Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናኢዜማ ሥርዓተ አልበኝነት በጋራ በቃ የሚባልበት ጊዜው ዛሬ ነው አለ

ኢዜማ ሥርዓተ አልበኝነት በጋራ በቃ የሚባልበት ጊዜው ዛሬ ነው አለ

ቀን:

ኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ዓርብ ጥር 22 ቀን 2012 ዓ.ም. ባወጣው ባለ ሰባት ነጥብ መግለጫ፣ ሥርዓተ አልበኝነትን በጋራ በቃ የሚባልበት ጊዜው ዛሬ ነው አለ፡፡ መንግሥት በራሱ ውስጥም ሆነ ከራሱ ውጪ ያሉትን ሥርዓተ አልበኞች በሕግ ሊቀጣ እንደሚገባ፣ ይህ ካልሆነ ግን ሕዝቡ ራሱን ወደ መከላከልና ሰላሙን ወደ ማስጠበቅ ሊገፋ ይችላል ሲል አስታውቛል፡፡ መንግሥት ተማሪዎቹን ከዕገታ የማስለቀቁን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጣና የሕዝቡን ልብ እንዲያሳርፍ አበክሮ እንደሚጠይቅ ገልጿል፡፡  

የኢትዮጵያውያን የፍትሕ፣ የእኩልነትና የዴሞክራሲ ጥያቄ በርካታ አሠርት ዓመታትን ያስቆጠረ ብቻ ሳይሆን የአያሌ ዜጎችን ሁለንተናዊ መስዋዕትነት የወሰደ ረጅም ጉዞ መሆኑን፣ በተለይ ባለፉት አምስት ዓመታት የሁሉንም ተሳትፎ ያማከለና አገዛዙ ከሚቋቋመው በላይ የሆነ ንቅናቄ የታየበት ትግል መደረጉንና ውጤቱም የዛሬዋን ሁኔታ መውለዱን ኢዜማ አስታውሷል፡፡

‹‹ከበርካታ የዓለም አገሮች ተሞክሮ እንዳየነው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ማዋለድ ከባድ ምጥ ያለበት የጭንቅ ጊዜ ማሳለፍ የግድ መሆኑን ነው፡፡ በኢትዮጵያችንም እያየን ያለነው ይህንኑ ነው፡፡ በእንዲህ ዓይነት አስጨናቂ ወቅት ይህን ሒደት እንደ አንድ ከባድ ታሪካዊ ኃላፊነት ወስደው የሚሠሩ የመኖራቸውን ያህል፣ ግርግር ፈጥረውና የራሳቸውን ፍላጎት በኃይል ለመጫን የሚፍጨረጨሩ ቡድኖችና ግለሰቦች መኖራቸውን በየዕለቱ በየቦታው የምናየው አሳዛኝ ክስተት ሆኗል፤›› ብሏል፡፡

ኢዜማ ከተመሠረተ ጀምሮ ለአገር ሰላምና ለሕዝብ መረጋጋት የራሱን ያልተቆጠበ አስተዋፅኦ እያበረከተ መገኘቱን፣ የተያዘው የሽግግር ሒደት ለአንድ ወገን የማይተውና የሁሉንም ተሳትፎ የሚጠይቅ እንደሆነ እንደሚያምን፣ ያም ሆኖ በዚህ ፈታኝ ወቅት የመንግሥት ሚና ትልቅና ከፍተኛ እንደሚሆን እገነዘባለሁ ሲል ገልጿል፡፡

በአገር አቀፍ ደረጃ የተከሰቱ ፈታኝ ሁኔታዎችንና የመንግሥትን ምላሽ በመገምገም በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያለውን አቋም ሲገልጽ፣ የየትኛውም በኢትዮጵያ አገረንግሥት ግዛት ውስጥ የሚንቀሳቀስ ቡድንም ሆነ ግለሰብ ተግባር የአገሪቱን ሕጎችና ያፀደቀቻቸውንና የተቀበለቻቸውን ድንጋጌዎች ባከበረ መንገድ ብቻ እንዲሆን ማድረግ የሚገባው ዛሬ እንደሆነ፣ ዜጎች በሕግ ጥበቃ እንደሚደረግላቸው ካልተረጋገጠላቸውና ከሕግ በታች መሆናቸውን ካልተረዱና ማንም እየተነሳ የፈለገውን አድርጎ ‹‹አልጠየቅም›› የሚል ማናለብኝነት ከሰፈነ፣ መቼም ማቆሚያ ወደማይኖረው የሁከት ዓለም ዘውብሎ እንዳይገባ ያሠጋል ብሏል፡፡

