Thursday, April 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህል“ቆሮማት” የዲራሼ የጋብቻ ሥርዓት

“ቆሮማት” የዲራሼ የጋብቻ ሥርዓት

ቀን:

በሔለን ተስፋዬ

ከአዲስ አበባ 560 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ጊዶሌ ከተማ ወይና ደጋ የአየር ጠባይ ያላትና ከጋርዱላ (ሆርማ-ቃሎ) ተራራ ሥር በሚፈልቀው ምንጭ ከመለምለሟ ባሻገር ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ ደኖች ተከባ የምትገኝ ከተማ ነች፡፡ በዚህ የተነሳ ወደ ከተማውና ተራራማው ቦታ ሲሄዱ መንፈስን የሚያድስ ቀዝቃዛ አየር ከማግኘት ባሻገር አዕምሮ ፀጥታ የሚገኝበት ሥፍራ ነው፡፡

በቆሎ፣ ማሽላ፣ ጤፍ፣ ሽምብራ፣ ሙዝ፣ ማንጎ፣ ብርቱካን፣ ፓፓያ፣ ሎሚና ሞሪንጋ ምርት በአካካቢው እንዲመረት ከተራራው የሚወርደው ጐሜረ አፈር ትልቁን ድርሻ እንዳለውና የአካባቢ አየር ንብረት ለእነዚህ ምርቶች ምቹ መሆኑን ብዙዎች ይመሰክራሉ፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በጊዶሌ ከተማና በዙሪያዋ ዲራሼ፣ ሞስዬ፣ ኩስሜና ማሾሌ ብሔረሰቦች ይገኛሉ፡፡ ቋንቋቸው የዲራሼ ቋንቋ ዲራይታት፣ የሞስዬ ሞስቻቻ፣ የኩስ ቋንቋ ኩስሚኛ፣ የማሽሎ ማሽልኛ በመባል እንደሚታወቅ አቶ ብሩ ሰማሎ የጻፉት የጋርዱላ ታሪክ ያስረዳል፡፡

የጊዶሌ ዙሪያ ማኅበረሰቦች የተለያዩ የለቅሶ፣ የሠርግ፣ የሥራ (የደቦ)፣ የሙዚቃ፣ የምግብ አሠራርና ሌሎችም በአካባቢው የተለመዱና እስካሁን የዘለቁ ትውፊታዊና ታሪካዊ ሥርዓቶች አሏቸው፡፡ ከእነዚህም ሥርዓቶች ውስጥ በዲራሼ ማኅበረሰብ የሚደረገው የቆሮማት (የጋብቻ) ሥርዓት ተጠቃሽ ነው፡፡

“ቆሮማት” የዲራሼ የጋብቻ ሥርዓት

ቆሮማት ማለት በዲራሼዎች ዘንድ የሚደረግ የሠርግ ሥነ ሥርዓት ነው፡፡ በዚሁም ሴቷ ከሦስት እስከ አራት ወራት የወንዱ ቤተሰቦች ዘንድ የምትቀለብበት ሥርዓት ነው፡፡ በዚህ ሥርዓት ሙሽሪት ልሠራ የምትችለው ነገር ቢኖር ጥጥ መፍተል ብቻ እንደሆነ አቶ ብሩ  ያስረዳሉ፡፡ የመቀለብ ሥርዓቱ የሚከናወነው በሙሽራው እህት ስትሆን ምንም ዓይነት ነገር እንዳይጐልባት ይደረጋል፡፡ እንደ አቶ ብሩ አገላለጽ በዚህ ጊዜ ሙሽሪት የምትነግሥበት ወቅት ነው ማለት ያስችላል ይላሉ፡፡

የጋብቻ ሥርዓት በፊት የሚቀድመው የትዳር ጓደኛ መረጣ ወይም በዲራይታት አጠራር (አዋይት) ዲራሼዎች ያከናውናሉ፡፡ የትዳር ጓደኛ መረጣ ከሚከናውንባቸው ቦታዎች መካከል ካላ አንዱና ዋነኛው ጥንዶቹ የሚናገናኙበት መንገድ ነው፡፡ ካላ ማለት ወጣት ሴቶችና ወንዶች በየጾታቸው ሆነው የደቦ እርሻ የሚያከናወኑበት የመተጋገዝና የመተባበር እሴታቸው ማሳያ ነው፡፡ የካላ ሥርዓት ውስጥ በቁጥር ከ14 እስከ 30 የሚደርሱ ወጣቶች ሰብሰብ ብለው ሥራው እንዲቀላጠፍና ቶሎ እንዲያልቅ የሚያደረጉበት መንገድ ነው፡፡

በዚህ የጋብቻ መረጣ ሥርዓት ማኅበረሰቡ ጥንቃቄ ከሚያደረግባቸው ነገሮች አንዱ ጥንዶቹ ከአንድ ጎሳ (ካፋ) እንዳይሆኑ ነው፡፡ ምክንያቱም የአንድ ጎሳ አባላት ከሆኑ እንደ እህትና ወንድም ይቆጠራሉና፡፡

