Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉየተፈጥሮ ጋዝ ኢንዱስትሪ ለመመሥረት ምን ያግደናል?

የተፈጥሮ ጋዝ ኢንዱስትሪ ለመመሥረት ምን ያግደናል?

ቀን:

በክንፈ ኪሩቤል

አሁን ያለው የአገሪቱ የኃይል አቅርቦት ከፍላጎቱ ጋር መመጣጠን እንዳልቻለ ግልጽ ነው፡፡ የሕዝብ ቁጠሩ በፍጥነት ዕያደገ ነው፣ ፍላጎት እየጨመረ ነው፡፡ ከውኃ፣ ከንፋስ፣ ከጂኦተርማል፣ ከፀሐይ፣ ወዘተ. የሚገኘው ኃይል በቂ አልሆነም፡፡ አሳሳቢው ጉዳይ አገራችን በየጊዜው በአየር ንብረት መለዋወጥ የተነሳ እየተጠቃች መሄዷ በምግብ አቅርቦትና በእርሻ ምርታማነት ላይ ተፅዕኖ ማስከተሉ ብቻ ሳይሆን፣ ለኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ፈተና መሆኑን እያየን ጭምር ነው፡፡ ስለሆነም በከርሰ ምድራችን ውስጥ ያለውን የተፈጥሮ ጋዝ ለመጠቀም ማሰብ የግድ ይላል፡፡ ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ጋዝ ኢንዱስትሪ ማቋቋም ብትችል ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አለው፡፡ ለዚህም መዋዕለ ንዋያቸውንና ቴክኖሎጂያቸውን ለመጠቀም የሚፈልጉ የምሥራቁም ሆነ የምዕራቡ አገሮችና ኩባንያዎች ለመኖራቸው አያጠያይቅም፣ የ100 ሚሊዮን ሕዝብ ገበያ አለ፡፡

የተፈጥሮ ደናችን ተመናምኖ ከአገሪቱ ስፋት አንፃር ለምን ከአሥር በመቶ ሊቀር ቻለ ብለን ብንጠይቅ ጉዳዩ ግልጽ ነው፡፡ የአራችን ብዙኃኑ ሕዝብ የገጠር ነዋሪ በመሆኑ፣ ምግብ ለማብሰል የዛፍ ውጤቶችን መጠቀም የግድ ስለሆነበት ዛፎችን በመቁረጥና ከሰል በማክሰል፣ ጭራሮ በመልቀም፣ ወዘተ. ችግሩን መወጣት ስለነበረበት ነው፡፡ ሁኔታው በከተማም እምብዛም ባይለይም የከተሜው ሰው ደግሞ በጥቂቱ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ ኬሮሲንና ቡታ ጋዝ በተጨማሪ ይጠቀማል፡፡ በቅርቡ እንደምናየው የሕዝቡ ገቢ ምንም ሳይጨምር የኤሌክተሪክ ኃይል ታሪፍ በመጨመሩ ኑሮውን የሚያስመርር እያደረገው ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ከገቢው አኳያ የኃይል አጠቃቀሙ ሊቀንስ ይችላል ኑሮውን ያዛባል፡፡ ለምሳሌ ኬሮሲንና ቡታ ጋዝ በውጭ ምንዛሪ የሚገዙ በመሆናቸውና ዋጋቸውም እየጨመረ በመምጣቱ፣ ተጠቃሚው እያነሰ ሊሄድ ግድ ነው ማለትም ለብዙኃኑ እንደ ቅንጦት ዕቃዎች ሊሆንበት ነው፡፡ የከሰሉም ዋጋ እንደዚሁ ነው፡፡ ሕዝቡ ግን አማራጭ አልተቀመጠለትም፡፡

