Tuesday, April 23, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

በኢሕአዴግ መቃብር ላይ የኢሕዴግን ድል?

(የመጽሐፍ ግምገማ)

ርዕስ- LAYING THE PAST TO THE REST

       The EPRDF and the Challenges of Ethiopian State-Building

ገጽ-355

አሳታሚ-Hurst & company,London

የታተመበት ዓ.ም- ኅዳር 2012 ዓ.ም.

ደራሲ- ሙሉጌታ ገብረሕይወት በርሔ (ዶ/ር)

ገምጋሚ- በኃይሉ ሚዴቅሳ

የሕወሓት/ኢሕአዴግ ትጥቅ ትግል የኢትዮጵያን የፖለቲካ ርዕደ መሬት ያንቀጠቀጠ መሆኑን መካድ አይቻልም፡፡ አገሪቱን በአዲስ የአስተዳደር ዘይቤ፣ ሥልትና ትርክት እንድትቆም ያደረገ የ17 ክረምቶች ትግል ውጤት ነው፡፡ የትጥቅ ትግሉን ሒደትና ውጤት ተገቢነትና ኢ-ተገቢነት የሚያሳዩ መጻሕፍት በአማርኛ በዛ ብለው አሉ፡፡ በውጭ ቋንቋዎች በተለይ በእንግሊዝኛ ግን ብዙ ማግኘት አይቻልም፡፡ ያሉትም ቢሆኑ ምሁራዊ በሆነ ትንታኔ በገለልተኛነት የተጻፉ ናቸው ማለት አይቻልም፡፡ ምናልባት የካናዳዊውን ፕሮፌሰር ጆን ያንግን ሥራ (Peasant Revolution) መጥቀስ ይቻል ይሆናል፡፡ እርሱም ቢሆን ንጽጽራዊ በሆነ መንገድ (Comparative analysis) አርሶ አደር አብዮት ማካሄድ የሚችል መደብ መሆኑን ለመሞገት እንጂ የትጥቅ ትግሉን አጀንዳዎችና ውጣ ውረዶች ተንትኖታል ማለት አይቻልም፡፡

በዚህ ረገድ የሙሉጌታ ገብረሕይወት (ዶ/ር) መጽሐፍ የተሳካለት ይመስላል፡፡ ሕወሓት ወደ ደደቢት ከመውረዱ በፊት የነበረችውን ኢትዮጵያን እንደ እርሾ የሚይዘው  “LAYING THE PAST TO THE REST” መጽሐፍ  የአገሪቱን መዋቅራዊና ፖለቲካዊ ችግሮች በስሱ ይዳስሳል (ከገጽ 17-40)፡፡ ‹‹ለ1966ቱ አብዮት መወለድ ምክንያት የሆነውን የዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ንጉሣዊ ሥርዓት ስረ መሠረት ካልተገነዘብን የኢሕአዴግ መራሹን ትጥቅ ትግል በቅጡ ለመረዳት ይቸግራል›› የሚሉት ደራሲው፣ በጥንታዊው የኢትዮጵያ ታሪክ ተንደርድረው ከአፄ ቴዎድሮስ እስከ ደርግ ዘመን የነበረውን ጊዜ በአለፍ ገደም ይጠቃቅሱታል፡፡ በዚህም ዘመናዊቷ ኢትዮጵያ የተዋቀረችበትን ስሪትና የገጠሟትን ተቃውሞዎች በመጠቃቀስ የሕወሓትን ትጥቅ ትግል ምክንያታዊነት ለማሳየት ይሞክራሉ፡፡ በተለይ የኢትዮጵያ ገበሬዎች (የባሌ፣ የጌዶና የጎጃም፣ የትግራይ ወዘተ) የኢትዮጵያ ተማሪዎችና ወታደሮች (በንቅናቄና በመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ) ንጉሣዊ ሥርዓቱን ሲቃወሙት እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡

ገበሬዎቹ የራስን በራስ ማስተዳደር ጥያቄ (ለምሳሌ የትግራይ ወያኔዎች አመጽ-ገጽ 27)፣ የግብርና በሀብት የመጠቀም ጥያቄ (ለምሳሌ የጌዶና የባሌ ገበሬዎች ገጽ-29)፣ በመሬት ሥሪት ለውጥ ምክንያት (የጎጃም ገበሬዎች ገጽ 30) ወዘተ ይዘው በተለይ የመጨረሻውን ንጉሥ ሲቃወሙ እንደነበር በማስታወስ ቀጥታ የሕወሓት/ኢሕአዴግ ትግል ውልደት የመደብና የብሔር ጭቆና ያመጣው እንደሆነ ያስነበቡናል፡፡ በተከታታይ ምዕራፎችም የድርጅቱን ዕድገትና ወደ መንግሥትነት ያደረጉውን ጉዞ ይተርካሉ፡፡ በመጨረሻም የዓቢይ አህመድ መንግሥት ለሥልጣን የመጣበትን መሠረታዊ ምክንያት ከኋላ ታሪክ ጋር በማገናኘት በቁጥብ ገለፃዎች ለማሳየት ይሞክራሉ፡፡