በዚህ ማኅበረሰብ ሌላኛው የጋብቻ ሥርዓት ውስጥ አንዱ የውርስ ጋብቻ ሲሆን ይህም ታላቅ ወንድም ሲሞት ታናሽ ወንድም ሚስት የሚወርስበት መንገድ ነው፡፡ የሥርዓቱ ስያሜ በድራይታት ቋንቋ ‹‹ደሃላ›› ተብሎ ይጠራል፡፡

በዲራሼ ማኅበረሰብ ወደ ጋብቻ ለመግባት የመተጫጨት (ሪበት) ሥርዓት ጋብቻው እንዲሰምር ከሚያደርጉት መካከል ይጠቀሳል፡፡ ምክንያቱም በዚህ በመተጫጨት ወቅት የጋብቻው መንደርደሪያና ሴቷ እሽታዊን የምትገልጽበት ወቅት በመሆኑ ነው፡፡

ለጋብቻ የደረሰ ወጣት ለጋብቻ የፈለጋትን እንስት (ሴት) መንገድ ላይ ሲያገኛት እጇን በመያዝና የተለያዩ ቀልዶች በመናገር ፍላጎቱን በዚህ መልኩ ይገልጽላታል፡፡

እርሷም እንደ ሴት ወጉ ካንገራገረችና በትንሽ ካስለፋችው በኋላ መለሳለስ ልታሳየው እንደምትችል አቶ ብሩ ይናገራሉ፡፡ እሱም የእሷን መለሳለስና ፍላጎቷን ካየ በኋላ ከዛጎልና ከብር የተሠራ ጌጣጌጦች በአንገቷ ያስርላታል፡፡ ስጦታው በዲራይታት ቋንቋ ‹‹ሪቦት›› ወይም የማጪያ ስጦታ በመባል ይታወቃል፡፡

በዚህ መንገድ ልጅቱን ካጨ በኋላ ሥርዓቱ ሊበላሽ የሚችልበት መንገድ ሊኖር እንደሚችል አቶ ብሩ ያስረዳል፡፡ እሱም ልጁ በሥራው ታታሪና ጎበዝ ካልሆነ ነው፡፡ ምክንያቱም ቤተሰብ ለማፍራትና እነርሱን ለማስተዳደር ካልበቃ ስጦታውን ልትመልስለት እንደምትችል ነው የሚነገረው፡፡

ይህ እንዳይፈጠር የእሷ አክስት የእሱን ጉብዝና፣ ጎሳና ያለውን አጠቃላይ ሁኔታ የማጣራት ሥራ በመሥራት ትዳራቸው እንዲሰምር በማድረግ ትልቁን አስተዋጽኦ ትወጣለች፡፡

ለትዳር መታጨቷን ቀድማ የምትናገረው የአባቷ እህት (አክስቷ) ነው፡፡ አክስቷ በዚህን ጊዜ የማማከር ሥራ ከመሥራት ባሻገር ለእናቷ ስለ ልጇ መታጨት የምትናገረው እሷ ናት፡፡

ከዚያም እናቷ ለአባቷ ቀስብላ ትናገራለች፡፡  አባት እንደ ወግና ሥርዓቱ ቆጣ ቢልም ሥርዓቱ ይፈጸም ዘንድ አባት ይለሳለሳል፡፡ በወንድ ቤተሰብ በኩል ይህ ሁሉ ሲደረግ ቤተሰቦቹ (እናትና አባቷ ላያውቁ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ከዚህ ሥርዓት ቀጥሎ ‹‹ሎህላ›› ወይም የጠለፋ ሥርዓት ሊከናውን ሲል አባት እንዲያውቅ ይደረጋል፡፡ የጠለፋው ሥርዓት የሚከናወነው በግድ (ኃይል በመጠቀም) እንዳልሆነ የሚናገሩት አቶ ብሩ የሚካሄደውም ለእርሷ ቤተሰቦች (ወንድሞቿ) ካላቸው ክብር የተነሳ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡

በዲራሼ የጋብቻ ሥርዓት ‹‹ሎህላ›› ወይም ጠለፋ አንድ የባህል ሒደት ነው፡፡ ነገር ግን ጠለፋ የመጨረሻው መቋጫ አይደለም፡፡ ጠለፋው ከተካሄደ በኋላ ፈቃደኝነቷን ለማረጋገጥ ከእሷ ቤተሰብ አክስቷ፣ እህቷና ሚዜዎች ባሉበት ፈቃደኝነቷ ትጠየቃለች፡፡ ፈቃደኛ ካልሆነች ወደ አክስቷና እህቷ ጎን ትቆማለች፡፡ ፈቃደኛ ከሆነች ከሚዜዎች ጋር በመሆን ከሦስት እስከ አራት ወራት ድረስ ትቀለባለች፡፡ ሥርዓቱ ይሰምር ዘንድ የሙሽራው እህት እንደ ሞግዚት እሷን የመንከባከብ ኃላፊነት ይጣልበታል፡፡ የተለያዩ ባህላዊ ምግብ መጠጥ ትመገባለች፣ ቅቤ እንዲሁም ገላዋን እያጠቡና ቡሉኮ እያለበሱ ለወራት ያነግሷታል፡፡ የመቀለብ ሥርዓቱ የሚካሄደው በወንዱ ዘመዶች ቤት ሲሆን በመካከላቸው ምንም ዓይነት ጾታዊ ግንኙነት አይታሰብም፡፡

በዲራሼ የጋብቻ ሥርዓት ሹጌታ (ኩሲያንታ) ወይም ጥሎሽ ትልቅ ቦታ እንዳለው ይነገራል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የልጅቷ ቤተሰቦች ሴት ልጃቸውን በመስጠት ላሳዩት በጎ ምላሽና በሁለቱ ቤተሰቦችና ጎሳዎች መካከል ለሚመሠረተው ግንኙነት ዕውቅና ለመስጠት እንደሆነ አቶ ብሩ ባህላዊ ሥርዓቱን ያስረዳሉ፡፡

ከዚህ ሥርዓት በኋላ የቃሮብ አንታ (ሙሽሪትን ጥያቄ) ሥርዓት ይከናወናል፡፡ የሙሽራዋ መቀለቢያ ጊዜ ሊያልቅ ሲቃረብ ያላገቡ ጓደኞቿ፣ እህቷና አክስቷ እሷን ለመጠየቅ ወደ ምትቀለብበት ቦታ እየጨፈሩና እየዘፈኑ ወደ ሙሽሪት ወዳለችበት ጉዟቸውን ያቀናሉ፡፡ ይህ ሥርዓት የሚከናወነው ሙሽሪት ለብቻ የመኖር ጉዞ ማብቃቱንና ወደ ትዳር መግባቷን ለማሳየት የሚፈጸም እንደሆነ ነው አቶ ብሩ ያስረዱን፡፡

‹‹ምቶት›› ወይም የጋብቻ ስጦታ የሚከናወነው የጫጉላ ሥርዓት ከመከናወኑ ቀደም ብሎ ነው፡፡ ከሙሽሪት ቤተሰብ የጋብቻ ስጦታ ለመውሰድ የባለቤቷ ሚዜዎች አብረዋት ይሄዳሉ፡፡ ስጦታውን የሚጠይቁት ሚዜዎቹ ሲሆኑ ቤተሰቦቿ ባላቸው አቅም ልክ የመቋቋሚያ ስጦታ ያበረክቱላታል፡፡ በሌላ በኩልም በሁለተኛነት የሙሽራውን እህት በማስከተል ከሁሉም ዘመዶቿ የምታሰበስብበት ሒደትም አለ፡፡

በቀጣይ የሚከናወነው ሥርዓት ወደ ሙሽራው ቤት የሚደረግ ጉዞ ‹‹እንገላ›› የሚባለው ሲሆን ጉዞው በክራርና በፊላ ጨዋታ ይታጀባል፡፡ በዚያም ቦታ የተለየ ድግስ ተደግሶና ልዩ የሠርግ ሥርዓት ተደርጎ ይጠብቃቸዋል፡፡

በጭፈራና በሆይታ ሙሽሪትን ወደ ሙሽራው ቤት ከተሸኙ በኋላ የአባት ምርቃትና (ሆሙሲሳ) የሙሽራው አባትና መላው ቤተሰብ በዋና ቤት ሆነው ይቀበሏቸዋል፡፡ በባህሉም መሠረት ምርቃት ከተከናወነ በኋላ የሙሽራው ሚዜ፣ ሙሽሪትና የሙሽራዋ ሚዜ ብቻ በቤቱ ውስጥ ይቀራሉ፡፡ ሙሽራው ግን ወደ ውስጥ ሳይገባ ሙሽሪትን ሁለቱ ሚዜዎች እያጫወቷት ቆይታ ካደረጉ በኋላ ቀስ ብላ ሴቷ ሚዜ ትወጣለች፡፡ ወንዱ ሚዜም ከቆይታ በኋላ ይወጣል፡፡ በዚህ ወቅት ሙሽራው ቶሎ ካልገባ ሙሽሪት በሩን ዘግታ ውጭ ልታሳድረው ትችላለች፡፡ በዚህ መልኩ የደራሼ ቆርማታ ሥርዓት በማከናወን ቤተሰብ ይመሠርታሉ፡፡ ከጋብቻም በኋላ የልጆች ስም አወጣጥና ሌሎችም በማኅበረሰቡ የተለመዱ ባህላዊ ሥርዓቶች አሏቸው፡፡

በዚህ የጋብቻ መረጣ ሥርዓት ማኅበረሰቡ ጥንቃቄ ከሚያደረግባቸው ነገሮች አንዱ ጥንዶቹ ከአንድ ጎሳ (ካፋ) እንዳይሆኑ ነው፡፡ ምክንያቱም የአንድ ጎሳ አባላት ከሆኑ እንደ እህትና ወንድም ይቆጠራሉና፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...