Sunday, April 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናጉለሌ ክፍለ ከተማና አዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት አካባቢን በመበከል ክስ ቀረበባቸው

ጉለሌ ክፍለ ከተማና አዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት አካባቢን በመበከል ክስ ቀረበባቸው

ቀን:

ተቋማቱ አዋጅ በመተላለፍ ማኅረበሰቡን ለጉዳት መዳረጋቸው ተጠቁሟል

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጉለሌ ክፍለ ከተማ ንግድና ኢንዱስትሪ ጽሕፈት ቤትና የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት፣ ሕግ ተላልፈው የአካባቢ ብክለት ፈጽመዋል የሚል ክስ ቀረበባቸው፡፡

ተቋማቱ የተከሰሱት በፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ጉለሌ ምድብ ፍትሐ ብሔርና ቂርቆስ ምድብ ፍትሐ ብሔር ችሎቶች ነው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የጉለሌ ክፍለ ከተማ ንግድና ኢንዱስትሪ ጽሕፈት ቤት ክስ የቀረበበት በክፍለ ከተማው ወረዳ አሥር ልዩ ስሙ ሸጎሌ መንደር ስድስት ተብሎ በሚጠራው ሥፍራ ከሸጎሌ የቁም እንስሳት ገበያ ማዕከል ጋር ተያይዞ ደርሷል በተባለ የአካባቢ ብክለት ነው፡፡

በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስድስት ውስጥ በመኖሪያ ቤቶች መካከል የሚገኘውና ከ30 ዓመታት በላይ የእንስሳት ዕርድና የሥጋ አቅርቦት በመስጠት ላይ የሚገኘው የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ደግሞ፣ በየዕለቱ በሚያወጣቸው የዕርድ ተረፈ ምርቶች የአካባቢ ብክለት ፈጽሟል የሚል ክስ ቀርቦበታል፡፡

የሕዝብ ጥቅም ለማስከበር ሲባል የቀረበ ክስ በሚል ክስ ለፌዴራል ፍርድ ቤት ያቀረቡት፣ ለሕዝብ ጥቅም ተሟጋች የሕግ አማካሪና ጠበቃ መሆናቸውን ለፍርድ ቤት ያሳወቁት አቶ መልካሙ ኦጎ የተባሉ የሕግ ባለሙያ ናቸው፡፡

ለፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ጉለሌ ምድብ ፍትሐ ብሔር ችሎት፣ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ንግድና ኢንዱስትሪ ጽሕፈት ቤት ላይ የቀረበው ክስ እንደሚያስረዳው፣ የሸጎሌ የቁም እንስሳት ገበያ ማዕከል ከአካባቢው ነዋሪዎች መኖሪያ ቤት ርቀቱ ሦስት ሜትር ነው፡፡ ገበያ ማዕከሉ ተገቢ የሆነ የማስተዳደር ጥንቃቄ እንደማይደረግለት፣ የንግድ ዘርፉ በባህሪው ጥንቃቄ የሚፈልግ ቢሆንም ለአካባቢው ነዋሪዎችም ሆነ ተላላፊ መንገደኞች በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 44 መሠረት ንፅህናና ጤንነቱ የተጠበቀ አካባቢ ሊኖር ሲገባ ያንን እንዲያጣ መደረጉን፣ በቁም እንስሳት ግብይት አዋጅ ቁጥር 819/2006 እና በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 341/2007 መሠረት መሟላት ያለባቸው መሥፈርቶች አለመሟላታቸውን ክሱ ያብራራል፡፡

ለቁም እንስሳት መሸጫ የሚሆን የቦታ ስፋት 20,000 ሜትር ካሬ መሆን ሲገባው፣ በሥራ ላይ ያለው የገበያ ማዕከል ስፋት ግን 5,000 ሜትር ካሬ መሆኑ በምሳሌነት ተጠቅሷል፡፡ የተለያዩ እንስሳትን በየዓይነታቸው ለይቶ ለማስቀመጥ ያልተመቻቸ፣ ለግብይት የማይመች፣ ተገቢውን አቅርቦቶች ያላሟላና ከደረጃ በታች መሆኑም በክሱ ተገልጿል፡፡ በጽሕፈት ቤቱ አዋጅና ደንቡን በመጣስ መሥፈርቱን ያላሟላና የሕዝብን ጥቅም በሚጎዳ መንገድ ማዕከሉን በማቋቋሙ፣ በነዋሪዎች የዕለት ተዕለት የኑሮ ሁኔታ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩንም ክሱ ያብራራል፡፡

ማንም ሰው አካባቢን ሊበክል ወይም በሌላ ሰው በኩል እንዲበክል ማድረግ እንደማይችል፣ በአዋጅ ቁጥር 300/95 አንቀጽ (3) ላይ ተደንግጎ የሚገኘውን በመተላለፍ ተከሳሽ አካባቢውን መበከሉንም በክሱ ተገልጿል፡፡

በተለይ በአካባቢው ነዋሪዎችም ላይ የእንስሳት ፍሳሽና ሽታ የሚያመጡ ነገሮች በቀጥታ ወደ መንደሩ እንደሚለቀቁ፣ የግብይት ማዕከሉ ጠባብ በመሆኑ እንስሳት ከማዕከሉ ውጪ ሲሸጡ በማምለጥ ሲሯሯጡ በሕፃናት፣ በአቅመ ደካሞችና በአካባቢው በሚንቀሳቀሱ ሰዎች ላይ ጭምር አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩን፣ ምቾት መንሳቱንና ደኅንነታቸውን ሥጋት ውስጥ እንደጣለውም በክሱ ተጠቁሟል፡፡ የገበያተኞችና የእንስሳት ድምፅ ነዋሪውን እየረበሸ መሆኑን፣ በማዕከሉ ጥበት በታጎሩበት ታፍነው የሚሞቱ እንስሳት በሕገወጥ መንገድ ላይ ስለሚጣሉ ከፍተኛ የሆነ ሽታ አካባቢውን እንደሚበክለውና ከፍተኛ የሆነ የጤና ችግር ማስከተሉንም የቀረበው ክስ ያብራራል፡፡