በተጨማሪ የደኖች መጨፍጨፍ ለምግብ ማብሰያነት ብቻ ሳይሆን፣ ለሕንፃ ግንባታ የሚውለው አጣና፣ የቺፕ ውድ ፍብረካ እንዲሁም የጣውላ እንጨት ፍላጎቶች ተጨማሪ ለደን ዕድገታችን መመናመን ምክንያት ናቸው፡፡ የሚጨፈጨፈውን ያክል ዛፍ መልሶ ማን ይተክላል? በደኖች መጨፍጨፍ ምክንያትና በካርቦን ዳይኦክሳይድ ልቀት የዓለም የአየር ንብረት መዛባቱ ገሃድ ሆኗል፡፡ የከባቢ አየር ሙቀት መጨመሩን የሕዝብ መነጋገሪያ ከሆነ ሰንብቷል፡፡ አገራችን ከሰሃራ በረሃ ደቡብ ያለች አገር እንደ መሆኗ ከበረሃው መስፋፋት አንፃር ሲታይ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ እንገኛለን፡፡

እናም ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በምርጫው አሸናፊነትን ካገኙ በሶማሌ ክልል ካሉብና ሂላላ ተብሎ በሚጠራው ሥፍራ ከ46 ዓመታት በፊት ከተገኘው የተፈጥሮ ጋዝ ውስጥ፣ የደን መጨፍጨፍን ሊታደግ የሚችልና ቡታ ጋዝን ከተፈጥሮ ጋዝን በማምረት ለምግብ ዝግጅት ስንል የምናውለውን የእንጨትና ከሰል አቅርቦት በመቀነስ በቡታ ጋዝ መተካት ያስችለናል፡፡ ይህን ለማሳካት እንዴት እንችላለን የሚል ጥያቄ ሊያስነሳ ይችላል፡፡ ለዚህ በቂ መልስ አለ፡፡ ጉዳዩ ትኩረት በማጣቱ ነው እንጂ የጋዝ ልማቱ ጉዳይ መስመር ይዞ ከተቀመጠ 27 ዓመታትን አሳልፏል፡፡

የቻይና ኩባንያ ተጨማሪ ጉድጓዶችን በኦጋዴን እየቆፈሩ እንዳሉ ይነገራል፡፡ ተጨማሪ ጋዝ መኖሩን እያመላከቱ ናቸው፡፡ በደርግ ዘመን ሩሲያውያን አሥር የጋዝ አመንጪ ጉድጓዶችን በካሉብ ቆፍረዋል፡፡ የምርታማነት ሙከራዎችን በበርካታ ጉድጓዶች አከናውነዋል፣ ውጤቶቹም አበረታች ነበሩ፡፡ 

በዘመነ ኢሕአዴግ እንዲፈርስ የተደረገው ‹‹የካሉብ ጋዝ ልማት ሼር ኩባንያ›› በወቅቱ ከዓለም ባንክ ባገኘው መጠነኛ ዕርዳታ ወደ ዘጠኝ በሚጠጉ የካሉብ ጉድጓዶች ላይ ጋዝ ለማምረት የሚያስችሉ መሣሪያዎችን በቻይናው ‹‹ዞንግያንግ ፔትሮሊየለም›› ኩባንያ እንዲገጠሙለት ቢያደርግም፣ ላለፉት 20 ዓመታት በላይ በጋዙ ጉድጓዶቹ አናት ላይ ባሉት ‹‹የክሪስማስ ትሪዎች›› ላይ ግፊት ለመኖሩ መረጃዎች አሉ፡፡

የካሉብ ጋዝ በኬሚስትሪው ከበካይና አደገኛው ከሆነው ሰልፈር (ድኝ) የፀዳ ስለሆነ ለምርትም ሆነ ለጤንነት ጠንቅ የማያስከትል መሆኑን፣ በእንግሊዝ የፒቪቲ ላቦራተር የተረጋገጠ ለመሆኑ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

