Monday, May 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

እኔ የምለዉኢኮኖሚያዊ ዕድገትንና የአገር ውስጥ ገቢን ምን አገናኛቸው?

ኢኮኖሚያዊ ዕድገትንና የአገር ውስጥ ገቢን ምን አገናኛቸው?

ቀን:

በአንድነት ኃይሉ

አንድ የተለመደ አባባል አለ፡፡ “ገቢ ለልማት” የሚባል፡፡ ስህተት ነው፡፡ ገቢ ሌላ ነገር፣ ልማት ሌላ ነገር ነው፡፡ ምንም አያገናኛቸውም፡፡ ልማት የሚከወነው በዕውቀት ነው፡፡ የገቢ ሥርዓት በሥራ ላይ መዋል ያለበት በሥራ ላይ የዋለውን ሀብት ለመከታተል ነው፡፡ አንድ አገር ሀብቷን በሥራ ላይ ማዋል ሳትችል የገቢ ሥርዓት ሊኖራት አይችልም፣ ወይም ከገቢ በፊት ልማቱ ነው የሚቀድመው፡፡ አገር መልማት ስትችል ነው ገቢ ሊኖራት የሚችለው፡፡ በግልጽ ቋንቋ ከገቢ በፊት ልማቱ ይቀድማል፡፡ ልማቱ ነው ገቢን የሚፈጥረው፡፡ ደሃ አገሮች ከድህነት ለመውጣት የምናደርገውን ትግል ከባድ ያደረገብን ሌላው ምክንያት ይኸው ነው፡፡ ነገሩ ተገላብጧል፡፡ ሁለት ነገሮችን ብቻ እንኳን ብናይ ጉዳዩ ግልጽ ይሆንልናል፡፡

የአንድ አገር የገቢ ሥርዓት በሥራ ላይ ከማዋሏ በፊት የየግለሰቡ የገቢ መጠንና ምክንያት ተለይቶ መታወቅ አለበት፡፡ ለምሳሌ የገቢ መጠንን ብናይ የቀን ገቢው 1‚000 ብር የሆነና 100 ብር የሆነ እኩል በሚጠቀሟቸው ነገሮች እኩል የሆነ ክፍያ እንዲጠየቁ መደረጉ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡ ዝቅተኛ ገቢ ያለው ሰው ጠንካራ የሆነ የገበያ ተሳታፊ አይሆንም፡፡ ይህ ማለት ግብይት ደካማ ስለሚሆን የምርት ዕድገትን ደካማ ያደርገዋል፡፡ የምርት ዕድገት ደካማ ነው ማለት ደግሞ ግልጽ ነው፡፡ የገቢ ምክንያቱን ብናይ ደግሞ የአንድ አገር ሕዝብ ገንዘብን የሚያገኝበት ምክንያት አንዱ አምርቶ፣ ሌላው ተቀጥሮ ወይም ነግዶ ሊሆን ይችላል፡፡ አምራች የሆነ ግለሰብና ተቀጣሪ ወይም ነጋዴ የሆነ ግለሰብ ገንዘብን የሚያገኝበት መጠን የተለያየ ነው፡፡ አንዱ አምርቶ ነው ሌላው ነግዶ፣ አንዱ ደግሞ ተቀጥሮ ይህ ማለት አምራቹ ከሁለቱም የተሻለ ነው፡፡

- Advertisement -

ከተቀጣሪው ደግሞ ነጋዴው አምራቹ እንዳመረተው መጠን ገቢው ከፍ ዝቅ ይላል፡፡ ነጋዴውም እንደዚያው፣ የተቀጣሪው ግን ቋሚ ነው፡፡ የዚህ ዓይነት የገቢ ምክንያትና ልዩነት የሚስተናገድበት አገር ውስጥ ወጥ የሆነ የገቢ ሥርዓት መዘርጋቱ ግብይት ላይ ከፍተኛ ችግር ስላለው፣ አሁንም ልማቱ በደካማ ግብይት ምክንያት ፈጣንና ሁሉንም አሳታፊ መሆን አይችልም፡፡ ታዲያ ገቢ ግብይቱን ወይም ልማቱን አላበላሸውም?

