር፣ ሚናውን በሚገባ የማይገነዘቡ በእሳቸው አባባል ‹‹የሚንቁት›› እንዳሉ በመግለጽ፣ ‹‹እንዴት ነው ታዲያ ጠንካራ መሆን የሚቻለው?›› ብለዋል፡፡ ተደራጅቶ ድምፁን በአንድነት ከማሰማት ይልቅ፣ ለንግድ ምክር ቤቱ መጠናከርና አቅም መገንባት ከመተባበር ይልቅ፣ ለሌሎች በተለይም ለፖለቲከኞች ያደሉ ነጋዴዎች እንደሚታዩ ወ/ሮ መሰንበት ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡ የመንግሥት አካላትም የንግድ ምክር ቤቱ ሊያያቸው የሚችሉ ጉዳዮችን በተናጠልና በግለሰብ ደረጃ ማየት እንደሚመርጡ ወ/ሮ መሰንበት ገልጸዋል፡፡ ‹‹ምክር ቤቱ ጠንካራ የሚሆነው አባላቱ ጠንካራ ሲሆኑ ነው፡፡ ምክር ቤቱ አባላቱን ይዞ በተናጠል ሄጄ ጉዳይ አላስፈጽምም፡፡ በምክር ቤቱ በኩል ጉዳዩ ይምጣልኝ የሚል አካል መፈጠር አለበት፤›› ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች