ለኢኮኖሚ ዕድገት የአገሬው ባለሀብት ሚና ከፍተኛ ሊሆን እንደሚገባ ይታመናል፡፡ ትክክልም ነው፡፡ ‹‹የአገሩን ሰርዶ በአገሩ በሬ›› ነውና፡፡ ይህንን እውነታ ሁሉንም ሰው ሊያስማማ ይችላል፡፡ እንዲህ መታሰቡ ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ለአገር ዕድገትና ለውጥ ከአገሬው በላይ ሊያስብ የሚችል ሌላ አካል እንደማይኖር ስለሚታመን ነው፡፡
የአገርን ኢኮኖሚ ለማሳደግ ቀዳሚ ምርጫ ሊሆን የሚገባው የአገሬው ባለሀብት፣ አቅሙና ዕውቀቱ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የአገሬው ባለሀብት የሥራ ባህልና አጠቃላይ ቁመናው ለአገር ኢኮኖሚ ዕድገት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ኢምንት ከመሆኑ አኳያ በአገር ውስጥ ባለሀብት ብቻ አገር ማቅናት እንደማይቻል ያሳያሉ፡፡
በአገር ውስጥ ባለሀብት ብቻም በየጊዜው የኢንቨስትመንት ፍላጎትን ማሟላት አይቻልም፡፡ ይህ እውነታ ነው፡፡ ስለዚህ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች የውጭዎቹን ማምጣት፣ ከሀብትና ዕውቀታቸው መገብየት፣ ኢንቨስት እንዲያደርጉ መወትወትና ድጋፍ መስጠት የግድ የሚሆነውም የአገር ውስጥ ባለሀብት አቅሙና ዕውቀቱ እስኪጎለብት መጠበቅ ስለማይሆን ነው፡፡
በርካታ አገሮችም ይህን ያደርጋሉ፡፡ ያዋጣቸውና የተጠቀሙ ብዙ ናቸው፡፡ ይህን በማድረጋቸው የሚፈልጉትንና የጠበቁትን ውጤት ያላገኙም ይኖራሉ፡፡ በምንም መመዘኛ ግን ለኢኮኖሚና ለአገር ዕድገት የአገሬው ባለሀብት ሚና ግምት ቢሰጠውና ቢታመንበትም የውጭ ባለሀብት እንዲመጣ የሚፈለግባቸው አስገዳጅ ሁኔታዎች በርካታ ናቸው፡፡ ለዚህም አሳማኝ ምክንያቶች አይጠፉም፡፡
የካፒታል አቅሙን፣ ዕውቀቱንና ጊዜውን ተጠቅሞ የመሥራት፣ እንዲሁም ቴክኖሎጂና የሠለጠነ የሰው ኃይል እጥረቶች ስላሉብን ወደ ሌሎችና አቅሙ ወዳላቸው እንድንማትር ያደርገናል፡፡ የአገር ውስጥ ባለሀብት በሁሉም መስክ አቅም እንዲኖረው ከታሰበ፣ የውጭ ኩባንያዎች ወደዚህ መጥተውና በሚመቻቸው ዘርፍ ውስጥ ገብተው መሥራታቸው እንደሚያስፈልግ አያጠራጥርም፡፡ በሌላ በኩል የአገር ውስጥ ባለሀብቶችና አገር በቀል ኩባንያዎች በአብዛኛው አገርን በሚለውጥ፣ ብዙኃኑን በሚጠቅም ኢንቨስትመንት መስክ ውስጥ ሲኳትኑ ብዙም አይታየም፡፡ በአብዛኛው የአጭር ጊዜ ሥራ ሠርቶ፣ በአብዛኛው ነግዶ ትርፍ የሚያጋበስበት መስክ ውስጥ በብዛት የመሸገውን አካል ወደ አምራችነትና ወደ ምርት ሥራዎች ማስገባት እስኪቻል ድረስ የውጭ ኩባንያዎችን መፈለግና የእነሱን ጭራ መከተል ያስፈልግ ይሆናል፡፡
በሌላ በኩል ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንትና የቢዝነስ ዕድሎችና ከባቢ ሁኔታዎች በተወሰነ ጊዜና አካባቢ የሚወሰኑ ባለመሆናቸው ምክንያት፣ ወደድንም ጠላን የውጭ ኢንቨስትመንት እንዲገባ የሚያስገድዱ ሁኔታዎች ይኖራሉ፡፡ ማንም በሩን አጥሮና ለአገር ውስጥ አምራች ብቻ ተብሎ የሚተገበር አሠራር በዓለም ላይ የለም፡፡
