Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናአዲስ አበባ ወደ ጎን እንዳትሰፋ የሚያደርግ የሕንፃ ከፍታ መጠንና ቁጥጥር ሕግ ሊወጣ...

አዲስ አበባ ወደ ጎን እንዳትሰፋ የሚያደርግ የሕንፃ ከፍታ መጠንና ቁጥጥር ሕግ ሊወጣ ነው

ቀን:

የአዲስ አበባ ከተማን የጎንዮሽ መስፋፋት ለመግታት ያለመ አስገዳጅ የሕንፃዎች ከፍታ መጠን ሕግና አፈጻጸሙን የሚቆጣጠር ደንብ፣ የከተማዋ አስተዳደር ሊያወጣ መሆኑን ምንጮች ገለጹ፡፡

በቀጣዮቹ ጥቂት ሳምንታት ለከተማዋ ካቢኔ ቀርቦ ውይይት ከተደረገበት በኋላ ይፀድቃል ተብሎ የሚጠበቀው ይኼ ሕግ፣ የአዲስ አበባ ከተማን ወደ ጎን መስፋፋት በመግታት ቀጣይ ዕድገቷ ወደ ላይ እንዲሆን ማድረግን ያለመ እንደሆነ ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ይህ አሠራር የአዲስ አበባን የአፍሪካ የፖለቲካ መዲናነት እንዲጎላና ውበቷም እንዲታደስ ያደርጋል ተብሎ እንደታመነበት፣ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮቹ ገልጸዋል፡፡ የተረቀቀው ሕግ ከተማዋ በፕላን የምትመራና ውበትንም እንድትላበስ ከማድረግ ባለፈ፣ የጎንዮሽ ዕድገቷ አንዲገደብ የማድረግ ዓላማንም አካቷል፡፡

በመሆኑም ከዚህ በኋላ በከተማዋ የሚገነቡ ማናቸውም ሕንፃዎች የመጨረሻ ወለሎች፣ ለከተማዋ ነዋሪዎች የሚቀርቡ መኖሪያ ቤቶችን የማካተት ግዴታ ይጣልባቸዋል፡፡ በዚህም መሠረት ከአራት እስከ አምስት የሚሆኑ የሕንፃ የመጨረሻ ወለሎች ለመኖሪያ ቤትነት ተዘጋጅተው ለተጠቃሚዎች እንዲተላለፉ የሚወጣው ሕግ ግዴታ እንደሚጥል ለማወቅ ተችሏል፡፡

ይህም የከተማዋ ወደጎን መስፋፋት የሚገድብ ከመሆኑ ባለፈ ከነዋሪዎች የመክፈል አቅም ጋር ተመጣጣኝ የሆኑ የመኖሪያ ቤቶች አቅርቦት እንዲጨምር፣ መኖሪያ ቤቶችን በማቅረብ ረገድ የግል ባለሀብቶች ሚና የሚያሳድግ ይሆናል ተብሎ እምነት እንደተጣለበት ምንጮቹ ገልጸዋል፡፡

በቅርቡ ይፀድቃል ተብሎ የሚጠበቀው ይህ ሕግ በከተማዋ የሚገነቡ ሕንፃዎች ላይ ይጣል የነበረውን የከፍታ ወሰን የሚያስቀር እንደሆነ የገለጹት ምንጮች፣ ሕንፃዎች የሚገነቡበት ይዞታ፣ የአፈር ባህሪና የመሸከም አቅም ካላስገደደ በስተቀር የሕንፃ ቁመት ወሰን ላይ ይጣል የነበረውን የከፍታ ገደብ ያስቀራል ብለዋል፡፡

ይሁን እንጂ በዓለም አቀፍ ስታንዳርድ መሠረት የአቪዬሽን (የአየር ትራንስርት) አካባቢዎችና የከተማዋ ቅርሶች በሕንፃዎች እንዳይዋጡ ሲባል፣ በእነዚህ አካባቢዎች የሕንፃ ከፍታ ገደብ ይጣላል ተብሏል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም አንዱ ሕንፃ ሌላውን እንዳይጋርድ፣ ከመሀል ከተማ እስከ ዳርቻ ድረስ የሚገነቡት ሕንፃዎች ዘመናዊ የከተማ ፕላንና የኪነ ሕንፃ ጥበብ ጠብቀው እርስ በእርስ የሚናበቡና ፍሰት ያላቸው እንዲሆኑ ማድረግ ሌላው ዓላማ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

በመሆኑም የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ማዕከል እንዲሆኑ በተለዩ አካባቢዎች የሚገነቡ ሕንፃዎች ቁመት እጅግ በጣም ረጅም እንዲሆን፣ የከተማዋ ሁለተኛ ዞን ተብለው በሚለዩ አካባቢዎች ደግሞ በዋናው ማዕከል ከሚገነቡ ሕንፃዎች ቁመት በመጠኑ አነስ ብለው እንዲገነቡ፣ በሦስተኛውና በመጨረሻው የከተማዋ ዞኖች በሆኑት አካባቢዎች የሚገነቡት ሕንፃዎችም እንዲሁ ከዋናው ማዕከልና ከሁለተኛው የከተማዋ ዞን ሕንፃዎች ቁመት እንደ ቅደም ተከተላቸው አነስተኛ እየሆኑ እንዲገነቡ ለማድረግ መታቀዱን ምንጮች ገልጸዋል፡፡

 ወደ ትግበራ ከገባ ሁለተኛ ዓመቱ ላይ የሚገኘው አሥረኛው የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን እንዳስቀመጠው ከሆነ፣ ከጥቁር አንበሳ ትምህርት ቤት አንስቶ ብሔራዊ ቴአትርና ለገሃርን አካቶ እስከ ጨርቆስ አካባቢ፣ እንዲሁም ወደ ምዕራብ ሜክሲኮ፣ ልደታና ሰንጋ ተራ ተብለው የሚጠሩ አካባቢዎች በሚቀጥሉት ዓመታት የአዲስ አበባ ዋና ማዕከል ይሆናሉ፡፡

በእነዚህ አካባቢዎች የሚገነቡ ሕንፃዎች መነሻ ከፍታ 70 ሜትር ሆኖ ከዚያ በላይ እስከተቻለው ከፍታ ድረስ መገንባት ማስተር ፕላኑ የሚፈቅድ ሲሆን፣ ከ70 ሜትር በታች የሆነ ግንባታ ማከናወን ግን አይቻልም፡፡

ሁለተኛ ደረጃ የከተማ ማዕከል ይሆናሉ ተብለው የተለዩት የዋናው ማዕከል አዋሳኝ አካባቢዎች ናቸው፡፡ በሦስተኛ ደረጃ የከተማ ማዕከልነት የተመደቡት ደግሞ ከሁለተኛው ከተማ ማዕከል አንስቶ እስከ ቀለበት መንገዱን ማዕከል ያደረጉ አካባቢዎች መሆናቸውን፣ የቀለበት መንገዱን ማዕከል ካደረጉ አካባቢዎች ውጪ እስከ ከተማዋ ጠርዝ የሚገኙት አካባቢዎች በአራተኛ ደረጃ የከተማ ማዕከልነት እንደሚመደቡ ማስተር ፕላኑ ያመለክታል፡፡

አሁን ያለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማዋን ማስተር ፕላን ጠብቆ እየሄደ መሆኑን ሪፖርተር ያነጋገራቸው ማስተር ፕላኑን በማርቀቅ ሒደት የተሳተፉ አንድ ባለሙያ ገልጸዋል፡፡

ለገሃር አካባቢ የተጀመረው ቅንጡ መኖሪያ መንደር ግንባታ፣ የጎተራ አካባቢ ዘመናዊ መንደር ግንባታ፣ የሸገር መናፈሻ ልማትና የሌሎች ፓርኮች ልማት፣ እንዲሁም የታቀደው የሕንፃ ከፍታ ሕግና ከዚሁ ጋር የተያያዘው የመኖሪያ ቤቶች ልማት ከሞላ ጎደል ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ከማስተር ፕላኑ የተናበቡ ፕሮጀክቶች እንደሆኑ ባለሙያው አመልክተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...