ሁለተኛ የገቢ ሥርዓትን በትክክለኛው ጊዜና ሰዓት በሥራ ላይ ካላዋልነው ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡ ሲጀመር ገንዘብን ከገበያ ውስጥ የምንሰበስብበትን ትክክለኛ ቦታና ጊዜ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ገንዘብ ከገበያ ውስጥ የሚሰበሰብበት ትክክለኛው ቦታ ከአምራች ላይ ነው፡፡ ከነጋዴና ከተቀጣሪ አይሰበሰብም፡፡ ከአምራች ላይ በሸጠ ቁጥር ትሰበስባለህ፡፡ ከነጋዴ ላይ ግን የምትሰበስብበት ትክክለኛው ጊዜ ደግሞ ዓመታዊ ትርፍ ግብር እንዲከፍል ብታደርገው ነው፡፡ ተቀጣሪ ያው ተቀጣሪ ነው፡፡ ከአገሪቷ የገንዘብ ሥርዓት ውስጥ ያለው ድርሻ በጣም ዝቅ ያለ ነው፡፡ ነገር ግን ከፍተኛ የሆነ ቁጥር የሚይዝ ነው፡፡

ስለዚህም የመግዛት አቅም እንዲኖረው በማድረግ ግብይቱን ጤናማ በማድረግ አምራች እንዲያመርት፣ ነጋዴ እንዲሸጥ ማድረግ ነው፡፡ ትክክለኛ ሥራ ለአንድ አገር ገንዘብ ተራ ነገር ነው፡፡ ምክንያቱም የአንድ አገር ልማት የሚከወነው በዕውቀት እንጂ፣ በገንዘብ አይደለም፡፡ ዕውቀት ሳያመርት ገንዘብ አይገዛም፣ ዕውቀት ለማምረት ግብዓቱ ጊዜ ነው፡፡ ጊዜ ደግሞ ለሁላችንም በነፃ እኩል የተሰጠን ሀብት ነው፡፡ ልማትን ለማምጣት ዕውቀታችንንና ጊዜያችንን በአግባቡ መጠቀም ብቻ ነው የሚጠበቅብን እንጂ፣ ልማት ከገቢ ጋር አይገናኝም፡፡ አንድ አገር ገንዘብን የምታዘጋጅበት፣ የምታሠራጭበትና የምትቆጣጠርበት የራሷ የሆነ ፍልስፍና ሊኖራት ይችላል፡፡

ለምሳሌ ቫት፣ ግብር፣ ኤክሳይዝ ታክስ፣ ወዘተ.፡፡ ይህንን ተግባራዊ ስታደርግ ምክንያቱ ልማት ከሆነ ውጤቱ ጥፋት ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ግብይትን ማዳከሙ ብቻ ሳይሆን፣ ልማትን ከገንዘብ ጋር ማገናኘቱ አደጋው የከፋ ነው፡፡ በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ገንዘብ በቀጥታ ወደ ገበያ ውስጥ የሚገባበት ምክንያትና መንገድ የተወሰነ ነው፡፡ የምንሰበስብበት መንገድና ምክንያት በጣም ከፍተኛ ከሆነ ዞሮ ዞሮ የገንዘብ ሥርጭቱንና የገበያውን ግብይት ሥርዓት ያበላሸዋል፡፡ ብናመርት እንኳን ዝቅተኛ ግብይት ነው የሚኖረን፡፡ አንድ አገር ገንዘብን ወደ ገበያ ለማስገባት በርካታ ነገሮችን መፍጠርና መጠቀም አለባት እንጂ፣ ገንዘብን ለመሰብሰብ ይኼንን ያክል ትኩረት መስጠት አደጋ አለው፡፡

አንድ አገር ገንዘብን ለመሰብሰብ ቀጥተኛ ተቋማት እንዳላት ሁሉ፣ ገንዘብን ወደ ገበያ ውስጥ ለማስገባት የዚያኑ ያህል በርካታ ምክንያት ሊኖራት ይገባል፡፡ ግለሰብ ገንዘብ ማዘጋጀት አይችልም፡፡ አገር ደግሞ የምታዘጋጀውን ገንዘብ ግለሰብ ዘንድ ሊደርስ የሚችልበትን በርካታ ምክንያት መፍጠር ይጠበቅባታል፡፡ እኔ እስከማውቀው ድረስ አገራችን ገንዘብ ብታዘጋጅም ከግለሰብ አንስቶ፣ እስከ ትልልቅ ተቋማት ድረስ ያሉ በርካታ ዕድሎችን በመጠቀም ገንዘብ ወደ ገበያ ውስጥ ሲገባ አላየሁም፡፡ ይህ የሚያመለክተው ገንዘብ ወደ ገበያ ውስጥ የሚገባበት ምክንያት በጣም ሩቅ መሆኑን ነው፡፡ ግለሰቦች በቂ ገቢና በገቢ ምንጫቸው የሚተማመኑ ከሆኑ ወይም ገንዘባቸውን ቢገበያዩበትም በቀላሉ መልሰው እንደሚተኩት የሚተማመኑ ከሆነ፣ አገር ጤናማ የሆነ የግብይት ሥርዓት ይኖራታል፡፡ ያኔ ነው ጤናማ የሆነ የገቢ ሥርዓት መዘርጋት የሚቻለው፡፡ አገር ጤናማ ገበያና ግብይት ሲኖራትና ግለሰቦች ጤናማ ገቢ ሲኖራቸው ሁሉም ነገር ትክክል ይሆናል፡፡

