የዓለም የጤና ድርጅት ሰሞኑን ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ በቻይና የተከሰተው ኮሮና ቫይረስ ዓለም አቀፍ የጤና ሥጋት መሆኑን አውጇል፡፡ እዚህ መደምደሚያ ላይ የደረሰውም ቫይረሱ ከቻይና በተጨማሪ ወደ ሌሎች አገሮች በመዛመቱ ነው፡፡ የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም እንዳስታወቁት፣ ቫይረሱ በሌሎች አገሮች መሠራጨቱ ለጤና ሥጋት ሆኖ እንዲታወጅ ምክንያት ሆኗል፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት ባወጣው መግለጫ መሠረት ለመጀመሪያ ጊዜ የኮሮና ቫይረስ በቻይና ውሃን ግዛት/ክልል የኖቭል ኮሮና ቫይረስ መከሰቱን ታኅሳስ 21 ቀን 2012 ዓ.ም. አረጋግጧል፡፡ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥርም እየጨመረ መሆኑንና እስከ ዓርብ ጥር 22 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ የተጠረጠሩ 12,167 ሲሆኑ፣ 7,711 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል፡፡ የ213 ሰዎች ሕይወት በቫይረሱ ማለፉን የዓለም ጤና ድርጅት ገልጿል፡፡
በሌላ በኩል 1,370 የሚሆኑት በቫይረሱ የተጠቁት አደገኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኙና 124 የሚሆኑት ደግሞ አገግመው ከሆስፒታል መውጣታቸው ተገልጿል፡፡ ከቻይና ውጪ በ20 አገሮች 98 ሰዎች ቫይረሱ እንዳለባቸው የተረጋጋጠ መሆኑን ድርጅቱ አስታውቋል፡፡ የበሽታው ሥጋት በቻይና በጣም ከፍተኛ ሲሆን፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ መሆኑን የዓለም የጤና ድርጅት እየገለጸ ነው፡፡
የጤና ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ሳይንስ ኢንስቲትዩት በኢትዮጵያ እየተደረገ ያለውን ዝግጅት በተመለከተ ሰሞኑን መግለጫ መስጠታቸው ይታወሳል፡፡ በቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ከቻይናና ከአጎራባች አገሮች ለሚመጡ መንገደኞች የሙቀት ልየታ (thermal screening) እና ፎርም የማስሞላት ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉ፣ የልየታ ሥራውን ለማጠናከር በቂ የሰው ኃይል መመደቡ፣ በቦሌ አለም አቀፍ ኤርፖርት ጊዜያዊ የለይቶ መከታተያ ክፍልና የሰው ኃይልን ጨምሮ አስፈላጊው ግብዓት መዘጋጀቱ፣ በበሽታው ለተጠረጠሩ መንገደኞች ጊዜያዊ ማቆያ ማዕከል እንዲሁ ዝግጁ መደረጉ ተገልጿል፡፡
በፅኑ ለታመሙና ከፍተኛ የሕክምና ክትትል ለሚያስፈልጋቸው ታካሚዎች በቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል የተለየ ክፍል መዘጋጀቱ፣ እንዲሁም በጤና ሚኒስቴር የሚመራ የኖቭል ኮሮና ቫይረስ የወረርሽኝ ቅድመ ዝግጅት የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትን በማካተት ብሔራዊ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ወደ ሥራ መገባቱ ተመልክቷል።
በኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሚመራ የቴክኒክ ቡድን ተቋቁሞ ሥራውን መጀመሩ፣ ከቻይና የመጡ አራት ተማሪዎች ተጠርጥረው በልየታ ማዕከል ውስጥ ሆነው ናሙና ከተወሰደ በኋላ ደቡብ አፍሪካ ተልኮ ተመርምሮ ውጤቱ ነጋቲቭ መሆኑ መገለጹ አይዘነጋም፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዓርብ ጥር 22 ቀን 2012 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል ስለሚደረገው ጥንቃቄ ለመገናኛ ብዙኃን አስጎብኝቷል፡፡ በዕለቱ የጤና ባለሙያዎች በወጪና ገቢ መንገደኞች ላይ የሚካሄደውን የጤና ምርመራ ለመገናኛ ባለሙያዎች አሳይተዋል፡፡