የዚህ ጽሑፍ ትኩረት በመጽሐፉ የተነሱ አንዳንድ ጉዳዮችን (ጥቂቶቹ ዛሬም መወያያ የሆኑ ናቸው) በመምረጥ መመልከት ነው፡፡ ደራሲው ኢሕአዴግ ትጥቅ ትግሉን መርቶበታል የሚሉት ሃልዮትና ሥልት ከድል በኋላ በመሸርሸሩ ለድርጅቱ ችግሮች መበራከት ምክንያት እንደሆነ ይጠቅሳሉ፡፡ ምን ማለታቸው እንደሆነ ለማየት እንሞክራለን፡፡

ሕወሓትና ደደቢት

የሕወሓት ትጥቅ ትግል በጥራዝ ነጠቅ ዕውቀትና በደመነፍሳዊ ውሳኔ የተጀመረ እንዳልሆነ ለማሳየት የሞከሩት የ‹‹LAYING THE PAST TO THE REST›› ደራሲ ድርጅቱ እንደገና በምትዋቀር ኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉንም ብሔር ብሔረሰቦች የማኖርን አጀንዳ ይዞ ዱር ቤቴ እንዳለ ይገልፃሉ፡፡ ‹‹የሕወሓት ትግል የትግራይ ሕዝብ የራሱን ዕድል በራሱ እንዲወስን የሚያደርገውን መብት ለማጎናፀፍ የተካሄደ ነው፡፡ ይህ መብት የሚገኘው ደግሞ እንደገና በምትገነባና በምትዋቀር ኢትዮጵያ እንደሆነ ድርጅቱን የመሠረቱት ሰዎች እምነት ነበር፡፡ ይህንን ለማድረግም ሕወሓት ከሌሎች ዴሞክራሲያዊ የብሔር ድርጅቶች ጋር መተባበር እንዳለባት ተረድተዋል፡፡ በሌሎች የአፍሪካ የነፃነት ንቅናቄዎች ባልተለመደ ሁኔታ የትግራይ ነፃነት ትግል የተመሠረተውና የተመራው ያለምንም የውጭ ኃይል ፖለቲካዊ እገዛ  በትግራይ ልጆች ነው›› (ገጽ43-44) በማለት በኢትዮጵያ ውስጥ የትግራይን ጥቅም ለማስጠበቅ የተጠነሰሰ አጀንዳ መሆኑን ያነሳሉ፡፡ ምንም ዓይነት የውጭ እገዛ እንዳላገኘም ከዚህ ገጽም በተጨማሪ በሌሎች ምዕራፎች አንስተውታል፡፡

የሕወሓት ትጥቅ ትግል የተማሪዎች ንቅናቄ ተቀጥላ (extension) እንደሆነ ለማስታወስም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የትግራይ ተወላጅ ተማሪዎች መስርተውት የነበረውን ማኅበር (TUSA) ያስታውሳሉ (ገጽ 44)፡፡ የማኅበሩ አባላት በዩኒቨርሲቲው ውስጥ እየተገናኙ፣ ግራ ዘመም ትንታኔ የያዙ የሕትመት ውጤቶች ላይ ይወያዩና ፖለቲካዊ ክርክሮች ያደርጉ እንደነበር በማውሳት የሕወሓት እርሾ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ንቅናቄ መሆኑን ያስነብባሉ፡፡ ይህ ማኅበርም እ.ኤ.አ በ1974  ክረምት ወደ ትግራይ ከተሞች ሄዶ ለሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች የማስጠናት እገዛ ባደረጉበት ሰሞን የጉዳዩ ተደራሲያን እየሰፉ መምጣታቸውን ያትታል መጽሐፉ፡፡

በዚህ መልኩ ፖለቲካዊ ክርክሮችን ያደርጉ የነበሩ ወጣቶች ትጥቅ ትግል ለማደረግ ወሰኑ፡፡ ለዚህም አንድ ቡድን ለወታደራዊ ሥልጠና ወደ ኤርትራ ሲላክ፣ አንደኛው ቡድን ከተማ ቀረ፡፡ ሦስተኛው ደግሞ በረሃ ወረደ፡፡ የመጀመሪያዋ ጥይትም የካቲት 11 ቀን 1967 ዓ.ም. ተተኮሰች፡፡ እዚህ ጋ እስካሁን ባለኝ ንባብ ያን ያህል አርኪ ምላሽ ያላገኘሁለትን ጥያቄ በበቂ ሁኔታ መልሶልኛል፡፡ ሕወሓት ካልጠፋ ቆላና በረሃ፣ ካልቸገረ ቦታ ለምን ደደቢትን መረጠ?