አገር ጤናማ ገበያ፣ ግብይትና ገቢ እንዴት ይኖራታል የሚለው ሌላ ጥያቄ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ሁሉ ሕዝብ ገቢ እንዲኖረው ብናደርግ ገቢውን እንዲጠቀምበት ወይም ግብይት ላይ እንዲያውለው ማድረግ ብንችል ምን ዓይነት አገር ይኖረን ነበር? በአንድ አገር ውስጥ አንድ ግለሰብ እንደ ዕድሜውና ዕውቀቱ መጠን ገቢ የለውም ማለት፣ በኢኮኖሚ ሥርዓቱ ላይ ሕይወት የለውም ሙት ነው ማለት ነው፡፡ ይህ ቁጥር ከፍተኛ ከሆነ ደግሞ እንኳንስ ልማቱ የገቢ ሥርዓት ሊኖረው ይቅርና ገንዘብንም በሥራ ላይ ማዋል ከባድ ይሆናል፡፡

ሁሉም ሰው አንድ ዓይነት ኢኮኖሚ ወይም ገቢ ሊኖረው አይችልም፡፡ ሕዝብ አንድ ዓይነት ሕይወት ይኑረው ከተባለ ማሰብ፣ መፍጠር፣ መመራመር ያቁም እንደ ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሊሆን አይችልም፡፡ ምክንያቱም የሰው ልጅ እንዳያስብ፣ እንዳይፈጥር፣ ወዘተ. ያቁም ማለት ከተፈጥሮ ሕግ ውጪ ነው፡፡ ነገር ግን እንደ ምክንያቱ ዓይነት ገንዘብ ግለሰብ ዘንድ ደርሶ ግብይት የሚፈጠርበትን ምክንያት መፍጠር መቻል ይጠበቅብናል፡፡

በአገራችን ገንዘብ ወደ ሥራ ውስጥ የሚገባበት ምክንያት ፈጣን፣ ግልጽና ቀላል መሆን አለበት፡፡ አብዛኞቹ ደሃ አገሮች ውስጥ ሆን ተብሎ ይሁን ሳያውቁት እንደሆነ ባላውቅም፣ ውድና ብርቅ የሆነው ዕውቀት ርካሽና ቀላል የሆነውን ገንዘብ ሲቸገር ማየት የተለመደ ነው፡፡ የሥራ ፈጠራ አለኝ ገንዘብ ግን ቸገረኝ ማለት የተለመደ ነው፡፡ የሚገርመው አገር የምታዘጋጀውን ገንዘብ ወደ ሥራ ውስጥ ለማስገባት የሚያስፈልጋት ምክንያት ነው፡፡ ምክንያቱ ሞልቶ ገንዘቡ የጠፋበት ምክንያት ነው የጠፋብኝ፡፡ ገንዘብ በመንግሥትና በግለሰብ ምክንያት ወደ ገበያ ውስጥ ካልገባ ልማቱ፣ ግብይቱና ገቢው እንዴት ሊፈጠር ይችላል?

ገንዘብን ብናዘጋጀውም ብንጠቀምበትም አጠቃቀማችን ግን የተሳሳተ በመሆኑ፣ ከመንግሥት አንስቶ እስከ ግለሰብ የገንዘብ ችግር አለብን ሲባል መስማት የተለመደ ነው፡፡ ነገር ግን መባል የለበትም፡፡ ገንዘብ በሥራ ላይ የምናውልበት ምክንያት እናጣለን እንጂ፣ ገንዘብን ወደ ሥራ ውስጥ የምናስገባበት ምክንያት እያለን ገንዘብ አጣን አይባልም፡፡ ምክንያቱም ገንዘብ ተራ የፋብሪካ ውጤት ነው፡፡ እንደሚያስፈልገንና እንደምንፈልገው የምናዘጋጀው፡፡

