ከፍተኛ የምርት እጥረት የሚታይበትን የምግብ ዘይት በአገር ውስጥ በማምረትና በማቀነባበር የገበያ ክፍተቱን ለመሙላት ደፍረው መዋዕለ ንዋያቸውን ያፈሰሱ ባለሀብቶች፣ መንግሥት ቃል የገባላቸውን ድጋፍ ከማድረግ መቆጠቡ ሳያንስ የፓርቲ ኢንዳውመንቶች፣ እንዲሁም የተፈቀደላቸው የመንግሥትና የግል ድርጅቶች ብቻ ፓልም የምግብ ዘይት ከውጭ እንዲያስገቡና ገበያውን ሙሉ በሙሉ እንዲቆጣጠሩ በማድረግ ጉዳት እያደረሰባቸው መሆኑን አስታወቁ፡፡
በአካል ተገኝተው ቅሬታቸውን ያቀረቡት ባለሀብቶች የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ለምግብ ዘይት የሚወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ለመቆጠብና የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን ዘይት ለማምረት እንዲሰማሩ በ2009 ዓ.ም. ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት፣ ድፍድፍ የፓልም ዘይት ወደ አገር በማስገባት፣ በማጣራትና በገበያው ፍላጎት መሠረት በማሸግና በተጓዳኝ የአገር ውስጥ ግብዓቶችን በመጠቀም፣ የምግብ ዘይት ሙሉ በሙሉ በአገር ውስጥ ለማምረት የሚያስችሉ ፋብሪካዎችን አቋቁመው ወደ ምርት መግባታቸውን ገልጸዋል፡፡
በመንግሥት ልዩ ድጋፍ በሚገኝ የውጭ ምንዛሪ ከውጭ የሚገባውን የፓልም ዘይት በመቀነስ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች የገበያ ድርሻ እንዲጨምር እንደሚደረግ በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ተስፋ አድርገው ሀብታቸውን ቢያፈሱም፣ የፋብሪካ መትከያ ቦታ እንዲያገኙና በመጀመርያዎቹ የምርት ሒደት ወራት የውጭ ምንዛሪ እንዲያገኙ ከመደረጉ በስተቀር የቀጠለ ድጋፍ እንደሌለና ችላ እንደተባሉ በቅሬታ ተናግረዋል፡፡
ሪፖርተር ያገኘው የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመለክተው፣ የአራቱ የኢሕአዴግ ድርጅቶች (ኢንዳውመንቶች) 96 በመቶ የሚሆነውን የምግብ ዘይት እስከ መስከረም ወር 2012 ዓ.ም. ድረስ በብቸኝነት ሲያስመጡ ነበር፡፡
በመስከረም ወር የፓርቲ ኢንዳውመንቶች ዘይት እንዳያስገቡ ከታገዱ በኋላ፣ ያሉትን ሦስት ወራት ደግሞ የኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት ሲያስገባ መቆየቱን መረጃው ያመለክታል፡፡ ከጥር ወር 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ለሚቀጥሉት ዓመታት ደግሞ ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች መርጠው በሚወክሏቸው ድርጅቶች አማካይነት፣ የምግብ ዘይት ከውጭ ገዝተው ለገበያ እንዲያቀርቡ ተወስኗል፡፡
በዚህ መሠረት ክልሎቹና ሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች የወከሏቸው 11 የግል ድርጅቶች የምግብ ዘይት ግዥ ከውጭ አገሮች ፈጽመው በአገር ውስጥ እንዲያከፋፍሉ የተወሰነ ሲሆን፣ ለዚህም ሲባል እነዚህ ድርጅቶች የውጭ ምንዛሪ በቅድሚያ እንዲያገኙ ባንኮች መታዘዛቸውን የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
ቅሬታቸውን ለሪፖርተር ያቀረቡት ባለሀብቶች እንደሚሉት ከሆነ፣ እነሱን ጨምሮ በተመሳሳይ መስክ ወደ ምርት የገቡ ሌሎች ኩባንያዎች በአንድነት እስከ 15 በመቶ የሚሆነውን የአገር ውስጥ የምግብ ዘይት ለመሸፈን የሚያስችል አቅም አላቸው፡፡
በመሆኑም የአገሪቱን አጠቃላይ የምግብ ዘይት ፍላጎት ማቅረብ እንችላለን ማለታቸው እንዳልሆነ የገለጹት ባለሀብቶቹ፣ የተመረጡ ድርጅቶች ብቻ ያለ ገደብ የውጭ ምንዛሪ እንዲያገኙ፣ የሚያስገቡት ዘይትም ከቀረጥ ነፃ እንዲሆን ድጋፍ እያገኙና በዚህም ምክንያት ከሞላ ጎደል የዘይት ገበያውን በተቆጣጠሩበት ሁኔታ ውስጥ፣ ምርቱን በአገር ውስጥ ለመተካት ሀብታቸውን ያፈሰሱ ባለሀብቶች ለጉዳት እየተዳረጉ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
መንግሥት አነስተኛ የውጭ ምንዛሪ በመጠቀም የፓልም ድፍድፍ አስገብተው በማቀነባበር ለገበያ ማቅረብ የጀመሩና ዘይት ሙሉ በሙሉ በአገር ውስጥ ለማምረት እየተጉ የሚገኙ ባለሀብቶችን ቢደግፍ፣ ምርቱን በአጭር ጊዜ ውስጥ ሙሉ በመሉ በአገር ውስጥ ማምረት እንደሚቻልና በዚህም የውጭ ምንዛሪን መቆጠብ፣ የግብርና ዘርፉን ከዘይት ኢንዱስትሪዎች ለማስተሳሰርና ቀላል ለማይባሉ ዜጎችም የሥራ ዕድል መፍጠር እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡
ነገር ግን መንግሥት ለእነሱ ያሳየው ቸልተኝነትና የምግብ ዘይት ከውጭ ብቻ እንዲገባ መርጦ እየሄደበት ያለው መንገድ፣ ምርቱን በአገር ውስጥ ምርት ለመተካት ዕቅድ እንደሌለው አመላካች ነው ብለዋል፡፡ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ያስቀመጠውን የፖሊሲ አቅጣጫ አምነው ሀብታቸውን ያፈሰሱ ባለሀብቶችንና ኢንዱስትሪዎቻቸውን ሊደግፍ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ለንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ወንድሙ ፍላቴ ለጉዳዩ ምላሽ እንዲሰጡ በስልክም ሆነ በአጭር የጽሑፍ መልዕክት ጥያቄ ቢቀርብም፣ ለኅትመት እስከገባንበት ዓርብ ምሽት ድረስ ምላሽ አልሰጡም፡፡
ሪፖርተር ያገኘው የምግብ ዘይት አቅርቦትን የተመለከተ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የዕቅድ ሰነድ፣ ምርቱን በአገር ውስጥ በመተካት እየወጣ ያለውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ማዳን ትኩረት የሚደረግበት ዘርፍ እንደሆነ ይገልጻል፡፡ ይሁን እንጂ የጊዜ ማዕቀፍን አያመለክትም፡፡ በአሁኑ ወቅት በየወሩ 40 ሚሊዮን ሊትር ዘይት ከውጭ እየተገዛ ለሸማቾች በመከፋፈል ላይ እንደሆነ መረጃው ያመለክታል፡፡