እስካሁን ከመጣንበት የንግድና የኢንቨስትመንት፣ እንዲሁም ከኋላ ቀር የሥራ ባህል መላቀቅ እስካልቻልን ድረስ በርካታ ዜጎችን የሚቀጥር፣ ከአገር አልፎ ከሌሎች የሚያስተዳድረንን የምርት ዕድል የሚፈጥሩ፣ ሥራ የሚያበራክቱ ኩባንያዎች በመጡ ቁጥር የእነሱን እያየን ሥራ መሥራቱ ላይ በእጅጉ ካልበረታንና ቶሎ ብለን የውጭዎቹን ተክተን ካልሠራን በቀር ሕዝብና አገርን ወደፊት ማራመድ አይቻልም፡፡ ትልቅ ዓላማ ይዞ የሚንቀሳቀስ ተቋም መፍጠር የግድ ይላል፡፡ ይህንን ለመፍጠር የግል ማኅበራትም ሆኑ የመንግሥት ኃላፊነት ይሆናል ማለት ነው፡፡
እውነት ለመነጋገር የአገር ውስጥ ባለሀብት አቅሙ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ ከ110 ሚሊዮን በላይ ለሆነ ሕዝብ ሊመጥን በሚችል ደረጃና ነገን በማሰብ ጭምር የተፈጠረ አይደለም፡፡ ሌላው ቢቀር ምሳሌ የሚሆኑ ኩባንያዎችን መፍጠር ይገባል፡፡ እንዲህ ያለውን አቅም ለመፍጠር ምን ይደረግ? የሚለው ላይ ሁሉም መሥራት ይጠበቅበታል፡፡ ለዚህም ወኔ ያስፈልጋል፡፡ ለራስ ብቻ ሳይሆን፣ አገርን ታሳቢ ያደረገ የሥራ አቅምና ድርጅት መፍጠርን ከዕለታዊ ትርፍ ባለፈ ደረጃ ጥቅም የሚያስገኙ ሥራዎች ላይ ማተኮር ይገባል፡፡
ከዛሬ ጥቅም የነገ የተሻለ ጥቅም ይበልጣል ብሎ ማቀድና ይህንንም በተግባር ማሳየት የሚያስችል ዕቅድ ሊኖረንም ይገባል፡፡ በተለይ በተለይ ከምናውቃቸው ሥራዎች ወጣ ብሎ አዋጭ በሆኑ ቢዝነሶች በግልም በጋራ በማቅረብ በርብርብ የመሥራት ባህልንም በማዳበር ሊጠቅሙ የሚችሉ ከብዙ ጥቂት ጠንካራ ተቋማትን ማፍራት የሚችልበት ዕድል ስላለ ይህንን ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ በባዶ እጅ የውጭ ኢንቨስትመንት እየገባ ነው ብሎ መከላከል አሁን ባለ ደረጃ አቅማችን አይሆንም፡፡ ብዙ ሥራ ፈጣሪና ሥራ ቀጣሪ ኩባንያዎች ግድ የሚሆኑት በሥራ ዕጦት አገር እየተሸበረች ስለሆነም ጭምር ነው ብሎ ማሰብን ይጠይቃል፡፡
የአገር ውስጥ ኩባንያዎች ጠንክረው እንዲወጡ ግን የባለሀብቱም የመንግሥትም የጋራ ራዕይ ወሳኝ ነው፡፡ የአገር ውስጥ ባለሀብት እየደቀቀ ከሄደ ግን አደጋው መጣ የምንለው ያኔ ነው፡፡ ስለዚህ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች በሁሉም መስክ ጠንክረው እንዲወጡ ማገዝ፣ የውጭ ኩባንያዎችም የአገሬውን ኩባንያዎች እንዳያቀጭጩ የማድረግ ሕግጋትንም ማስቀመጥ ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ሥነ ምግባር ያለው የግሉ ዘርፍ መፍጠር ነው፡፡ በመሆኑም በመንግሥት በኩል የግል ዘርፍ የአገር ኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ሞተር ነው የሚለውን በጽሑፍና በቃላት ለዘመናት የሰማነውን ዲስኩር በተግባር እንዲለወጥና በትክክል የአገር ባለሀብት የኢኮኖሚው አንቀሳቃሽ እንዲሆን አጋዥ የሆነ ፖሊሲ እንዲኖረው ያሻል፡፡
የውድድር ሜዳውን በማመቻቸት ማገዝ ተገቢ ነው፡፡ ለዚህ ግን አቅም ከሌለና የግሉ ዘርፍ ሊሠራው የማይችለው ከሆነ፣ መንግሥትም የውጭ ባለሀብትም ገብቶ ሊሠራና ሊሰማራበት ይገባል፡፡ የውጭ ኩባንያዎችን የሚተኩ ተቋማትን እግር በእግር እየተተኩ መሥራት የሚችሉበት አመቺ የአሠራር ማዕቀፍ ያስፈልጋል፡፡ በጥቅሉ የግሉ ዘርፍ እንዲጠነክር በውጤት የሚታይ የሥራ ሒደት መተግበር አለበት፡፡