ሁሉም የፖለቲካ አስተሳሰቦችን በነፃነትና በሠለጠነ መንገድ መግለጽ፣ በሥልጣን ላይ ያለውንም ሆነ ሌሎች ፓርቲዎችን መተቸት፣ ማጋለጥ አልፎም በምርጫ ከሥልጣን ማውረድ የተለመደና ተገቢም ሊሆን እንደሚችል ኢዜማ አስረድቷል፡፡ ‹‹አገርን የሚያዋርድ ተግባር መፈጸም ግን ለማንም ያልተፈቀደ የአገር ክህደት ወንጀል መሆኑ በግልጽ ሊታወቅ ይገባል፡፡ በሕዝብ፣ በሃይማኖቶች፣ በብሔረሰቦች፣ በሰንደቅ ዓላማና በመሳሰሉት የአገር መገለጫዎች ላይ የሚፈጸም ማንኛውም የነውር ተግባር አስተማሪ የሆነ ቅጣት የሚያስከትል መሆን አለበት፤›› ሲል አክሏል፡፡

ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የሚሰጠው ትኩረት ከዚህ በፊት ከነበረው የተለየና የወቅቱ የፖለቲካ ትኩሳት የሚጠብቃቸው መሆን እንዳለበት እንደሚያምን፣ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች ግቢዎች የተከሰቱ ችግሮች የሕዝቡን ልብ ሰብረው ያለፉ ክስተቶች መሆናቸውን፣ ከሁሉም በላይ በደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ይማሩ በነበሩ ተማሪዎች ላይ የተደረገው ዕገታ ውሉ የጠፋና የመንግሥትን የተማሪዎችን ሕይወት የመጠበቅ ኃላፊነት አለመወጣት ያጋለጠ መሆኑን አስታውቋል፡፡ ከዚህ ቀደም መንግሥት ስለተማሪዎቹ ዕገታ ወቅቱን የጠበቀና ትክክለኛ መረጃ ለተማሪዎቹ ቤተሰቦችና ለሕዝብ እንዲሰጥ ኢዜማ መጠየቁንም አስታውሷል፡፡ ‹‹ሆኖም መንግሥት ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃ የመስጠት ከፍተኛ ክፍተት ታይቶበታል፡፡ ከዚህ አንፃር መንግሥት ተማሪዎቹን ከዕገታ የማስለቀቁን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጣና የሕዝብን ልብ እንዲያሳርፍ አበክረን እንጠይቃለን፤›› በማለት አቋሙን አስታውቋል፡፡

‹‹በየትኛውም አካባቢ የሚፈጸም ግፍ ለየትኛውም አካባቢ ለሚገኝ ሰላም ጠንቅ ነው እንዲሉ፣ ለተማሪዎቻችን የመቆም ጉዳይ የአንድ ወገን ወይም የአንድ ክልል ጉዳይ ሊሆን አይገባውም፡፡ የሁላችንንም ተናብቦ መሥራት ግድ ይላል፡፡ ከዚህ አንፃር የታገቱ ልጆቻችንን በሰላም ለማስለቀቅ ሕግና ሥርዓትን በተከተለ መንገድ በአገራችን በሁሉም አካባቢዎች በሕዝባችን የሚደረጉ ሀቀኛ ጥረቶችን እንደግፋለን፤›› ሲልም ኢዜማ አስረድቷል፡፡ ገርንና ሕዝብን የማወክ አንድ አካል የሆነው የሞጣ መስጊዶችን የማቃጠል ድርጊት በአጥፊዎቹ ላይ አስተማሪርምጃ ተወስዶ ለሕዝብ ይፋ እንዲደረግ፣ መስጊዶቹን አድሶና ምዕመናኑን ክሶ ወደ ቀድሞው ሰላማዊ አገልግሎት ለመመለስ የሚደረጉትን የአብሮነት እንቅስቃሴዎችን እንደሚደግፍም ገልጿል፡፡