መጽሐፉ ስለጉዳዩ ሲያብራራ፣ ‹‹ደደቢት ባላት ርቀትና የመሬት አቀማመጥ ብቻ አይደለም ለትግሉ መነሻነት የተመረጠችው፡፡ በዋናነት ስሁል ገሰሰ [ከሕወሓት መሥራቾች አንዱ] በተለይ በደደቢት ዙሪያ ገባ ባሉ ሦስት መንደሮች የነበረው ክብር ነው፡፡ ይህ መሆኑ የትጥቅ ትግሉ መሥራቾች በአካባቢው ማኅበረሰብ ዘንድ ጥሩ ወዳጅነት እንዲመሠርቱ ይረዳል በሚል ነው፡፡ ስሁል በአካባቢው ያለው ተወዳጅነት ሕወሓትን በበጎ ዓይን እንዲታይ አድርጎታል፡፡ …የአካባቢው ማኅበረሰብ ያለምንም ማቅማማት ስሁል ላለበት የታጣቂ ቡድን ድጋፍ ሲያደርግ ነበር›› (ገጽ48) ይላል፡፡ ስሁል ገሰሰ ከ50 ዓመት በላይ የሆነ ጎልማሳ እንደነበር የሚያወሳው መጽሐፉ፣ ከሕወሓት ምሥረታም በፊት ሰውዬው የንጉሣዊውን አገዛዝ በመተቸትና በመቃወም የሚታወቅ፣ በዚህ አቋሙ በማኅበረሰቡ ስለሚወደድም እስከ ፓርላማ ድረስ አካባቢውን እንዲወክል ተመርጦ የገባ ታዋቂ ሰው እንደነበር ይተርካል፡፡ የዚህ ሰው የትውልድ ቦታ ለሕወሓት ትጥቅ ትግል መነሻነት እንድትሆን የተመረጠችውም በዚህ ምክንያት መሆኑን ይተርካል፡፡

ሕወሓትና የትግራይ ‹ሪፐብሊክ›

በመጽሐፉ ውስጥ ሕወሓት ለምን እንደሚታገልና የመታገያ መንገዱ፣ የፖለቲካ አቋሙና ግቡ ምን ሊሆን እንደሚችል በብዛት ተተርኮ እናገኛለን፡፡ በአገሪቱ ያለውን የብሔር ጭቆና ማሸነፍ የሚቻለው በብሔራዊ ትግል ነው የሚል አቋም እንደነበረውና ለዚህም እንደተጋለ በብዙ ሰነዶች ላይ እናገኛለን፡፡ ይሁን እንጂ ሕወሓት ቀዳሚ ዓላማው የትግራይን ሪፐብሊካዊ መንግሥት የማቋቋም ነበር ብለው ብዙዎች አስተያየት ሲሰጡ ይሰማል፡፡ በLAYING THE PAST TO THE REST መጽሐፍ ውስጥም ጉዳዩ ሽፋን ተስጥቶታል፡፡ በተለያዩ ፖለቲከኞች ሕወሓት የትግራይ ሪፐብሊክን ሊመሠርት የታገለ ተደርጎ የሚቀርበውንና በመጀመሪያው ማኒፌስቶ የተቀመጠውን ጉዳይ የሚመለከተውን አወዛጋቢ ነጥብም ደራሲው በመጽሐፋቸው አንስተውታል፡፡ ‹‹እ.ኤ.አ በ1976 የካቲት በዲማ የተካሄደው የድርጅቱ ጉባዔ ለተመረጠው አዲሱ አመራር የፖለቲካ ፕሮግራሙን እንዲቀርጽ ኃላፊነት ሰጠው፡፡ የተመረጠው አመራር ደግሞ ከራሱ የተውጣጡ ጥቂት ሰዎችን መርጦ ፕሮግራሙን እንዲያዘጋጁ ሰየማቸው፡፡ አዘጋጅተውና አሳትመውም ለሕዝብ እንዲሰራጭ ተልዕኮ ሰጠ፡፡ ማኒፌስቶው በአጭር ጊዜ ውስጥ ሱዳን ታትሞ መጣ፡፡ በመግቢያው ላይ …በኢትዮጵያ ያለው የፖለቲካ ትግል በትምክህተኛና በንዑስ ከበርቴ መዳፍ ላይ  የወደቀ መሆኑን ያነሳና በፖለቲካው መድረክ ያሉት እነዚህ ኃይሎች ያላቸው መጠላላት ለዴሞክራሲያዊ ኅብረት እንደማያመች አትቶ መፍትሔው ነፃ ዴሞክራሲያዊት ትግራይን ሊሆን እንደሚገባው ያመላክታል፡፡ ይህ ግን ለዴሞክራሲያዊ አንድነት እንታገላለን ከሚለው የድርጅቱ አቋም ጋር የሚቃረን ነበር፡፡ ማኒፌስቶው ታትሞ እንደመጣ የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ በፍጥነት ተወያየ፡፡ ይህንን ጉዳይም አወገዘ፡፡ ጉዳዩን ጠባብ ብሔርተኝነት ነው ሲልም ኮነነው፡፡ …በወቅቱ አመራር የነበሩ ሰዎች እንደሚሉት ይህ ጉዳይ (ትግራይን ነፃ አገር እናደርጋለን የሚለው) በሁሉም አመራሮች የተወገዘና ግልጽ ስህተት ተደርጎ ተወስዷል፡፡ እናም ስህተቱ ታርሟል›› (ገጽ56) ይላል፡፡

ሕወሓት የታገለው ማንን ነው?