የካሉብ ጋዝ ከፍተኛው መጠን የሜቴን ጋዝ ያለው ቢሆንም፣ ለአገሪቱ ጥቅም መዋል የሚችል የፕሮፔንና የቡቴን ጋዝ ያዘለ በመሆኑ፣ የአገራችንን የደን ጭፍጨፋ ለመቀነስ ያለው አስተዋጽኦ ቀላል አይሆንም፡፡ ይህንን ጋዝ ጥቅም ላይ ለማዋል በ1980ዎቹ ዓመታት የዓለም ባንክ ጥረት አድርጓል፡፡ ግን የወቅቱ መንግሥት ድጋፍ ስላልነበረው በከንቱ ቀርቷል፡፡

አገራችን ዛሬ በኃይል አቅርቦት ችግር ውሰጥ ወድቃለች፡፡ የተፈጥሮ ጋዛችን እያለ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ስንችል በግድቦች ውስጥ የውኃ መጠን በመቀነሱ፣ ሳቢያ አገሪቱ በኃይል ቀውስ ውስጥ በየጊዜው ትገኛለች፡፡ ምክንያቱም ዝናብን በፈለግነው መጠንና ጊዜ ማዝነብ የፈጣሪ ፈቃድ ስለሆነ ነው፡፡

በውጭ ምንዛሪ ከጎረቤት አገሮች የምናስገባውን ቡታ ጋዝ ለመግዛት የሚችል ጥቂት የኅብረተስብ ክፍል አለ፡፡ አሁን በውድ ዋጋ እየተገዛ ነው፡፡ ነገር ግን ለብዙኃኑ ተደራሽ አይደለም፡፡ ስለሆነም ይህን ከ40 ዓመታት በላይ ሳንጠቀምበት የቆየውን የተፈጥሮ ጋዝ እንደ ነዳጅ ኃይል አቅርቦት ብንጠቀምበት አብዛኛው የአገራችን ሕዝብ ለምግብ ማብሰል ሲባል ለእንጨትና ለከሰል የሚጨፈጭፈውን ደን ለመታደግ ያስችላል፡፡ ከጤና አኳያ ቡታ ጋዝ ከጭስ የፀዳ በመሆኑ በበካይ ጭስ የማይጎዳ ጤናማ ኅብረተሰብ ይኖረናል፡፡

ለምሳሌ ቡታ ጋዝን በአገራችን ለማምረት ብንወስን የሚከተሉት ኢንቨስትመንቶችና የሥራ ዘርፎች ይከፈታሉ፣  የቡታ ጋዝ አመላላሽ የቦቴ ኩባንያዎችና እነርሱን የሚያገለግሉ ሰርቪስ ሰጪዎች ድርጅቶች ይፈጠራሉ፣ የቡታ ጋዙን ከቦቴ ተቀብለው በሲሊንደር የሚሞሉ ጣቢያዎች ይቋቋማሉ፣ በመላው አገሪቱ ቡታ ጋዙን ለማከፋፈል የሚወከሉ ሰዎች ወይም ድርጅቶች ይፈጠራሉ፣ በሃገር ውስጥ ደረጃውን ጠብቀው የቡታጋዝ ሲሊንደር የሚያመርቱ ፋብሪካዎች ይጀመራሉ፣ ለቡታ ጋዝ ምድጃ አምራች ኩባንያዎች የመሳሰሉት ይፈጠራሉ፣ ለወጣቱ ትውልድ የሥራ ዕድልም ይከፈታል፡፡ መንግሥት በማዕድንና ኢርጂው ዘርፍ በቂ ክትትልና ቁጥጥር የሚያደርግበትን የመዋቅርና የሕግ ማዕቀፍ በማዘጋጀት ኢንቨስትመንቱን መደገፍ ይችላል፡፡