ደሃ አገሮች የግለሰቦችን ሀብት በመጠቀም ገንዘባቸውን ወደ ገበያ ውስጥ ማስገባት ሳይጀምሩ እንኳን ኤክሳይስ ታክስ፣ የገቢ ሥርዓትን እንኳን መዘርጋቱ የተሳሳተ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ከገቢው በፊት ገበያው ሳይፈጠር፣ ከገቢው በፊት ገንዘብ በሥራ ላይ ሳይውል፣ ከገቢው በፊት ግለሰቦች ገቢ ሳይኖራቸው እንኳን ኤክሳይስ ታክስ  ቫትና ግብር መተግበሩ ስህተቱ የከፋ ይሆናል፡፡

የአንድ አገር የገቢ ሥርዓት የሚገናኘው ከገንዘብ ሥርጭቱ ጋር ነው፡፡ ከልማቱ ጋር አይደለም፡፡ አንድ አገር ገንዘብን የምታዘጋጅበትና የምታሠራጭበት በቂ ምክንያት ሊኖራት ይገባል፡፡ ገንዘብን ካሠራጨች ደግሞ የምትከታተልበት አንደኛው መንገድ ገቢ ነው፡፡ በገንዘብ ሥርጭት ውስጥ በመንግሥት በኩል ወደ ገበያ የገባውን ብር ግለሰብ ነው የሚቀበለው፡፡ ገንዘብ ግለሰብ ዘንድ ገብቶ መቀመጥ የለበትም፡፡ ምክንያቱም የገንዘብ የመጨረሻ ዓላማው ግብይትን ማከናወን ነው፡፡ ግብይት ላይ መዋል አለበት፡፡ ለዚህ ሲባል መንግሥት በሌላ በኩል በግለሰብ ላይ የፍላጎት ዕድገት ይፈጥርበታል፡፡ ይህ የፍላጎት ዕድገት የገንዘብ እጥረት እንዲፈጠርበትና ወደ ሥራ እንዲገባ ያደርገዋል፡፡

በአጭር ቋንቋ ፍላጎትና ዕድገት የገንዘብ እጥረትን ይፈጥራል፡፡ የገንዘብ እጥረት የሥራ ፍላጎትን ይፈጥራል፡፡ የግለሰብ የገንዘብ ፍላጎቱ በአደገ መጠን የሥራ አቅርቦቱም የተመጣጠነ መሆን አለበት፡፡ ልብ እንድትሉልኝ የምፈልገው የገንዘብ እጥረትና የገንዘብ ዕጦት የተለያዩ መሆናቸውን ነው፡፡ የግለሰብ የገንዘብ እጥረት ሊሟላ የሚችልበት በርካታ አማራጮች መዘጋጀት አለባቸው፡፡ ብድር፣ ተደራራቢ ሥራ ወይም ጥሩ ተከፋይ ለመሆን የግል ተሰጥኦውን መጠቀም እንዲችል ዕድሎችን ማመቻቸት ጤናማ ኢኮኖሚ ሥርዓት፣ ጤናማ የሆነ የገንዘብ ሥርጭት እንዲኖር ያስችላል፡፡ ጤናማ የሆነ የገንዘብ ሥርጭት ካለ ጤናማ የሆነ ግብይትና ገቢ በአገር ውስጥ እንዲኖር ያስችላል፡፡

እኔ እስከማውቀው ድረስ ግለሰብ ሆኖ በቀጥታ ገንዘብን ለማሠራጨት ምክንያት የሆነ ሰው አላውቅም፡፡ ከእንደ እኔ ዓይነት ትንሽ ሰው እስከ ትልልቅ ምሁራን የፈጠራ ሰዎች ድረስ ገንዘብን በቀጥታ ሊጠቀሙበት የሚችሉበት ዕድል ወይም ሕግ የለም፡፡ ወይም አገር ገንዘብን ወደ ሥራ የምታስገባባቸውን ምክንያት አድርጋ እየተጠቀመች አይደለም፡፡ የትኛውም ግለሰብ ከገንዘብ በላይ የሆነ ሀብት ይዞ ገንዘብ ቸገረኝ የሚባልበት አገር ውስጥ ነው ያለነው፡፡ ይህ የሚያመለክተው ገንዘብ ወደ ገበያ ውስጥ የሚገባበት ምክንያትና መንገድ የተሳሳተ መሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ ግለሰብ ገንዘብ ለማግኘት ምንም ነገር ያደርጋል ማለት ነው፡፡ ገንዘብን ወደ ገበያ ውስጥ የሚገባበትን ምክንያት አድርጎ መሥራት አለመቻል በርካታ ስህተቶችን ይፈጥራል፡፡ ግለሰብ ገንዘብን ብቻ የሚሠራና ለሕግ ተገዥ ያለመሆን ዕድሉ ሰፊ ይሆናል፡፡ ገንዘብ ርካሽ ሀብት ነው፡፡ ማንም ሰው በቀላ ሊያገኘው፣ ሊጠቀምበትና መልሶ የሚተካው አድርገን የገንዘብና የገበያ፣ የግብይት፣ የገቢ ሥርዓታችንን ካልሠራነው የስህተቱ ድምር ውጤት አገርን ያሳጣናል፡፡