17 ዓመታትን በረሀ የከረሙት የትግራይ ወጣቶች ምን ዓላማ ይዘው ወደ ትጥቅ ትግል እንደወረዱ እነሱም ዛሬ በእሳት ዳር ጨዋታዎች የሚተርኩት ጉዳይ ነው፡፡ ይህ መጽሐፍም ሽፋን ከሰጣቸው በርካታ ጉዳዮች መካከል ‹‹ሕወሓት ለምን ታገለ?›› የሚለው ጉዳይ ይጠቀሳል፡፡ ከማን ጋር ታገለ የሚለውንም ዳስሶታል፡፡ የመጀመሪያውን ጉዳይ ከላይ በስሱ ለመግለጽ ስለሞከርሁ እንለፈውና ሕወሓት ደም የተቃባቸውንና የታገላቸውን አካላት እንመልከት፡፡

ከመጽሐፉ መረዳት እንደምንችለው ሕወሓት በዚያ ዘመን ትግራይን ከረገጡ ሁሉም ድርጅቶች ጋር ተዋግቷል፣ አሸንፏልም፡፡ ሕወሓት አንድም ጥይት ያልተታኮሰው ከሻዕቢያና ኋላ ላይ ኢሕአዴግን አብሮ እንዲመሠርት ካደረገው ኢሕዴን ጋር ብቻ ነው፡፡ በተቀረ በትግራይ ምድር ላይ ገብቶ ትግል ማድረግ የፈለገውንና የጀመረውን ሁሉ ተዋግቷል አሸንፏልም፡፡ እዚህ ላይ የትግራይ ነፃነት ግንባር (ትነግ) ቀዳሚው ነው፡፡

ትነግ እ.ኤ.አ በ1972 በትግራይ የተመሠረተና በጀብሐ ይደገፍ የነበረ ድርጅት እንደሆነ የሚያነሱት ዶ/ር ሙሉጌታ በምሥራቃዊ ትግራይ (አጋመ አካባቢ) ይንቀሳቀስ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ከሕወሓት ጋርም የመጀመሪያው መገናኘት የተፈጠረው ሕወሓት ድርጅታዊ ሥራውን ወደ ምሥራቃዊ ትግራይ ለማስፋት በፈለገ ጊዜ እንደሆነም ይጠቅሳሉ፡፡ በሁለቱ ድርጅቶች ዘለግ ያለ ውይይት ከተደረገ በኋላ ሕወሓት ትነግን እንዳጠፋው ጽፈዋል፡፡ ምክንያታቸውንም አስቀምጠዋል፡፡ ‹‹ትነግ የትግራይን ጥያቄ የቅኝ ግዛት ጥያቄ አድርጎ የማቅረብ ዝንባሌ ነበረው፡፡ ለዚህ መፍትሔ ብሎ ያስቀመጠውም የትግራይን ነፃ አገርነት ነው፡፡ ይህንን ደግሞ ሕወሓት አብዝቶ የሚቃወመው ነገር ነው›› በማለት ሕወሓት ትነግን ያጠፋበትን ታሪክ ያስቀምጡታል፡፡ ቀጥለው የሚያነሱት ድርጅቱ የራሱን አመራሮች የገደለና ኢ-ዴሞክራሲያዊ መሆኑን ነው፡፡ የተለያዩ ሰዎች የጻፏቸውን ማጣቃሻዎች ዋቢ በማድረግም ሕወሓት በሌላ ድርጅት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባቱን ይኮንናሉ (ገጽ 76)፡፡

ጠራናፊት የተሰኘውን የፊውዳል መንግሥት ርዝራዥም የማኅበረሰብን ሀብት የሚዘርፍ፣ ሴቶችን የሚደፍርና ሕዝብን የሚበዘብዝ በመሆኑና ለደደቢት መመረጥ ምክንያት የሆነው ስሁል ገሰሰም በዚህ ድርጅት ሰዎች በመገደሉ ሕወሓት በአዲ ነብሪ ኢድ፣ በሽራሮና በአዲ ነብሪ ኢድ መሰል በተደረጉ ውጊያዎች እንደደመሰሰው ይተርካሉ (ገጽ 78)፡፡

