በተመስገን ተጋፋው
ለሙዚቃ ዕድገት የራሱን ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ ሙዚቃዎቹን በመጫወትና ለሕዝቡ በማድረስ ተደራሽ ሥራ ሠርቷል፡፡ በኢትዮጵያ ሆነ በሌሎች አገሮች ላይ የሙዚቃ አሻራውን ትቶ አልፏል፡፡ ተስፋዬ ገብሬ፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይ በ1970ዎቹና 80ዎቹ መጀመርያ ተደማጭ ከነበሩት ዘፈኖቹ መካከል ‹‹መጋቢት 28 የድላችን ቀን ይከበር ዘላለም በአገራችን››፣ ‹‹ስፖርት ለጤንነት ለምርት ለወዳጅነት. . .›› ይገኙበታል፡፡
ተስፋዬ በአዲስ አበባ አራት ኪሎ በመባል በሚጠራው አካባቢ ከአባቱ አቶ ገብሬ ምንዳዬና ከእናቱ ወ/ሮ ብዙነሽ ቡላ እ.ኤ.አ. ታኅሳስ 23 ቀን 1939 ነበር የተወለደው፡፡ ተስፋዬ ለሁለቱ ጥንዶች የበኩር ልጅ ነው፡፡ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርቱን በአስፋወሰን ትምህርት ቤት፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በሽመልስ ሀብቴ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አጠናቋል፡፡ በወቅቱም ውጤታማ ተማሪዎች እየተመረጡ ወደሚገቡበት የተግባረዕድ ትምህርት ቤት ገብቶ የሙያ ትምህርቱን ተከታትሏል፡፡
ተስፋዬ በማኅበራዊ ጉዳዮች ንቁ ተሳትፎ ለማድረግ የነበረውን ምኞት ለማሳካት በአሥር ዓመቱ የወጣት ወንዶች ክርስቲያናዊ ማኅበር (ወወክማ) የስካውት አባል በመሆን ንቁ ተሳትፎ ያደርግ ነበር፡፡ ተሳትፎውም በአጭር ጊዜ ውስጥ የማኅበሩ ሊቀ መንበር እንዲሆን አድርጎታል፡፡
ገጸ ታሪኩ እንደሚያስረዳው የሙዚቃ ሕይወቱ የሚጀምረው እ.ኤ.አ. በ1950 መጨረሻ አካባቢ ላይ ላማስኮት በተባለ የጣሊያን የምሽት ክበብ ውስጥ ነው፡፡ በወቅቱ በሙዚቃ አፍቃሪዎች ዘንድ ከፍተኛ ተደማጭነትን አግኝተው የነበሩትን የፍራንክ ሲናትራ፣ ዲንማርቲን፣ ኤልቪስ ፕሪስሊና የሌሎች ታዋቂ ዘፋኞችን ሙዚቃዎች በመዝፈን ከፍተኛ የሆነ ተቀባይነትን አግኝቶ ነበር፡፡ የራሱ ድርሰት የሆኑ ሙዚቃዎችንና የመድረክ ተውኔቶችን ማቅረብ የጀመረው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ እያለ ሲሆን፣ ሥራዎቹንም ለሕዝቡ ከማቅረቡ በፊት ለጓደኞቹና ለቤተሰቡ በማሳየት ነበር፡፡
ተስፋዬ በዘመኑ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ ከፍተኛ አሻራ ባሳረፉት በታዋቂዎቹ የኢትዮጵያ ሀገር ፍቅር ማኅበር ኃላፊዎች በአቶ መኮንን ሀብተ ወልድና በድምፃዊ ኢዩኤል ዮሐንስ ጥያቄ ሀገር ፍቅርን እንደተቀላቀለ ይነገራል፡፡ የተስፋዬ የሙዚቃ ፍቅርና ችሎታው ወደ ዘመናዊ ሙዚቃ የሚያዘነብል ቢሆንም፣ የሀገር ፍቅር ማኅበርን በመቀላቀል እስካሁን ድረስ ከሕዝቡ ጆሮ ያልጠፉትን ‹‹የፍቅር ምግብና የፍቅር ሰላምታ የሚሉትን ዘፈኖች ለአድናቂዎቹ አቅርቧል፡፡ ‹‹ስፖርት ለጤንነት ለምርት ለወዳጅነት›› ‹‹መጋቢት 28 የነፃነታችን ቀን ይከበር ዘለዓለም በአገራችን›› የተስፋዬ ገብሬ ሥራዎቹ ናቸው፡፡
ተስፋዬ በጂቡቲ በኩል ከኢትዮጵያ እንዲወጣ ያመቻቹለት ታዋቂው የቱሪዝም ባለሙያ የነበሩት አቶ ኃብተ ሥላሴ ታፈሰ ናቸው፡፡ ሮም እንደደረሰም ቪቼንዞ ሲላቶ ወይም ኤንዞዴ አስመራ ያሰባሰበው የሙዚቃ ቡድን ተቀላቅሏል፡፡ የሙዚቃ ቡድኑን ያቋቋሙት በአስመራ ጉብኝት ወቅት የተዋወቃቸው ጓደኞቹ በመሆናቸው በጣሊያን የሙዚቃ ሕይወትን ለመቀላቀል ብዙም አልከበደውም፡፡
ተስፋዬ ኦርኬስትራ ስፔታኮሎ፣ ኦርኬስትራ ኤላ ሱአ፣ ኦርኬስትራ ቤንቴኒ፣ ኤሞንቲና ሄንግል ጉአልዲ በተባሉ የሙዚቃ ቡድኖች ውስጥ አባል በመሆን ለበርካታ ዓመታት ሙዚቃዎችን ተጫውቷል፡፡