ሌላው ሳልነካው ማለፍ የማልፈልገው ግብርን ከነጋዴ ላይ መሰብሰቡ ተገቢ ነው፡፡ ነጋዴ ግን ለመንግሥት ገቢ እንዲሰበስብ ማድረጉ ትልቅ ስህተት ነው፡፡ የነጋዴን የገቢ መጠን መወሰን ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን በገቢው መጠን የመበደር መብት ባልተመቻቸበት አገር ውስጥ ገቢው ላይ ብቻ መሥራት፣ እንደምናየው የግብይት ሥርዓቱ የተበላሸ ይሆናል፡፡ ወይም የገንዘብ ትርፍ ላይ ብቻ ያተኮረ ነጋዴ እንዲኖረን ያደርጋል፡፡ ይህ ደግሞ ስህተት ብቻ ሳይሆን በደልም ነው፡፡ ምክንያቱም ማንም ሰው መኖር ያለበት እንደ ተፈጥሯዊ ማንነቱ ነው፡፡ ማንም ሰው የሚፈቅድለት፣ የሚገድበው የሚያመቻችለት መሆን የለበትም፡፡ ችግሩ ግለሰቡ ላይ ብቻ የሚቆም ብቻ ሳይሆን፣ አገራዊ ዕድገቱ የተገታ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ የአገር ዕድገት የሚረጋገጠው ግለሰቦች ለራሳቸው ሲሉ የሚኖሩት ፍላጎታቸው ድምር ውጤት ነው፡፡

ማንም ሰው የመበደር ዕድል ሊኖረው ይገባል፡፡ የብድሩ መጠን ነው ሊለያይ የሚችለው፡፡ ለነጋዴ እንደ ገቢው መጠን፣ ለአምራች እንደ ፍላጎቱ መጠን፣ ለግለሰብ እንደ ዕውቀቱ፣ ጊዜው፣ ጉልበቱና የዕድሜው መጠን ማዘጋጀት ከቻልን በቀላሉ ገንዘባችንን ልንጠቀምበት የምንችል ዕድል፣ በቀላሉ ገበያችንን የምንፈጥርበት ዕድል፣ በቀላሉ ገንዘባችንን የምንቀባበልበት ዕድል፣ ወዘተ. በሕዝቦች መሀል መፍጠር ቻልን ማለት ነው፡፡ ግለሰብ ጤናማ ገቢ ካለው ጤናማ ግብይት ይኖረናል፡፡ ነጋዴ ጤናማ የሆነ የብድር ሥርዓት ከዘረጋንለት ጤናማ የሆነ ግብይት ይኖረናል፡፡ ለአምራችና ጤናማ የሆነ ብድር ካዘጋጀን ጤናማ ምርት ይኖረናል፡፡

በአንድ አገር ውስጥ ጤናማ ገቢ ጤናማ ግብይትን፣ ጤናማ ኢኮኖሚን ይፈጥራል፡፡ ጽሑፌን ስጠቀልለው በቅርቡ ኤክሳይስ ታክስ የሚባል የገቢ ሥርዓት ሊጣል መሆኑ ሁሉንም ሰው እያነጋገረው እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እኔን ጥያቄ የሆነብኝ በኢትዮጵያ ውስጥ የተተገበሩት የገቢ ሥርዓቶች በሙሉ ቅደም ተከተሉን ጠብቀው ነው ወይ የሚለው ነው፡፡ ገንዘብን ከመሰብሰብ በፊት ገንዘብን ማሠራጨት ይቀድማል፡፡ ዋጋ ከመተመን በፊት ማምረት ይቀድማል፡፡ ታዲያ ይህንን ሁሉ የገቢ ሥርዓት በሥራ ላይ ያዋልነው በቂ የሆነ የገንዘብ ሥርጭት፣ ምርት፣ ዕድገት፣ ወዘተ. ገንዘብ ገበያ ውስጥ ገብቶ ነው? መቼም በነጋዴውና በአምራች መካከል ያለው ልዩነት ለማንም ግልጽ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ አመሠግናለሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...