Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበአህያ ሀብት ላይ የተደቀነው ሥጋት

በአህያ ሀብት ላይ የተደቀነው ሥጋት

ቀን:

በምዕራብ አርሲ ከሚገኙ ዝናብ አጠር አካባቢዎች ሲራሮ አንዷ ነች፡፡ በዚህ አካባቢ የሚኖሩ አርሶ አደሮች በመስኖ የሚጠልፉት ወንዝ የላቸውም፡፡ ንፁህ ውኃም ብርቃቸው ነው፡፡ እንደ ዝናብ ሁኔታ ማሳቸው ያፈራል አልያም ጦሙን ይከርማል፡፡ ከሚሸጡት ምርት ይልቅ የሚገዙት የበዛ በችግር የሚኖሩ አርሶ አደሮች ብዙ ናቸው፡፡

በወጣትነት ዕድሜው ወደ ትዳር የገባው አቶ ኢሳ አራርሶ ሲራሮን መኖሪያ ካደረጉ አርሶ አደሮች መካከል ነው፡፡ እንደ አብዛኛው የኢትዮጵያ አርሶ አደር በኑሮ የተጎሳቆለ ነው፡፡ አንገቱ ላይ የጠቀለላት ቡራቡሬ ሽርጥ ዕድሜ የጠገበች ትመስላለች፡፡ ላስቲክ ጫማውም እንዲሁ እርጅና የተጫነው ነው፡፡ እርፍ የጨበጡ እጆቹ ያው ሻካራ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ አቶ ኢሳ ኑሮ የፈተነው ከዕድሜው በላይ የኖረ የሚመስል ገበሬ ነው፡፡

ሦስት ልጆቹን ለማሳደግ ከማሳው የሚሰበስበው ምርት በቂው አለመሆኑን ያውቃል፡፡ ለዚህም ኑሮውን ለመደጎም ጋሪ ይጠራል፡፡ ጋሪውን የምትጎትትለት አንዲት አህያ በወጉ የተሠራ መንገድ በሌላት ሲራሮ ላይ ታች ብላ በቀን ከ50 እስከ 60 ብር የተጣራ ገቢ ታስገኝለታለች፡፡ የተለያዩ ወጪዎች ስላሉበት ግን በቂ አይደለም፡፡ ስዚህም የአህዮቹን ቁጥር ከተቻለ አራት ካልሆነ ግን ወደ ሁለት ለማሳደግ ቆርጦ ተነሳ፡፡

ለዚህ የሚያስፈልገውን ገንዘብም አባል ከሆነበት ከአንድ የቁጠባ ማኅበር ተበደረ፡፡ ከቁጠባ ማኅበሩ የተበደረው 3000 ብር ግን የፈለገውን ለማድረግ በቂ አልነበረም፡፡ የአንድ አህያ ዋጋ በፊት ከነበረው በእጅጉ ጨምሯል፡፡ ‹‹የትናየት መንገድ መሄድ የምትችል ውኃ የመሰለች›› አህያ ከጥቂት ጊዜያት በፊት በ1,500 ብር ትገኝ ነበር፡፡ ዕድሜ አህያ እያሳደዱ ወደ ኬንያ ለሚጭኑ ደላሎች የአንድ አህያ ዋጋ በ5,500 ብር ለመግዛት ያደረገው ጥረት ሳይሳካ ቀረ፡፡

በሲራሮ ሰኞ፣ ረቡዕና ዓርብ የሳምንቱ የገበያ ቀናት ናቸው፡፡ የአካባቢው አርሶ አደሮች ያላቸውን በጋራ፣ በፈረስና አህያ ጭነው ወደ ገበያ ይወጣሉ፡፡ ከየአካባቢው አህያ እየሰበሰቡ በመላክ የሚያተርፉ ደላሎች ደግሞ ኤፍኤስአር መኪኖችን አስከትለው በየገበያው እየዞሩ አህዮችን ይቃርማሉ፡፡ እህል ጭነው ገበያ የወጡ አህዮች ወደ ቤታቸው ሳይመለሱ በከባድ መኪና እየተጫኑ ይወጣሉ፡፡ ለአንድ አህያ የሚጠራው ገንዘብ ከ1,500 ተነስቶ 7,000 የደረሰውም ገበያው እየደራ በመሄዱ ነው፡፡ በዚህ መካከል አቶ ኢሳ ከሁሉም ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡ የተበደሩትን ገንዘብ አጥፍተዋል፡፡ ደላሎቹ የራሳቸውን ኪስ በመሙላት የተጠመዱ አዲስ በአቋራጭ የሚከብሩበትን መንገድ ያገኙ ግዴለሾች ናቸውና የአቶ ኢሳ እንግልት፣ በገፍ ከአገር የሚወጡት አህዮች መጨረሻ አያሳስባቸውም፡፡ በእያንዳንዱ አህያ ከ500 እስከ 600 ብር እንደሚታሰብላቸው ይነገራል፡፡