እ.ኤ.አ. ከ1970 እስከ 1972 ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ኦርኬስትራ ስፔታኮሎ (ኦርኬስትራ ካሲዳይ) እየተባለ በሚጠራ ስብስብ ውስጥ ቆይቷል፡፡ የካሲዳይ ቡድን አባልና ሦስተኛ ትውልድ የሆነችው ካሮሌና ካሲዳይ በሰጠችው ምስክርነት በካሲዳይ የሙዚቃ ቡድን ውስጥ ለመጀመርያ ጊዜ የተቀጠረ ጥቁር አፍሪካዊ መሆን ችሏል፡፡ ተስፋዬ የሠራቸው ሥራዎች ዘመናዊና ብዙም ያልተለመዱ ናቸው፡፡ በተለይ ሊስቻዋ በሚባለው የሙዚቃ ዓይነት በጣም ተወዳጅ አቀንቃኝ ነበር፡፡ የድምፁ ልቀትና መድረክ አያያዙ የተመልካችን ቀልብ የሚገዛ ነበር፡፡
ተስፋዬ ካሲዳይ ኦርኬስትራ በቆየበት ጊዜ ሊሲቻዎ የተባለውን ልዩ የሆነውን የጣሊያን የሙዚቃ ዓይነት በመላው ጣሊያን በፍጥነት ማስተዋወቅ ችሏል፡፡ በዚህ የሙዚቃ ዘርፍ ሴኮንዶ ካሲዳይና ራኡል ካሲዳይ ከሚባሉ ዝነኛ ዘፋኞች እኩል ታዋቂነትንና ተደማጭነትን አግኝቷል፡፡ ከታዋቂው የሙዚቃ አቀናባሪ ሄንግል ጉአልዲ ጋር በመሆን ወደ አሜሪካ በማቅናትና N.B.C በተባለው የቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ ሙዚቃዎቹን በማቅረብ አድናቆትን አትርፏል፡፡
ከፍተኛ ውጤት ካስመዘገባቸው ሥራዎቹ መካከልም በጣሊያንኛ የጃዝ ሙዚቃን በመጫወት በብሔራዊ ቴሌቪዥን ለአሜሪካ አድናቂዎቹ ማቅረቡ ነው፡፡ ተስፋዬ ከሌሎች ዘፋኞች በተለየ ችሎታውን በተለያዩ ቋንቋዎች ለሕዝቡ በማድረስ ይታወቅ ነበር፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያትም በእንግሊዝኛ፣ በጀርመንኛ፣ በጣሊያንኛ፣ በዓረብኛ፣ በፈረንሣይኛ በግሪክ፣ በስፓኒሽና በሩሲያኛ ከሚናገሩ የቋንቋው ተናጋሪ እኩል ማቀንቀን በመቻሉ ነው፡፡
ተስፋዬ ካሳተማቸው አልበሞች መካከልም ሮሚና፣ ፕሪጌራ ዶጂ፣ ሰላም ለኢትዮጵያ በዋነኛነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ የተስፋዬን ዘፈኖች የሚያደራጁለት ጓደኞቹ፣ የባንድ አባላትና ተባባሪ ጸሐፊዎቹ ነበሩ፡፡ ከፍተኛ ዕገዛ ያደርግለት የነበረው የቅርብ ጓደኛው ጃኒ ካራንቲ ነው፡፡
መረጃዎች እንደሚያሳዩት ተስፋዬ ተዘጋጅተው ለሕዝቡ ያልቀረቡ ወደ 100 የሚጠጉ ሥራዎች አሉት፡፡ እነዚህ ሥራዎቹ ተሽጠው በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚሠሩ የበጎ አድራጎት ሥራዎች እንዲውል በኑዛዜው ላይ አስቀምጧል፡፡
ተስፋዬ በጣሊያን ውስጥ ከአንጄላ ፒዚግላ ጋር ትዳር መሥርቶ ይኖር እንደነበር ተነግሯል፡፡ እ.ኤ.አ. ኅዳር 19 ቀን 1982 በኮለን ካንሰር ታሞ በ43 ዓመቱ ከዚህ ዓለም ተሰናብቷል፡፡
ተስፋዬ ገብሬ የሠራቸውን ሥራዎች ለማስታወስ ከጥር 19 እስከ ጥር 28 ቀን 2012 ዓ.ም. በጣሊያን ባህል ማዕከል የፎቶ ዓውደ ርዕይ እየተካሄደ ይገኛል፡፡ የዓውደ ርዕዩ አዘጋጅ አቶ ማርቆስ ተግይበሉ እንዳሉት ተስፋዬ የሠራቸውን ሥራዎች ለማስታወስና አሁን ላይ የሚገኘው ትውልድም እንዲያውቀው ለማድረግ ኤግዚቢሽኑ አስፈላጊ መሆኑን ተናግሯል፡፡ በጣሊያን አገር በምትገኘው ሚስቱ አማካይነትም 100 የሚሆኑ ሥራዎቹ ታትመው ለሕዝቡ እንደሚደርሱም አቶ ማርቆስ ገልጸዋል፡፡
ከዚህ በኋላም ተስፋዬ ገብሬን ሕዝቡ እንዲያውቀው ለማድረግም ከኤግዚቢሽን በተጨማሪ ስለሱ የሚያወጋ መጽሐፍን ለመጻፍ በዝግጅት ላይ እንደሚገኙ አቶ ማርቆስ አስረድተዋል፡፡ ኤግዚቢሽኑም ተስፋዬ ገብሬ በኢትዮጵያም ሆነ በሌሎች አገሮች ላይ ለሙዚቃ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ካደረጉ ዘፋኞች ተርታ አንዱ መሆኑን የሚያሳይ ዓውደ ርዕይ ነው በማለት አዘጋጁ ተናግረዋል፡፡