ሕወሓት ታገልኳቸው የሚላቸው አብዛኞቹ ድርጅቶች (ደርግንም ጭምር) ልክ እንደሱ ሶሻሊስት ናቸው፡፡ ርዕዮተ ዓለማዊ ልዩነት ኖሮት የተዋጋው ከኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኅብረት (ኢዲዩ) ጋር ብቻ ነው፡፡ ኢዲዩ የፊውዳል ሥርዓቱ እንዲመለስ ይታገል የነበረ አፍቃሬ ዘውድ ድርጅት ብቻ ሳይሆን በርዕዮተ ዓለምም ቀኝ ዘመም ነው፡፡ ለዚያም ነው የ‹LAYING THE PAST TO THE REST› ደራሲ ‹‹በምዕራባዊያን ይደገፍ ነበር›› የሚሉት፡፡ በወቅቱ በሕወሓትና በኢዲዩ መካከል ያለው ወታደራዊ አቅም ፍፁም የማይገናኝና የኢዲዩ ጦር ከፍተኛ ብልጫ እንደነበረው አትተው በውጊያ ግን ሕወሓት እንዳሸነፈ ያስነብቡናል፡፡ አሲምባ ሰፍሮ የነበረውን ኢሕአፓን ወታደራዊ ክንፍም -ኢሕአሠ- ሕወሓት በውይይት መግባባት ባለመቻሉ በጠብመንጃ እንደተለያዩና ይኼኛውም በሕወሓት ድል አድራጊነት እንደተጠናቀቀ ይገልፃሉ (ገጽ 77-84)፡፡ ጀብሐን በማጥፋት ሒደት ሻዕቢያና ሕወሓት የነበራቸውን ቅንጅትም ጽፈውታል፡፡

ሕወሓት ኦሮሞ ነፃነት ግንባርን (ኦነግ) አብሮ ለመሥራት ተደጋጋሚ ጥያቄዎችንና ማግባባቶችን አድርጎ እንደነበር የሚጠቅሰው መጽሐፉ፣ በሚንቀሳቀስበት ወለጋ ድረስ መጥቶ (የድርጅቱ ደኅንነት ኃላፊ ክንፈ ገብረመድኅን) ለማነጋገር ሞክሮ ‹‹ኦነግ ተራማጅና ሕዝባዊ ድርጅት አለመሆኑን የሕወሓት ሰዎች በነበራቸው ቆይታ ስለተረዱ›› ከኦነግ ጋር በጋራ ለመሥራት የነበረው ዕቅድ መክሸፉን ያስረዳሉ፡፡

ሕወሓት 17 ዓመታትን በትጥቅ ትግል የቆየ ድርጅት መሆኑን አዲሱ ትውልድ ተደጋግሞ ተነግሮታል፡፡ ይሁን እንጂ በተለይ የመጀመሪያዎቹን ሦስት ዓመታት ያጠፋው በትግራይ ክልል ያሉ ድርጅቶችን በማጥፋትና በመዋጋት እንደሆነ ይህ መጽሐፍ ያስገነዝባል፡፡ እንዲያም ሆኖ የደርግ ዘመቻዎች አልተለዩትም፡፡ ድርጅቱ ከበርካታ መሰል የፖለቲካ ኃይሎች ጋር ደም ተቃብቶና ተዋግቶ ነው ትግራይ ላይ ከደርግ ጋር መዋጋት የቀጠለው፡፡

ሕወሓትና ሻዕቢያ

በአሁኑ ዘመን ምሥራቅ አፍሪካ ውስጥ እንደነዚህ ሁለት ድርጅቶች የሚናናቅና የሚጠላላ ያለ አይመስለኝም፡፡ ይህ መናናቃቸው ግን አሁን የተጀመረ እንዳልሆነ መጽሐፉ ምስክር ነው፡፡ እንዲያውም ግንኙነቱን ‹‹ከአንገት በላይ የነበረ ወዳጅነት› (Strained Relationship with EPLF) ሲል ነው የሚገልጸው መጽሐፉ፡፡

በሁለቱ ድርጅቶች የግንኙነት ሰሞናት ሕወሓት ሻዕቢያን አብዮተኛ ድርጅት አድርጎ ይመለከተው እንደነበር የሚያስታውሱት ደራሲው፣ ‹‹ይሁን እንጂ ሻዕቢያ ሶቪየት ኅብረትን እንደ ትክክለኛ ሶሻሊስት ድርጅት የሚያይ መሆኑ›› ድርጅቱ ከሕወሓት ጋር በሃልዮት ደረጃ እንደሚያለያየው ያነሳሉ፡፡ ምክንያቱም ሕወሓት ሶቪየትን ‹ሶሻል ኤምፔሪያሊስት› ብሎ ነበር የሚጠራት፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሻዕቢያ ወታደሮችን የሚመለምልበት፣ ነፃ የወጡ ግዛቶችን የሚያስተዳድርበትና የመሬት ሽግሽግን በተመለከተ የወሰደው አቋም፣ አንድም ጊዜ ጠቅላላ ጉባዔ አለማካሄዱ ወዘተ በሕወሓት ዘንድ የቅሬታ ምንጭ እንደሆነ ያነሳሉ፡፡