ዋናው ቁምነገር ቡታ ጋዝ በአገራችን ተመርቶ በተመጣጣኝ ዋጋ ለሕዝባችን ቢደርስ የደን ጭፍጨፋው በእጅጉ ይቀንሳል፡፡ የምንተክላቸው ችግኞች በለጋ ዕድሜያቸው አይቆረጡም፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ወደ 50 በመቶ ገደማ የሚጠጉት የገጠሩ ሴቶች(እናቶቻችን፣ እህቶቻችን) እጅግ አድካሚ ከሆነው የእንጨት ለቀማና ሸክም ይገላገላሉ፡፡ ለዚህ የሚጠፋው ጊዜ ለሌላ ምርታማ ሥራ ይውላል፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ ከእንጦጦ ተራራ እንጨት በመልቀም የሚተዳደሩትን ሴቶች ሕይወት ወጣ ብሎ ማየቱ በራሱ ገላጭ ነው፡፡ ቡታ ጋዝ ንፁህ ማገዶ ስለሆነ የገጠሩም ሆነ የከተማው ሕዝብ ጤንነት ይሻሻላል፣ የውጭ ምንዛሪንም ያድናል፡፡

ባለፉት 27 ዓመታት በተለያዩ ምክንያቶች የተፈጥሮ ጋዙ ሳይለማ ቆይቷል፡፡ ለምሳሌ ከጋዝ ኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት፣ ከተፈጥሮ ጋዝ የዩሪያ ማዳበሪያ ለማምረትም እንደሚቻል ይታወቃል፡፡ የአገር ውስጥ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች (ለምሳሌ ድሬዳዋ) አንፃራዊ ቅርበት ለጋዙ ስላለው በቧንቧ መስመር ተጠቃሚ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ይህንን የሚደግፍ ፖሊሲ አልነበረም፡፡ አገራችን ለውስጥ ፍጆታዋ ከበቂ በላይ ክምችት እንዳላት የተጠና ቢሆንም እንደ ኳታር፣ኢራን፣ እስራኤል፣ ታንዛኒያ፣ ሞዛምቢክ፣ ወዘተ ያህል አስተማማኝ ለውጭ ኤክስፖርት የሚሆን የክምችት መጠን ለመኖሩ አጠያያቂ ሊሆን ይችላል፡፡ ፍለጋው ሲቀጥል ተጨማሪ ክምችት ማግኘት እንችላለን፡፡

በከፍተኛ ደረጃ የተፈጥሮ ጋዝንም ሆነ ድፍድፍ ነዳጅን ማልማት ከፍተኛ ካፒታል ይጠይቃል፡፡ ሆኖም የጋዙን ልማት በአነስተኛ ደረጃ ጀምሮ ቀስ በቀስ ወደ መካከለኛ ደረጃ ለማሸጋገር እንደሚቻል ማቀድ ይቻላል፡፡  ሌላው የሽያጭና ግዥ ዋጋ ጉዳይ ነው፡፡ ለምሳሌ የነዳጅ ድፍድፍ የበርሜል ሽያጭ ዋጋና የተፈጥሮ ጋዝ ሽያጭ ዋጋ በእጅጉ የተለያዩ ናቸው፡፡ የተፈጥሮ ጋዝ ዋጋ በብሪቲሽ ተርማል ዩኒት ሲሰላ የጋዙ ዋጋ ተመን በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ ስለሆነም ጋዝን አቀዝቅዞ ኤክስፖርት ለማድረግ የሚጠይቀው የካፒታል ኢንቨስትመንት በብዙ ቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ሲሆን፣ ባለው ዝቅተኛ የጋዝ ዋጋ ኢንቨስተሩ ያወጣውን የካፒታል ወጪ መልሶ ለአገሪቱ ትርፍ የማምጣቱ ጉዳይ የአጭር ጊዜ ጉዳይ ስለማይሆን ከፍተኛ ጥንቃቄ የተሞላ የባለሙያዎችን ጥናት ይጠይቃል፡፡ ስለሆነም መንግሥት ማተኮር ያለበት የአገሪቱን ሕዝብ በአጭር ጊዜ ውስጥ በገሃድ ተጠቃሚ የሚያደርግና ለችግሮቻችን መፍትሔ ሊሰጥ የሚችል ፕሮጀክት መንደፍ ነው፡፡ ምክንያቱም የጋዝ ጉድጓዶቹ ዝግጁ ከሆኑ ዘመናትን አሳልፈዋልና፡፡