‹‹በቅርቡ የጥምቀት በዓል አከባበር ወቅት በተወሰኑት አካባቢዎች በተለይም በአቦምሳ የከተራ በዓል ሳይከበር የቀረበትን ሁኔታ ታዝበናል፡፡ የጥምቀት በዓል ሃይማኖታዊ ይዘቱን ጠብቆ እንዳይከበር እንቅፋት የሆኑ አካላትም ለሕግ እንዲቀርቡና ተገቢ ቅጣት እንዲያገኙ፤›› ሲል ጥያቄ አቅርቧል፡፡

ኢዜማ የምርጫ ወረዳዎችን አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች እንዲሁም ሕዝባዊ ውይይቶች በሚያካሄድበት ጊዜ ጥቂት ሥርዓተ አልበኞች የሚፈጥሩት ግርግር ሕዝብን የሚወክል እንዳልሆነ ቢረዳም፣ በአጠቃላይ በፖለቲካ ድባቡ ላይ የሚፈጠረው የስሜት መሻከር እንደሚያሳስበው አስታውቋል፡፡ ‹‹በተለይም ወደ ምርጫ ለመግባት ዝግጅት እያደረግን ነው በሚባልበት በዚህ ወቅት፣ ሕዝቡ ሕገ መንግሥታዊ የሆነውን የመሰብሰብ መብቱን መጠቀም የማይችልበት ሁኔታ ይታያል፡፡ ባሳለፍነው ሳምንት የተከሰቱ በተለይ የጎንደርና የሸዋ ሮቢት ድርጊቶችን ተከታትሎ አጥፊዎችን እንዲቀጣ አቤቱታችንን ለመንግሥት አቅርበናል፡፡ ኢዜማ ላይ የሚከሰቱ ችግሮች ሁለት ገጽታ አላቸው፡፡ አንደኛው ከመንግሥት መዋቅር የሚመጣ ሲሆን፣ ሁለተኛው ከዚያ ውጪ የሆኑ ሥርዓተ አልበኞች የሚፈጥሩት ነው፤›› ብሏል፡፡

‹‹ባለጌና ጨዋ በተጣሉ ጊዜ ለጊዜውም ቢሆን ባለጌ ያሸነፈ ይመስላል የሚል የቆየ የአገራችን ብሂል አለ፡፡ ይህም ጨዋው በሕግ ስለሚያምንና የሕግ አስከባሪ ባለጌውን ይቀጣል ብሎ በማመን ነው፡፡ በእኛ መዋቅርም የሚታየው ይኸው ሕግን የማክበር ጉዳይ ነው፡፡ ይህም ቢሆን ልክ አለው፡፡ ከገደብ ያለፈ ነውር ሲፈጸም አመራሩም፣ አባሉም፣ ደጋፊውም ራሱን፣ ፓርቲውንና አገሩን የመጠበቅ ተፈጥሯዊ መብት አለው፤›› ካለ በኃላ፣ ኢዜማ አገርንና ሕዝብን ለድርድር አያቀርብም ሲል አስረድቷል፡፡ ‹‹ይህንንም ደግመን ደጋግመን ተናግረናል፡፡ መንግሥት በራሱ ውስጥም ሆነ ከራሱ ውጪ ያሉትን ሥርዓተ አልበኞች በሕግ ሊቀጣ ይገባል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ሕዝቡ ራሱን ወደ መከላከልና ሰላሙን ወደ ማስጠበቅ ሊገፋ ይችላል፡፡ ይህም በየትኛውም መመዘኛ ስህተት ሊሆን አይችልም። በመጨረሻም የዴሞክራሲ ግንባታ ሒደቱን መጠበቅ ለሁላችንም የሚጠቅም፣ አገርና ሕዝብን የሚታደግ ብቸኛው መንገድ መሆኑን አውቀን እንድንጓዝበት መልዕክታችንን እያስተላለፍን፣ ሥርዓተ አልበኝነትን በጋራ በቃ የምንልበት ጊዜው ዛሬ መሆኑን በአፅንኦት እንገልጻለን፤›› በማለት መግለጫውን ደምድሟል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...