እንዲያም ሆኖ ‹‹የጋራ ድል እንፈልጋለን የሚለው ጉዳይ የጋራ አጀንዳ ስለሆነ ትብብራቸው እንደቀጠለ ነበር፡፡ የሁለቱን ድርጅቶች ጉዳይ የወሰነ አጋጣሚ ግን  እ.ኤ.አ በ1983ቱ የሕወሓት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ተፈጠረ፡፡ ሻዕቢያ በጉባዔው ላይ እንዲገኝ ጥሪ ቀርቦለት ስለነበር በሊቀመንበሩ ሮመዳን መሐመድ ኑር የተመራ ልዑክ አጋርነቱን ለማሳየት ተሳተፈ፡፡ በሁለቱ ድርጅቶች ቀጣይ ግንኙነቶች ላይም ከጉባዔው ጎን ለጎን ውይይቶች ተደረጉ፡፡ ሻዕቢያዎች የሕወሓት ሠራዊት በድጋሚ ኤርትራ እንዲገባ ጠየቁ፡፡ ይህንን ሕወሓት አስቀድሞ ተጠይቆ እምቢ ብሏል፡፡ ቀጥለውም ‹‹ሕወሓት ሠራዊቱን በጥልቀት ወደ ሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች ያስገባ፡፡ ይህ ሲሆን መንግሥት በኤርትራ ያሰፈረውን ሠራዊት እንዲበትንና እናንተ ወደምትንቀሳቀሱበት አካባቢ እንዲያሰፍር ያደርገዋል› የሚል ጥያቄ አቀረቡ›› የሚሉት ዶ/ር ሙሉጌታ የሻዕቢያን ልዑክ ‹ተስፋ አስቆራጭ› ሲሉ ይገልፁታል፡፡

‹‹ወደ ሌላው አካባቢ የሕወሓት ሠራዊት የሚገባው የሕዝብን ትግል ከሚመሩ ሌሎች የኢትዮጵያ ኃይሎች ጋር በሚደረግ ትብብር ብቻ ነው›› ሲሉ ሕወሓቶች መመለሳቸውን የሚጠቅሱት ፀሐፊው፣ ‹‹ሻዕቢያዎች ከፍተኛ አለመረጋጋትና ፍርሃት ይታይባቸው›› እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ‹‹ከዚህ ውይይት በኋላ የተወሰኑ የሕወሓት አመራሮች ከሻዕቢያ ጋር ስላለ ግንኙነት ጥያቄዎችን ማንሳት ጀመሩ፡፡ ውይይቱ በመርህ ላይ ይመስረት ወይስ ተራማጅ በሆኑ ፍላጎቶች የሚለው ጉዳይ ውይይት ተደረገበት›› የሚሉት ደራሲው፣ ‹‹በ1977 ድርቅ ወቅት በሁለቱ ድርጅቶች መካከል የነበረው ግንኙነት ከቁጥጥር ውጭ ሆነ›› በማለት በወቅቱ ድርቁ ያጠቃውን የትግራይ ሕዝብ ወደ ሱዳን እንዳይሄድ ሻዕቢያ የሚቆጣጠራቸውን ግዛቶች በመዝጋት መከለክሉን ይገልፃሉ (ገጽ 115-116)፡፡

ሻዕቢያ በትጥቅ ትግሉ ወቅት የድንበር ማካለል ጥያቄ አንስቶ እንደነበርም በመጽሐፉ ተገልጿል፡፡ ይሁን እንጂ ‹‹እኛ መንግሥት አይደለንም የድንበር ማካለልን ጉዳይ የሚወስነው በሕዝብ የሚመረጥ የኢትዮጵያ መንግሥት እንጂ ሕወሓት አይደለም፡፡ ስለዚህ አሁን የድንበር ማካለልን ጉዳይ እኛ ልንፈጽም የምንችልበት ውክልና የለንም›› በሚል ከሕወሓት ምላሽ እንደተሰጠው ይገልፃል፡፡                                                                                                                                            

ኢሕአዴግና ኢትዮጵያ

በ1980ዎቹ መባቻ ኢሕአዴግ ከተመሠረተ በኋላ የትጥቅ ትግሉ ከትግራይ ወጣ፡፡ የግንባሩ መርህም ብሔር ብሔረሰቦች በጋራና በአንድነት የሚኖሩባት እንደገና የምትዋቀር ኢትዮጵያ እንድትሆን ከስምምነት መደረሱን መጽሐፉ ያስታውሳል፡፡ ‹‹የኢሕአዴግ ፕሮግራም ወሳኝ ነጥቦችን አስቀመጠ፡፡ ለበርካታ ዓመታት የተገለሉ አናሳዎችም የሚሳተፉባት ኢትዮጵያ እንድትመሠረት›› እና ለዚህም ተባባሪ እንዲኮን ጥሪ መቅረቡን ይገልፃል ገጽ 149፡፡