የዓለም ባንክ ከ33 ዓመታት በፊት ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ጋዙዋን በመካከለኛ ኢንዱስትሪ ደረጃ እንድትመሠርት ወደ 176 ሚሊዮን ዶላር ብድር ፈቅዶ፣ ለዚሁም ጉዳይ ጂዲሲ በሚባል የአሜሪካ አማካሪ ድርጀት አስፈላጊውን ጥናት እንዲያጠና ድጋፍ አድርጎ ነበር፡፡ የጥናቱን ውጤት ተመርኩዞ በወቅቱ የዓለም ባንክ ያቀረበው ሐሳብ ጋዙን ለማልማት መንግሥትና የግል ዘርፉ በሽርክና አክሲዮን ኩባንያ እንዲመሠርቱ ምክረ ሐሳብ በመስጠቱ በወቅቱ ‹‹የካሉብ ጋዝ ሼር›› ኩባንያ የሚባል ተመሥርቶ ብዙ ግለሰቦች የአክሲዮን ድርሻ ገዝተው እንደነበር በመገናኛ ብዙኃን ሲነገር ሰምተናል፡፡ እንዲያውም የክልሉ ተወላጆች ለጋዝ ልማቱ ካላቸው ፍላጎት የተነሳ አብዛኛዎቹን የግል አክሲዮኖች እንደገዙ ይነገር ነበር፡፡ ሆኖም በአገሪቱ የመጀመሪያው ጠቅላይ ሚኒስትር ትዕዛዝ ምክንያቱ ግልጽ ባልሆነ መንገድ (በወቅቱ የነበሩ ባለሥልጣናት ምክንያቱን ያውቁት ይሆናል) ኩባንያው እንዲፈርስ ስለመደረጉ መረጃዎች አሉ፡፡ በካሉብ ጋዝ ኩባንያ መፍረስ የተነሳ የዓለም ባንክም የፈቀደውን ብድር ለመሰረዝ ተገደደ፡፡

ስለዚህ አሁን የደን ሽፋን ለመጨመር ለታቀደው ዓላማ መሳካት ካለፈው ስህተቶቻችን ልምድ በጎውን ተምረን፣ አገሪቱ ዛሬ እየገጠማት ካለው ዘርፈ ብዙ ችግሮች መካከል አንደኛው የምግብ ማብሰያ ኃይል አቅርቦትን ለመፍታት በተለይ የኢነርጂ መስኩን በጋዝ ልማት ለማጠናከር ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) መንግሥትም ሆነ ሌላ ተመራጭ  መንግሥት፣ ይህንን አቅጣጫ ትኩረት ቢያደርግበትና ወደ መፍትሔ ዕርምጃ ከአሁኑ ቢተኮርበት መልካም ይሆናል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አወዛጋቢው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጉዳይ

በኢትዮጵያ የሕገ መንግሥት ማሻሻል ጉዳይ ከፍተኛ የፖለቲካ ውዝግብ የሚቀሰቀስበት...

 መፍትሔ  ያላዘለው  የጎዳና  መደብሮችን  ማፍረስ

በአበበ ፍቅር ያለፉት ስድስት ዓመታት በርካቶች በግጭቶችና በመፈናቀሎች በከፍተኛ ሁኔታ...

የተናደው ከቀደምቱ አንዱ የነበረው የአዲስ አበባ ታሪካዊ ሕንፃ

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ መናገሻ ከተማቸውን...

የአከርካሪ አጥንት ሕክምናን ከፍ ያደረገው ‘ካይሮፕራክቲክ’

በአፍሪካ ከጀርባ ሕመም ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች ለከፍተኛ የአካል...