በአህያ ሀብት ላይ ሥጋት የደቀነው የቻይናውያን ባህላዊ መዋቢያና መድኃኒት ‹‹ኢጃዎ›› ምርት ገበያ ላይ ያለው ተፈላጊነት በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ከተቀቀለ የአህያ ቆዳ ተጨምቆ ከሚወጣ ‹‹ጀላቲን›› የሚዘጋጅ ሲሆን፣ የተለያዩ በሽታዎችን ያክማል፣ የፊት ቆዳ ጤንነትንም ይጠብቃል ተብሎ ይታመናል፡፡ ከዓመታት በፊት ኢጃዎ ባለፀጎች ብቻ የሚጠቀሙት ውድ ምርት ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን መካከለኛ ገቢ ያላቸው ቻይናውያን ቁጥር ሰፊ መሆኑን ተከትሎ የኢጃዎ ተጠቃሚዎች ቁጥር አብሮ ጨመረ፡፡

በአሁኑ ወቅት ያለው ዓመታዊ የኢጃዎ ገበያ አምስት ሚሊዮን አህዮችን መስዋዕት ማድረግን ይጠይቃል፡፡ የኢጃዎ ምርት አሁን ባለበት ሁኔታ የሚቀጥል ከሆነ በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ውስጥ የዓለም የአህያ ሀብት በ50 በመቶ ሊጠፋ እንደሚችል የሚያረጋግጡ አኃዞች እየወጡ ነው፡፡ ጉዳዩ የዓለም መነጋገሪያ ከሆነ የቆየ ቢሆንም የቻይና ኩባንያዎች ግን ሰፊ የአህያ ሀብት ያላቸውን አገሮች ዒላማ እያደረጉ ማራቆትን ተያይዘውታል፡፡

በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ ሰፊ የአህያ ሀብት ያላቸውን አገሮች አራቁተዋል፡፡ አሁን ደግሞ ተራው ባላት የአህያ ሀብት ብዛት ከዓለም ሦስተኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ ሆኗል፡፡ ኢጃዎን የሚያመርቱ የቻይና ኩባንያዎች ኢትዮጵያ ገብተው የአህያ ቄራ ከፍተው በሕዝቡ ቅሬታ መውጣታቸው የሚታወስ ነው፡፡ በወቅቱ የሕዝቡ ቅሬታ ገና ለገና የአህያ ሥጋ ተደባልቆ ሊበላ ይችላል ከሚል ሥጋት የመነጨ ነበር፡፡ ይሁንና የኩባንያዎቹ ዋና ተልዕኮ ለኢጃዎ ምርት የሚሆን የአህያ ቆዳ መሰብሰብ ነበር፡፡ ሪፖርተር ባለፈው ዕትሙ በጋማ ከብቶች ደኅንነት ዙሪያ ከሚሠሩት አቶ ደስታ አረጋ ጋር በነበረው ቃለ መጠይቅ ከዚህ የተባረረው የቻይና ኩባንያ በኬንያና ኢትዮጵያ ድንበር ላይ የአህያ ቄራ መክፈቱን መናገራቸውን አስነብቧል፡፡ በአሁኑ ወቅት በኬንያ ከሚታረዱ አህዮች መካከል 80 በመቶ የሚሆኑት ከኢትዮጵያ በሕገወጥ መንገድ የሚጋዙት እንደሆነም መረጃ እየወጣ ነው፡፡

ጉዳዩ ሕዝብንና መንግሥት ጆሮ ከደረሰ በኋላ ደላሎች በድብቅ ለመንቀሳቀስ ጥረት እያደጉ ነው፡፡ ገበያውም የመቀዛቀዝ ነገር አሳይቷል፡፡ በሲራሮ 7,000 ብር ገብቶ የነበረው የአንድ አህያ ዋጋ አሁን ላይ ወደ 4,000 ብር ዝቅ ማለቱን አቶ ኢሳ ይናገራሉ፡፡

ጉዳዩ ግን አሁንም ድረስ አሳሳቢ መሆኑን የሚናገሩት በጋማ ከብቶች ደኅንነት ባለሙያ አቶ እንግዳወርቅ ጉራቻ ናቸው፡፡ አቶ እንግዳወርቅ ሰፊ የጋማ ከብት ሀብት ባለባት ሀላባ ቁሊቶ ዞን የታዘቡትን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

‹‹ደላሎቹ ይህንን ሥራ ይሠሩ የነበረው በአብዛኛው ሳይታወቅ በፊት ነበር፡፡ አሁን ከታወቀ በኋላ ግን የሚሠሩት በድብቅ ሆኗል፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች ገዝተው ያመጣሉ፡፡ እዚህ ደግሞ ሐሙስ ዕለት ከሚውለው ትልቅ ገበያ ላይ ሰብስበው ጭነው ይወጣሉ፤›› ብለዋል፡፡

ደላሎቹ አብዛኛውን ገዝተው የሚወስዱ ቢሆንም አንዳንዴ ከማኅበሩ እየሰረቁ ይወስዱ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ በዚህ ሥራ የተሰማሩ ደላሎች በጋማ ከብት ማደሪያና መዋያ ቦታዎች ኑሯቸውን ያደረጉ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል፡፡ ለምሳሌ ከቀናት በፊት የሰው አህያ ሰርቆ ሲጭን እጅ ከፍንጅ የተያዘ ግለሰብ መኖሪያው ከጋማ ከብቶች ማደሪያ ቦታ ቀጥሎ የሚገኝ ግቢ ውስጥ እንደሆነ አቶ እንግዳወርቅ ገልጸዋል፡፡

ከየአካባቢው በኤፍኤስአር መኪኖች የሚጫኑ አህዮች በሞያሌ በኩል እንደሚወጡ፣ ሞያሌ ላይ አህዮቹን ተቀብላ የቀንድ ከብት ወደ ሀላባ የምትልክ አንዲት ነጋዴ መኖሯን እንደተደረሰበት ይናገራሉ፡፡ ሴትየዋ ሕገወጥ የአህዮችን ንግድ ለማስቆም የሚደረገውን ጥረት ‹‹ሕጋዊ ፈቃድ አለኝ›› እያለች ደላሎቹን እንደምታደፋፍርም አቶ እንግዳወርቅ ተናግረዋል፡፡

የመንግሥት አካላትም ፖሊስም መጠየቅ በመጀመሩ በአሁኑ ወቅት እንቅስቃሴው በድብቅ ሆኗል፡፡ በአንድ መኪና ከ50 እስከ 60 አህዮችን ጭነው ሲንቀሳቀሱ እጅ ከፍንጅ የተያዙም አሉ፡፡ ይሁንና ተጠርጣሪዎቹ የሚዳኙበት የሕግ አግባብ ባለመኖሩ፣ ፖሊስ ጣቢያ እንዲገቡ የተደረጉ አህዮችን ምግብና ውኃ ማግኘት ስላለባቸው ተመልሰው እየተለቀቁ መሆኑን ሰምተናል፡፡ ከሰሞኑ በሻሸመኔ ከተማ አህዮቹን ጭኖ ሊወጣ ሲል የተደረሰበት ግለሰብ አህዮቹ በቁጥጥር ስር ሲውሉ፣ እሱ ግን አምልጦ እንደነበር፣ መጨረሻ ላይ ጉዳዩ የሚታይበት የሕግ አግባብ ባለመኖሩ አህዮቹን የሚንከባከብ ሰው በማስፈለጉ ባለቤቱ  ተጠርቶ አህዮቹን መልሶ እንዲረከብ ተደርጓል፡፡

አህዮቹን እየጫኑ የሚወጡ ግለሰቦች ከአንዱ ከተማ ወደ ሌላ አድርሰው የሚመለሱ መሆኑን፣ አህዮቹ ድንበር እስኪያቋርጡ ያለው ቅብብሎሽና የንግድ ሰንሰለት ረዥም መሆኑን፣ ይህም አስፈላጊውን ዕርምጃ ለመውሰድና ሕገወጥ ንግዱን ለማስቀረት ከባድ እንዳደረገው እየተነገረ ነው፡፡ በዚህ መካከል እንደ አቶ ኢሳ ያሉ አርሶ አደሮች ዋጋ እየከፈሉ ነው፡፡ አጠቃላይ ሁኔታውም ዝቅተኛ የርቢ መጠን ላላቸው አህዮች ዘር መጥፋት የሚያቀርብ ይመስላል፡፡ ለዚህም የሚመለከታቸው ሁሉ ተረባርበው መፍትሔ ሊሰጡት ይገባል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...