እዚህ ላይ መንግሥት ስንሆን ምን እንሠራለን፣ የሽግግር መንግሥትስ እንዴት ይመሥረት፣ እነማን ይሳተፉ፣ በዚህ ላይ የኛ ድርሻ ምንድን ነው? ወዘተ የሚለው ጉዳይ ሰፊ ውይይት እንደተደረገበትም ያስታውሳሉ፡፡ በዚህ ረገድ ሁለት የቢሆን ዕድሎች (ኬዝ ሴናሪዮስ) ቀረቡ፡፡ የከፋ ዕድል ‹‹ጦርነቱ ከደርግ ጋር በሚደረግ ውይይት ሊቋጭ ይችላል፡፡ አሁን ያለውን የፀጥታና ወታደራዊ አቅሙንም በሽግግር መንግሥቱ ውስጥ ተሳታፊ ሊያደርግ ይችላል›› የሚል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የተሻለ አማራጭ ተብሎ የተቀመጠው ‹‹ጦርነቱ በእኛ አሸናፊነት ይጠናቀቃል›› የሚል ነው (ገጽ150)፡፡

ይህንና ሌሎች ጉዳዮችን የያዘ ስትራቴጂካዊ ሰነድም ተዘጋጀ፡፡ ‹‹ይህ ስትራቴጂክ ሰነድ በሽግግሩ ወቅት ፓርቲና መንግሥት ሊኖራቸው የሚገባን ግንኙነት ያስቀመጠ ነው፡፡ በዚህም የፓርቲው አመራር በቁልፍ የመንግሥት ጉዳዮች ላይ የተገደበ እንዲሆን ተመክሯል›› ይላል የዶ/ር ሙሉጌታ መጽሐፍ፡፡ ከኢሕአዴግ ምሥረታ በኋላ ትጥቅ ትግሉ ሦስት ዓመታትን ብቻ ፈጅቶ ተጠናቀቀ፡፡ ኢሕአዴጎች ካስቀመጧቸው ሴናሪዮዎች ውስጥም እነሱ በጎ ሲሉ የጠሩት አሸናፊነታቸው ዕውን ሆነ፡፡

በሽግግር ወቅት ‹‹የደርግ ሠራዊት››

ኢሕአዴግ ደርግ የሚያዘውን የፀጥታና መከላከያ ኃይል ይዞ ወደ ሽግግሩ እንዳይገባ እንደሚፈልግ ከላይ አይተናል፡፡ ስለዚህ የአፍሪካ ግዙፍ ሠራዊት የሚባለውን ጦር ዕጣ ፈንታ የሚወስነው ይኼው አሸናፊ ኃይል ሆነ፡፡

‹‹ኢሕአዴግ ወደ አዲስ አበባ ሲገሰግስ ከ250 ሺሕ የሚልቅን የመንግሥት ሠራዊት በተለያዩ ጊዜያዊ ማዕከሎች አሰባስቧል፡፡ 50 ሺሕ የሚሆን ደግሞ ወደ ሱዳን፣ ጅቡቲና ሶማሊያ ድንበሮች አፍግፈጓል፡፡ ከ150 ሺሕ የሚልቀው ደግሞ ወደ ማኅበረሰቡ ገብቷል፡፡ ከ30 ሺሕ የሚበልጡ ወታደሮች ደግሞ በጦር ሆስፒታሎች ውስጥ ሕክምና እየተደረገላቸው ነበር፡፡ ሽግግሩን ሰላማዊና ውጤታማ ለማድረግ ከዚህ ሠራዊት ጋር መነጋገር ያስፈልግ ነበር›› የሚሉት ደራሲው የዚህን ሠራዊት ዕጣ ፈንታ የሚወስን ኮሚሽን ኢሕአዴግ ሥልጣን በያዘ በሁለተኛው ሳምንት አቋቋመ፡፡ የዚህ ኮሚሽን ኮሚሽነርም የዚህ መጽሐፍ ደራሲ ሙሉጌታ ገብረሕይወት በርሔ (ዶ/ር) ሆኑ፡፡

‹‹በፖለቲካዊ ዕይታ ይህ የተሸነፈ ሠራዊት አዲስ ልትዋቀር ለተነሳችው ኢትዮጵያ በጎ ሚና እንደማይኖረው ኢሕአዴግ ያውቃል፡፡ በሌላ በኩል በግድ ተመልምሎ ወደ ውትድርና የገባ ስለሆነ በዚህ ሙያ የመቀጠል ፍላጎት አለው ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ተቋማዊና ሕጋዊ በሆነ ሁኔታ የሚመራ ሳይሆን በወታደራዊ ደኅንነት ምሥጢራዊ ተፅዕኖዎች ሥር እንዲቆይ የተደረገ ነው፡፡ ጦሩ በተለይ በምሥራቅና በሰሜን ኢትዮጵያ የሚታወቀው በደም አፍሳሽነቱ ነው፡፡ በእነዚህ ምክንያቶች በኢሕአዴግ ለሚመራው አገር መከላከያ ኃይል መሆን የማይችል ጦር መሆኑ ታመነበት፡፡