የንግድ ማዕከሉ ከፍተኛ የሆነ ድምፅ፣ ፍሳሽ፣ ሽታና ሌላም ብክለት መፍጠሩንና በቋሚ ነዋሪዎችና በተላላፊ መንገደኞች ላይ በጤናቸው፣ በኢኮኖሚያቸውና በማኅበራዊ ሕይወታቸው ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ መፍጠሩን፣ በከተማ አስተዳደሩ አካባቢ ጥበቃና በአረንጓዴ ልማት ኮሚሽን፣ በዕንባ ጠባቂ ተቋም፣ በሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ በክፍለ ከተማው ጤና ጽሕፈት ቤትና በበርካታ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ተቋማት በተደረገ ምርመራና ማጣራት ድርጊቱ መወገዙንና ለኅብረተሰቡ ጤናም አደገኛ መሆኑ መረጋገጡን ክሱ ያብራራል፡፡ በመሆኑም በማኅበረሰቡ ላይ እያደረሰ ካለው ከፍተኛ ጉዳት አንፃር የሸጎሌ ቁም እንስሳት የግብይት ማዕከል ከቦታው እንዲነሳ፣ ያደረሰው ጉዳት በባለሙያ ተጠንቶ የፍትሐ ብሔር ክስ የማቅረብ መብታቸው እንዲጠበቅላቸው ውሳኔ እንዲሰጣቸው የሕግ ባለሙያው ዳኝነት ጠይቀዋል፡፡

በተመሳሳይ በፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቂርቆስ ምድብ ችሎት፣ አካባቢን በመበከል ክስ የቀረበበት የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ነው፡፡ ክሱም እንደሚያስረዳው፣ ድርጅቱ የእንስሳት ዕርድና ሥጋ አቅርቦት አገልግሎት የሚሰጥበት ቦታ በሺዎች የሚቆጠሩ የከተማ ነዋሪዎች በትራንስፖርትና በእግር የሚተላለፉበት ቦታ ላይ ነው፡፡ ድርጅቱ በየዕለቱ የሚያወጣቸው የዕርድ ተረፈ ምርቶች ማለትም አጥንት፣ ደም፣ ቁርጥራጭ ሥጋዎችና ሌሎች ተረፈ ምርቶች በአግባቡና ደረጃውን በጠበቀ የቆሻሻ አወጋገድ መንገድ ተከትሎ እንደማያስወግድ ክሱ ያብራራል፡፡

ተረፈ ምርቶችን መልሶ ለመጠቀም በሚያስችል ቴክኖሎጂ በመታገዝ፣ የኅብረተሰቡን ጤናና አካባቢውን በማይጎዳ መንገድ ለአገልግሎት ባለማዋሉ፣ ፈሳሾችን በአካባቢው በመልቀቅና ጠጣሮችን በግቢው በማከማቸት፣ በካይ ጋዞችን በአካባቢውና ነዋሪዎች ላይ ላለፉት 30 ዓመታት እየለቀቀና እየበከለ መሆኑ በክሱ ተገልጿል፡፡ ድርጅቱ ተገቢ ያልሆነ ድርጊቱን እንዲያቆም የአካባቢው ነዋሪዎች በተደጋጋሚ የጠየቁ ቢሆንም፣ ሊታረም እንዳልቻለም ተጠቁሟል፡፡

አዋጅ ቁጥር 300/95 አንቀጽ (3) ድንጋጌን ከመተላለፍ በተጨማሪ ከላይ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ንግድና ኢንዱስትሪ ጽሕፈት ቤት ክስ ላይ የተጠቀሱ ተቋማት በመመርመር ያረጋገጡት፣ ከድርጅቱ የሚወጣው ፍሳሽ ቆሻሻና በካይ ጋዝ በቀጥታ የአካባቢውን ነዋሪዎች ለችግር እየዳረገ መሆኑን ማረጋገጣቸውንና የሚመለከታቸው ተቋማት ማስጠንቀቂያ ጭምር ሰጥተውት እንደነበር ተብራርቷል፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎችና ተላላፊ መንገደኞች ንፁህና ጤንነቱ በተጠበቀ አካባቢ የመኖር ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን እንዲያጡ መደረጋቸውንም አክሏል፡፡

በመሆኑም ቄራዎች ድርጅት ካለበት ቦታ እንዲነሳና በጠቅላላ ኅብረተሰቡ ላይ የደረሰውን የጤና፣ የኢኮኖሚና የሞራላዊ ጉዳትን በሚመለከት ወደፊት በባለሙያ ተጠንቶ የፍትሐ ብሔር ክስ ማቅረብ እንዲቻል ውሳኔ እንዲሰጥ ለሁለቱም ችሎቶች የዳኝነት ጥያቄ ቀርቧል፡፡ ፍርድ ቤቶቹም በከሳሽና በተከሳሾች መካከል የሚደረገውን ክርክር ለመስማት ለመጋቢት 2 እና 4 ቀን 2012 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥተዋል፡፡     

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...

‹‹ደስታ›› የተባለችው አማርኛ ተናጋሪ ሮቦት በሳይንስ ሙዚየም

‹‹እንደ ሮቦት ዋነኛው አገልግሎቴ ውስብስብ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችንና አሠራሮችን...