‹‹በኢኮኖሚም ቢሆን አገሪቱ ለዚህ ግዙፍ ሠራዊት የሚሆን አቅም አልነበራትም፡፡ ደካማው ኢኮኖሚ ብዙ የውጭ ዕዳ ያለበት ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን ግዙፍ ሠራዊት ይዞ መቀጠል ከኢኮኖሚ አንፃርም አዋጭ አልነበረም፡፡ በመሆኑም ኢሕአዴግ ለኢትዮጵያ የሚያስፈልገው አነስተኛ መጠን ያለው ሠራዊት ብሎ አመነ፤›› በማለት የመንግሥትን ሠራዊት የሚቀረውን አስቀርቶ ሌላውን እንደሚፈልገው ለማድረግ ኮሚሽኑ መሰየሙን ይገልጻሉ (ገጽ 167-170)፡፡ ኋላ ላይም የተለየ ወታደራዊና ቴክኒካዊ ክህሎት ያላቸውን ወታደሮች በማስቀረት፣ የተሸነፈውን መንግሥት ሠራዊት ወደየቤተሰቡ መመለስ መቻሉን ይዘክራሉ፡፡

መጽሐፉ

የዚህ መጽሐፍ ጸሐፊ ምንም እንኳን የትጥቅ ትግሉ ተሳታፊ (ከ1968 ዓ.ም. ጀምሮ) እና ከድል በኋላም እስከ 1993 ዓ.ም. ድረስ የመንግሥት ባለሥልጣን የነበሩ እንደሆኑ መጽሐፉ ውስጥ እናነባለን፡፡ ይሁን እንጂ ምሁራዊ ገለልተኛነት በሚንፀባረቅበት መንገድ ታሪኩን ለማስቀመጥ ወደ ኋላ አላሉም፡፡ በዚህም በትጥቅ ትግሉ ወቅት የነበሩ አጨቃጫቂ ነገሮችን (ለምሳሌ ሕወሓት ለዕርዳታ የመጣን ሀብት ለጠብመንጃ መግዢያ አውሎታል የሚለውን)፣ ኢሕአዴግ የመንግሥትን ሥልጣን ከያዘ በኋላ የሚነገሩ አወዛጋቢ ነገሮችን (ለአብነት የኢፈርትና መሰል ድርጅቶች ጉዳይ) በማንሳት ግራ ቀኙን ለማሳየት እና ፍርዱን ለአንባቢ ትተዋል፡፡

በድፍረት እንደ አንደኛ መደብ ተራኪ ሆነው ያቀረቡት እርሳቸው የተሳተፉባቸውንና የመሯቸውን ጉዳዮች ነው፡፡ በተለይም የመንግሥትንና የራሱን የኢሕአዴግንም ሠራዊት ‹ዲሞብላይዝ› ለማድረግ ኃላፊነቱ እርሳቸው ላይ ወድቆ ስለነበር በዚህ ረገድ ያለውን ጉዳይ ባግባቡ ለማቅረብ ሞክረዋል፡፡

የመጽሐፉ ንዑስ ርዕስ ኢሕአዴግ በብሔረ መንግሥት ግንባታ ላይ የገጠሙትን ፈተናዎች የሚጠቁም ቢሆንም በበቂ ሁኔታ ግን ጉዳዩ ተተንትኗል ማለት አይቻልም፡፡ ኢሕአዴግ ንድፈ ሐሳብንና ገቢራዊነትን ከአመራርነት ጋር አጣምሮ መጓዙ ለድል እንዳበቃው ቢገልፁም፣ ይህ ከኢትዮጵያ የብሔረ መንግሥት ግንባታ ጋር ያለውን ግንኙነት ዳስሰውታል ማለት አዳጋች ነው፡፡ መጽሐፉ እንደ አንድ የጥናት ሥራ ‹የቴዎሪ ማዕቀፍ› ተቀምጦለት ቢተነተን መልካም ነበር፡፡ ይህ ግን በመጽሐፉ ውስጥ የለም፡፡ በቂ ምክረ ሐሳቦች አሉት ማለትም አይቻልም፡፡ በተለይ የመጽሐፉ ንዑስ ርዕስ ይዞት የተነሳው ጉዳይ ወሳኝና አንገብጋቢ እንደመሆኑ መጠን የተሻሉ ምክረ ሐሳቦች ይጠበቁ ነበር፡፡ ደራሲው ግን ይህንን ነፍገውናል፡፡

መጽሐፉ ብዙ ነገሮችን ያጽፋል፡፡ በርካታ ጉዳዮችን አንስቶ የሚጥል መጽሐፍ ነው፡፡ እያንዳንዳቸው ጉዳዮች ብዙ ያጽፋሉ፡፡ የእኔ ትኩረት ብዙም ባልተነገረላቸው ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው፡፡ አመሰግናለሁ!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles